>
2:31 am - Tuesday January 19, 2021

ዜጎችን በአደባባይ የሚደበድብ ‹‹መንግስት›› [በላይ ማናዬ]

∙የስቃይ ድምጾች በሦስተኛ ፖሊስ

ካዛንቺስ በተለምዶ እንደራሴ በተባለው ቦታ ቅዳሜ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም ረፋድ ላይ የሆነው እንዲህ ነው….

በቅርቡ በሰማያዊ ፓርቲ እና በሌሎች 8 ፓርቲዎች ስምምነት የተመሰረተው የ9ኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ ለአንድ ወር የሚቆይ የመጀመሪያ ዙር የትግል መርሃ-ግብር ማሳረጊያ ሊደረግ በነበረው የ24 ሰዓት የአዳር የተቃውሞ ሰልፍ ያሉ ሁኔታዎችን ለመዘገብ የሰልፉ መነሻ በሆነው የሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ተገኝቼ ነበር፡፡ ሰልፉ ይጀምርበታል ከተባለው ጊዜ መዘግየቱን አስመልክቶ ከቢሮ ወጣ ብዬ ሁኔታውን ለመቃኘት እየሞከርኩ ነበር፡፡ ድባቡ ፍጹም ዝብርቅርቁ የወጣ ነበር፡፡ ሰልፍ ለመውጣት የወሰኑት ሰዎች በቢሮው ውስጥ መሰናዷቸውን እያደረጉ በነበረበት ሰዓት ከቢሮ ውጭ ያሉ ፖሊሶችና ሲቪል የለበሱ የደህንነት ኃይሎች ደግሞ ቁጥራቸው በየደቂቃው እየጨመረ አካባቢውን መክበብ ተያይዘውት ነበር፡፡
Mambers of Semayawi party 1ሁኔታውን በአንክሮ ለተመለከተው በደቂቃዎች ውስጥ ‹ፍጥጫ› ሊጀመር እንደሚችል አመላካች ነበር፡፡ የ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ የእውቅና ደብዳቤ ለአስተዳደሩ አስገብቻለሁ፣ ስለሆነም ሰልፉን ለማድረግ ወስኛለሁ ሲል መንግስት በበኩሉ ሰልፉን ‹ፈቃድ አልሰጠሁትም› ሲል አስታውቆ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ትብብሩ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ‹ማሳወቅ› እንጂ ‹ማስፈቀድ› አይጠበቅብኝም ሲል አዋጅ ጠቅሶ ደብዳቤ ለአስተዳደሩ አስገብቶ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
በዚህ አለመግባባት ውስጥ ተሁኖ ነበር የአዳር ሰልፉ ሊካሄድ ሽርጉድ ይባል የነበረው፡፡ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ሰልፉ ከሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ውስጥ ተጀመረ፡፡ የሰልፉ አጀማመር በራሱ የሚገርሙ ነገሮች ነበሩት፡፡ ባላሰብኩት ፍጥነት ቢሮ ውስጥ የነበሩት ሰዎች በአንዴ ሰብሰብ ብለው ቀጥታ ከበር እንደወጡ መፈክሮችን እያሰሙ በፈጣን እርምጃ ወደፊት ተስፈነጠሩ፡፡ እርምጃየን በእነሱው ፍጥነት ልክ አስተካክየ መቅረጸ-ድምጼን አበራኋት፡፡ ‹‹ነጻነት! ነጻነት! ነጻነት!….›› እያሉ መፈክሩን አስተጋቡት፡፡
ፖሊሶች በሰልፈኞች ፍጥነት ግር የተሰኙ መሰሉ፡፡ ሰልፈኞቹ በጣም ብዙ ፖሊሶች በተሰደሩበት መንገድ ፊት ለፊት ቀጥታ ገሰገሱ፡፡ ይህኔ ፖሊሶች እርምጃ ለመውሰድ ተቁነጠነጡ፡፡ ሰልፈኞች መፈክራቸውን ለወጡ፤ ‹‹ፖሊስ የህዝብ ነው! ፖሊስ የህዝብ ነው! ፖሊስ የህዝብ ነው!›› እያሉ ለፖሊሶች መልዕክት ለማስተላለፍ ሞከሩ፡፡ ይህኔ ሁኔታዎች ከመቅጽበት ተለዋወጡ፡፡ እዛ የነበረው የ‹ፀጥታ ሰራተኛ› በሙሉ እንደንብ ሰልፈኞች ላይ ሰፈረ፡፡ እንደደነበረ ፈረስ ያገኙትን መርገጥ ጀመሩ፡፡ በሰልፈኞች ላይ የሆነው ሁሉ በእኔም ላይ ሆነ፡፡ የመጀመሪያው ዱላ ካረፈብኝ በኋላ ያለውን የዱላ ብዛት አሁን አላስታውስም፡፡ ብቻ ዘግናኝ ነበር!
በእርግጠኝነት በሂደቱ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ አንዳንድ ደስ የማይሉ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ቀድሜ ብገምትም፣ የሆነው ግን ከግምቴም በላይ እጅግ አሳፋሪ ድርጊት ነበር፡፡ ሴቶች እና እድሜያቸው ከ70 በላይ የሆኑ አዛውንቶች ርህራሄ አልተደረገላቸውም፡፡ እንዲያውም በእነሱ ላይ ሳይበረታ አልቀረም፡፡ ያ ሁሉ ፖሊስና ‹ሌሎች የፀጥታ ሰራተኞች› እንደአሸን የፈሉ ነበሩ፡፡ አንድም ዱላ ሳይሰነዝሩ ሰልፉን ማገት በተቻላቸውም ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ትዕዛዝ ይመስላል፤ ዜጎችን ደብድብ የሚል ትዕዛዝ! ያሳፍራል፣ ያሸማቅቃል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አቧራ ላይ ተጥለው ተደበደቡ፡፡ ሴቶች ሆዳቸውን ተረገጡ፡፡ አዛውንቶች ዘለፋ ከተሞላበት ኃይለ-ቃል ጋር ድብደባ ተፈጸመባቸው፡፡ ጋዜጠኛ ሰልፍ ላይ ተገኝተህ መዘገብ አትችልም ተብሎ ተቀጠቀጠ፡፡ አቶ ኤርጫፎ ኤርደሎ እና አቶ ቀኖ አባጆቭር (አባዬ) ተይዘው ከእኛው ጋር ሲንገላቱ ሳይ በእኔ ላይ የደረሰውን ሁሉ ረሳሁት፡፡ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው በሚሆኑ ‹የጸጥታ ሰራተኞች› የአሳፋሪው እርምጃ ሰለባዎች ሆኑ፡፡ በእርግጥ እነ አባዬ ስለእኛ እንጂ ስለራሳቸው አልተሰማቸውም፡፡ እኛ ደግሞ በእነሱ ላይ ስለሆነም የበለጠ እናዝን ነበር፡፡
ይህ ሁሉ ድርጊት በካዛንቺስ እንደራሴ አካባቢ ከመሆኑ ከደቂቃዎች በፊት ብዙ ዜጎች በመስቀል አደባባይ እና በሌሎች ስፍራዎች እየተያዙ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ መንግስት የተቃውሞ ድምጽ የሚያሰሙ ዜጎችን ለማፈን ቆርጦ እንደተነሳ ተገነዘብኩ፡፡ በዕለቱ የሆነው ተራ እስር አልነበረም፤ አፈሳ ነበር የተደረገው፡፡ ጅምላ እስር ነበር የተፈጸመው፡፡ ካዛንቺስ እንደራሴ አካባቢ የሆነው ግን በኃይልና በድብደባ የታጀበ ነበር፡፡ በድብደባ እራሱን ስቶ የቆየው ወጣት አቤል ኤፍሬምን ጨምሮ ብዙዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን በመኪና እንደእቃ እንድንጫን ተደርገን ካዛንቺስ አካበቢ ወደሚገኘው ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተጋዝን፡፡ ጣቢያ እንደደረስን በአንድ ቦታ እንድንሰበሰብ ተደርገን በፎቶ እና ቪዲዮ ካሜራ ቀረጻ ተደረገብን፡፡ የሚገርመው ራሱን ስቶ ወድቆ የነበረው አቤል ሳይቀር በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ህክምና ሳያገኝ ቀረጻው ይደረግበት ነበር፡፡ ግራ ቀኜን ዞር ዞር ብዬ የተያዙ ሰዎችን አስተዋልኩ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃልን ጨምሮ የተለያዩ የፓርቲ አመራሮች ተይዘዋል፡፡ አንዳንድ በዚያ ሲያልፉ የተገኙ፣ ስለጉዳዩ ምንም የማያውቁ ሰዎችም አብረው ተጀምለው ተይዘዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በሁኔታው ተደናግጠው የሚያለቅሱ ሰዎች ይገኙበት ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ሰልፍ ይሁን ሌላ የሚያውቁት ጉዳይ አልነበረም፡፡ እንዲሁ በቦታው ስለተገኙ ብቻ የተያዙ ነበሩ፡፡
ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እያለን ከመስቀል አደባባይ የተያዙ ሰዎችም በጣቢያው እንደሚገኙ ተገነዘብኩ፡፡ በጣም ብዙ ፖሊሶች ግቢውን ሞልተውታል፡፡ ብዙዎች ሰልፈኞችን ይሳደባሉ፤ አንዳንዶች አሁንም ለመደባደብ ሲቋምጡ አስተዋልኩ፡፡ ገረመኝ! ከመደብደብ የሚገኘው ትርፍ ምንድን ነው? ቀደም ብሎ በተያዝንበት ቦታ ላይ ብዙ ከተደበደብን በኋላም ቢሆን ድብደባው እንዲቆም ትዕዛዝ የሰጡት የየካ ክ/ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ዘውዴን በዓይኔ ፈለኳቸው፡፡ ግን ላገኛቸው አልቻልኩም፤ የእውነት ከድብደባው የሚገኘውን ትርፍ ማወቅ እፈልግ ነበር፡፡ ፍርሃቴ ልበለው አልያ ድንጋጤዬ ብን ብሎ ጠፍቶ ስለነበር ማናቸውንም አይነት ጥያቄ ልጠይቃቸው እፈልግ ነበር፡፡ የእውነት በወገኖቼ መካከል መገኘቴን እንኳ እጠራጠር ነበር፡፡ እንዴት ሰው አንዲት ጠጠር እንኳ በእጁ ሳይዝ፣ በሰላም ድምጹን ስላሰማ ብቻ ይህን ያህል ድብደባ በራሱ ወገኖች፣ በመንግስት ኃይሎች ይደርስበታል?
ስድስተኛ ብዙም አልቆየንም፤ የቪዲዮ እና የፎቶ ቀረጻው እንደተጠናቀቀ ወዲያውኑ ወደሌላ ፖሊስ ጣቢያ እንድንዛወር ተደረግን፡፡ የደረስንበት ፖሊስ ጣቢያ ፖፖላሬ ፖሊስ ጣቢያ ነበር፡፡ በዚህ ፖሊስ ጣቢያ ደርሰን ትንሽ ጊዜ እንደቆየን ቃላችንን እንድንሰጥ ተደረግን፤ ድጋሜ ፎቶ እንድንነሳ ሆነ፣ አሻራም ተነሳን፡፡ ይህን አድርገው ወደተለያዩ ክፍሎች ካጨቁን በኋላ ምሽት ላይ እንድንወጣ ታዘዝን፡፡ በዚህ ጊዜ በታሳሪዎች መካከል የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጡ ጀመር፡፡ አንዳንዱ ልንፈታ ነው ሲል ሌላው ደግሞ ወደ ካምፕ ሊወስዱን ነው ይል ነበር፡፡ ቀሪዎች ደግሞ ወደሦስተኛ ፖሊስ ልንወሰድ እንደሆነ ግምታቸውን ሰነዘሩ፡፡ እነዚህኛዎቹ ልክ ነበሩ፡፡ ጉዙው ወደ ሦስተኛ ነበር፡፡ በፖለስ መኪና እና ሞተር ሳይክል ታጅበን፣ የሳይረን ድምጽ በሚያሰማ ሞተረኛ መሪነት ሦስተኛ ፖሊስ (የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት) ተወሰድን፡፡
ወደሦስተኛ ፖሊስ እንድንዛወር የተደረግነው ታሳሪዎች ከመስቀል አደባባይ የተያዙትን አይጨምርም፤ ቁጥራችንም 44 ነበርን፡፡ ሌሎቹ እስከተፈቱበት ዕለት ድረስ እዚያው ፖፖላሬ ጣቢያ ቆይተዋል፡፡ ሦስተኛ ፖሊስ እንደደረስን በሁለት እንድንከፈል ግድ ሆነ፡፡ በአመራር ደረጃ ላይ ያሉት ወደቀዝቃዛ ክፍል (በረዶ ቤት) እንዲገቡ ሲደረጉ፣ ሌሎቹ ደግሞ በተለያዩ ክፍሎች (ጨለማ ክፍልን ጨምሮ) እንድንገባ ተደረግን፡፡ በዚያው በህዳር 27/2007 ዓ.ም ዕለት የሦስተኛ ፖሊስ ቆይታችን አሃዱ ተባለ፡፡ (በነገራችን ላይ አብዛኞቻችን ታሳሪዎች ለ24 ሰዓታት ያህል ምግብና ውሃ በአፋችን አልዞረም ነበር፡፡)

የስቃይ ድምጾች በሦስተኛ ፖሊስ

ሦስተኛ ፖሊስ አሁን ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት የሚገኝበት ስፍራ ነው፡፡ ቦታው ድሮ በሚታወቅበት ገጽታው ሳይሆን በቅርቡ በተገነባው ዘመናዊ ህንጻው ተጀቡኖ በግርማ ሞገስ የሚታይ ነው፡፡ ይህ ቦታ በፌደራል ፖሊስ የማዕከላዊ ምርመራ ጣቢያን ተጎራብቶ የሚገኝ ነው፤ (አንዳንዶች ከማዕከላዊ ጋር በምድር ዋሻ ይገናኛል ይላሉ፤ ይህን በተመለከተ እንደ ቀልድ ከእስር በወጣንበት ቀጣይ ቀን ሞባይል ስልኬን ልወስድ ወደጣቢያው ባመራሁበት ወቅት ለመርማሪዬ ፖሊስ በቀልድ መልኩ ጥያቄ አንስቼለት ነበር፡፡ መርማሪው ‹‹ማዕከላዊ እና እኛ አንገናኝም!›› ነበር ያለኝ በጥያቄየ ግር በመሰኘት አተያይ እያየኝ)፡፡ ሦስተኛ ፖሊስ በህንጻው ዘመናዊ ይሁን እንጂ በአሰራር ግን ብዙ ገራሚና አሰቃቂ ድርጊቶችን የሚያስተናግድ ቦታ መሆኑን በቆይታየ ለመታዘብ ችያለሁ፡፡

ወደ ጉዳዬ ስመለስ፣ ሦስተኛ የገባን ዕለት (ህዳር 27) በሌሊት ምርመራ ሲደረግብን ነበር ያደርነው፡፡ በፖፖላሬ ፖሊስ ጣቢያ የሰጠነውን ቃል በመድገም ሙሉ ማንነታችን ከመዘገቡ በኋላ ሌሎች ምርመራዎችም ተደረጉምብን፡፡ በምርመራው ወቅት ከሞላ ጎደል ድብደባ አልደረሰብንም፡፡ ምናልባትም በተያዙበት ወቅት የተደበደቡት ይበቃቸዋል ተብሎ ሊሆን ይችላል፡፡ በቀጣዩ ቀን ሁላችንም ፍርድ ቤት እንድንቀርብ የተደረግን ሲሆን ፖሊስ ፍርድ ቤቱን 14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠየቀ፤ የትብብሩ አመራሮች በበኩላቸው በሰልፈኞቹ በኩል የተፈጸመ አንዳችም ህገ-ወጥ ተግባር አለመኖሩን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ በነጻ እንዲያሰናብተን ጠየቁ፡፡ በተለይ የትብብሩ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ‹‹ኢህአዴግ በዘንድሮው ምርጫ ሙሉ ለሙሉ እንደምናሸንፈው ስላወቀ ነው ያሰረን፤ ይህም ህገ-መንግስቱን የጣሰ ነው›› ሲሉ አስረድተው ነበር፡፡
በዚሁ ፍርድ ቤት በቀረብን ጊዜ ብዙ አስገራሚ ነገሮችን ታዝቤያለሁ፡፡ በተለይ በታሳሪዎች በኩል የደረሰባቸውን ድብደባ ተከትሎ ህክምና አለማግኘታቸውን፣ እንዲሁም አመራሮቹ በበረዶ ቤት ስለሚገኙ ለጤናቸው አስጊ ስለሆነ የተሻለ አያያዝና ህክምና እንዲደረግላቸው ለፍርድ ቤቱ ባስረዱ ጊዜ የዕለቷ ዳኛ ያሉትን አልረሳም፤ ወደ ፖሊሶች ዞር ብላ ‹‹የጠየቁትን ህክምና እንዲያገኙ አድርጉ፣ ለእናንተም ለመቅጣት እንድትችሉ በህይወት ይቆዩላችሁ›› ነበር ያለችው፡፡ ጆሮዎቼን ማመን ነበር ያቃተኝ! ሁኔታው ሰው ቅጣት እንዲቀበል ብቻ ነው በህይወት መቆየት ያለበት ማለት ነው ብዬ ራሴን እንድጠይቅ አድርጎኛል፡፡
ፍርድ ቤት የነበረን ቆይታ አብቅቶ ወደ ሦስተኛ ተመለስን፡፡ ምርመራውም ቀጠለ፡፡ በምርመራ ወቅት ተመሳሳይና አሰልቺ ጥያቄዎች ነበር በተደጋጋሚ የሚቀርቡልን፡፡ በጣም አስገራሚው ነገር ደግሞ መርማሪዎቹ የኢሜልና ፌስ ቡክ አካውንት እስከ ይለፍ ቃል (password) ድረስ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው ነበር፡፡
ኢሜልና ፌስቡክ ይኖረኝ እንደሆን ጠየቀኝ፡፡ እንዳለኝ ነገርኩት፡፡ አስከትሎ አካውንቱንና ፓስወርዱን እንድነግረው ጠየቀኝ፡፡ ‹እንዴት ይሆናል፣ ይሄኮ የግል ጉዳይ ነው፤ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዴት ስጠኝ ትላለህ?› ስል መልሼ ጠየቅኩት፡፡ ፈቃደኛ ባለመሆኔ አንዴ በንዴት ሌላ ጊዜ በማባበል አይነት የጠየቀውን እንድነግረው ሞከረ፡፡ በአቋሜ መጽናቴን ሲያይ፣ ‹‹ይሄኮ የመንግስት አሰራር ስለሆነ ነው፤ ባትናገርም እኮ መንግስት ያውቀዋል›› አለኝ፡፡ አልመለስኩለትም፡፡ እሱም ‹‹ኢሜልና ፌስቡክ አካውንት አለው፣ ግን ለመናገር ፈቃደኛ አይደለም›› ብሎ የምርመራ መዝገቡ ላይ ሲያሰፍር አነበብኩ፡፡
ከምርመራ ክፍል ወጥቼ ሌሎች ታሳሪዎች ጋር ስንገናኝ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን እንዳስተናገዱ ነገሩኝ፡፡ ለመሆኑ ይሄ ምን አይነት የመንግስት አሰራር ይሆን?
የሦስተኛ የስድስት ቀናት ቆይታዬ ለእኔ ብዙ ነገሮችን እንድቃኝ ያስቻለኝ ስለነበር መታሰሬን በግድም ቢሆን ሳልወደው አልቀረሁም፡፡ ምናልባት ባልታሰር ኖሮ እኒያን ሁሉ ባለብዙ ታሪክ እስረኞች አላውቃቸውም ይሆናል፡፡ በታዳጊ ሃና ላላንጎ አስገድዶ መደፈር ምክንያት ተጠርጥረው በእስር ላይ ከሚገኙት አምስት ተጠርጣሪዎች እስከ በነፍስ ግድያና ሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው እስከገቡት ወንድሞች ጋር ብዙ ታሪኮችን አደመጥኩ፡፡ በምርመራ ወቅት የደረሰባቸውን እና እየደረሰባቸው ያለውን ሰቆቃም ለመገንዘብ ቻልኩ፡፡
ሦስተኛ ፖሊስ በዘመናዊ ህንጻ ውስጥ ኋላቀር የምርመራ ዘዴ የሚተገበርበት ስፍራ መሆኑንም ከብዙ ሰዎች ላይ በደረሰው በደል አየሁ፡፡ በምርመራ ወቅት በተፈጸመባቸው ድብደባና ሌሎች የማሰቃያ ዘዴዎች ምክንያት የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እዛ ቤት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በረዶ ቤት (የትብብሩ አመራሮች ታስረውበት የነበረው ቤት) አንዱ የምርመራ ወቅት ማቆያ አሰቃቂ ስፍራ ነው፡፡ ሌላው ‹ቆመህ እደር› የሚባል ሲሆን ተጠርጣሪዎች ለቀናት በዚህ ስፍራ ቆመው ውለው ቆመው እንዲያድሩ የሚደረግበት እንደሆነ በዚህ ሁኔታ ላይ ያለፉ ታሳሪዎች አጫውተውኛል፡፡ ብዙዎች በ‹ቆመህ እደር› ያለፉ ሰዎች የተለያዩ የአካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ሰለባ ይሆናሉ፡፡
እውነትም በሦስተኛ ፖሊስ ያለው የምርመራ ስልት እጅግ ኋላቀር ብቻ ሳይሆን ኢ-ህገ-መንግስታዊም ጭምር ነው፡፡ በዚህ ስፍራ ተጠርጣሪዎች ሰውነታቸው በስፒል ይጠቀጠቃል፣ ትልቅ ሃይላንድ ውሃ ተሞልቶ ብልታቸው ላይ ይንጠለጠላል፣ እግራቸውን ከፍተው ቆመው እንዲያድሩ ይደረጋል፣ ከፍተኛ ድብደባ ይፈጸማል፣ ከብዙዎቹ እስረኞች አፍ እንደሰማሁትና በአካላቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት በዓይኔ እንዳየሁት፡፡ በዚህ አይነት ምርመራ የሚያልፉ ሰዎች ምርመራቸው እስኪያልቅ (ለሳምንታት) ከቤተሰብ ጋር መገናኘት አይፈቀድላቸውም፡፡ በነገራችን ላይ በሰልፉ ወቅት የተያዝን እና በሦስተኛ የነበርን ወንድ እስረኞች በሙሉ ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ እንድንገናኝ አይፈቀድልንም ነበር፡፡
በሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ባለው ከባድ የማሰቃየት የምርመራ ዘዴ የተሰቃዩ ተጠርጣሪዎች አንዳንዶቹ ራሳቸውንም ለማጥፋት ሙከራ አድርገው ያልተሳካላቸውን አግኝቼ አናግሬያቸው ነበር፡፡ አንድ ተጠርጣሪ ራሱን ለማጥፋት የገፋፋውን ምክንያት እንዲህ ሲል አስረዳኝ፣
‹‹ምርመራው እጅግ ኢሰብዓዊ ነው፡፡ ራስህን ትጠላለህ፡፡ በቃ በግድ እመን ነው የሚሉት፡፡ ወንጀሉን ሳትፈጽም እዚህ ተጠርጥረህ ብትገባ በግድ ወንጀለኛ ነኝ በል ትባላለህ፡፡ ድብደባው ፋታ የለውም፡፡ በየዕለቱ ማታ ማታ እየወሰዱ ሶስተኛ ፎቅ ላይ ይቀጠቅጡሃል፡፡ ሰው አትመስላቸውም፡፡ በሀሰት የጠየቁህን አንድ ወንጀል ብታምንላቸው ሌላ ወንጀል ፈጥረው እመን ይሉሃል፡፡ በቃ መዝገቡ ክፍት ነው፤ አንተን ይጠብቃል እመን ይሉሃል፡፡ ከነገ ዛሬ ማሰቃየቱ ያበቃል ስትል ማብቂያ የለውም፡፡ ስለሆነም ከዚህ ሁሉ ስቃይ ለምን አልገላገልም ብለህ ታስባለህ፡፡ በዚህ ጊዜ ትዝ የሚልህ ደግሞ ራስን ማጥፋት ነው፡፡››
ይህ የብዙ ሰዎች አንደበት የተናገረው እውነታ ነው፡፡ ድርጊቱ በህግ ያልተፈቀደ ቢሆንም ምርመራው ግን በዚህ መልኩ እንደሚከናወን ብዙዎች አስረዱኝ፡፡ የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 19 (5) ስለተያዙ ሰዎች እንዲህ ይላል፣ ‹‹የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም፡፡ በማስገደድ የተገኘ ማስረጃም ተቀባይነት አይኖረውም፡፡››
ሌላ ተጠርጣሪ በምርመራ ወቅት ያጋጠመውን ገጠመኝ የግዱን እየሳቀ አወጋኝ፡፡ ‹‹ለምርመራ በገባሁበት ክፍል ውስጥ መርማሪዎቼ በዱላ ተቀበሉኝ፡፡ ከጥያቄ በፊት ዱላ ይቀድማቸዋል፡፡ ደብድበው ደብድበው ሲደክማቸው እኔን እግሬን ከፍቼ እንድቆም በማዘዝ እነሱ ኮምፒተር ላይ ፊልም እያዩ መዝናናት ጀመሩ፡፡ ከሰዓታት በኋላ ሽንት ቤት እንዲወስዱኝ ለመንኳቸው፡፡ ተሳለቁብኝ፡፡ እየቆየሁ እየቆየሁ ስሄድ ሽንቴን መቆጣጠር እንዳልቻልኩ በመግለጽ ‹ስለወንድ ልጅ አምላክ› ስል በድጋሜ ተማጸንኳቸው፡፡ ሊሰሙኝ አልቻሉም፡፡ ከዚያ ‹በቃ እዚሁ እሸናለሁ› ብዬ ሽንቴን ለቀቅኩት፡፡ በጣም ታፍኜ ስለነበር ሽንቴ እጅግ መጥፎ ጠረን ፈጠረ፡፡ ይገርምሃል ለእኔ ሳይሆን ለቢሯቸው አዝነው እንደውሻ አባርረው ከቢሮ አስወጡኝ፡፡››
ለመሆኑ እነዚህን የስቃይ ድምጾች ሰሚያቸው ማን ይሆን?

Filed in: Amharic