>

ፖሊስ እስረኞቹን ነጥሎ ለማጥቃት እየጣረ ነው ‹‹አብረውን የታሰሩት ካልተፈቱ ብቻችን አንወጣም፡፡›› ሴት እስረኞች

ነገረ ኢትዮጵያ

ፖሊስ በሰላማዊ ሰልፉ ወቅት ታፍሰው የታሰሩትን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎችን ነጣጥሎ ለማጥቃት ጥረት እያደረገ መሆኑን የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ በሰልፉ ወቅት ከታሰሩት መካከል በዛሬው ዕለት አብዛኛዎቹ ሴት ታሳሪዎችና የተወሰኑ ወንዶች ብቻ የመታወቂያ ዋስ አምጥተው እንዲወጡ የተነገራቸው ቢሆንም ታሳሪዎቹ ‹‹አብረውን የታሰሩት ካልተፈቱ በስተቀር ብቻችን አንወጣም፡፡›› እንዳሉ ተሰምቷል፡፡

በጉዳዩ ያነጋገርናቸው አቶ ዮናታን ተስፋዬ ‹‹ፖሊስ በተመሳሳይ ወንጀል ያዝኳቸው ያላቸውን ሰላማዊ ታጋዮች አንዱን በመታወቂያ ዋስ ውጣ ብሎ ሌላውን አስሮ በማቆየት ልዩነት የፈጠረው በዚህ አጋጣሚ ያሰጉኛል የሚላቸውን አመራሮችና ግለሰቦች ለማጥቃት ቀዳዳ እየፈለገ እንደሆነ ያሳያል›› ሲሉ ገልጾልናል፡፡

ለአዳሩ ሰልፍ ቅስቀሳ ላይ እያሉ በተመሳሳይ ጉዳይ ታስረው ከነበሩትን የሰማያዊ ፓርቲ አባላት መካከል አንዳንዶቹን በመፍታት ስጋት ይፈጥሩብኛል ብሎ የሚያስባቸውን በተለይም የፓርቲውን አመራሮች አሁንም ድረስ አስሮ እንደሚገኝ በመግለጽ ስልቱ የተለመደ ነው ያሉት አቶ ዮናታን አሁን በአንድ በኩል እየደረሰበት ያለውን ጫና ለማርገብ የተወሰኑትን በመፍታት አመራሮቹን ለማጥቃት የተደረገ ስልት ነው ብለዋል፡፡

ገዥው ፓርቲ በሰልፉ ላይ በተገኙት አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ በፈጸመው ጭካኔ ከደረሰበት ጫና በተጨማሪ ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ በሚፈጸምባቸው በደል አዲስ አበባ ፖሊስ (ሶስተኛ) የሚገኙት እስረኞች ዛሬ ታህሳስ 1/2007 ዓ.ም የርሃብ አድማ መጀመራቸውና ፖፖላሬ የሚገኙትም እስር ቤት ሆነው ትግላቸውን እንደሚያጠናክሩ መግለጻቸው ስርዓቱን ጫና ውስጥ እንደከተተው የገለጹት የህዝብ ግንኙነቱ ፖሊስ በህገ ወጥ መንገድ የያዛቸውንና ጭካኔ የፈጸመባቸውን ሁሉንም እስረኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና መነጣጠል ሊፈታ ይገባል ብለዋል፡፡

Filed in: Amharic