>

የምርጫ ሽርጉድ በ2015ቷ ኢትዮጵያ (ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም)

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ

በ2015 በሚካሄደው ፓርላሜንታዊ “ምርጫ” መቅረብና መወሰን ያለበት አንድ ጥያቄ ይህ ነው፤ “የኢትዮጵያ ህዝቦች አሁን እ.ኤ.አ 2014 ያሉበት የኑሮሁኔታ ከቀድሞ 2010 ወይም 2005 ከነበሩበት የኑሮ ሁኔታ ይሻላል ወይ?” ህዝቦች ካለፉት ዓመታት በተሻለ ሁኔታ ላይ የማይገኙ ከሆነ አንደ አሮጌ ሸማ መቀየር መቀየር ይኖርባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ሰዎችና እንደ አሮጌ ሸማ ናቸው፡፡ በየጊዜው ካልታጠቡና ካልተለወጡ ይበሰብሳሉ ይገማሉም፡፡ በጣም የሚገርም ነገር ነው! ምስኪን ኢትዮጵያውያ አንድ የበሰበሰ የገማ ሸማ ለሌላ 5 ዓመታት በጠቅላላው ለ25 ዓመታት ስትለብስ አያሳዝንም?

እ.ኤ.አ. ጁን 2010 በቅርቡ ያረፉት የአቶ መለስ ዜናዊ ፓርቲ የሆነው “ኢህአዴግ” (“የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር”) 99.6 በመቶ ድምጽ በማምጣት ድልን ተቀዳጀሁ ያለበትን እርባናየለሽ ንግግር በመተቸት የተሰማኝን ሀዘን ገልጨ ነበር፡፡ የእራስ በእራስ የእንኳን ደስ ያላችሁ ንግግራቸው፣ አቶ መለስ ያንን አስደንጋጭ የምርጫ ውጤት “ይህ የኢህአዴግ የጥረት ውጤት በአገራችን ላሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የማያሻማ መልዕከት አስተላልፏል“ በማለት ዲስኩራቸውን አሰምተዋል፡፡ በዚያ ንግግራቸው በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2010 በግልጽ ተመዝግበው የሚገኙት 79 የፖለቲካ “ፓርቲዎች” በጥቅሉ የአንድ ከመቶን ሩብ ቁራጭ አንክዋን የማይሞላ ድምፅ ማግኘት ያልቻሉትን የይስሙላ ፓርቲዎች ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2010 በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ምርጫውን ተዘዋውሮ ከተመለከተ በኋላ የምርጫ ውጤት እርባናየለሽነት እና ኢታማኒነት በማስመልከት በወቅቱ እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላልፏል፣ “የምርጫ ሂደቱ ዓለም አቀፍ የምርጫ ሂደት መስፈርትን አያሟላም፣ በተለይም የምርጫ ሂደቱ ግልጽነት እና ለሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲዎች እኩል የሆነ የፖለቲካ ጨዋታ ምህዳር የለውም፡፡“ የቀድሞው የቦትስዋና ፕሬዚዳንት በነበሩት ኬቱሚሌ ማሲሬ የሚመራው 60 አባላትን ያካተተው የአፍሪካ ህብረት (አህ) የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን ምርጫውን ተዘዋውሮ ከተመለከተ በኋላ ሀፍረት ሳያሳዩ አይን አውጥተዉ እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላልፎ ነበር፣ “ምርጫው ነጻ እና ፍትሀዊ ነበር፡፡ የታዛቢ ቡድኑ አባላት ገዥው ፓርቲ የተቃሚ ፓርቲ አባላትን ያስፈራራበት እና ያሸማቀቀበት ወይም ደግሞ የመንግስትን ንብረት በህገወጥ መልክ ለገዥው ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ስኬታማነት የተጠቀመ መሆኑን የሚያረጋግጥ ምንም ዓይነት ማስረጃ አላገኘንም፡፡“ የሚል የሸፍጥ የታዛቢነት ተልዕኮውን አከናውኗል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የአሜሪካው መንግስት (ዋይት ሃውስ) እንዲህ በማለት የአዞ እንባውን አንብቷል፣ “የዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን በኢትጵጵያ ስለተካሄደው የ2010 ምርጫ ባቀረበው ዘገባ መሰረት ምርጫው ዓለም አቀፍ መስፈርትን የማያሟላ በመሆኑ አሜሪካ ያላትን ስጋት ትገልጻለች“ በማለት የይስሙላ ዲስኩሩን ለማሰማት ሞክሯል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የገማ ሸማዋን አንደለበሰች ቁጭ ብላለች፡፡

የአለፉት ምርጫዎች የሙት መንፈሶች፤

እ.ኤ.አ በ2010 በተካሄደው ምርጫ አቶ መለስ 99.6 በመቶ ድምጽ በማግኘት “ድልን” ለመቀዳጀት በማሰብ የእራሳቸውን መንገድ በመከተል ፓርቲያቸው እንዲመረጥ በኃይል አስገድደዋል፣ ጉቦ ሰጥተዋል፣ አስፈራርተዋል እንዲሁም መራጩ ህዝብ በፍርሀት ቆፈን ውስጥ ተወሽቆ የመምረጥ መብቱን በአግባቡ እንዳይጠም አድርገዋል፡፡ ከገጠሩ ህዝብ ድምጽ ለመሸመት እና በግዳጅ ድምጽ ለማግኘት በሚል ሰይጣናዊ ስልት የውጭ የሰብአዊ መብቶችን እና የኢኮኖሚ እርዳታዎችን ከታለመላቸው ዓላማ ውጭ በማጠፍ ለእኩይ የምርጫ አላማቸው ማስፈጸሚያ እንዲውሉ አድርገዋል፡፡ የወጣቱን ታማኝነት ለመግዛት በማሰብ ለዘለቄታው የሚያቆዩ እና ለሀገሪቱም ሆነ ለወጣቶቹ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን የሚያስገኙ ስራዎችን ሳይሆን ለጊዜው ብቻ ከርስን ለመሙላት የሚያገለግሉ ተራ ስራዎችን ለማደል ተፍጨርጭሯል፡፡ የመንግስት ሀብቶችን እና ንብረቶችን ለእራሳቸው ፓርቲ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ዘመቻ እንዲውሉ አድርገዋል፡፡ የእርሳቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለመለየት እና ለማኮላሸት ሰፊ የቁጥጥር ፕሮግራሞች የስለላ እና የመረጃ አቀባይ መረቦችን የመዘርጋት ስራዎችን አደራጅተዋል፡፡

አቶ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ በ2010 በተካሄደው ምርጫ 99.6 በመቶ ድልን ለመቀዳጀት በተዘጋጁበት ወቅት እንደ ስልት የተጠቀሙት ለሰው ልጅ ክብር በማይሰጠው አፋቸው በኃይል የማስፈራሪያ ንግግር ማድረግ እና በተደባዳቢ እጃቻቸው ደግሞ ትልቅ ዱላን መጨበጥ ነበር፡፡ ቁጣን በማነሳሳት እና የጥላቻ ዘመቻን ዓላማ በማድረግ “እረብሻ ለማስነሳት” በሚሞክሩት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስዱ ያስፈራሩ ነበር፡፡ በመጨረሻዋ ደቂቃ እራሳቸውን ከምርጫ ሂደቱ የሚያገሉ እና ወጣቶች በየመንገዶቹ አደባባዮች በመውጣት ለአመጽ እንዲሰለፉ ቅስቀሳ የሚያደርጉ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ወደ እስር ዘብጥያ እንደሚወረውሯቸው በድፍረት ይዝቱ ነበር፡፡ የእርሳቸውን ምናባዊ 78 የሚሆኑ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው በዝረራ ካሸነፉ በኋላ የማስመሰያ የወይራ ዝንጣፊ ይዘው ቀረቧቸው፡፡ የተቃዋሚ አመራሮች የእራሳቸውን ጭራዎቸ በእግሮቻቸው መካከል የሚይዙ ከሆነ እና የአቶ መለስን እግር የሚስሙ እስከሆነ ድረስ የእርሳቸውን ምህረት እንደሚያገኙ መተማመኛ ተሰጣቸው፡፡ በቀጣይነትም አቶ መለስ እንዲህ አሉ፣ “በዚህ ምርጫ ወቅት ከህዝቡ የምርጫ ድጋፍ ባለማግኘት ስኬታማ ላልሆናችሁ እንዲሁም በፓርላማው መቀመጫ ይኑራችሁም አይኑራችሁም የህዝቡን ፍላጎት እስካከበራችሁ እና የአገሪቱን ህገመንግስት እንዲሁም ሌሎችን ህጎች እስካከበራችሁ ድረስ በሁሉም አገራዊ ጉዳዮች ላይ እናንተን እያማከርን እና እያሳተፍን የምንሰራ መሆናችንን ቃል እንገባለን፡፡ ይህንን ቃል የምንገባው ከእናንተ ጋር በአጋርነት መስራት ስላለብን ብቻ አይደለም… ሆኖም ግን እናንተ የመሳተፍ እና የመደመጥ መብት ስላላችሁ ጭምር እንጅ፡፡“ የአቶ መለስ ቃልኪዳኖች እነርሱን እንደበቀቀን ለመደጋገም ከሚያወጡት ትንፋሽ የበለጠ ፋይዳ የላቸውም፡፡ በዚያው በነበር የሚቀሩ ናቸውና፡፡

የአቶ መለስ ዜናዊ ሙት መንፈስ በ2015፣

የአቶ መለስ ዜናዊ ሙት መንፈስ፣ የሸክስፒርን ቃላት በመዋስ “በጨለማው የሲኦል ውስጥ ጢስ አንደምያንጃበበው “በኢትዮጵያ 2015 ምርጫ ላይ ያንጃብባል፡፡ አቶ መለስ በቀን ብርሀን የተዘረፉ እና የተጭበረበሩ ምርጫ ዋና ደራሲ ነበሩ፡፡ የምርጫ ማጨበርበሪያ እና የዘረፋ ጨዋታ ድርሳኑን እና መጽሀፉን የጻፉት የውርስ ስልጣኑን ከመጨበጣቸው በፊት በጫካ ውስጥ እንደነበሩ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 እርሳቸው እና ፓርቲያቸው በመጠኑም ቢሆን በእራስ የመተማመን በአዎንታዊ መልኩ ልዩ በመሆን የዴሞክራሲ በሩን ገርበብ አድርገው ለመዝጋት ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ከሁኔታዎች ወዲያውኑ ትምህርቱን በሚገባ ቀሰሙ፡፡ በምንም ዓይነት መልኩ ለትክክለኛ ተቃዋሚዎች ምንም ዓይነት ቀዳዳ የመስጠት ጨዋታ በፍጹም መደገም እንደሌለበት ጽኑ አቋም ያዙ፡፡ በዚያው ዓመት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ሁሉንም ቁንጮ የተቃዋሚ አመራር አባላትን፣ ነጻ ጋዜጠኞችን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመራሮችን በጅምላ አሰሩ፡፡

እ.ኤ.አ የ2015 አጠቃላይ የምርጫ ዘረፋ ወንጀል ስልቱ በአቶ መለስ የተቀመረው የተለመደው አሮጌው አሰራር ነው፡፡ አቶ መለስ ለኢኮኖሚው “የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ” ብለው እንዳዘጋጁት ሁሉ በተመሳሳይ መልኩ በፖለቲካውም መስክ እንደዚሁ “ታማኒነት የጎደለው የኢትዮጵያ የምርጫ ዘረፋ ዕቅድ (ታኢምዘዕ)“ በሚል እንዴት አድርገው ምርጫን መዝረፍ እንደሚችሉ የሚመሩበት መጽሀፍ ጽፈዋል፡፡ የታኢምዘዕ ዕቅድ አንድ ቀላል የሆነ ሀሳብን መተግበር ብቻ ነው፡፡ ይኸውም “ኢህአዴግ” ብቻ ነው ለኢትዮጵያ ተቆርቁአሪ!: “ኢህአዴግ” ብቻ ነው ለኢትዮጵያ ቁአሚ ተጠሪ! “ኢህአዴግ” የኢትዮጵያ ብቸኛ ተከላካይ፣ አቅራቢ እና ጠባቂ ነው! “ኢህአዴግ” በኢትዮጵያ ብቸኛ የመረጋጋት፣ ሰላም፣ ልማት እና መሻሻል ዋስትና ነው፡፡

የታኢምዘዕ ዕቅድ እ.ኤ.አ በ2015 የሚካሄደውን አገር አቀፋዊ ምርጫ መቶ በመቶ ማሸነፍ ነው፡፡ ከዚህ ባነሰ ውጤት ማሸነፍ የአቶ መለስን መታወስ ክብር ማሳጣት እና ዘለፋ ነው! ዕቅዱ ተግባራዊ መሆን የሚችለው የታኢምዘዕ ጠባቂ እረኞች በምርጫ ጨዋታቸው ላይ ያሉት አብዛኞቹ ተጫዋቾች ለማታለል እና ሁሉንም ተጫዋች ሰብስበው በመያዝ መቆጣጠር ከቻሉ ነው፡፡

የህወሀት (“ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ”) አገዛዝ በማስመሰያ ስሙ “ኢህአዴግ” እያለ እራሱን የሚጠራው ኃላፊነት የጎደለው የወሮበላ ቡድን ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለዓለም አቀፍ አበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች በአገሪቱ ሰላምን እና ስርዓትን ለማስያዝ እንዲሁም በዚህች አገር የእርስ በእርስ የብጥብጥ ቀውስ እንዳይመጣ አቅሙ ያለው እና ማድረግ የሚችል ብቸኛ ድርጅት እርሱ ብቻ እንደሆነ ለማሳመን እና በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለመቆየት ማናቸውንም ዓይነት ዕኩይ ተግባራት ከመፈጸም እንደማይቆጠብ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለም፡፡ ህወሀት (ይቅርታ “ኢህአዴግ”) ይህች አገር እንደ ሩዋንዳ ሁሉ ወደ የእርስ በእርስ ጦርነት ትዘፈቃለች በማለት የኢትዮጵያን ህዝብ እና በገንዘብ የሚረዱትን የውጭ ድርጅቶች ለማሳመን ጥረት ያደርጋል፡፡ “ከኢህአዴግ” ውጭ ይህች አገር በጎሳ መበጣጠስ፣ በግጭት እና እንደ ሱዳን ወደ ጦርነት ትገባለች በማለት የማስፈራሪያ ውዥንብራቸውን ያሰራጫሉ፡፡ “ከኢህአዴግ” ውጭ ወይም “ኢህአዴግ” በስልጣን ላይ እስካልቆዬ ድረስ “ጭራቆቹ” “አማራዎች” ስልጣንን ይነጥቃሉ፡፡ “ከኢህአዴግ” ውጭ “ኦሮሞዎች” ስልጣንን በመንጠቅ “አማራዎችን” ይቀጣሉ፡፡ “ከኢህአዴግ” ውጭ “ትግራውያን” “በአማራዎች” እና “በኦሮሞዎች” ጣምራ ስቃይ ይደርስባቸዋል፡፡

በብሄር ብሄረሰቦች ብዝሀነት የበለጸገችው የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ከቤታቸው እንዲፈናቀሉ ይገደዳሉ፣ መሬቶቻቸውን ይነጠቃሉ፣ እንዲሁም በቋንቋዎቻቸው የመናገር መብቶቻቸውን ያጣሉ እያለ “ኢህአዴግ” ያናፍሳል:: “ከኢህአዴግ”ከሌለ በመጥፎነቱ የሚታወቀው አስቀያሚው ደርግ ከተቀበረበት መቃብር እራሱን ብቅ ማድረግ ይጀምራል፡፡ ከኢህአዴግ ከሌለ “የሙስሊሙ ማህበረሰብ” የሻሪያ ህግ በኢትዮጵያ ላያ በኃይል እንዲጫን ያደርጋል፡፡ ከኢህአዴግ ከሌለ “የሙስሊሙ” እና “የክርስቲያኑ ህዝብ” በመካከለኛው አፍሪካ ሬፐብሊክ እንደሚስተዋለው እርስ በእርስ ይተራረዳሉ፡፡ “ከኢህአዴግ” ከሌለ በናይጀሪያ እንዳለው ቦኮሀራም የተባለው ጽንፈኛ አክራሪ የእስልምና ቡድን ሁሉ የኢትዮጵያ የእስልምና አክራሪዎች በኢትዮጵያ ላይ ታላቅ አደጋ ያመጣሉ፡፡ “ከኢህአዴግ”ከሌለ በሙስና እና በሌብነት እራሳቸውን ከበርቴ ያደረጉ ሙሰኞች እና መንታፊ ሌቦች ሀብታቸውን እንዲነጠቁ ተደርጎ ወደ እስር ቤት ዘብጥያ ወይም ወደ ግዞት ይወረወራሉ፡፡ “ከኢህአዴግ” ከሌለ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተሽመድምዶ ይወድቃል፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከ11-15 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ስታስመዘግብ የቆየችው ምዕናባዊ ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት ይቆማል፡፡ “ኢህአዴግ” ከሌለ በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የኢኮኖሚ ዕድገት አይኖርም፡፡ “ከኢህአዴግ” ከሌለ ሰማይ ተሰብሮ ይወድቃል፣ እናም ከዋክብቶቹ ከሰማይ ወደ ኢትዮጵያ ምድር ላይ ወድቀው ይንኮታኮታሉ፡፡ “ኢህአዴግ” ከሌለ ኢትዮጵያ አትኖርም!!!

በቀላል አነጋገር ሲገለጽ “የኢህአዴግ” የምርጫ ማሸነፍ ዕቅድ አሮጌውን የፍራቻ እና የጥላቻ ስልት በተግባር ላይ ማዋል ነው፡፡ ስልጣናቸውን ለመጠበቅ አማራዎችን ማስፈራራት ከቻሉ እና ኦሮሞዎችን በታላቅ ፍርሀት ውስጥ መወሸቅ ከቻሉ “ምርጫዉን” አሸንፈው በስልጣን ላይ ይቆያሉ፡፡ ኦሮሞዎች አማራዎችን እንዲጠሉ ማድረግ ከቻሉ “ምርጫዉን” አሸንፈው በስልጣን ላይ ይቆያሉ፡፡ የኦሮሞዎችን አዕምሮ በታሪክ ጸጸት ንትርክ ውስጥ በመዝፈቅ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ንጹሀን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን እልቂት እንዲረሱ ማድረግ ከቻሉ “ምርጫዉን” አሸንፈው በስልጣን ላይ ይቆያሉ፡፡ ትናንሽ የጎሳ ብሄረሰቦችን “ኢህአዴግ” ወደፊት የማይኖር ከሆነ ዓለም በእነርሱ ላይ ትጨልማለች በማለት ማሳመን ከቻሉ “ምርጫዉን” አሸንፈው በስልጣን ላይ ይቆያሉ፡፡ የክርስቲያኑ እና የሙስሊሙ ማህበረሰብ በፍርሀት፣ በጥላቻ እና እያንዳንዳቸው እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ ማድረግ ከቻሉ “ምርጫዉን” አሸንፈው በስልጣን ላይ ይቆያሉ፡፡ የእነርሱ ሀብታም ደጋፊዎቻቸው “ኢህአዴግ” የማይኖር ከሆነ በእርግጠኝነት ሀብቶቻቸውን እንደሚያጡ እና ወደ እስር ቤት ዘብጥያ እንደሚጣሉ ወይም ደግሞ ወደ ግዞት እንደሚወርዱ በማስፈራራት ማሳመን ከቻሉ “ምርጫዉን” አሸንፈው በስልጣን ላይ ይቆያሉ፡፡ ኢህአዴግ አበዳሪ ድርጅቶቹን እና ለጋሽ ድርጆቹን ኢህአዴግ በስልጣን ላይ የማይኖር ከሆነ በኢትዮጵያ ሰማይ እና ምድር ይገለባበጣል፣ ብሄራዊ ጥቅሞቻቸውም ይቀራሉ በማለት ለማሳመን (ለማታለል) ከቻሉ “ምርጫዉን” አሸንፈው በስልጣን ላይ ይቆያሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2015 በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ “ኢህአዴግ” የሚያሸንፍ ወይም የማያሸንፍ መሆኑን መጠየቅ ጸሐይ ከጠለቀች በኋላ ጨለማ ምድር ላይ ይሰፍናል ወይ እንደማለት ያህል ነው፡፡ ለእነርሱ ቀላል ነገር ነው፡፡ የምርጫ ዘረፋ ወንጀል የጨዋታ ደራሲነት አቶ መለስ መስርተዉታል: የእርሳቸው ቀሪ ሎሌዎች በአሁኑ ጊዜ ኃላፊነቱን ተረክበዋል፡፡ የወባ ትንኝ ተመራማሪው እና በብርሀን ፍጥነት ወደ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተሾሙት እንዲሁም እ.ኤ.አ እስከ 2015 ድረስ በዚሁ የስልጣን እርከን የሚቆዩትን የቴዎድሮስ አድኃኖምን ቀጣይ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር በማሞቅ ላይ የሚገኙት የይስሙላው “ጠቅላይ ሚኒስትር” ኃይለማርያም ደሳለኝ እርሳቸው እና ባልደረቦቻቸው የሚያከናውኗቸው ተግባራት ሁሉ በአቶ መለስ ራዕይ የሚመሩ (በጭፍን) ናቸው በማለት ሌት ከቀን እንደ በቀቀን ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 የአቶ መለስ ራዕይ ምርጫውን መቶ በመቶ ማሸነፍ ነበር፡፡ ያንን ራዕይ ሙሉ ለሙሉ በማሸነፍ ለማሳካት የአንድ በመቶ አራት አስረኛ ብቻ ቀርታቸዋለች፡፡

አቶ ኃይለማርያም እና ጓዶቻቸው በአሁኑ ጊዜ ከትልቅ ፈተና ውስጥ ወድቀው ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2015 የሚካሄደውን ምርጫ ቢያንስ በ150 በመቶ በማሸነፍ የአቶ መለስ ባለዕዳነታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ የምርጫ ማሸነፊያ ነጥብ ወሰናቸው ከወርቃማው 99.6 በመቶ ካነሰ በጣም አሳፋሪ ሁኔታ ነው የሚፈጠረው፡፡ ቢያንስ መቶ በመቶ በማሸነፍ እና አቶ መለስ በኩራት ሲታወሱ እንዲኖሩ ለማድረግ አቶ ኃይለማርያም እና ጓደኞቻቸው በ2010 ለገበሬው ከሰጡት ማዳበሪያ በላይ መለገስ አለባቸው፡፡ የገጠር ደኃ ቤተሰቦቸን ደምጽ ለመግዛት “ለምርታማነት ደህንነት መረብ የሚከፈለውን ክፍያ/Productive safety net payments” ቢያንስ በእጥፍ ማሳደግ አለባቸው፡፡ እንደዚሁም ወጣቶችን ለማታለል እና ታማኝነታቸውን በማረጋገጥ ድምጻቸውን ለማግኘት እንዲቻል “የማይክሮ ፋይናንስ” ብድር መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለከተማ ኗሪዎች ኮንዶምኒየሞችን ለመስጠት ብዙ የባዶ ቃልኪዳን ተስፋዎችን መስጠት አስፈላጊ ይሆንባቸዋል፡፡

በሚቀጥሉት 11 ወራት ውስጥ “ኢህአዴግ” እራቁት ገላ ካገኘች የወባ ትንኝ ስራ የበለጠ ስራ ጥድፊያ አለባቸው :: በጥንቃቄ፣ በብልሀት እና ቀስ በቀስ በርካታ የጎሳ ቡድኖችን እርስ በእርስ በማጋጨት እና ጥላቻ እንዲኖር በማድረግ እና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ደግሞ ድምጽ ለመግዛት በመርጨት የታኢምዘዕ ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ፡፡ ቀደም ሲል ስኬታማ የሆኑበትን የከፋፍለህ ግዛ ስልት አጠናክረው ይቀጥሉበታል፡፡ ለሩብ ምዕተ ዓመት የጎሳ ጥላቻ እሳት ላይ ነዳጅ በማርከፍከፍ ስኬታማ ሆነዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሰላማዊ የሆኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን በመግደል በጎሳ ጥላቻ ላይ ነዳጅ በመጨመር ላይ ይገኛሉ፡፡ (ከሳምንት ገደማ በፊት ቢቢሲ በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል ከመናገሻ ከተማዋ በስተምዕራብ በኩል በ80 ማይሎች ርቀት ላይ በምትገኘው አምቦ ከተማ 47 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን መግደሉን መዘገቡን ልብ ይሏል)፡፡ በክርስትና እና በእስልምና እምነቶች ተከታዮች መካከል የጥላቻ ነዳጅ ለማርከፍከፍ በጣም አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን ይህንን ዕኩይ ምግባር ከመፈጸም አይቦዝኑም፡፡ በቆሻሻ እና እርባናየለሽ ማታለሎች የተካኑ ናቸው፡፡ የሀገር ውስጥ ገንዘብ አዳዮቻቸው ማለትም ኢኮኖሚውን አንቀው የያዙት የሙስና መጋቢ ወፍራም ዝሆን ደጋፊዎች እገዛ ለማድረግ በመዘጋጀት ወደ እነርሱ ይጎርፋሉ፡፡ ከዚህም በላይ ከታኢምዘዕ ጠባቂዎች ጋር አንድ ዓይነት ዕጣፈንታን ይጋራሉ፡፡ በተፈጥሮ አበዳሪ እና ለጋሽድርጅቶች እዚህም እዚያም በመርገጥ በመንተባተብ ስለነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ ለምንም የማይውሉ የይስሙላ ቃላትን ያዥጎደጉዳሉ፡፡ እናም የሚሰጡትን የውጭ እርዳታ እና ብድር ከህግ አግባብ እና ከታቀደለት ዓላማ ውጭ ለፓርቲ ፖለቲካ ጥቅም ሲያውሉት አይተው እንዳላዩ በመሆን ጆሮ ዳባ ልበስ ይላሉ፡፡

ለመሆኑ ተቃዋሚዎችስ ምን እያደረጉ ነው?

የምን ተቃዋሚ?! የገዥው አካል ዘዋሪዎች ተቃዋሚዎችን ከመናቅ የዘለለ ምንም ነገር የላቸውም፡፡ በተደጋጋሚ እንደምናገረው አቶ መለስ እና አጫፋሪዎቻቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የእነርሱ የምሁርነት የበታች እንደሆኑ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኦባማ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ የሆኑት ሱሳን ራይስ እንዳረጋገጡት አቶ መለስ የሚቃወሙዋቸውን ሁሉ “የማይረቡ እና ደደቦች” ናቸው ብለው ያምኑ ነበር፡፡ አቶ መለስ ለህዝብ ይፋ መግለጫ በሚሰጡበት ጊዜ ከሌሎች የበለጡ መስለው ለመታየት፣ ከሌሎች የበለጠ የሚያስቡ በመምሰል፣ ከሌሎች የበለጠ ጥቅም የሚያሳድዱ መሆናቸውን፣ ከሌሎች የበለጠ ተጫዋች ለመምሰል፣ በማታለል ከሌሎች በልጦ ለመታየት መሞከር እና ተቀናቃኞቻቸውን ስልታዊ በሆነ መንገድ በማንኛውም ቀን መትተው መጣል የሚችሉ መሆናቸውን ግልጽ አድርገዋል፡፡ ችለዋልም፡፡ የአቶ መለስ ደቀመዛሙርት በአሁኑ ጊዜ በጌታቸው አስተህምሮ እና ራዕይ ይመራሉ ፡፡ እንደ እርሳቸው ሁሉ እነዚህ ደቀመዝሙሮቹም ተቃዋሚ ኃይሎች ለመስራት የተኮላሹ፣ ተነሳሽነት የሌላቸው፣ ለምንም የማይጠቅሙ እና ለእነርሱ ስልጣን ምንም ዓይነት የስጋት ምንጭ ሊሆኑ እንደማይችሉ እምነት አላቸው፡፡ የእነርሱን የስልጣን ተቀናቃኞች ብዙ ክትትል፣ ስነስርዓት እና ቅጣት እንደሚያስፈልጋቸው ወጣት አጥፊዎች በመቁጠር በአንድ መስመር ላይ ለማሰለፍ ይሞክራሉ፡፡ እንደ ልጆች ሁሉ ለአንዳንዶቹ ከረሜላ–ስራ፣ መኪኖች፣ ቤቶች–እና ሌሎችም ለእነርሱ ድጋፍ ሊያሰጡ የሚያስችሉ ባይሆኑም አፍ የሚያሰይዙ ወይም ደግሞ ጸጥ ሊያስደርጉ የሚችሉ ነገሮች ይሰጧቸዋል፡፡ ሌሎችን በዚህ መንገድ ሊገዙላቸው የማይችሉትን ደግሞ ያስፈራሯቸዋል፣ ያስሯቸዋል፣ ያሰቃዩአቸዋል ወይም ደግሞ ማቋረጫ በሌለው መልኩ ክትትል እና የማሸማቀቅ ስራ ይፈጸምባቸዋል፡፡

እውነታው ሲመረመር ግን በአገሪቱ ውስጥ ያሉት የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች እና በውጭ ያለው የዲያስፖራው ማህበረሰብ በሚያስቸግር ሁኔታ ተከፋፍሏል፡፡ ጥቂት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በአገሪቱ ከተደቀነው አደጋ ይልቅ የእነርሱ ስልጣን ያሳስባቸዋል፡፡ ለጋራ መድረክ የሚያገለግል በመተባበር የጋራ የሆነውን ጠላት ተባብሮ ለመጣል ቅን የሆነ ተነሳሽነቱ እና ፍላጎቱ የላቸውም፡፡ የተቃዋሚው ማህበረሰብ “የኢህአዴግን” ያልተገደበ የገንዘብ ምንጭ ጫና ለመቋቋም የሚያስችል የገንዘብ የሀብት እጥረት ይታይባቸዋል፡፡ ተቃዋሚ ጋዜጠኞች ይታሰራሉ፣ ማስፈራራትም ይደረግባቸዋል፡፡ ወጣት ጦማረኞች እንኳ በማይረባ ሽብርተኝነት ስም ለእስር እና ለስቃይ ይዳረጋሉ፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ የለም፡፡ በከተማ የተደራጀ ማንኛውንም ዓይነት የተቃውሞ ምልክት ለማስወገድ በማሰብ ገዥው አካል በልማት ስም ከቀያቸው ያፈናቅላል፡፡ ነገሮች ገፍተው ከመጡ የአቶ መለስ ሎሌዎች አለቃቸውን መሪ ዕቅድ ተግባራዊ ከማድረግ አይመለሱም፡፡ አቶ መለስ በአንድ ወቅት ለአንድ የአሜሪካ የዲፕሎማት ሰው እንዲህ ሲሊ ተናግረው ነበር፣ “ተቃዋሚዎችን ባለን ኃይል ሁሉ እንደመስሳቸዋለን፡፡“ ህወሀት (ይቅርታ ኢህአዴግ ለማለት ፈልጌ ነው) የ2015ቱን “ምርጫ” በመግፋት ወይም በመደቆስ “ያሸንፋል”::

ትልቁ ተዋቂ የማይታወቁ፣ የማይታወቅ የማይታወቅ?

የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የቀድሞው የመከላከያ ጸሀፊ የነበሩት ዶናልድ ሩምፊልድ አንዳንድ ጊዜ የየንቆቅልሽ የሚያደናግር ንግግር ማድረግ ይወዳሉ፡፡ እንዲህም ብለዋል፣ “የምናውቃቸው ነገሮች አሉ፣ የምናውቃቸው ነገሮች አሉ፣ እኛ እራሳችንም ታዋቂ የማይታወቁ እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ይህም ማለት የምናውቃቸው የማናውቃቸው ጥቂት ነገሮች አሉ፡፡ ሆኖም ግን የማናውቃቸው የማናውቃቸውም ነገሮቸ አሉ፣ አንዳንድ የማናውቃቸው ነገሮች የማናውቃቸው ናቸው፡፡”

አቶ መለስ በ”ኢህአዴግ” (እራሳቸው ብቻቸውን ነበር “ኢህአዴግን” የመሰረቱት)፡፡ የ”ኢህአዴግ” ውስጥ አእምሮም ጡንቻም ነበሩ፡፡ ዋናው ገዢ ብቻ አልነበሩም: ዋና የስልት ነዳፊ ዋና አዛዥም ነበሩ፡፡ ሁሉም የአቶ መለስ ሎሌዎች የጭንቅላት አቅም ተደምሮ የእርሳቸውን ጭንቅላት አራት አስረኛ አይሆንም:: በአሁኑ ጊዜ “በኢህአዴግ” ውስጥ አቶ መለስን ሊተካ የሚችል አንድም ሰው እንደሌለ የታወቀ የማይተወቅ ነው ፡፡ የኢትዮጵያ የይስሙላው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ “የአቶ መለስን ጫማ” ሊሞሉ እንደማይችሉ በአንድ ወቅት ተናግረዋል፡፡ ትክክል ናቸው፡፡ “በኢህአዴግ” ውስጥ ማንም አይችልም! በ2015 የአቶ መለስን ሚና ቦታ የሚሞላ ካልሆነም ደግሞ ጫማቸውን የሚሞላ ማን እንደሚሆን የሚታወቅ የማይታወቅ እንቆቅልሽ ነው፡፡ (ያ ታዋቂ የሆነ የማይታወቅ እንቆቅልሽ ሰው ማን አንደሆነ አውቃለሁ)፡፡ የሚታወቁ የማይታወቁዎቹ ከስልጣን መጋረጃ በስተጀርባ አድፍጠው አፈታሪክ ለሆነው ፍጹም ሚስጥራዊነት በቁጣ እና በስሜታዊነት የሚሰሩ ናቸው፡፡ አቶ መለስ ካረፉ ጀምሮ በህወሀት በርካታ ተናንሽ ቡድናዊ ትግል እርስ በእርሱ የመተረማመስ የተደበቀ የማይታወቅ ነገር አለ ይላሉ አናውቃለን የሚሉት ፡፡ የማይታወቀውን የማይታወቅ ለማወቅ በህወሀት የተለያዩ ትናንሽ የሽኩቻ ቡድኖች በአንድ ላይ ተሰባስበው እንዲቆዩ ያስቻላቸው ኢኮኖሚያዊው የጋራ ፍላጎታቸው ይላሉ አናውቃለን የሚሉት፡፡ የህወሀት የሽኩቻ ቡድኖች እርስ በእርስ እየተጠላለፉ ያሉት እና ችግሩ ፈንድቶ በግልጽ በአደባባይ እንዳይወጣ ያደረገው ብቸኛው ነገር በዘራፊ ሌቦቹ መካከል ያልተጻፈ እርስ በእርስ የመጠባበቅ ስነምግባር ስላለ ነው ይላሉ፡፡ ሌቦች ከሌቦች ጦርነት ምንም ዓይነት የአሸናፊነት አይኖርም፡፡ሁሉም ጥቅማቸዉን ያጣሉ:: ስለህወሀት ዋና ውስጣዊ የስልጣን አሰራር ብዙ የሚታወቁ የማይታወቁ ነገሮች አሉ፡፡ ይህም ሆኖ የማይታወቀውን የሚያውቁት አይናገሩም እናም የሚናገሩት ደግሞ የማይታወቀውን አያውቁትም፡፡

በ2015 ስለሚካሄደው ምርጫ ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች ምን ያደርጋሉ?

ለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች እ.ኤ.አ በ2015 በኢትዮጵያ ስለሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ነጻ እና ፍትሀዊ እንዲሆን ለማገዝ ወይም ደግሞ በትክክል ስለመከናወኑ ለማረጋገጥ የሚያደርጉት ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡ ትንሽም ቢሆን አንኳን የሚያሳስባቸው ነገር አይደለም፡፡ ነጻ እና ፍትሀዊ ያልሆነ ምርጫ እንዲካሄድ የሚያስችል የምርጫ ትወና ነው የሚፈልጉት፡፡ እነርሱ ለመከተል የሚፈልጉት ያረጀ እና ያፈጀ ጸሁፍ አላቸው፡፡ እ.ኤ.አ ጁን 2010 “ለዉጭ ሰዎች እውነታውን መናገር” በሚል ርዕስ የትችት መጣጥፍ አቅርቤ ነበር፡፡ ትችቱ ትኩረት ያደረገው ስለአቶ መለስ እና አገዛዛቸው የተመለከተ ሲሆን አበዳሪ እና እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በእርሳቸው ላይ ያላቸው አመለካከት “ምንም ዓይነት ጭራቃዊነት ነገር አልሰማንም፣ ምንም ዓይነት ጭራቃዊነት ነገር አላየንም፣ ምንም ዓይነት ጭራቃዊነት ንግግር አልተነገረም“ የሚል ሆኖ ይገኛል፡፡ “አቶ መለስ ለበርካታ ዓመታት የተረጋጋ ሁኔታ አለ በማለት ለምዕራባውያን ለጋሽ ድርጅቶች የውሸት ዘገባ በማቅረብ የግድ እውነት እንደሆነ አድርገው እንዲቀበሉ በማድረግ እረገድ አጋጣሚውን ተጠቅመውበታል፡፡ 80 ሚሊዮን የሚሆነውን የኢትዮጵያን ህዝብ ተበታትኖ በብሄር ጦርነት እንዳይተላለቅ እና በአገሪቱ ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳይመጣ አገሪቱን እንደ ሙጫ በማጣበቅ አንድ አድርገው እንዳቆዩአት ለማሳመን ሞክረዋል፡፡ ለጋሽ ድርጅቶቹ ይህ ነገር ኃላፊነት የጎደለው በሀሰት ላይ የተመሰረተ አፈታሪክ ጨዋታ መሆኑን አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ሆኖም ግን ጆሮዳባ በማለት አብረው በመጓዝ ላይ ነበሩ፡፡”

እውነታዎቹ በእራሳቸው ይናገራሉ፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ስላለው የሰብአዊ መብት አጠባበቅ እና ስለዴሞክራሲ ማበብ ማለቂያ በሌለው መልኩ የማስመሰያ የሽንገላ ጩኸት እያሰሙ በተጨባጭ ግን ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል በአስር ቢሊዮኖች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ከካዝናቸው እያወጡ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለሚገኘው ገዥ አካል በእርዳታ ስም ሲያዥጎደጉዱ ቆይተዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 አቶ መለስ በግል በሰጡት ትዕዛዝ በመቶዎች የሚቆጠሩ ያልታጠቁ ሰላማዊ ሴጎች በጥይት ሲቆሉ በነበረበት ጊዜ እነዚህ የውጭ ድርጅቶች በገሀድ እየተመለከቱ አንድም ዓይነት እርምጃ አልወሰዱም፡፡ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ እና የነጻውን ፕሬስ የሚሸብብ አፋኝ ህግ በገዥው አካል አዋጅ ሆኖ ሲወጣ እነዚህ የውጭ ድርጅቶች ከንፈራቸውን ከመምጠጥ ያለፈ ያደረጉት ተጨባጭ ነገር የለም፡፡ በተጨባጭ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን እና የሰላማዊ ዜጎችን እንቅስቃሴ የሚገድበው የጸረ ሽብር እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እየተባለ የሚጠራው አዋጅ ሲወጣ የውጭ አበዳሪ እና ለጋሽ ድርጅቶች በመጠኑም ቢሆን አቃስተዋል፣ ተንፈራግጠዋል፡፡ የአቶ መለስ አገዛዝ ለሩብ ምዕተ ዓመታት ያህል ያልተቋረጠ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ እና በሰው ልጆች ላይ ወንጀል ሲፈጽም እየተመለከቱ እና እየሰሙ እነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ምንም ዓይነት እርምጃ አልወሰዱም፡፡ ሆኖም ግን በሚያስደንቅ ሁኔታ እነዚህ መንታ ምላስ ሀፍረተቢስ “ዲፕሎክራሲዎች” (በዲፕሎማሲ ስም የሰብአዊ መብት ጥበቃ እያሉ የሚያላዝኑ አስመሳዮች) የሞራል ዝቅጠታቸውን በተቃዋሚዎች ላይ በመደፍደፍ እራሳቸውን ነጻ ለማድረግ ይቃብዛሉ፣ ይውተረተራሉ፣ ይዳክራሉ፡፡ እውነት ግን ያው ምንጊዜም እውነት ናት፣ እናም ከአቋሟ ንቅንቅ አትልም፡፡ የሌባ ዓይነደረቅ መልሶ ልብ ያወልቅ እንዲሉ በዚሁ በመንታ ምላሳቸው እንዲህ ይላሉ፣ “በተቃዋሚዎች በኩል አስተማማኝ የሆነ አማራጭ አይታይም፡፡“ ተቃዋሚዎች በዕለት የዕለት ህይወታቸው በአምባገነኑ ማን አለብኝ ባይ ገዥ አካል ማስፈራሪያ እየተደረገባቸው፣ እየተዋከቡ፣ በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር እየዋሉ እና ወደ እስር ቤት እየተወረወሩ እውነታውን በተጨባጭ እየተመለከቱ የአምባገነኑን የጥቃት ሰለባዎች አስተማማኝ የሆነ “አማራጭ አይታይም” በማለት ድፍረት የተቀላቀለበት የወቀሳ ተስፈኘነትን በማራመድ ላይ ይገኛሉ፡፡

አሁን ባለው ገዥ አካል ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ በኢትዮጵያ በፍጹም ሊኖር የማይችለው ለምንድን ነው?

ምንም ቢሆን ከጎመን ቅቤ ጨምቆ ማውጣት አይቻልም ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ከአንድ ከለየለት አምባገነናዊ ስርዓት ዴሞክራሲን መጭመቅ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ የዴሞክራሲው ጭላንጭል በሌለበት የአፈና ስርዓት የዴሞክራሲ ጭማቂ አይታሰብምና፡፡ ከጫካ አውሬ ስርዓት ወደ የሰለጠነ መንግስታዊ አስተዳደር ለመሸጋገር ቅንነት የተቀላቀለበት ወሳኝ የሆነ ሽግግር ማድረግን ይጠይቃልና፡፡ ዴሞክራሲያዊ የመንግስት አስተዳደር አድናቆትን፣ መደማመጥን እና የዴሞክራሲ መርሆዎችን ማለትም የህግ የበላይነት፣ የስልጣን ክፍፍል፣ የቁጥጥር እና የኃይል ሚዛንን መጠበቅ እና በአስተዳደር ሂደቱ ህገመንግስታዊነትን በትክክል መተግበርን ይጠይቃል፡፡ የህወሀት አምባገነኖች እነዚህን መርሆዎች ለመተግበር ልምዱ የላቸውም ወይም ደግሞ በተጨባጭ ሊገነዘቧቸው የሚያስችል ችሎታዉም እውቀቱም የላቸውም፡፡ ጫካ በነበሩበት ወቅት አንድም ጊዜ ቢሆን ነጻ ምርጫ አካሂደው አያውቁም፡፡ የህግ የበላይነትን መጠበቅ ለእነርሱ የተሳሳተ አካሄድ ነው ምክንያቱም እነርሱ እራሳቸውን ህግ አድርገዋልና፡፡
በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው የመቆየት ዓላማን ማሳመኛቸው “በጫካ ቆይታቸው ውስጥ መስዋዕትነትን ከፍለናል” የሚል ነው፡፡ እነርሱን የሚቃወሟቸውን ግለሰቦች እና ቡድኖች ሁሉ እነርሱ በሄዱበት መልኩ ጫካ በመግባት ተዋግተው ስልጣናቸውን መቀማት እንደሚችሉ ይጠብቃሉ፡፡ የሲቪል ነጻነት እና መብት እንደ ምዕራቡ ዓለም መስጠት በጣም ውድ የሆነ የተንደላቀቀ ኑሮ አድርገው በመቁጠር ይቀልዱበታል ምክንያቱም የመንግስት ስልጣኖች ዴሞክራሲዊ በሆነ ህገመንግስታዊ ስርዓት ውስጥ የግለሰቦችን መብት በሚያከብር ስርዓት ውስጥ በፍጹም አልኖሩምና፡፡ በአጭሩ በጥላቻ ድንቁርና ከተሞሉ ከጫካ ከመጡ ኃላፊነት ከማይሰማቸው ወሮበላ ስብስቦች ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን የተላበሰ ሰላማዊ መንግስት ይመጣል ብሎ መጠበቅ ከሀሳባዊ ምኞት የዘለለ አይሆንም፡፡ ከዚህ አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ መልኩ ጎቴ እንዲህ በማለት ምልከታቸውን አቅርበዋል፣ “ድንቁርናን በስራ ላይ ማየት ያህል አስፈሪ ነገር የለም፡፡“ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያን ደንቆሮ ገዥዎች ልብ ብላችሁ ተመልከቷቸው!

በሚፈነዳ ደማሚት ላይ መቀመጥ፣

ህወሀት (ኢህአዴግ) ደማሚት በተሞላ ፈንጅ ላይ ተቀምጧል፡፡ የድርጅቱ መሪዎች በማንአህሎኝነት እና በእብሪት በመወጠር እራሳቸው የለኮሱት የጎሳ እሳት እየተንቀለቀለ በአንድ ወቅት እራሳቸውን አንድዶ ዶግ አመድ የሚያደርጋቸውን እውነታ አላስተዋሉም፡፡ እራሳቸው እየኮተኮቱ ያሳደጉት ጥላቻ፣ ፍርሀት እና በቀልተኝነት አንድ ቀን አቅጣጫውን ወደ እነርሱ እንደሚያዞር ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ አንዱን ጎሳ ከሌላው ጋር በማጋጨት፣ የአንዱን የኃይማኖት እምነት ተከታይ ከሌላው ጋር በማጣላት በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለዘላለም እንደሚኖሩ እምነት አላቸው፡፡ የህወሀት አይን አውጣ አፈቀላጢዎች ሁሉንም የጎሳ ቡድኖች ለጥቂት ጊዚያት ሊያሞኙ ይችላሉ፣ ጥቂት የጎሳ ቡድኖችን ደግሞ ለሁልጊዜ ሊያታልሉ ይችላሉ፣ ሆኖም ግን ሁሉንም የጎሳ ቡድኖች ለሁልጊዜ ሊያሞኙ ከቶውንም አይችሉም፡፡

ታላቁ አፍሪካዊ የአሜሪካ ደራሲ ጀምስ ባልደዊን እንዲህ በማለት ጽፈዋል፣ “ጥላቻ ሁሉንም ነገር ሊደመስስ የሚችል፣ ጥላቻ ፈልፋዩን እና አራጋቢውንም ጭምር በአንድ ላይ ዶግ አመድ አድርጎ ሳያነድ የማይመለስ ዘመን የማይሽረው ተፈጥሯዊ ህግ ነው፡፡“

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ላሉት አምባገነኖች የሚከተለውን ምክር እለግሳለሁ፣ መቀበል አለመቀበል የእነርሱ ፋንታ ነው፡፡ ድሮ በአሜሪካ ባርነት ተንሰራፍቶ አፍሪካውያንን/ትን እንደ ተራ ሸቀጥ ለከባድ የጉልበት ስራ ወደ ሀገራቸው በሚያግዙበት ዘመን እና የአፍሪካ ባሮች ተስፋቸው በጨለመበት እና ፍራቻ በነገሰበት ወቅት ለአፍሪካውያን/ት ባሮች በተደረሰ የሙዚቃ ግጥም ላይ ሰፍሮ የሚገኘው የአምላካዊ ትንበያ እንዲህ ይላል፣ “አምላክ ለኖህ የቀስተ ደመና ምልክት ሰጠው፣ አሁን ጎርፉ አቁሟል በሚቀጥለው ጊዜ የሚመጣው ዉሃ አይደለም እሳት ነው!”

ድምፃችንን እንደለመዱት ይስረቁት እንጂ በፈቃደኝነት አውጥተን አንስጥ!

በ2015 “ምርጫ” በአምባገነኖች ላይ ድልን እንቀዳጅ!

በአምባገነኖች መቃብር ላይ ፍቅር፣ መተሳሳብ እና አንድነቷ የተጠበቀች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንገንባ!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

Filed in: Amharic