>
12:27 pm - Tuesday January 26, 2021

የዓለም ወንጀለኞች ፍርድ ቤትን/ICCን ከአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖች ማዳን [ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም]

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ሕግ የችግሩን ውስብስብነት በማረጋገጣቸው ሽንፈታቸውን አምነው ተቀበሉ!

ይህ ወር “በጨለማው አህጉር” ጨለማ እና ተስፋየለሽ ወር ሆኗል! አንድ ከፍተኛ የሀገር መሪ በሰው ልጆች ላይ አስከፊ በሆነ የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀል ተከስሶ ከቀረበ በኋላ ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በቀላሉ በመውጣት በእራስ መተማመን ስሜት እንደ ቼሻዬር ድመት ጥርሶቹን እስከ ጆሮው ድረስ በመገልፈጥ እና እንደበራሪ ወፍ እየከነፈ “ከአመቤት ፍትህ” በነጻ ተሰናብቶ ሲሄድ ማዬት በአፍሪካ ታሪክ የመጨረሻው መጥፎ ጊዜ መድረሱን አስታወቀኝ፡፡
የኬንያ መስራች አባት እና የመጀመሪያው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት የጆሞ ኬንያታ ልጅ የሆኑት ኡሁሩ ኬንያታ እ.ኤ.አ ዴሴምበር 2007 የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ከኬንያ ድህረ ምርጫ ጋር ተያያዞ ተከስቶ በነበረው ቀውስ ምክንያት ደርሶ ለነበረው ጅምላ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ እ.ኤ.አ ማርች 8/2011 በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ህግ በአምስት ዓይነት ከፍተኛ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸው ነበር፡፡ እንደ የዓለም የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ ኡሁሩ ኬንያታ በዚያን ጊዜ የኬንያ መንግስት ሚኒስትር ሆነው ሲሰሩ በነበሩበት ጊዜ የእርሳቸውን የገዥው ፓርቲ አባላትን የሚቀናቀኑትን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አመጽ ሆን ብለው ለማጥፋት በማሰብ ዕቅድ ነድፈዋል፣ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ አድርገዋል፣ እናም ለተግባራዊነቱ አስተባብረዋል፡፡ ኬንያታ “ሙንጊኪ ድርጅት” ያተባለውን የኬንያ የማፊያ ቡድን በመጠቀም ንጹሀን ዜጎች እንዲገደሉ፣ እንዲጋዙ፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንዲፈጸምባቸው እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ረገጣዎች እዲካሄዱባቸው አድርገዋል፡፡ በዚያን ጊዜ በተፈጠረው ውዝግብ ወደ 1,200 የሚሆኑ ንጹሀን ዜጎች እንደተገደሉ እና ወደ 700 ሺ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ እንዲፈናቀሉ ተደርገዋል፡፡ በኬንያታ ላይ የቀረቡት ሁሉም ክሶች እ.ኤ.አ ጃኗሪ 2012 በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የቅድመ ምርመራ ክፍል II ተረጋግጠዋል፡፡
እ.ኤ.አ ዴሴምበር 5/2014 የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ሕግ የሆኑት ወይዘሮ ፋቱአ ቤንሱዳ ከዚህ ክስ ጋር በተያያዘ መልኩ ድል መደረጋቸውን እና መሸነፋቸውን ያመኑ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ወይዘሮዋ በኬንያታ ላይ የቀረቡትን የክስ ውንጀላዎች ውድቅ በማድረግ ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ፋይሉ የተዘጋ መሆኑን ግልጽ አድርገዋል፡፡ ቤንሱዳ የኬንያ መንግስት ለምስክርነት የሚቀርቡ ሰዎችን በተከታታይ በማጥቃት እና በማስፈራራት በሚል የከሰሱ ሲሆን በኬንያታ ላይ ክሱ እንዲቋረጥ ተደረገበትን ዋና ምክንያት እንዲህ በማለት ገልጸውታል፣ “በዚህ ጉዳይ ላይ የቀረቡትን ማስረጃዎች ስመለከት የሚስተር ኬንያታን ክሶች ከማቋረጥ በስተቀር ሌላ ምንም ዓይነት አማራጭ የለኝም፡፡ አስቀድሞ በተያዘ እና ተጨባጭነት በሌለው ሀሳብ ሳልመራ በእውነታ ላይ የተመሰረተ ተጨማሪ ማስረጃዎች የሚቀርቡ ከሆነ ክሱን እንደገና በአዲስ መልክ የማየው ይሆናል፡፡“ ቤንሱዳ እራሳቸውን ነጻ በማድረግ እፎይታን የተጎናጸፉ በሚመስል መልኩ እንዲህ ብለዋል፣ “ዛሬ ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍትህ የጨለማ ዕለት ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን የዛሬው ውሳኔ እ.ኤ.አ በ2007 እና በ2008 በኬንያ ህዝቦች ላይ ለደረሰው እልቂት እና ስቃይ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የፍትህ ያለህ እያሉ ለሚጮሁት ዜጎች ሁሉ ለፍትህ እና ለተጠያቂነት የተሰጠ የመጨረሻው ቃል አይደለም፡፡“
ይፋ በተደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ኬንያታ በጣም የተበሳጩ ለማስመሰል እንዲህ ብለዋል፣ “የሰብአዊ መብቶች ቡድኖች እና ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሸፍጥ ዱለታ በማድረግ የሰብአዊ መብት ረገጣ ሰለባ የሆኑትን ንጹሀን ዜጎችን ለመቅጣት የሚያደርጉት ክህደት እስካለ ድረስ ፍትህ የለም፡፡ የዚህ የውሸት አሳዛኝ ተውኔት በቃላት ልገልጸው ከምችለው በላይ ነው፡፡“ ኬንያታ በድል አድራጊነት እንዲህ በማለት አወጁ፣ “አንዱ ወረደ፣ ሁለቱ ይቀራሉ“ (ተመሳሳይ ክስ የቀረበባቸውን የእርሳቸውን ምክትል እና የጋራ ተከላካይ የሆኑትን ዊሊያም ሮቶን እና የሬዲዮ ኦፕሬተር የሆኑትን ጆሹዋ አራፕ ሳንግን ለመጥቀስ ፈልገው የተናገሩት)፡፡ ሩቶ እና ሳንግም ሰውን ከመግደል፣ አስገድዶ ከመድፍር፣ እና ሌሎችን በሰው ልጆች ላይ ከተፈጸሙ ወንጀሎች ነጻ ሆነው ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የመሰናበቱ ሁኔታ ይኖር ይሆን? ለኬንያታ የተደረገው መልካም ነገር ለሩቶ እና ለሳንግም መደረግ አለበት፡፡ እንደዚሁም ሁሉ እነርሱም በጊዜ ተሰናብተው ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ በቁስል ላይ እንጨት መስደድ እንዲሉ የኬንያታ የሕግ አማካሪ ጠበቃ ጭራሽ እጸድቅ ብዬ ባዝላት ተንጠልጥላ ቀረች ሆነና የሀሰት ምስክሮችን በመቀበል እና የኬንያታን ታማኝነት በሚያሳንስ መልኩ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ህግ የክስ ሂደቱን ተቀብለው ሲያዩ በመቆየታቸው ለኬንያታ ይቅርታ እንዲጠይቁ ሀሳብ አቅርቧል፡፡ ይኸ ነው እንግዲህ የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀለኞች እና የእነርሱ ተከላካዮች ዓይን ያወጣ ድፍረት፡፡ እነርሱ የፈጁት እና ያስፈጁት ህዝብ ደም በዓለም የፍትህ አደባባይ የውሻ ደም ሆኖ ሲቀር እና በነጻ መለቀቃቸው አልበቃ ብሎ የይስሙላም ቢሆን በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ህግ ፊት ቀርበው መጠየቃቸው ክብራቸውን የሚነካው ሆኖ ጭራሽ አፋቸውን ሞልተው ይቅርታ ይጠይቁን በማለት መሳለቅ ጀመሩ፡፡ የኸ በእውነት በፍትህ ላይ መቀለድ ነው ከማለት በስተቀር ምን ሊባል ይችላል!
በእርግጥ ከድህረ ምርጫው ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ውዝግብ ከዕልቂቱ የተረፉትን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የኪብራ፣ የኪሱሙ፣ የናቫሻ፣ የናኩሩ እና የሌሎችን አካባቢ ከተሞች ድሆች፣ ምንም የሌላቸው ምስኪ ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች ኬንያታ እንዴት አድርጎ የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በማታለል ላይ እንዳሉ እና ለበርካታ ዓመታት የፍትህን መምጣት በመጠባበቅ ላይ ያሉትን ሁሉ ለመጠየቅ የሞከረ የለም፡፡ ሥልጣን ያላቸው ሁሉ በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩ እረዳትየለሾች፣ ኃይልየለሾች እና ተከላካይየለሽ የኬንያ የሰብአዊ መብት ረገጣ ሰለባዎች ደንታቸው አይደለም፡፡ ሥልጣን ላላቸው በእውነታው ላይ ያላቸው አስተሳሰብ ይኸው ነው፡፡ ስለጥቃት ሰለባዎቹ ደንታ የላቸውም፡፡
አንድ በአፍሪካ አህጉር የምትገኝ ሀገር መሪ በበርካታ ዓይነት የሰብአዊ መብት ረገጣዎች ክስ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርደ ቤት ክስ ተመስርቶበት በሂደት ላይ እያለ የማታለል ተውኔት በመስራት፣ የማታለል ዕቅድ በማውጣት እና የፍትህ ሂደቱን በማወክ ፍትህን በአፍ ጢሟ በመድፋት (ምስክሮችን በማስፈራራት፣ ለምስክርነት ጉዳይ ተባባሪ እንዳይሆኑ በማድረግ፣ ምስክሮች የተነገራቸውን እንዲያደርጉ በማስገደድ፣ የፍርድ ሂደቱ በጣም በተፋጠነ መልኩ እንዲካሄድ በማድረግ እና እውነታውን በመደበቅ ውሸትን በማንገስ) ደረቱን ገልብጦ የቅጥፈት ሳቁን እየገለፈጠ ተጀንኖ ሲሄድ በ10 ሺዎች ኬንያውያን/ት ላይ ብቻ የተፈጸመ የሰብአዊ መብት ረገጣ አይደለም፡፡ ይህ ድርጊት በሰው ልጆች ላይ ሁሉ የተፈጸመ አሳፋሪ እና አስደንጋጭ ድርጊት ነው፡፡ ይህ እኩይ ድርጊት በህግ የበላይነት ላይ የተሰነዘረ ዘለፋ ነው፡፡ ይህ አሳፋሪ ድርጊት በአፍሪካ ኢፍትሀዊነት በፍትሀዊነት ላይ ድል የተቀዳጀበት ሁኔታ ነው፡፡
ነግሪያችሁ ነበር…ኬንያታ በነጻ ተሰናብቶ ይሄዳል ብዬ ነግሪያችሁ ነበር!

ለመናገር በጣም የምጠላው ነገር ነው፡፡ ሆኖም ግን ነገሪያችሁ ነበር፡፡ ተናግሬ ነበር! ኬንያታ ከዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በነጻ ተሰናብተው የዋቱሲን ዳንስ እየደነሱ በማለት ቀደም ሲል ተናግሬ ነበር፡፡ የማውቀው ጉዳይ ነውና!
እ.ኤ.አ ኤፕሪል 2014 “የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መከላከል፡ ምስክሮችን የምስክርነት ቃል ከመስጠት ለማስተጓጎል የቀረበ ፕሮግራም” በሚል ርዕስ ትችቴን በምጽፍበት ወቅት ኬንያታ በነጻ ተሰናብተው እጃቸውን በኪሳቸው ከትተው እየተጎማለሉ እንደሚሄዱ አውቅ ነበር፡፡ ቀደም ሲል በጥር ውስጥ ይህ ድርጊት ሊፈጸም እንደሚችል ጠረኑ ሸትቶኝ ነበር፡፡ በሚያዝያ ወር ላይ ያ ጠረን ጠንዘቶ ነበር። በዚያን ጊዜ ኡሁሩ ኬንያታ ሊለቀቁ እንደሚችሉ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ያመንኩበት ጊዜ ነበር፡፡ ኡሁሩ ሙጋይ ኬንያታ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ቀርበው ሊዳኙ እንደማይችሉ ለእኔ ግልጽ ሆኖልኝ ነበር፡፡ ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ህግ እና ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የተሰማኝን ሀዘን ስገልጽ ነበር፡፡ ካሉበት የስልጣን ወንበር ላይ ሆነው በጉዳዩ ላይ ከሌላ ከበስተጀርባ ከሚመጣ ነገር ከፍተኛ ሙቀት ሲሰማቸው ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ኬንያታ አስቀድሞ የተቀመጡ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ዓለም አቀፋ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እና የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ሕግ፣ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እና የምዕራቡ ዓለም በአጠቃላይ በጥቂት የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በሚቆጠቁጥ “የዘር ማደን” እና “በኒዮሊበራል ርዕዮት ዓለም” አራማጅነት ክስ እየቀረበባቸው በነገር ይቃጠሉ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ከ2013 አጋማሽ ጀምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፣ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታውን ምክር ቤት እና የምዕራቡን ዓለም በዘር አዳኝነት በመፈረጅ ኬንያታ እና ግብረአበሮቻቸው በኬንያ ህዝብ ላይ የፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ወንጀል የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየስ ከበሯቸውን ይደልቁ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአፍሪካ ህብረት ተዘዋዋሪ የወቅቱ ሊቀመንበር የሆኑት ኃይለማርያም ደሳለኝ የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እና የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ሕግ የጥቁር አፍሪካ መሪዎችን ለማጥቃት የተደራጀ የዘር አዳኝ ነው በማለት የማዋረድ ቁጣቸውን መግለጽ ጀመሩ፡፡ ይህ አነጋገር እ.ኤ.አ በ2003 ብዙም ፋይዳ በሌለው የተጋነነ እና ከፍ ባለ ድምጽ ብዙም እርባና በሌለው ሆኖም ግን ከየትም ሳይኮርጁ የእራሳቸውን እምነት እንደወረደ በመናገር ከሚታወቁት ከሮበርት ሙጋቤ እንዲህ ከሚለው ንግግር ፍጹም የተለዬ አልነበረም። ሙጋቤ ሲናገሩ “አሁንም ቢሆን እኔ የጊዜው ሂትለር ነኝ፡፡ ይህ ሂትለር አንድ ዓላማ ብቻ አለው፣ ለእራሱ ህዝቦች ፍትህን ማስፈን፣ ለህዝቦቹ ሉዓላዊነት መከበር ጥረት ማድረግ፣ ለእራሱ ህዝቦች ነጻነት እውቅና ትግል ማድረግ እና የሀገሬው ህዝብ በተፈጥሮ ሀብቶቻቸው የመጠቀም መብቱ እንዲረጋገጥ ማድረግ ነው፡፡ ሂትለርነት ማለት ይህ ከሆነ እኔም አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን 10 ጊዜ ሂትለር ልሁን፡፡ እንግዲህ 10 ጊዜ ያህል ሂትለር ለመሆን ነው የቆምነው፡፡“ ሙጋቤ “የአፍሪካ የሂትለር የዘረኝነት ፍልስፍና አራማጅ” በመሆናቸው ኩራት ይሰማቸዋል፡፡ ኃይለማርያም ደግሞ በተቃራኒው “ከትልቁ የነጭ ዘር አዳኝ” ለማምለጥ ይሸሻሉ፡፡ ምን ዓይነት የሚገርም ነገር ነው ጎበዝ!
ኃይለማርያም እና ግብረ አበሮቻቸው በአፍሪካ ህብረት የስብሰባ አዳራሽ የዓለም ወንጀለኞች ፍርድ ቤትን ስም ጥላሸት ለመቀበት ለመጨረሻ ጊዜ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2013 በአፍሪክ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር የሮምን ስምምነት (በሰው ልጆች ላይ የሰብአዊ መብት ረገጣ በሚያደርሱ ወንጀለኞች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ዓለም አቀፍ ስልጣን) በመጣስ በጅምላ ለቀን እንወጣለን የሚል ማስፈራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡ በሌላ አገላለጽ የዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትን በአፍሪካ ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ለመጣል ዕቅድ ነድፈዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ለአፍሪካ እና ለመሪዎቿ ልዩ የሆነ አሳፋሪ ወቅት ነበር፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ዘር ለማጥፋት ዘር አዳኝ እንስሳት እንደመጡባቸው በመቁጠር በፍርሀት በሀዘን እና በጉልህ በሚታይ ጭንቀት ተወጥረው ደህንነትን ለማግኘት በሚል በአዲስ አበባ ከተማ ተሰበሰቡ፡፡ ከተሰበሰቡም በኋላ በአፍሪካ ላይ በመጣው ዘር አዳኝ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ ጫጫታ የበዛበት ሆኖም ግን ባዶ ማስፈራሪያ ወይም ደግሞ ተቃውሞ እንደሚያደርጉ ዛቱ፣ ድምጻቸውን ከፍ በማድረግ የተጋነነ ዲስኩራቸውን ለቀቁት፣ እናም ያልተገራ እና አጅ እግር የሌለው ያልተያያዘ ንግግራቸውን አሰሙ፡፡ በመጨረሻም ከሮም ስምምነት በጅምላ ጥሎ መውጣት የሚለው የፈሪዎች ማደናገሪያ በመሆን ተቀይሶ የነበረው ስልት በውድቀት ተቋጨ፣ እነርሱም ሳይወጡ ተንተባትበው ቀሩ፡፡
እኔ በግሌ የኬንያታ የፍርድ ሂደት ስኬታማ በሆነ መልኩ ቢካሄድ ኖሮ በጣም ጠቃሚ ነገር ይሆን ነበር የሚል እምነት አለኝ!

እ.ኤ.አ የ2007 ድህረ ምርጫ ውዝግብን ተከትሎ በኬንያ በተፈጠረው እልቂት እጃቸው አለበት ተብሎ በመታየት ላይ የቆየውን የፍርድ ቤት ሂደት ጉዳይ ትኩረት በመስጠት በሙሉ ፍላጎት ስከታተለው ቆይቻለሁ፡፡ የኬንያታን፣ የእርሳቸውን ምክትል ዊሊያም ሩቶን እና የሬዲዮ ዲስክ ኦፕሬተር የሆኑትን ጆሹአ አራፕ ሳንግ (በሰው ልጆች ላይ በተፈጸሙት የሰብአዊ መብት ወንጀሎች በርካታ የክስ ዓይነቶች ተመስርተዋል) የክስ ጉዳዮችን በንቃት ስከታተል ቆይቻለሁ፡፡ በሩቶ እና በሳንግ ላይ በመካሄድ ላይ የነበሩ በመቶዎች ገጽ የሚቆጠሩ የፍርድ ቤቱን ሂደት የያዙ ሰነዶችን አንብቢያለሁ፣ እንደዚሁም ደግሞ የፍርድ ሂደቱን የሚዘግቡ ዘግይተው የወጡ ጥቂት የቪዲዮ ምስሎችን ተመልክቻለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በእነዚህ ተከላካዮች ላይ የሚካሄደውን የፍርድ ቤት ችሎት ሂደት የሚተቹትን እና ዘገባ የሚያካሂዱትን በርካታ ጋዜጦች አንብቢያለሁ፡፡ ከዚህም በላይ በየሳምንቱ ሰኞ በማቀርበው “የሰኞ ዕለት ትችቶቼ/Monday Commentaries” ላይ ስለኬንያታ እና ሩቶ የህግ ሂደት ጉዳይ በስፋት ስዘግብ ቆይቻለሁ፡፡
በእነዚህ በሰው ልጆች ሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ላይ ተጠርጥረው ክስ በተመሰረተባቸው ተጠርጣሪ ጉዳዩን የበለጠ ተጨባጭነት ባለው ሁኔታ ግልጽ ለማድረግ፣ የኬንያታ የክስ ሂደት በመቋረጡ እና ምናልባትም የሮቶ እና የሳንግ የክስ ሂደቶችም በተመሳሳይ መልኩ ሊቋረጡ እንደሚችሉ በመገመት በጫካ ውስጥ እንደሚገኝ ጅራተ ረዥም ቆርጣሚ አውሬ የምበሳጨው ለምንድን ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ በተካሄደው ሌላ ድህረ ምርጫ በተፈጠረው ውዝግብ ወደ ኋላ መለስ በማለት ከተፈጠረው ዕልቂት ጋር ይዛመዳል፡፡
እ.ኤ.አ ሜይ 16/2005 ከምርጫው ዕለት አንድ ቀን በኋላ አሁን በህይወት የሌሉት መለስ ዜናዊ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ማሸነፋቸውን ካረጋገጡ በኋላ የጦር እና የደህንነት ኃይሉን የአዛዥነት ስልጣን በእርሳቸው ቁጥጥር ስር በማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጁ፡፡ የአዲስ አበባን ፖሊስ በፌዴራል ፖሊስ እና ልዩ ስልጠናን በወሰደ ልዩ ኃይል ተኩት፡፡ ምንም ዓይነት ስብሰባዎች በህዝብ እንዳይካሄዱ ከለከሉ፡፡ መለስ ማንኛውንም የተቃውሞ እንቅስቃሴ በሚያደርግ ዜጋ ሁሉ አስፈላጊ የሆነ ጥብቅ እርምጃ መውሰድ እንዲችሉ ለመች ወሮበላ ጦር ኃይላቸው ትዕዛዝ ሰጡ፡፡
እ.ኤ.አ በ2006 መለስ እራሳቸው ያቋቋሙት የምርመራ ኮሚሽን 193 ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ያልታጠቁ ንጹሀን ዜጎች መገደላቸውን እና 800 የሚሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ደግሞ መቁሰላቸውን በመጥቀስ አመልካች ጣታቸውን በእርሳቸው ላይ ቀሰሩ፡፡ ሆኖም ግን በድህረ 2005 ምርጫ በገዥው አካል ታጣቂዎች እጅ የነበረው ትክክለኛው ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ቁጥር ከዚህ በላይ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን የአጣሪ ኮሚሽኑ ዘገባ ከተወሰነለት ቀን እና ቦታ ውጭ የማዬት እና የማጣራት ስልጣን ስላልተሰጠው ይኸ አብሮ በዘገባው ቢካተት ኖሮ ቁጥሩ ከዚህ የበለጠ ከፍተኛ ይሆን እንደነበር ጥርጥር የለውም፡፡
በአንድ ወቅት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ቤንጃሚን ፍራንክሊን እንዲህ ብለው ነበር፣ “ጉዳቱ ያልደረሰባቸው ሰዎች ጉዳቱ እንደደረሰባቸው ሰዎች ሁልጊዜ እስከሚበሳጩ ድረስ ፍትህ አገልግሎት ልተሰጥ አትችልም፡፡“ በአሜሪካ በምቾት እኖር ስለነበር በመለስ እልቂቶች አልተጎዳሁም ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 በመለስ የተፈጸመውን አስደንጋጭ እልቂት በተገነዘብሁ ጊዜ በመበሳጨት ከቁጥጥሬ በላይ ሆኘ ነበር፡፡ የሸክስፒርን ቃላት በመዋስ፣ “እንደተናወጠ ባህር እብድ ሆኘ ነበር፡፡“
በዚያን ጊዜ በእኔ የቁጣ መንፈስ ውስጥ ሁለት አንገብጋቢ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ እነርሱም 1ኛ) በመለስ ለተፈጸሙ እልቂቶች ድምጼን ከፍ አድርጌ መጮህ አለብኝ ወይስ ደግሞ ጆሮዳባ ልበስ ብዬ አይቶ እንዳላዬ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ እና መናገር እየቻለ አፉ እንደተለጎመ ሰው በዝምታ ባህር ውስጥ ሰምጦ ጸጥ ማለት? 2ኛ) በመለስ ስለተካሄዱት የእብሪት እልቂቶች በቀጣይነት ምን መደረግ አለበት? የሚሉት ነበር፡፡
ለመጀመሪያው ጥያቄ የነበረኝ ምላሽ ሙሉ በሙሉ በሞራል ስብዕና ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ይኸውም በእብሪት በተወጠረ አምባገነን እኩይ የእብሪት ተግባር በወገኖቼ ላይ እንደዚህ ያለ አስደንጋጭ እና አሳፋሪ እልቂት እየተፈጸመ እያየሁ አላየሁም ብዬ ዝም ልል አልችልም፣ አልሰማሁም ብዬ ልቀመጥ አልሞክርም፣ መናገር አልችልም ብዬ አፌን ለጉሜ አልቀጥልም የሚል ነበር፡፡ በዚህም መሰረት መለስ እና የሰይጣናዊ ድርጊታቸው ተባባሪ የሆኑትን የጥፋት መልዕክተኞች በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሀሳብ የፍርድ ሚዛን ላይ በማቅረብ ፍትህን ለማግኘት በሚል ድምጼን ከፍ አድርጌ በመጮህ እና የተፈጸመውን እኩይ ድርጊት ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ በማሳወቅ የሞራል ስብእና ጥያቄውን ለመፍታት ሞከርኩ፡፡ ይህንን ተግባር እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሬ በቆራጥ እና በማያወላውል ሁኔታ ተግባራዊ አደረግሁት፡፡
ወደ ሁለተኛው ጥያቄ ስንመጣ ያንን ለመሰለ አሳፋሪ እና አስደንጋጭ የመለስ እልቂት ተጠያቂ የሚሆኑት ማለትም መለስን ጨምሮ የፖሊስ እና የደህንነት ኃላፊዎች፣ ፖሊሶች፣ የደህንነት እና በእልቂት ተግባሩ ላይ የተሳተፉት ወታደራዊ ኃይሎች በሙሉ ለፍትህ አካል በመቅረብ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው እምነት አሳድሪያለሁ፡፡ ይህ በህግ ተጠያቂ የመሆን ጉዳይ የቱንም ያህል ጊዜ ቢወስድ ምንም አይደለም፡፡ ዋናው ቁምነገር የጊዜ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይልቁንም ታላቁ እና ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ፍትህ የማግኘቱ ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የዘገየ ፍርድ እንደተካደ ይቆጠራል በሚለው አባባል ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ እምነት የለኝም፡፡ ፍትህ አንዳንድ ጊዜ እንደሚዘገይ ባቡር ሊቆጠር እንደሚችል አምናለሁ፡፡ የዘገዬ ባቡር በተደጋጋሚ የሚሰማውን ከፍተኛ ጩኸት እያሰማ ከባድ እና ግዙፍ የሆነ ጭነትን ተሸክሞ የሚጓዝ ነው፣ ሆኖም ግን የቱንም ያህል ጊዜ ቢዘገይ መድረሱ አይቀርም፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ናዚዎች ባደረሱት እልቂቶች ተጠያቂ በሚሆኑት እብሪተኞች ላይ ፍትህ ሳይሰጥ ለአስር ዓመታት ያህል ዘግይቷል፡፡ (የቀድሞውን የናዚ የጥበቃ አባል የነበረውን ጆሀን ሀንስ ብሪዬርን ለህግ ለማቅረብ 70 ዓመታትን እንደወሰደ ልብ ይሏል)፡፡ ብሪዬር የናዚ የእስረኞች ማጎሪያ እና በጀርመን ይዞታ ስር ወድቃ ወደነበረችው የፖላንድ ግዛት ወደሆነችው አውስችዊዝ ከተማ ተጭነው ይሄዱ በነበሩ አንድ ሙሉ ባቡር የሆኑ ዜጎች ላይ እ.ኤአ በሜይ 1944 እና ኦክቶበር 1944 መካከል በተፈጸሙ እልቂቶች ላይ ተባባሪ እና ተዋናይ ሆኖ በፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል እ.ኤ.አ ጁላይ 2014 በ158 የክስ ዓይነቶች ክስ ተመስርቷል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ መለስ እና የእኩይ ምግባር ተባባሪዎቻቸው በ193 መሳሪያ ያልታጠቁ ሰላማዊ አመጸኞ ላይ በፈጸሙት አሰቃቂ እልቂት እና በሌሎች 763 ዜጎች ላይ በተደረገው የግድያ ሙከራ ወንጀል የፈለገውን ያህል ጊዜ ቢወስድም አንድ ቀን በፍርድ አደባባይ ቀርበው ተጠያቂ መሆናቸው እንደማይቀር እርግጠኛ እና ባለሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡
እ.ኤ.አ ኦገስት 2012 መለስ በሰው ልጆች ላይ ለፈጸሙት የእልቂት ወንጀል ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ የሁሉ የበላይ በሆነው እና ይግባኝ በሌለው ፍርድ ቤት ፍርዳቸውን አግኝተዋል፡፡ የአሰቃቂ ወንጀለኝነት ዋጋቸውን በዓይን ከማይታየው እረቂቁ አምላክ በፍጥነት እና በድንገት ተቀብለዋል፣ ቅዱሱ መጽሐፍ ሁሉም የዘራውን ያጭዳል እንዳለው ይላልና፡፡
ሁሉም የአፍሪካ አምባገነኖች በአንድ ዓይነት የአምባገነንነት ትምህርት ቤት ውስጥ ገብተው የተማሩ ይመስላል፡፡ አንዱ አምባገነን አንድ የአምባገነንነት ሥራ ከሰራ ሌሎቹ አምባገነኖች ደግሞ የእርሱን አሻራ ተከትለው ከእርሱ የበለጠ ወይም የተሻለ አድርገው ይሰራሉ፡፡ አንዱ የሌላውን በማስመሰል ወይም ደግሞ እርስ በእርሳቸው በመኮራረጅ የአምባገነንነት ተግባራቸውን ያከናውናሉ፡፡ የእነርሱ ተግባራት ሁሉ እንደ ጅቦች ዓይነት ነው፣ ጅቦች የአፍሪካ አምባገነኖች ጥሩ ተምሳሌዎች ናቸው፡፡
ለእኔ እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ ተካሂዶ በነበረው ድህረ ምርጫ ውዝግብን ተከትሎ በተፈጠረው ሁከት እና እ.ኤ.አ በ2007 በኬንያ ተካሂዶ በነበረው ድህረ ምርጫ ውዝግብ በተፈጠረው ሁከት እና አለመረጋጋት መካከል ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ ተካሂዶ በነበረው ምርጫ በተፈጠረው የምርጫ ዘረፋ ውዝግብ ምክንያት መለስ በተቃዋሚዎቻቸው ላይ ከወሰዱት የግድያ ዕልቂት ኡሁሩ ኬንያታ እና የእርሳቸው ተከላካዮች ጠቃሚ ትምህርት ወስደዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኬንያታ እና ግብረአበሮቻቸው በ2005 በኢትዮጵያ የተካሄደውን የድህረ ምርጫ ውዝግብ ተከትሎ አምባገነኑ መለስ የምርጫ ተቃዋሚዎቻቸውን ለማጥቃት በማሰብ ከግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን ዘርን እና ጎሳን መሰረት አድርጎ በተደራጀ አጥቂ የወሮበላ ቡድን ሌላውን ጎሳ እና ሰላማዊ የህብረተሰብ ክፍል ዒላማ በማድረግ ግድያ እና ጭፍጨፋ አካሂደው እስከ አሁን ድረስ ከቃላት ማስጠንቀቂያ በላይ ምንም ዓይነት የወንጀለኛነት ተጠያቂነት ሳይኖርባቸው በጠብመንጃ አፈሙዝ ኃይል በስልጣን ወንበር ላይ ተንጠልጥለው መቀመጣቸውን ልብ ብለው ተመልክተዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ይኸ ጉዳይ ለእነርሱም ጠቃሚ እንደሚሆን በመገመትም ትኩረት ሰጥተው ተከታትለዋል፡፡ በእርግጥ መለስ ዜናዊ በቢሊዮን ዳላር በሚቆጠር እርዳታ እና ብድር ከምዕራቡ ዓለም እና ከአበዳሪ እና እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ሲንበሸበሹ እንጅ ሲከለከሉ ወይም ማዕቀብ ሲጣልባቸው አላዩም፡፡ እንዲያውም ከዚህ አልፎ መለስ በሰው ልጆች ላይ የእልቂት ወንጀልን የፈጸሙ ጭራቅ የአፍሪካ አምባገነን መሪ መባላቸው ቀርቶ በተቃራኒው አንበሳው የአፍሪካ መሪ እየተባሉ ሲንቆለባበሱ እና ሲወደሱ አሁሩ ኬንያታ እና ግብረአበሮቻቸው በውል አስተውለው ነበር፡፡ ይህ ከሆነ ታዲያ እነኬንያታ የመለስን የዕልቂት ተውኔት ለምን በኪበራ፣ በኪሱሙ፣ በናይቫሻ እና በናኩሩ አካባቢዎች ላይ አይተገብሩትም? ከሁሉም በላይ ለኢትዮጵያ ጥሩ የሆነው ሁሉ ለኬንያም ጥሩ ነገር ነው፡፡ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ከምርጫ ማግስት ጀምረው ህዝቦቻቸውን ገድለው እና ጨፍጭፈው ስልጣንን በምርጫ ካርድ ሳይሆን በጠብመንጃ አፈሙዝ ካረጋገጡ በኋላ ከምዕራብ አሀገሮች እና ከአበዳሪ እና እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የእርዳታ እና የብድር ልገሳ ይንበሸበሻሉ የሚለው አባባል እውነት አይደለምን?
በኬንያታ እና በግብረአበሮቻቸው የወንጀል ተጠያቂነት ላይ የሚደረግ ክልከላ፣

እ.ኤ.አ በ2007 በኬንያ የተደረገው ምርጫ ተከስቶ በነበረው ውዝግብ በሰው ልጆች ላይ ለተፈጸሙት ግድያዎች እና እልቂቶች ተጠያቂ ናቸው በሚል ኡሁሩ ኬንያታ እና ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ ላይ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ መመስረቱን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ክሱ ውድቅ እንዲደረግ እልህ አስጨራሽ የሆነ ትግል አካሂደዋል፡፡ በዚህም ሳይገደቡ እንዲያውም ማንኛውም የአፍሪካ ሀገር መሪ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት መጠየቅ የለበትም የሚል አሳፋሪ ዲስኩርን በማቅረብ የአፍሪካን ነጻ ህዝቦች የማረድ እና የመፍጀት መብታቸው እንዳይነካ ለማድረግ በነቀዘው አዕምሯቸው ስሌት በእውን የሚሆነውን ሳይሆን ቅዠታቸውን ገልጸዋል፡፡ ትንሿን ብዕሬን እና የኮምፒውተር መክፈቻ ቁልፎቼን በመጠቀም የአፍሪካ መሪዎች እየተባሉ የሚጠሩት አምባገነኖች በህዝቦች ላይ የሚሸርቡትን ደባ እና እልቂት በማጋለጥ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ የሰብዊ መብቶች ህጎች እና መርሆዎች እንዲከበሩ እና በአፍሪካ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ባለው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ በመሆን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሳሰማ ቆይቻለሁ፡፡
የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በኬንያታ እና በሌሎች ግብረአበሮቻቼው ላይ የመሰረተውን ክስ በማስመልከት ለመጀመሪያ ጊዜ ባወጣሁት ሙሉ ትችቴ ላይ የአፍሪካ ህብረት መሪዎች በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመውን ወንጀል ለህግ ለማቅረብ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማምከን ሲባል የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉዳዩን የዘር አደን በሚል ወደማይገናኝ አቅጣጫ ለመውሰድ እና ሁከት እና ግርግር በመፍጠር አጥፊዎቹ ለህግ እንዳይቀርቡ ለማድረግ ያቀረቡትን አሳፋሪ ድርጊት በጽኑ ተቃውሚያለሁ፡፡ እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 29/2013 “እውን ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በዘር አደን ላይ ነውን?“ በሚል ርዕስ ባወጣሁት ትችቴ በዚያው ዓመት ግንቦት ላይ ኃይለማርያም ዳሳለኝ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ በግልጽ ጦርነት የሚቀሰቅሱ ቃላትን ሲያዘንቡ ድርጊቱ አሳፋሪ እና አሳዛኝ መሆኑን በመገለጽ ተቃውሞዬን አሰምቼ ነበር፡፡
ኃይለማርያም የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በአፍሪካ ኬንያታን፣ ኦማር አልበሽርን እና ሌሎችን የአፍሪካ መሪዎችንም ለማጥቃት እየተንቀሳቀሰ ያለ “ዘር አዳኝ” ድርጅት ነው በማለት ከያዙት የስልጣን ቁመና ጋር የማይመጥን መሰረተቢስ የሆነ ውንጀላ እና ሰንፋጭ ቃላትን ሰንዝረዋል፡፡ ኃይለማርያም አሳፋሪ እና አስደንጋጭ በሆነ መልኩ እንዲህ በማለት አውጀዋል፣ “በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ ከተመሰረተባቸው ሰዎች ውስጥ 99 በመቶ የሚሆኑት ከአፍሪካ አህጉር ውስጥ ናቸው፡፡ ይህ ድርጊት የሚያሳዬው በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የአሰራር ስርዓት ላይ ችግር ያለበት መሆኑን ነው፣ እናም ያንን ድርጊት አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ ሂደቱ ቀድሞ ከነበረበት የበለጠ ወደከፋ ደረጃ በመሸጋገር አሁን ወደ ዘር አዳኝነት ለተውጧል፡፡“ እስቲ ጎበዝ ረጋ ብለን በሰከነ አዕምሮ ነገሮችን ሁሉ እናስተውል፡፡ ኃይለማርም ደሳለኝ የኢትዮጵያ መሪ እና የአፍሪካ ህብረት የተዘዋዋሪ የወቅቱ ሊቀመንበር ሆነው ከያዙት ስልጣን እና ከተቀመጡበት ወንበር የማይመጥን በሀገር ውስጥ የሚያራምዱትን የዘርኝነት ጭራቃዊ አስተሳሰብ ወደ አህጉር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ በማድረግ ይህንን የመሰለ ከበሰለ መሪ የማይጠበቅ እንቶ ፈንቶ ንግግር ሲያሰሙ ማዳመጥ በኢትዮጵያዊነታችን ልናፍር ይገባል፡፡ ያልሰለጠኑት እና ጭራቃዊ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው የአፍሪካ አምባገነን ሙሰኛ ስብስብ መሪ ተብዮዎች የወቅቱ ሊቀመንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ እርሳቸው እና የእራሳቸው ዘረኛ ፓርቲ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እንደሚያደርጉት የጎሳ አስተሳሰብ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤትም 99 በመቶ ክስ የተመሰረተባቸው አፍሪካውያን ናቸው የሚሉን ይህ ቁጥር በተንተን ይበል እና ለሁሉም ዓለም ኮታ ይሰጠው ነው? ሊገነዘቡት የሚገባው አብይ ጉዳይ 99 በመቶ ብቻ ሳይሆን መቶ በመቶም ቢሆን ለአፍሪካ አምባገነኖች የሚመጥናቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይደለም፡፡ መታዬት ያለበት የቁጥሩ ብዛት ሳይሆን ተጨባጭ የወንጀሎች መከሰት ነው፡፡ የአፍሪካ አምባገነኖች የሚሉን እነአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ፣ ኢስያ ወዘተ በህዝብ እልቂት ላይ ባይሳተፉም ኮታ ይሰጥ እና ይከሰሱ ከሚል አስተሳሰብ የሚመነጭ ከሆነ እንደዚህ ያለ ሰው ወይም ቡድን ወደ አዕምሮ ህክምና እንዲሄድ ማገዝ እንጅ ከእርሱ ጋር ትችት እሰጥ አገባ መግባት ፋይዳቢስ ይሆናል፡፡ ስለሆነም የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዘር አዳኝ ሳይሆን ወንጀለኛ አዳኝ መሆኑን ተገንዝባቸው ህዝብን ከመግደል እና ከመጨፍጨፍ መቆጠብ ነው፡፡
ኃይለማርያም ከ99 በመቶ ጉዳይ ጋር ምን እንዳቆራኛቸው የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 ፓርቲያቸው 99 በመቶ የሚሆነውን የይስሙላ ፓርላማ መቀመጫ ወንበር እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር 99.6 በመቶ የሚሆነውን አሸነፍኩ በማለት ይዟል፡፡ ስለዚያ ጉዳይ ለበርካታ ዓመታት ቅሬታዬን ሳሰማ ቆይቻለሁ፡፡ ሆኖም ግን ኃይለማርያም በድፍረት የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ ከመሰረተባቸው ሰዎች መካከል 99 በመቶ ከአፍሪካ ነው ብለው ይከራከራሉ! መግደል፣ ማሰር፣ ማሰቃዬት፣ ማፈን፣ ማጋዝ፣ መሰወር፣ ከህግ አግባብ ውጭ የሰውን ሀብት መዝረፍ፣ ዜጎችን ማፈናቀል፣ ወዘተ እስካላቆማችሁ ድረስ ነገ መቶ በመቶ ይሆናል፣ ተግባባን የድሁር አስተሳሰብ አራማጆች?!

የኃይለማርያም የ99 በመቶ የICC የአፍሪካውያን መከሰስ ቅሬታ ጉዳይ አንድ በዘራፊነቱ የሚታወቅን አሜሪካዊ ወሮበላ ዘራፊ አስታወሰኝ፡፡ ዘራፊው ዊሊ ሱቶን ይባላል፣ እናም ለምን ባንኮችን ትዘርፋለህ ተብሎ ሲጠየቅ የመለሰው መልስ እንዲህ የሚል ቀላል እና አስቂኝ ነበር፣ “ምክንያቱም ገንዘቡ ያለው እዚያ ስለሆነ ነው፡፡“ እንደዚሁም ሁሉ ለምንድን ነው የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት 99 በመቶ የሚሆኑት የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ወንጀል ተጠርጣሪዎች ከአፍሪካ የሚሆኑት? “ምክንያቱም እነዚህ ገዳዮች እና የሰብአዊ መብት ደፍጣጮች ያሉት እዚያ ስለሆነ ነው!”
ኃይለማርያም እራሳቸውን እና ፓርቲያቸውን ለማዳን እና ከፍትህ ለመደበቅ ሲሉ በኦጋዴን፣ በጋምቤላ እና በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2005 በኢትዮጵያ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረው ውዝግብ በመንግስት ታጣቂ ኃይሎች በጠራራ ጸሐይ በአደባባይ የተፈጸመውን ግድያ እና እልቂት ዘር አዳኝ ባለማለት ሸፍጥ ሰርተው ዞር ለማለት የሞከሩትን ደባ ለማጋለጥ ስሞግት ቆይቻለሁ፡፡
እ.ኤ.ጀአ ኦክቶበር 6/2013 “የአፍሪካን አምባገነኖች ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለመታደግ“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት የአፍሪካ መሪዎች እየተባሉ የሚጠሩት የዓለም አቀፉን የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ስም ጥላሸት በመቀባት በኬንያታ እና በሩቶ ላይ የመሰረተውን ክስ እንዲያቋርጥ ይህ ተፈጻሚነት ካላገኘ ግን ድርጅቱን በማጥፋት በአፍሪካ እንቀብረዋለን በማለት ያቀረቡትን አሳፋሪ ድርጊት እና የያዙትን አቋም ተቃውሜው ነበር፡፡ ኃይለማርያም በICC ላይ እያራመዱ ያሉትን ድሁር አስተሳሰብ ነቅሸ በማውጣት በጽናት እና በአይበገሬነት ስሞግት ነበር፡፡ ኃይለማርያም በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ ሲያደርጓቸው የነበሩትን ያልተገሩ እና መረን የለቀቁ የቃላት ውርወራዎች በተለይም ICC በአፍሪካ “ዘር አዳኝ” ነው በማለት ያቀረቡትን ኃላፊነት የጎደለው ክስ እና ICC አፍሪካን ዒላማ ያደረገ የፖለቲካ መሳሪያ በመሆን ከፍ ወዳለ ደረጃ በማሳደግ በአሁኑ ጊዜ ኬንያን ለመጉዳት እየተንቀሳቀሰ ነው በማለት ያቀረቧቸውን መሰረተቢስ የቃላት እና የሀረጎች ስብስብ የሆኑትን አረፍተነገሮች ሁሉ የዲፕሎማሲያዊ ንግግሮች አለመሆናቸውን እና ከተጨባጭ እውነታው ውጭ ያፈነገጡ ናቸው በማለት ጭምር ሳወግዝ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ኦክቶበር 10/2013 “ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ምስክርነት“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት ላይ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንደገና በእጅ አዙር ቅኝ ገዥነት በአፍሪካ ላይ ጭቆናውን ለመቀጠል መሳሪያ ሆኖ በመቅረብ የዘር አደና እያካሄደ ነው በማለት የቀረበውን ተራ አሉባልታ በጽኑ በማውገዝ ICC እና የICC ዋና ዓቃቤ ህግን ከዘር አዳኝነት እና ከእጅ አዙር ቅኝ ገዥነት ውንጀላዎች ነጻ የሆነ ለአምባገነኖች መቅሰፍት እና ለፍትህ ዋና ምሰሶ መሆኑን በመግለጽ በጽናት ተሟግቻለሁ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በኬንያታ እና በሩቶ ላይ በICC የተመሰረቱት ክሶች እንዲቋረጡ ካልተደረገ በስተቀር የሮም ስምምነትን በመጠቀም ከድርጅቱ በጅምላ እንወጣለን የሚለውን የማስፈራሪያ ንግግር እንዲያቆሙ ለአፍሪካ ህብረት ጥሪ አቅርቤ ነበር፡፡ የአፍሪካ መሪዎች ICCን ዘር አዳኝ እያሉ እርባናየለሽ ንግግር እያደረጉ እራሳቸውን ከማዋረድ በመቆጠብ ይልቁንም ሰብአዊ መብቶችን ባለመደፍጠጥ እና የህዝቦቻቸውን መብቶች በማክበር ጭራቃዊነትን እና ድህነትን መዋጋት እንዳለባቸው በአጽንኦ ጠይቄ ነበር፡፡ በአፍሪካ ሜዳ ላይ የሚገኙ አጋዘኖች አንበሳን ሲያዩ በፍርህት ቆፈን ውስጥ ወድቀው እንደሚፈረጥጡት ሁሉ እነርሱም በህግ እና በህግ ብቻ በመመራት ለሰብአዊ መብት ደፍጣጮች መቅሰፍት፣ መብቶቻቸው ለተረገጡ የጥቃት ሰለባ ህዝቦች ደግሞ መድኃኒት ሆኖ እያገለገለ ያለውን የፍትህ ምሰሶ የሆነውን ICCን ሲያዩ መደንበር እንደሌለባቸው መክሬ እና ሞግቼ ነበር፡፡ የአፍሪካን ህብረት አመራር የእውነተኞቹን የአፍሪካ ታጋዮች በእራስ የመተማመን ባህል ለማሳደግ ጥረት ማድረግ እንጅ በፍርኃት ቆፈን ውስጥ ተወሽቆ በመራድ ከትልቁ የነጭ ዘር አዳኝ ለማምለጥ መሸሽ እንደ አፍሪካ አጋዘኖች እንጅ እንደ መንፈሰ ጠንካራ እና ሀቀኛ የአፍሪካ መሪነት አያስቆጥርም፡፡
እ.ኤ.አ ኦክቶብር 13/2013 “የአፍሪካ ህብረት ከICC በጅምላ ለቆ የመውጣት ስልት“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት የአፍሪካ ህብረት አመራሮች እየተባሉ ለሚጠሩት ትኩረት በመስጠት በጅምላ እረግጦ በመውጣት (በሮም ስምምነት መሰረት ከድርጅቱ እንዳለ ለቆ መውጣት በሚል ሲያስፈራሩ የነበሩባቸውን ቃላት በመውሰድ የተጠቀምኩት) ለማስፈራራት የሚደረገውን ጥረት ትክክል እንዳልሆነ ግልጽ አድርጊያለሁ፡፡ በዚያው ወር በተደረገው አስቸኳይ ድንገተኛ ጉባኤ የአፍሪካ ህብረት መሪዎች በሚያሳፍር መልኩ በአንቀጽ 16 የሮም ስምምነት መሰረት የኬንያ ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም የሱዳን ፕሬዚዳንት የክስ ሂደት ጉዳይ እንዲራዘም የሚል ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በመቅረብ ውይይት ማድረግ እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ በሮም ስምምነት መሰረት እረግጠን በጅምላ እንወጣለን የሚለው ዕቅድ ወደቀ፡፡ ለዚሁ ጉዳይ የጸጥታው ምክር ቤትን ቀርበው ያናገሩ እና ከዚያ በኋላ በፍርሀት የተውት ይመስለኛል፡፡
እ.ኤ.አ ኦክቶበር 20/2013 “በአፍሪካ በላብ በመዘፈቅ ሲባንን የሚያድረው ማን ነው?“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት እንዲህ የሚሉትን የኬንያታን ንግግሮች እያሰብኩ እና እያነሳሁ ያለውን እውነታ ለመግለጽ ሞክሪያለሁ፣ ”ክቡራት እና ክቡራን ያለውን ቅዠት በተለይም በሀገሬ እና በእኔ እንዲሁም በምክትሌ ላይ ያለውን ቅዠት እና ይህንን ለመቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለእናንተ መንገር አልፈልግም፡፡“ ይልቁንም በኬንያታ በመጥረቢያ መመታት እና በጋዝ የተሞላ ቦምብ በማፈንዳት ቤቶቻቸው ሲቃጠሉ ማየት ነው ታላቅ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ሆኖ የሌሊት ቅዠት የሚያመጣ ብዬ የማስበው፡፡ ተሳስቼ ኖሯል፡፡ ለካስ ከመጥረቢያ መችዎች እና በጋዝ የተሞላ ቦምብ ሲያፈንዱ ከነበሩት ወንጀለኞች በስተጀርባ ሆነው ሲያቀነባብሩ የነበሩትም እንደዚሁ በሰሩት የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንወጀል ለህግ ቀርበው ተጠያቂ እንደሚሆኑ በማሰብ እነርሱም በሌሊት ቅዠት ሲባንኑ እና በነጭ ላብ ሲዘፈቁ ኖሯል፡፡ (የመጨረሻዋን እስትንፋስ እስከሚያገኙ ድረስ እነዚህ እጃቸውን በደም ታጥበው የተቀመጡ ወንጀለኞች በሌሊት ቅዥት ሲባንኑ እና በነጭ ላብ ሲዘፈቁ ማደራቸው ይቀጥላል የሚል እምነት አለኝ፡፡)
እ.ኤ.አ ጃኗሪ 2014 “ኬንያታ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፡ የዘገዬ ፍትህ እንደተካደ ይቆጠራልን?“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት በክስ ሂደቱ ላይ ተደጋጋሚ መዘግዬቶች፣ የቀጠሮ ማስተላለፍ ሁኔታዎች እና የውሸት መረጃዎች እንዲሁም የሀሰት ምስክሮች እየተቀነባቡሩ ይቀርቡ ስለነበር በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝን ስጋት ገልጨ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ምን እንደተሰማኝ ለመግለጽ ቃላት አልነበሩኝም፡፡ ሆኖም ግን ይህ ነገር በነጻ ሊሰናበት ይችላል ብዬ መንገር አልፈልግም፡፡ ሆኖም ግን የድርጊቱ አይቀሬነት ትንሽ ትንሽ ሽታ ከመሽተቱም በላይ በአሁኑ ጊዜ ጉልህ እና የጎረና ሽታ ይሸተኛል፡፡ ይኸ ነገር ኬንያታን ከICC እጅ አስወጥቶ ለመልቀቅ በመድረክ ላይ እየተሰራ ያለ ተውኔት ነውን? የሚሉ ትችቶቼን ሳቀርብ ነበር፡፡ የፈሩት ይደርሳል፣ የጠሉት ይወርሳል ሳይሆን አልቀረም፡፡
እ.ኤ.አ ኤፕሪል 2014 “ICCን መታደግ፡ ምስከሮችን ለመከላከል የተዘጋጀ ፕሮግራም“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት ተሸንፌ የተቀበልኩ መሆኔን አመንኩ፡፡ የዓለም ማህበረሰብ በኬንያታ እና በግብረአበሮቻቸው ላይ የተመሰረተው ክስ መቋረጡ የማይቀር መሆኑን የርዕሰ ወሬዎቹ የመጀመሪያ መወያያ ርዕስ እደረገ ማቅረብ ጀመረ፡፡ ሆኖም ግን ይህ ተውኔት አሁንም እንደሚቀጥል አምኛለሁ፡፡ ICCን ለመታደግ እና በሰብአዊ መብት ረገጣ ከፍትህ ፊት በማቅረብ ፍትህን ማግኘት እንዲቻል እና በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን ውጤታማ የሆነ የICC ምስክሮችን ደህንነት ለመከላከል የሚያስችል የዩናይት ስቴትስን አርአዓያ የተከተለ የመከላከያ ፕሮግራም መመስረት አለበት የሚል ሀሳብ አቅርቤ ነበር፡፡
በኬንያ የመጀመሪያው ቁጥር አንድ ሀብታም የሆኑት ኬንያታ ከግድያ፣ ከአስገድዶ መድፈር፣ ከማጋዝ ወንጀሎች አመለጡ…
ታላላቆቹ የገንዘብ ተቋማት በችግር ላይ ከወደቁ በኋላ የዩኤስ አሜሪካ እና አብዛኛው የዓለም ምጣኔ ሀብት እ.ኤ.አ በ2008 ከቀውስ ውስጥ በገባበት ጊዜ የዩኤስ አሜሪካ መንግስት የማንሰራራት የተሀድሶ እገዛ ለማድረግ ወሰነ፣ ምክንያቱም በጣም ታላላቅ ተቋማት ስለሆኑ መውደቅ አይኖርባቸውም የሚል እምነት በማሳደሩ ነበር፡፡ ህግን የሚጥሱትን ደመወዝ እየተከፈላቸው የሚሰሩትን እና ኮርፖሬሽኖችን ከሌሎች ኮርፖሬሽኖች እንዲሁም ከገንዘብ ተቋማት ጋር በጥብቅ የሚያስተሳስሩትን ወንጀለኞች መቅጣት አልፈለጉም፣ ምክንያቱም እነርሱን መቅጣት ማለት በዓለም የኢኮኖሚ ስርዓት ላይ አጠቃለይ የሆነ ጥፋት ማምጣት ይሆናል በማለት ተናገሩ፡፡
በእኔ አስተያየት ይህ አመክንዮ በተመሳሳይ መልኩ ለኬንያታም ጉዳይ ይሰራል፡፡ ኬንያታ በጣም ትልቅ፣ ሀብታም እና ከዓለም አቀፍ ኃያላን ጋር የተሳሰሩ ናቸው፡፡ የታይም መጽሔት ኡሁሩ ኬንያታን “ሀብታሙ ሰው” ብሏቸዋል፡፡ ኡሁሩ ኬንያታን በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በቁጥጥር ስር ማዋል እና ማሰር ለቀሪው አፍሪካ መጥፎ ሁኔታን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በኬንያታ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ መስጠት ICCን ወደ እያንዳንዱ የአፍሪካ ወሮበላ ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር በር እንዲያንኳኳ ያስገድደዋል፡፡ በኡሁኑ ጊዜ ICC እያንዳንዱን የአፍሪካ ወሮበላ አምባገነን በእርግጠኝነት መርምሮ በመያዝ ለፍትህ ሊያቀርበው ይችላልን? እንግዲህ ከዚህ አንጻር ለማለት የሚፈለገው በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ህግ እና በኡሁሩ ሙጋይ ኬንያታ መካከል በነበረው ጉዳይ ላይ የፍርድ ብይኑ መሆን የነበረበት “ገንዘቦች ተናገሩ፣ ኬንያታ በነጻ በረሩ” ነው፡፡

የኬንያታ ጉዳይ በICC ላይ በዉስጥ አጅ አንዲቆም ተደርጎ ይሆን?
የኬንያታን ጉዳይ ICC በቋሚነት የያዘው ለመሆኑ ለማወቅ በንቃት የሚከታተሉ እና የሚገምቱ ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡የኬንያታ ጉዳይ በICC ላይ በዉስጥ አጅ አንዲቆም ተደርግዋል ይላሉ። ከእነዚህ ውስጥ አይደለሁም፡፡ ሆኖም ግን ጥቂት የማነሳቸው ጥያቄዎች አሉኝ፡፡ እነርሱም፡ 1ኛ) የICC ዋና አቃቤ ህግ የሆኑትን ቤንሱዳን የሚያስፈራራው ኃይል የኬንያታን ጉዳይ በማዘግየት ቀስ በቀስ እንዲቋረጥ በማድረግ ጥሩ ነገር እንደተሰራ እና ለተመልካቹ አሳማኝነት እንዲኖረው አድርገዋልን? 2ኛ) የኡሁሩ ኬንያታ የክስ ጉዳይ የሆድ ቁርጠት፣ የጥርስ ቁርጥማት፣ የደረት ውጋት፣ የእራስ ምታት የሆነባቸው እና በድርጊቱ ሲቃሳቱ፣ ሲጮሁ፣ በጉጉት ሲከታተሉት እና ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ በመግለጽ ሲያጉተመትሙ የቆዩት የአፍሪካ ህብረት መሪዎች እየተባሉ የሚጠሩት የወሮበላ አምባገነን ስብስቦች በICC ዋና ቃቤ ህግ በሆኑት በቤንሱዳ ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር አስገድደዋቸዋልን? 3ኛ) የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ለጸጥታው ምክር ቤት እና ለICC ስለዘር አዳኞች ያቀረቡት አቤቱታ የኬንያታን የክስ ሂደት እንዲቋረጥ በማድረጉ ሂደት አስተዋጽ አድርጓልን? 4ኛ) የኬንያታ የክስ ሂደት ጉዳይ ከሚጠበቀው በላይ እንዲዘገይ መደረጉ የኬንያታን የክስ ጉዳይ በሀቀኝነት ለመመርመር የተደረገ ጥረት ወይስ ደግሞ ICC ማለት የሚሰራው በግልጽ ያልታወቀ ድርጅት ስለሆነ ከእርሱ ጋር መጫወት አቁሙ የሚል መልዕክት ለአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ለማስተላለፍ ተፍልጎ ነበር? ሁሉንም የተፈጸሙ እልቂቶች ማቀዝቀዝ የተሻለ ነው፡፡ 5ኛ) በአሁኑ ጊዜ የመረብ/internet ቴክኖሎጅ በተስፋፋበት ዘመን ከጨካኝ የአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖች ጋር በማበር መሳቅ የሚያዋጣ ሆናልን? 6ኛ) የኬንያት የክስ መቋረጥ የመጨረሻ መልዕክቱ፡ “በአሁኑ ጊዜ ኬንያታ እንዲሰናበት ተደርጓል፣ ሆኖም ግን ይህ ለሁሉም የአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖች ትምህርት ይሁን፣ በሌላ ጊዜ ግን ICC ምህረት የማያደርግ መሆኑን ዕወቁ“ ለማለት ይሆን?
በእኔ ቅን አስተሳሰብ የኬንያታ ክስ ጉዳይ ከነበሩት ምስክሮች ጋር አብሮ ለፍርድ ቤቱ መላክ እና የፈለገው ነገር ቢመጣ ማየት ነበር፡፡ ለሁሉም ሙሉ ክብር በመስጠት በነበረው ማስረጃ መሰረት ቤንሱዳ የኬንያታን የክስ ሂደት ከማቋረጣቸው ጋር አልስማማም፡፡
ዓቃቤ ህጎች በበጥባጭነታቸው የሚታወቁትን የወንጀል ተጠርጣሪዎች የህግ ሂደት በመከታተል በርካታ ጊዚያትን ማባከን የተለመደ ተግባራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል እ.ኤ.አ በ1988 በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ውስጥ በኒዮርክ የፌዴራል ፍርድ ቤት 20 በኒውጀርሲ የሉቼስ የወንጀል ቤተሰብን የወሮበላ የክስ ጉዳይ ዓቃብያን ህጎች ሲከታተሉት ከርመው በመጨረሻ በአሜሪካ ታሪክ ታላቁ የፍርድ ሂደት ተብሎ የተነገረለትን ጉዳይ በማቋረጥ የወንጀል ተጠርጥሪዎቹ በነጻ እንዲሰናበቱ ተደርጓል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የማፍያ ወንጀል ቤተሰብ ዋና አለቃ የሆነውን ጆን ጎቲን የጥፋተኝነት ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ሶስት ጊዚያት ክስ መስርቶበት ነበር፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ዓቃብያነ ህጎች ታላላቅ የክስ ጉዳዮችን ሲያጡ ማጣታቸው የእነርሱን ውሳኔ ጽናት ያለው እንዲሆን ያበረታቷቸዋል፡፡ ከስህተቶቻቸው ትምህርትን ይቀስማሉ እናም ጠንካራ፣ የሚማሩ እና ከቀድሞ የበለጠ ተናጋሪዎች ሆነው ይመጣሉ፡፡
በእኔ አመለካከት የኬንያታ የክስ ጉዳይ እንደዚያ ነበር መሆን የነበረበት፡፡ በነበረው ማስረጃ መሰረት የኬንያታን የክስ ሂደት ማካሄድ አስፈላጊ ነበር ምክንያቱም ያ ትክክለኛ እና ፍትሀዊ አሰራር ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኬንያታ ስማቸውን ለማደስ ጥሩ አጋጣሚ ይሆንላቸው ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ እ.ኤ.አ ማርች 2012 ኬንያታ እንዲህ ብለው ነበር፣ “እውነታው እንደሚወጣ ሙሉ እምነት አለኝ፣ እናም በጊዜ ሂደት ጥፋተኛ ያለመሆኔ ግልጽ ሆኖ ይወጣል፡፡“ እውነታው ነጥሮ ሊወጣ የሚችልበት ብቸኛው መንገድ የተሟላ የህግ ሂደት ሲኖር ነው፡፡ ፍትሀዊ የሆነ የህግ ሂደት ብቻ ነበር ኬንያታ የሚፈልጉትን ከጥፋተኝነት ነጻ ሊወጡ የሚችሉበትን ነገር ሊያመጣ ይችል የነበረው፡፡ ኬንያታ ከጥፋተኝነት ነጻ ሆነው ሊሰናበቱ እንደሚችሉ ግልጽ ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ በምንም ዓይነት መንገድ ቢሆን ስማቸውን ሊያድሱ አይችሉም ምክንያቱም ተመስርተውባቸው የነበሩ ክሶች ፍትሀዊ የሆነ የህግ ሂደትን ሳይከተሉ እንዲቋረጡ ተደርገዋልና፡፡ ኬንያታ በሰው ልጆች ላይ ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎች ከታሪክ ፍርድ ሊያመልጡ እንደማይችሉ ሊያውቁ ይገባል፡፡ የእርሳቸው ትሩፋት በሰው ልጆች ላይ በተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ረገጣ ክሶች መቋረጥ ምክንያት በፍጹም ለዘላለም ሊጸዳ አይችልም፡፡ የእርሳቸው የቤተሰብ ስም በክሶቹ መቋረጥ ምክንያት የነበራቸውን ክብር ያጣሉ፡፡ ኬንያታ የሰብአዊ መብቶችን መደፍጠጣቸውን እያወቁ የቀረበባቸው ክስ ፍትሀዊ ባልሆነ መልኩ መቋረጡን እያወቁ ወደ ቀብራቸው ይሄዳሉ፡፡ በቀብር ሀውልታቸው ላይ የሚጻፈው ጽሁፍ እንዲህ የሚል ይሆናል፣ “የሰብአዊ መብትን የጨፈለቁ ወንጀለኛ!“
ጥቂት የረዥም ጊዜ አንብቢዎቼ በኬንያታ ላይ ሲካሄድ የቆየው የክስ ሂደት በመቋረጡ ምክንያት ባሳየሁት ፈጣን እና ስሜታዊ ምላሽ ሳይደነቁ አይቀሩም፡፡ በጽናት እንደቆመ እንደ አንድ የመከላከል የህግ ባለሙያ በወንጀል ተጠርጥሮ ክስ ከተመሰረተበት ጎን በመቆም ወደ ሲኦል እንዲወርድ ወይም ደግሞ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ማድረግ አልነበረብኝምን? የእኔ የሚማርኩ ነጻ የመሆን፣ ከምንም ጥርጣሬ በላይ እውነት መሆኑን የማረጋገጥ እና የህግ የበላይነት መረጋገጥ የህግ መርሆዎች ምንድን ነካቸው?
በኬንያታ እና በሌሎች ተባባሪዎቻቸው የክስ ሂደት ጉዳይ መቀጠል እንደነበረበት ባለኝ ጽኑ አቋም ላይ የአስመሳይነት ባህሪ አላሳየሁም አላለሁ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ኬንያታ ፍትህን እንደ ጸሀይ እንዳትበራ እንዳደናቀፉ እና ገፍትረው ወደ ገደል እንደጣሏት ቅንጣት ያህል ጥርጥር የለኝም፡፡ እንደዚህ ያለ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የፍትህ ሂደቱ ቅደመ ሁኔታ አስተማማኝ የሆነ መሰረት ይሰጣል፡፡ ኬንያታ የሰው ልጆችን ሰብአዊ መብት ረግጠው አምልጠዋል ምክንያቱም እራሳቸውን ጥፋተኛ ለማድረግ የሚያስችል በቂ የሆነ ማስረጃ ባለመገኘቱ ብቻ አልነበረም፣ ሆኖም ግን ፍትሀዊ የሆነ ስራ ባለመስራታቸው ምክንያት ነው፡፡ አሁን በህይወት የሌለው አሜሪካዊው የማፊያ መሪ ጆን ጎቲ በምስክሮች ላይ ጣልቃ በመግባት እና ለዳኞች ጉቦ በመስጠት ፍትሀዊ ፍርድን እንዲነፈግ በማደረግ በሸፍጥ እና በደባ ነጻ ተብሎ ተሰናብቷል፡፡ እንደ ጎቲም ሁሉ ኬንያታም አድርገዋል፡፡
በግዥ፣ በማጭበርበር፣ ተማኝነት በሌለው ተሞክሮ እና በሚስጥራዊ አካሄድ በድብቅ የተገኘን የህግ አሸናፊነት ድል በምንም ዓይነት ሁኔታ በዘፈቀደ ላልፈው እና ልቀበለው አልችልም፡፡ ተከላካይ ምስክሮችን በሚያስፈራራበት ጊዜ፣ ተከላካይ ለምስክሮች እና ለዳኞች ጉቦ በሚሰጥበት ጊዜ እና በሂደት ላይ የነበረ ክስ እንዲቋረጥ ሲደረግ ይህ አካሄድ በምንም ዓይነት የህግ የበላይነትን አያመለክትም፡፡ ያ የፍትህ መጨንገፍን እና በፍትህ በእራሷ ላይ ወንጀል መስራትን በጉልህ ያመላክታል፡፡
ኬንያታ የክስ ሂደቱን መቋረጥ ፍትሀዊ እና አግባብነት ያለው ሆኖ አያገኙትም፡፡ ክሶቹ እንዲቋረጡ ተደርገዋል ምክንያቱም ምስክሮችን አስፈራርተው እና ጉቦ ሰጥተዋል፣ እንዲሁም መንግስታቸውን የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ህግ ማስረጃዎችን ሲጠይቁ ላለመስጠት ተቃውሟል፣ እናም ፍጹም ተባባሪነቱን ሳይሳይ ቀርቷል፡፡ እ.ኤ.አ ፌብሯሪ 2013 ዋና ዓቃቤ ህግ ቤንሱዳ ከኬንያታ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ሁሉ ጉቦ ተቀብለዋል ወይም ደግሞ የክስ ሂደቱ እንዲቋረጥ ለምስክሮቹ ጉቦ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ ቤንሱዳ እንዲህ የሚል መግለጫ ሰጥተው ነበር፣ “አራተኛው ምስክር እ.ኤ.አ ሜይ 2012 በተደረገለት ቃለመጠይቅ ክስ ከተመሰረተባቸው ከኡሁሩ ተወካይ የምስክርነት ጉዳይ እራሱን እንዲያገልል ተነግሮት የገንዘብ ጉቦ እንደተሰጠው እና እንደተቀበለ ግልጽ አድርጓል…ምስክሩ ጉቦ የመቀበሉን ዕቅድ ለማረጋገጥ የኢሜይል አድራሻውን እና የባንክ ቁጥሩን መስጠቱን ተናግሯል፡፡ እንደዚህ ያሉትን የተሰባሰቡ መረጃዎች በመያዝ የፍርድ ሂደቱ ይህንን ሰው በምስክርነት መጥራቱ አስፈላጊ አይደለም ብሎ አምኖበታል፡፡“ ዓቃቤ ህጓ ከኡሁሩ ኬንያታ መንግስት ስለ ክስ ጉዳዩ ሊያስረዱ የሚችሉ መረጃዎችን የመጠየቅ እና የማግኘት መብት እያላቸው ኬንያታ ማንኛውንም መንገድ ሁሉ እንዲዘጋ በማድረግ ከመንግስታቸው ምንም ዓይነት መረጃ እንዳይገኝ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ሲከላከሉ ቆይተዋል፡፡
ፍትሀዊ የፍርድ ሂደት ማለት በተቀመጡት ህጎች መጫወት እና ማሸነፍ ማለት እንጂ ህጎችን በመጣስ እና በፍትህ ላይ በማላገጥ የሚገኝ ፍትህ ማለት አይደለም! ኬንያታ የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዳይሰጥባቸው ለማድረግ ጊዜ ወስደው ታግለዋል፡፡ በእርግጥ በፍትህ አደባባይ ጥፋተኝነታቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ ነጻ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የዓእምሮ ፍርድ ኃጢያት የሰሩ ጥፋተኛ ሰው ናቸው፡፡ በእርሳቸው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ሰለባ በነበሩት በሺዎች በሚቆጠሩ ኬንያውያን/ት አዕምሮ ውስጥ ኬንያታ በትክክል የጥፋት ውሳኔ ሊተላለፍባቸው የሚገባ ጥፋተኛ ናቸው፡፡ በእራሳቸው ህሊና ኬንያታ እራሳቸው ጥፋተኛ እንደሆኑ በደንብ ያውቃሉ፣ ጥፋተኛ፣ ጥፋተኛ!!!
የአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖች በአሸሸ ገዳሜ ጭፈራ ላይ፣
የአፍሪካ የወሮበላ አምባገነን መሪዎች የኬንያታን የክስ ጉዳይ በጥንቃቄ ሲከታተሉ በመቆየት በአሁኑ ጊዜ ከትከሻቸው ላይ ታላቅ ሸክም እንደወረደላቸው በመቁጠር እፎይ እንደሚሉ ምንም ዓይነት ጥርጥር የለኝም፡፡ አፎዬ! ብለዋል በረዥሙ፡፡ የኬንያታ የክስ ሂደት ያለምንም መሰናክል በተሳካ ሁኔታ ቢካሄድ ኖሮ ለሚቀጥለው ባለወር ባለተራ ይሆኑ ነበር፡፡ አሁን ምንም የሚያስጨንቃቸው ነገር የለም፡፡ በኬንያታ የክስ ጉዳይ ላይ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የተታለለ ቂል ነው በማለት ድምጻቸውን ዝቅ አድርገው እየተጠቋቆሙ በለሆሳስ ድምጽ ይስቃሉ፡፡ አሁን ጊዜው የሻምፓኝ ጠርሙሶችን መክፈት እና እጅ ለእጅ በመያያዝ የአሸሸ ገዳሜ እስክስታውን እንዲህ በማለት ማቅለጥ ነው፡

በአጋርህ ቂልነት ዝፈን ጨፍር ደንስ፣
ከወጥመዱ ICC ስትል ጥርግ እብስ፡፡
የICC ጉጠት አያጠብቅ የላላ፣
በእኛ ብልህነት እቁቡ ተበላ፡፡
እንግዲህ ምን ቀርቶን ICCን ካሸነፍን፣
ሻምፓኝ መጠጣት ነው እስክስታ እየወረድን፡፡
የICCዋ ዋና ወይዘሮ ማንሱዳ፣
እኛን ልታሳስር ስትል ሰንዳ ሰንዳ፣
ሙቀጫውን ሆነች ተንከባላ ወርዳ፡፡
ስለዚህ እንጠጣ እንጨፍር እንደንስ፣
ICCን ቀብረናል ሁለተኛ ላይደርስ…

የአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖች የወንድማቸውን የኬንያታን ጉዳይ በመመልከት በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ የንቀት እና ደረትን የመንፋት እንቅስቃሴዎችን ያሳያሉ፡፡ ለዚህም ነው በህግ የበላይነት የምናምን ሰዎች ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ከምንም በላይ ICCን ለማዳን መረባረብ ያለብን፡፡
ICCን ከአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖች ማዳን እንችላለን?
እ.ኤ.አ ኦክቶበር 6/2013 “የአፍሪካን አምባገነኖች ከICC መታደግ“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችት ስለአፍሪካ አምባገነኖች ጤንነት የተጨነቅሁ በመምሰል ለመቀለድ ሞክሬ ነበር፡፡ አሁን በእውነት ICCን ከዓለም አቀፍ ወንጀለኞች እና በአፍሪካ በከፍተኛ የስልጣን ቦታ ላይ ከተቀመጡት ሸፍጠኞች (የICC ደጃዝማቾች) እንዴት መጠበቅ እንዳለብን ነው እያስጨነቀኝ ያለው፡፡
የኬንያታ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ሰለባ የሆኑት በእርግጠኝነት በICC ተሸናፊ መሆን አዝነው ቆመዋል፡፡ ICCን ማዳን ይቻላል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ የክስ ሂደቱ በICC ዋና ዓቃቤ ህግ እንዲቋረጥ መደረጉን ተከትሎ የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ እንዲህ የሚል ዘገባ አቅርቧል፣ “የኬንያን ድህረ ምርጫ ውዝግብ ተከትሎ በደረሰው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ዜጎች እስከ አሁንም ድረስ ፍትህ አልተገኘም የሚል ስሜት አላቸው፡፡ አብዛኞቹ ከዓርብ ዕለቱ እወጃ በፊት ጀምሮ በነበረው የICC የፍርድ ሂደት ላይ እምነት አልነበራቸውም“
ስለICC ፍጻሜ መቃረብ የሚቃወሙ እና መጥፎ ሁኔታ ይከተላል ብለው የሚተነብዩ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የኬንያታን የክስ ሂደት ጉዳይ በመመልከት ICC ከዚህ በኋላ ወድቋል እናም ታማዕኒነትን አጥቷል፡፡ ተሸርሽሮ አልቋል፣ የእዩልኝ የይስሙላ ፍርድ ቤት ሆኗል፡፡
በICC ላይ ያለኝ የእኔ እምነት እና በICC ዋና ዓቃቤ ህጓ እየተራመደ ያለው አካሄድ ተፋልሷል፣ ልዩነት እንጅ አንድነት የለውም፣ ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን ከICC በመውጣት መጓዝ አልጀመርኩም፡፡ ICC በሰብአዊ መብት ደፍጣጮች ተፈጽመው የተንሰራፉ ወንጀሎችን በመለየት፣ በመመርመር እና በሰው ልጆች ላይ ወንጀል የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን ወደ ፍትህ አደባባይ በማቅረብ ICCን ጠንክሮ እንዲወጣ እና የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን እንዲሁም ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ ማድረግ ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ ማለት ግን በICC ላይ ጠንካራ ጥያቄዎች ሊጠየቁ ወይም ሊቀርቡ አይችሉም ማለት አይደለም፡፡
ICC እና የICC ዋና ዓቃቤ ህግ ሊያከናውኗቸው የሚገቡ ጥቂት ስራዎች እንዳሉ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ICC 34 ዳኞች፣ ከ700 በላይ የሚሆኑ ሰራተኞች እና 166 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ በጀት አለው፡፡ ባለፉት 12 ዓመታት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ በማድረግ በስራ ላይ አውሏል፡፡ በዚህ አንድ ቢሊዮን ዶላር ICC ሁለት ብቻ የክስ ጉዳዮችን (ከዴሞክራቲክ ኮንጎ የጀርማኔ ካታንጋን እና የቶማስ ሉባንጋ ዲሎን) አጣርቶ የጥፋተኝነት ውሳኔዎችን ሰጥቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቅድመ የፍርድ ሂደት ጊዜ ስም ዝርዝራቸው ተመዝግቦ ተይዞ እራሳቸውን ደብቀው ያሉትን ጨምሮ ከሶስት ደርዘን የሚያንሱ ተጠርጣሪዎችን ጉዳዮች ብቻ ለመከታተል ተሞክሯል፡፡ የፎርቤ መጽሔት የሚከተሉትን አግባብነት ያላቸው ጥያቄዎችን ጠይቋል፡
በፍትህ ላይ ዋጋ ልታስቀምጥ አትችልም ሆኖም ግን በማንኛውም መለኪያ ለእያንዳንዱ የጦር ወንጀለኛ የፍርድ ብይን 500 ሚሊዮን ዶላር ማውጣት በጣም ግዙፍ የሆነ ገንዘብ ነው፡፡ እንደዚሁም ደግሞ እነዚህ 34 ዳኞች ቀኑን ሙሉ ምን ሲሰሩ ነው የሚውሉት? በሁለት የጦር ወንጀለኞች ላይ የተደረገው 12 ዓመታትን የወሰደ የምርመራ ጊዜ እና የጥፋተኝነት ውሳኔ ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞችን የሚያስደነግጥ ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡
የእኔ ጥያቀዎች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፡ 1ኛ) የእነዚህ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች ትንሽ መጠን እንኳ የሰብአዊ መብት ረገጣው ሰለባ የሆኑትን ተጎጅዎች መልሶ ለማቋቋም ተግባራት ማካካሻ ሊሆኑ ይችላሉን? 2ኛ) በሰብአዊ መብት ረገጣ ተዋናይ የሆኑትን አስፈሪ የሰብአዊ መብት ደፍጣጮች ማሰብ ብቻ ሳይሆን የሰብአዊ መብት ረገጣው ሰለባ ስለሆኑት ወገኖች ማሰብስ ጠቃሚ አይደለምን? 3ኛ) በፍትህ ላይ ዋጋ ልታስቀምጥ አትችልም የሚለው እውነት ከሆነ የሰብአዊ መብት ረገጣው ሰለባ በሆኑት ሰዎች ስቃይ ላይም ዋጋ ልታስቀምጥ አትችልም የሚለውስ እንደዚሁ እኩል ጠቃሚ አይደለምን?
ICC እና የICC ዋና ዓቃቤ ህግ ውጤታማ ለመሆን እና በኬንያታ የክስ ጉዳይ ላይ የተፈጸመውን ስህተት ለማረም ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ማድረግ አለባቸው፡፡ እነርሱም 1ኛ) የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የማፊያ ቡድኖች አለቆችን ለመቅጣት እንደሚያደርገው ሁሉ ICCም የአፍሪካን ወሮበላ አምባገነኖች በዚያው መልክ መቅጣት አለበት፣ 2ኛ) የዩስ አሜሪካንን የምስክሮች ጥበቃ ፕሮግራምን ዓይነት አሰራር በመከተል ምስክሮች ያለምንም ችግር ከዋና ዓቃቤ ህጉ እና ከፍርድ ቤቱ ጋር መገናኘት እና መተባበር እንዲችሉ ለማድረግ ውጤታማ የሆነ የምስክሮች መከላከያ ፕሮግራም አዘጋጅቶ በስራ ላይ ማዋል ናቸው፡፡
በእኔ እይታ የአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖች በዋናነት በንጹሀን ዜጎች ላይ ደባ የሚፈጽሙ ሸፍጠኛ ወንጀለኞች ናቸው፡፡ ቆሮዎቹ/ዋናዎቹ ወሮበላ አምባገነኖች ጠቅላይ ሚኒስትሮች እና ፕሬዚዳንቶች የሚሉ የማዕረግ ስሞችን ይይዛሉ፣ ሆኖም ግን ስብዕናቸው እና አሰራራቸው የደረጃ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር የማፊያ ወሮበሎች ወይም አለቆች ከሚሰሩት ጋር መሳ ለመሳ ናቸው፡፡ የማፊያ አለቆች ወታደሮቻቸውን በመሳሪያነት በመጠቀም እንደብረት ቀጥቅጠው እንደ ሰም አቅልጠው ይገዛሉ፡፡ የአፍሪካ ወሮበላ አምባገነንኖችም እንደዚሁ ናቸው፡፡ የማፊያ አለቆች በእረዳቶቻቸው ፍጹም ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር አላቸው፡፡ የአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖችም እንደዚሁ አላቸው፡፡ የማፊያ አለቆች ከጠላቶቻቸው ጋር የሚያደርጓቸው መስተጋብሮች ሁሉ ጭካኔ የተሞላባቸው ናቸው፡፡ የአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖችም እንደዚሁ ናቸው፡፡ የማፊያ አለቆች ከእነርሱ የወንጀለኛ ድርጅቶች በመላ አህጉሪቱ ውስጥ ትርፍ ለማግኘት ንግድ በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡ የአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖች ከማዕከላዊ ግምጃ ቤት ገንዘብ የመዝረፍ ፖለቲካን ያራምዳሉ፣ እናም በሀገር አቀፍ ደረጃ ባሉ የንግድ ድርጅቶች ላይ በሙስና ይዘፈቃሉ፡፡
እ.ኤ.አ ፌብሯሪ 2012 “ወሮበላ ዘራፊነት፡ ከፍተኛው የአፍሪካ አምባገነንነት“ በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ትችቴ ላይ ለመሞገት እንደሞከርኩት ዴሞክራሲ የህዝብ፣ ለህዝብ፣ በህዝብ አስተዳደር ከሆነ ወሮበላ ዘራፊነት ደግሞ የሌቦች፣ ለሌቦች፣ በሌቦች የተቋቋመ መንግስት ነው፡፡ በቀላል አነጋገር ወሮበላ ዘራፊነት በማጅራት መች ሌቦች እና ዘራፊዎች (ቀማኞች) በልካቸው ተሰፍቶ የተቋቋመ የማፊያ ቡድን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው አፍሪካ በግል በሚመሩ እና ደም ለጠማቸው የአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖች ጥቅም ብቻ የሚሰሩ የወሮበላ አምባገነንነት ስርዓት የተንሰራፋበት መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡ በወሮበላ ዘራፊነት ስርዓት የፖለቲካ ስልጣን መያዝ እና በስልጠን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለመቆዬት የሚደረገው ጥረት ለህዝቦች እድገት ሳይሆን ሀብትን ህገወጥ በሆነ መልኩ የህዝብን ገንዘብ በመዝረፍ እና ለብዙሀኑ ህዝብ ህልውና መሰረታዊ የሆኑትን ውስን ሀብቶች በመቀራመት ሀብት ለማግበስበስ እና እራስን በሀብት ለማበልጸግ ነው፡፡
የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የዩኤስ የፌዴሬራል ዓቃብያነ ህግን የአሰራር ስልት በመከተል በአፍሪካ የሰብአዊ መብት ደፍጣጭ ወንጀለኞች ላይ ሊሚደረገው ምርመራ እና የፍርድ ሂደት ስርዓት ላይ ወሮበላ ዘራፊዎችንም የማካተት ስራን ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል፡፡ የዩኤስ አሜሪካ ዓቃብያነ ህጎች በመጨረሻም የጎቲን የበታች ኃላፊ የሆነውን ሳልቫቶር ግራቮን በቅጽል ስሙ “ሳሚ ኃይለኛው/Sammy the Bull” እየተባለ ይጠራ የነበረውን ወሮበላ በማቅረብ አግባብተው እና አሳምነው የወሮበላዎችን ጸጥታ በመስበር በምስክርነት እንዲገባ በማድረግ ጎቲን በቀላሉ ያዙት፡፡ የICC ዋና ዓቃቤ ህግ በእውነት በሰብአዊ መብት ረገጣ የተጠረጠሩ በከፍተኛ የስልጣን ርካብ ላይ ያሉ እና ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ገጽታ ያላቸውን የአፍሪካ አምባገነኖችን ለመያዝ እና የህግ ሂደታቸው በአግባቡ እንዲታይ የሚፈልጉ ከሆነ ከአፍሪካ ገዥዎች መረጃ ሊሰጡ የሚችሉትን መርጠው መያዝ እና ተቀራርቦ በመስራት የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ የሚያመላክቱ በቂ የሆኑ መረጃዎችን ማሰባሰብ አለባቸው፡፡
በሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀል የተጠረጠሩ የአፍሪካ መሪዎችን ለመያዝ እና የፍርድ ሂደታቸውን ለማከናወን ዋነኛ ሆኖ ያለው እና ወደፊትም የሚኖረው ችግር ክስ ከተመሰረተበት ተጠርጣሪ ወንጀለኛ ሀገር ውስጥ ታማኝነት ያለውን ምስክር ፈልጎ ማግኘት እና ከተገኘም በኋላ እውነተኛውን ምስክርነት ለመስጠት ተባባሪ እንዲሆን አግባብቶ ከመያዙ ላይ ነው፡፡ የኬንያታ የክስ ጉዳይ እንደሚያሳዬው በአፍሪካ ምስክሮችን አግኝቶ በአፍሪካ ተወሽቀው ባሉ ፕሬዚዳንቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች እና በሌሎችም ላይ የምስክርነት ቃል ለመስጠት ፈቃደኛ ምስክሮች ፈልጎ ከማግኘት ይልቅ በገሀነም ላይ የበረዶ ኳስ ፈልጎ ማግኘት የቀለለ ይሆናል፡፡ ውጤታማ እና ጠንካራ የሆነ የምስክሮች ጥበቃ ፕሮግራም ያለመኖር አሁንም ወደፊትም የICC ስስ ብልት ወይም ደግሞ ደካማ ጎን ሆኖ ይቀጥላል፡፡
ቀደም ሲል “ICCን መታደግ፡ ምስክሮችን ለመከላከል የቀረበ የጥበቃ ፕሮግራም“ በሚል ርዕስ አቅርቤው በነበረው ትችቴ ያለኝን ሀሳብ አካፍዬ ነበር፡፡ ምስክሮችን መጠበቅ የICC ትልቁ ችግሩ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2013 የዓለም አቀፍ የህግ ባለሙያዎች ማህበር የዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ፕሮግራም (ዓህማ)፣ ”በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ምስክሮች፣ ምስክሮችን ለመጠበቅ፣ ለመደገፍ እና መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ የICC ተግዳሮቶች“ በሚል ርዕስ ዘገባ አቅርቦ ነበር፡፡ ዘገባው በICC የምስክርነት ጥበቃ ጥረቶች እና አገልግሎቶች ላይ መሰረታዊ የሆኑ ጉድለቶች እንዳሉ ጠቁሞ ነበር፡፡ እነዚህ ጉድለቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፣ “የመንግስትን ድጋፍ ከማግኘት አንጻር፣ ለምስክሮች ቁሳዊ እና ስነልቦናዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ኪደረገው ድጋፍ አኳያ፣ የሎጂስቲክስ ስራዎችን ከመስራት አንጻር፣ ጤናቸው በተጠበቀ መልኩ እስከ ሄግ ድረስ ከሚሄዱበት አኳያ እና ሰዎች ወደፊት ሊደርሱባቸው ስለሚችሉ አደጋዎች ወይም ደግሞ በምርመራ እና የፍርድ ሂደቱ በሚካሄድበት ወቅት ስለሚደረግባቸው ጣልቃገብነቶች“፡፡
የአፍሪካ ወሮበላ አምባገነኖች እና ሌሎችም በሰው ልጆች ላይ ወንጀልን በሚፈጽሙት ላይ እና የሮም ስምምነት ታማኝነትን ባተረፈ መልኩ እንዲቆይ እና ጠንካራ ሆኖ የአፍሪካን አምባገነኖች የሚቋቋም ሆኖ አንዲዘልቅ ከተፈለገ የICC ዋና ዓቃቤ ህግ እና ፍርድ ቤቱ እራሱ የምስክርነት ማስፈራራቶችን፣ በምስክሮች ላይ ጣልቃ መግባትን፣ ለምስክሮች ጉቦ መስጠትን እና ዳኞችን የተሳሳተ ብይን እንዲሰጡ ተጽዕኖ የመፍጠርን ጉዳዮች ሊከላከሉበት የሚያስችል ሌሎች ውጤታማ የሆኑ መንገዶችን መፈለግ አለባቸው፡፡ የICC ዋና ዓቃቤ ህግ እራሳቸው ተነሳሽነቱን በመውሰድ የዩኤስ አሜሪካ ምስክሮች ፕሮግራምን (WITSEC) በጥንቃቄ በመመርመር እና እንዴት ወደተግባር መለወጥ እንደሚቻል በማቀድ የICCን “ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የምስክሮች ጥበቃ ፕሮግራም“ ማዘጋጀት ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ WITSEC በተደራጁ ወንጀለኞች ከህግ ሂደቱ በፊት፣ እየተካሄደ እና ከፍርድ ሂደቱ መጠናቀቅ በኋላ ማስፈራሪያ ለደረሰባቸው እና በአደጋ ላይ ላሉ ምስክሮች ውጤታማ የሆነ ጥበቃ ይሰጣል፡፡ በዩኤስ ፕሮግራም ምስክሮች እና ቤተሰቦቻቸው አዲስ ማንነት እና ምዝገባ ይደረግላቸዋል፣ እንዲሁም የቦታ ለውጥ እንዲያደርጉ ይደረጋል፡፡ ፕሮግራሙ እ.ኤ.አ ከ1971 መተግበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ወደ 10 ሺ የሚሆኑ ምስክሮች እና ቤተሰቦቻቸው በWITSEC ፕሮግራም ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በሚያስደንቅ ሁኔታ 95 በመቶ የሚሆኑት ምስክሮች ደግሞ ወንጀለኞች የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡
የዩኤስ አሜሪካ መንግስት ለማፊያ ዝቅተኛ ኃላፊዎች፣ ለማፊያ መሪዎች፣ ለተደራጁ የወንጀለኛው ቡድን አማካሪዎች እና ወታደሮች የፍርድ ሂደት ላይ ቸልተኝነት የማሳየት እና WITSECን እንዲቀላቀሉት እንደሚያደርግ ሁሉ የICCም ዓቃቤ ህግ እንደዚሁ በተመሳሳይ መልኩ ምስክሮች ከነቤተሰቦቻቸው ወደ ሌላ ሀገር መዛወርን ጨምሮ የተሟላ ጥበቃ ለማድረግ እና በአፍሪካ አምባገነን የሰብአዊ መብት ደፍጣጮች ላይ ለሚመሰክሩ ታማኝ ምስክሮች የሚስብ ማበረታቻ ለመስጠት መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ያለICC የምስክርነት ጥበቃ ፕሮግራም ታማኝ የሆኑ ምስክሮችን ትብብር የማግኘት ዕድሉ በጣም የመነመነ ነው፡፡ WITSEC ገና በመጀመሪያው ስራውን ሲጀምር እና ታላላቅ ወንጀለኞችን ለመያዝ ሲባል ከሌሎች ወንጀለኞች ጋር ህብረት መፍጠር እና መረጃ ማግኘት የሞራል ዝቅጠት ነው በማለት በርካታ ሰዎች የተሰማቸውን ስሜት ገልጸው ነበር፡፡ ዓላማው መጨረሻውን ይወስናል የሚለውን የኮንግሬስ ፖሊሲ ተችተው ነበር፡፡ ማፊያዎች ከንግድ ስራ ውጭ ባይሆኑም እንኳ የሸፍጥ ህጎች እና የWITSEC ፕሮግራም በዩኤስ አሜሪካ በተለያዩ መልኮች በተደራጁ ወንጀለኞች ላይ ጠቃሚ የሆነ እድገትን አሳይቷል፣ እናም የተደራጁ ወንጀለኞች ደካማ እና ከፍተኛ አደጋ እንዳያደርሱ አስችሏል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በስልጣን ላይ ያሉ በርካታ የአፍሪካ የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀለኞች ማንም ቢሆን በእነርሱ ላይ የምስክርነት ቃሉን ደፍሮ እንደማይሰጥ እና ከሰጠም በኋላ በሀገር ውስጥ መኖር እንደማይችል እርግጠኛ በመሆን በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርደ ቤት እየሳቁ እየተሳለቁ ይገኛሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ICC ይህንን መሰረታዊ ትምህርት ከኬንያታ የክስ ጉዳይ መማር አለበት፡፡ ፍትህ ዋጋ የላትም ሆኖም ግን በፍትህ አልባነት ለተጎዱ የጉዳት ሰለባዎች ትንሽ ፍትህ መስጠት የምስክሮች መከላከል አንዱ መሰረታዊ ፕሮግራም ነው፡፡ ተለዋጩ የማስመሰያ የፍትህ ክፍል፣ ታማዕኒነት የሌለው ፍትህ በዓለም አቀፍ ደረጃ እና የፍትህ ክፍል ኢፍትሀዊነትን መናገር “ባዶ ጩኸት እና ብስጭት ምንም ነገር የማይገልጽ” ሸክስፒር እንዳለው፡፡
ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ እ.ኤ.አ በ2015 በሚካሄደው የይስሙላ ምርጫ በኋላ የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀል ሊፈጽሙ ይችላሉን?
የኬንያታ ጉዳይ በኡሁኑ ጊዜ ያለኝን ትኩረት የሳበኝ ሲሆን የዚህም ዓይነት ክስተት እ.ኤ.አ በ2015 በኢትዮጵያ ይካሄዳል እየተባለ በሚነገርለት ምርጫ እየተባለ በሚጠራው የይስሙላ ምርጫ ላይ የሰብአዊ መብት ረገጣ ወንጀል ሊፈጸም ይችላል፡፡ የ2015ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ እ.ኤ.አ በ2010 እንደተካሄደው ምርጫ ሁሉ የይስሙላ ምርጫ ነው፡፡ በ2010 ገዥው ፓርቲ፣ ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ 99.6 በመቶ የሚሆነውን የፓርላማ መቀመጫ አሸነፈ፡፡ የእኔ ስጋት ህወሀት በ2015 በሚካሄደው ምርጫ አራት አስረኛዋን የምርጫ ድምጽ ለማሟላት ሲል በሚያደርገው ጥረት የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ያካሂድ እና ምርጫውን መቶ በመቶ በማሸነፍ ድሉን ሊያበስር ይችላል፡፡
ለዚህ ስጋቴ ነባራዊ የሆነ መሰረት አለኝ፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች ኃይለማርያም አሁን በህይወት የሌሉትን የእርሳቸው መምህር እና ተምሳሌት የሆኑትን የመለስ ዜናዊን ራዕይ ለማስፈጽም ተግተው እንደሚሰሩ በተደጋጋሚ ይናገራሉ፡፡ እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 21/2012 ኃይለማርያም በግልጽ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይደረግ “የመስስን ራዕይ አስፈጽማለሁ” ነበር ብለው ያወጁት፡፡
እኔ እስከገባኝ ድረስ የመለስ ታላቁ ትሩፋት ጨለማ እና በደም የጨቀዬ እጅ ሲሆን 193 ያልታጠቁ ንጹሀን ዜጎችን በግፍ የገደሉ እና ሌሎች 763 ሰዎችን ደግሞ በተኩስ ያቆሰሉ ደም እንደ ውኃ የጠማቸው ሰው ነበሩ፡፡ አሁን ኃይለማርያም እና የእርሳቸው አሻንጉሊት አለቆች የመለስን በደም የተጨማለቀ ስብዕና እና አሻራ በመከተል ባልታጠቁ ዜጎች ላይ እልቂትን በመፈጸም የይስሙላውን የ2015 ምርጫ አሸነፍን ብለው ያውጃሉን?
ማስረጃው ግልጽ ይመስላል፡፡ ኃይለማርያም እና የእርሳቸው የህወሀት አለቆቻቸው የይስሙላውን ምርጫ መቶ በመቶ ለማሸነፍ እንዲህ የሚል ዕቅድ አውጥተዋል፡
ምዕራፍ አንድ – (የተጠናቀቀ) – ሁሉንም ነጻ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች እና ሁሉንም ነጻ ይህትመት ውጤቶች መዝጋት እና ጋዜጠኞችን፣ ዘጋቢዎች እን የማህበራዊ ድረ ገጽ ጸ ህፊዎችን ማሰር፡፡
ምዕራፍ ሁለት – (በመካሄድ ላይ ያለ) – ማዋከብ፣ ማስፈራራት፣ ማሰር እና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን እና ሌሎች ህወሀትን በሚቃወሙት ላይ ሁሉ ክስ መመስረት እና በቀጠሮ እያመላለሱ ማሰልቸት እና ማበሳጨት፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እና አመራሮች በሰላማዊ መልክ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ በመውጣታቸው ብቻ ተደብድበዋል፡፡ (የድብደባዎችን ተውኔት እና በቁጥጥር ስር የዋሉትን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ለማየት እዚህ ጋ ይጫኑ)፡፡
ምዕራፍ ሶስት – (የሚመጣ) አገሪቱን መበጥበጥና ተቅዋሚዎች አሸባሪዎች አገር አያጠፉ ነው ብሎ ሀዝቡን ማዋከብና መረበሽ ።
ምዕራፍ አራት – የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅና (በ”ምርጫ” ሶስት ወር ዉስጥ የሚደረግ ከዚአም በሁዋላ በሰራ የሚቀጥል ) ወታደራዊ አርምጃ መውሰድ።
ምዕራፍ አምስት – የመለስ ዜናዊን የሁለትሺ አምስት ምርጫ የጭፍጨፋ ትሩፋት በድጋሜ ማክበር።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ህዳር 8 ቀን 2007 ዓ.ም

Filed in: Amharic