>

“የደም ከፈን!” ኦባንግ ለስዊድኑ ባለሃብት ማስጠንቀቂያ ላኩ

SMNE
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ ለታዋቂው የስዊድን ጨርቃጨርቅ ዓለምአቀፍ ቸርቻሪ H&M Hennes & Mauritz AB (H&M) ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራአስኪያጅ ካርል ዮሐን ፔርሶን ከህወሃት/ኢህአዴግ ጋር ስለሚያደርገው የንግድ ውል ኩባንያቸው ሊገጥመው ስለሚችል አደጋ ማስጠንቀቂያ ልከዋል፡፡

ሰኞ በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገ ሥነስርዓት ሚ/ር ፔርሶን የ2014 በንግድ የማያዳላ ተሸላሚ መሆናቸውን አስመልክተው በላኩት ደብዳቤ ላይ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ ሊጀምር ያለው የንግድ ስምምነት ፍጹም አድሏዊነት የተሞላበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎች እንደተመለከተው H&M ኩባንያ ከኢህአዴግ ጋር ለሚያደርገው ውል ለሸሪክነት የተመረጡት አምስት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ሶስቱ የህወሃት የግል ሃብት የሆነው የኤፈርት አባል ኩባንያዎች መሆናቸውን ኦባንግ በደብዳቤያቸው አሳውቀዋል፡፡

ሌላው ኩባንያ ደግሞ የህወሃት/ኢህአዴግ ቀኝ እጅ የሆኑትና በኢትዮጵያ ውስጥ የፈለጉትን ዓይነት ንግድ ያላንዳች የህግ ገደብ እንዲሁም ተገቢውን ግብር ሳይከፍሉ ንጹህ ትርፍ የሚያጋብሱት የሼኽ መሓመድ ሁሴን አላሙዲ ኩባንያ መሆኑን “ጥቁሩ ሰው” ኦባንግ ሜቶ አመልክተዋል፡፡ የአምስተኛው ሸሪክ ኩባንያ ማንነት እስካሁን አልታወቀም፡፡

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) በመርህ ደረጃ ልማት፣ ዕድገት፣ የንግድ ሽርክና፣ ወዘተ የሚደግፍ መሆኑን በደብዳቤው ላይ የተመለከተ ሲሆን ችግር የሚሆነው ግን እንዲህ ያለው ሽርክና በሰብዓዊ መብትና ሌሎች የዜጎችን መብት በመርገጥ በአምባገነንነት ለተቀመጠው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ዕድሜ ማራዘሚያ የመሆኑ ጉዳይ እንደሆነ ኦባንግ አመልክተዋል፡፡

ለአንድ ወገን (ለአንድ ዘር/ጎሣ) ፍጹም አድሏዊ በሆነ መልኩ “የራሴ” የሚላቸውን እየጠቀመ በሥልጣን ከቆየው ህወሃት ጋር በንግድ ውል መተሳሰር በመልካም አሠራሩ ለታወቀው እንደ H&M ላለው ኩባንያ ስም ወደፊት ትልቅ ችግር እንደሚፈጥር በደብዳቤው በዝርዝር ተመልክቷል፡፡ ከዚያም ባሻገር በአፍሪካ በሴራሊዮን “የደም አልማዝ” በመውሰድ ራሳቸውን እያበለጸጉ እንዳሉት ሁሉ ከህወሃት ጋር በጨርቃጨርቅ ንግድ ሽርክና መጀመር “የደም ከፈን” እያመረቱ ማትረፍ እንደሆነ በማስጠንቀቅ ኩባንያቸው ሊደርስበት የሚችለውን አስቸጋሪ መዘዝ ኦባንግ በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰው የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ለባለሃብቱ ሰጥተዋል፡፡

ለሚገዛው ሕዝብ ቅንጣት ታህል ሐዘኔታ የማይሰማው ህወሃት/ኢህአዴግ በፖለቲካው መስክ ፓርላማ ብሎ ባስቀመጠው መሰብሰቢያ 99.6በመቶ መቀመጫውን መቆጣጠሩን፣ አፋኝ የመያድ፣ የጸረ ሽብርተኝነት ወዘተ ሕግጋትን በማውጣት ተቃዋሚዎቼ ናቸው የሚላቸውንን ሁሉ በአሸባሪነት እየከሰሰ ለእስር፣ ለግድያ እና ለስደት እንደሚዳርግ፤ በሰብዓዊ መብት ረገጣ በተደጋጋሚ የተወነጀለ መሆኑን፣ ወዘተ ማስረጃዎችን በመጥቀስ አቶ ኦባንግ አስረድተዋል፡፡ ለማስታወስም ያህልም በኦጋዴን ክልል በጋዜጠኛነት ተሰማርተው የነበሩት ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞች 438 ቀናት ታስረው ቢፈቱም በጸረ አሸባሪነት ሕጉ 11ዓመት ተፈርዶባቸው እንደነበር በመግለጽ የጋራ ንቅናቄው ዋና ዳይሬክተር የኢህአዴግን የጭከና አገዛዝ ሊዘነጋ የማይገባ መሆኑን ለስዊድኑ ባለሃብት አስገንዝበዋል፡፡

ኩባንያቸው ሽርክና የሚያደርግባቸው ኤፈርትና የአላሙዲን ድርጅቶች የሰራተኛ መብቶችን በመርገጥ፣ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቦታ በግዳጅ በመንጠቅ፣ የዜጎችን ጉልበት ያለ አግባብ በመበዝበዝ፣ በሙስና የተጨማለቀና አድሏዊ አሰራር በመከተል፣ ወዘተ ተነግሮ የማያልቅ ግፍ የፈጸሙና እስካሁንም እየፈጸሙ ያሉ በመሆናቸው በተለይ ለሴቶች “የሥራ ዕድል” ይከፍታል የተባለው የኩባንያቸው ኢንቨስትመንት በምስኪን እና ደጋፊ አልባ ኢትዮጵያውያን ደም የዓለምን ሕዝብ የዲዛይነር ጨርቃጨርቅ ሳይሆን “የደም ከፈን” ለማልበስ መዘጋጀቱ ሊያስቡበትና ሊጠነቀቁበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን በጥብቅ በማሳሰብ የጋራ ንቅናቄው ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ ደብዳቤያቸውን አጠናቀዋል፡፡
የደብዳቤው ሙሉ ቃል  ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ በመጫን ያንብቡ፡፡

http://solidaritymovement.org/141120-Letter-to-Karl-Johan-Persson.php

 

Filed in: Amharic