>

አገር እንዴት? ትግል እንዴት? ብለን ስንዳውር በበኩላችን የታየን ይኸው ነው...!!! (በአካል ዘለቀ)

 አገር እንዴት? ትግል እንዴት? ብለን ስንዳውር በበኩላችን የታየን ይኸው ነው…!!!

በአካል ዘለቀ

በኢትዮጵያ ምድር ለኢትዮጵያዊያን የተካሄደው ተጋድሎና የተከፍለው መስዋእትነት ርዝመቱና ስፋቱ ከየአቅጣጫው ቢዘረጋ ከሩቅ ምሥራቅ ሀገሮች እስከ አሜሪካና ቻይና ደርሶ ቢመለስ እንጅ ቅጥያ ያስፈልገዋል ተብሎ አይገመትም። በሀገራችን ረጅም ታሪክ ውስጥ በየዘመኑ የተደረጉት ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ተጋድሎዎችና መስዋእትነቶች ኢትዮጵያ መንምናና ደክማም ቢሆን የህይወት ዝኃዋን አቆይቶ እንደሆን እንጅ ሌሎች ወደደረሱበት ሥልጣኔና ዕድገት አላደረሳትም። ይህ ለምንና እንዴት ሆነ ብሎ ለመጠየቅ አንድ ደረጃ ላይ የአንድ ትውልድ ግዴታ ሊሆን ይገባዋል። ኢትዮጵያን ለዘመናት ሰቅዞና ወጥሮ ለያዛት የማያንቀሳቅስ ችግርና የዕድገቷ ኋላቀርነት  እስካሁን በነበረው ቀጣይ ትግል ውስጥ ያለፉ ሀገር ወዳዶችና ታጋዮች የሚሰጡት ምክንያታዊ ግንዛቤ የሀገራችን ጄኦፖለቲካዊ አቀማመጥና የተፈትሮ ተሰጥዖ ዓይናቸውን ለጣሉባት ሁሉ ማራኪ በመሆኑ ያለምንም ማቋረጥ በመከላከል ውስጥ ማለፍ ስለተገደደች ነው ይላሉ። ታሪካዊው ማንነትና ዳፋው የሚካድ ባይሆንም ዛሬ አንቱ የተባሉና አዘቅዝቀው የሚያዩን ሀገራትም በየፊናቸው በየራሳቸው ባህርይና ተፈትሮ ውስጥ ያጋጠሟቸውን ከእኛዋ አገር ያልተናነሱ ፈተናዎችንና ውጣ ውረዶችን አልፈው ነው  አስደናቂ ታሪካዊ ግስጋሴዎችን አድርገው ከደረሱበት የደረሱት። አብዛኞቹ ሀገራት አውዳሚ ብሄራዊና ዓለም አቀፋዊ ጦርነቶችን ተዋግተው፤ አስከፊ የሆኑ የእርስ በርስ እልቂቶችን አካሂደው፤ ቅኝ ገዥዎችንና ወራሪዎችን ተጋፍጠው፤ ካለመኖር ወደ መኖር የሚያስችል መራር ትግል አካሂደው፤ … ነው ከደረሱበት የደረሱት። ራሳችን ፈልቅቀን በመግለጥ ውስጣችን እንመርምር ከተባለ እኛን ያጋጠመን አስቸጋሪ እጣ ፋንታም ያንሳል ባይባልም ከብዙዎች የተለየ አልነበረም። ሃቁ ይህ ከሆነ እጅ ሳይሰጡ ከታገሉላት አባቶቻችንና እናቶቻችን የተረከብናት ኢትዮጵያ እንዲህ ተጎልታ የቀረችበት ምክንያት ሊፈለግና ሊመረመር ይገባዋል። ስለሆነም ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች መጤን ከሚገባቸው ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች መካከል መዳሰስ የሚገባቸው ናቸው። የመጀመሪያው ጉዳይ በተሸጋገርንባቸው ዘመናት ሁሉ ተከታታይ መንግስታት ሳያስተካክሏቸው የቀሩ የእርስ በርስ ግንኙነት ዝንፈቶች ሲሁኑ፤ ሁለተኛው ደግሞ በየዘመናቱ ያገኘናቸውን መልካም ገጠመኞች በውስጣችን ተቻችለንና የወደፊቱን ዕጣ ፋንታችን መዝነን ለመሸጋገሪያነት መጠቀም ያለመቻል ድክመት ነው።
አገር የግልና የጋርዮች ባህርይ አላት። እንደግል ሃብትና ንብረትነቷ እያንዳንዱ ዜጋ ህግና ሥርዓትን መሠረት አድርጎ ያለምንም ገደብና ጥያቄ ተንቀሳቅሶ ሊገለገልባትና ሊጠቀምባት የሚገባ ሲሆን፤ እንደ የጋራ መኖሪያነቷ ደግሞ የደኅንነቷ ጥያቄና ዋስትና በሁሉም ትክሻ ላይ የሚያርፍ ነው። አገር ማንነት ነችና ለዜጎቿ የጋራ ውርስ ስትሆን፤ በየግል ደግሞ ዜጎች የተለያየ ፍላጎት እንዳላቸው ሁሉ የተለያየ ጥቅም ይሻሉና ለያንዳንዱ ዜጋ እንደማንኛውም ሌላ ዜጋ እኩል የግል መጠቀሚያና መገልገያ ሁና መመቸት ይኖርባታል። ስለሆነም የአንድ አገር ሥርዓተ መንግሥት እነዚህን ግላዊና የጋራ ባህርይዎች እርስ በርሳቸው ተደጋጋፊና ተወራራሽ እንዲሆኑ አስማምቶ እጅና ጓንት ማድረግ ይጠበቅበታል። የሥርዓቱና የመንግሥት መሪዎች አገር በግልም ሆነ በጋራ የሕዝብ መሆኑን አውቀው ውሳኔያቸውንና መመሪያችውን ህዝብ ተሳስቶም ቢሆን ምክረ ሃሳባቸውን ተቃርኖ በሚሰጣቸው አቅጣጫና ይሁንታ (ምንም እንኳ ከብዙሃኑ ህዝብ ዓውደ-ሃሳብ በላይ የጥቂት አንጣሪዎች ሃሳብና አመለካከት ሊበልጥና ሊሻል ይችልላ ብሎ ማስብ በራሱ ስህተት ላይ የሚጥል ቢሆንም) ተከትለው ማስፈጸም ኖርባቸዋል። የቆየውን የሀገራችን ታሪክ ስንመረምር ጎልቶ የምናገኘው ከላይየተጠቀሱት የባህሪዎች ጥምረትና ስምረት ሳይሆን በጋራ ባህሪዎቻችን ላይ ያተኮረና ሚዛን የደፋ ሲሆን ለየግል ፍላጎቶቻችንና ጥቅሞቻችን ግን ግድየለሽና ኃላፊነት የጎደለው ሆኖ ይስተዋላል። ይህ ማለት ኢትዮጵያን እንደ ሀገር በመከላከልና በመጠበቅ ዙሪያ አመርቂ ሥራዎች እየተሠሩ በየግል የዜጎችን ጥቅሞች፤ ነጻነቶችና መብቶች በማስከበር ረገድ ‘ዕድል ያውጣችሁ’ ተብለው ስለተዘነጉ በህገ ሥራዓቱ ውስጥ የጋራ ባህሪያችን ከሆነው አትንኩኝ ባይነታችንና ተከላካይነታችን ጋር አልተቆራኙም። የሀገር ሃብት የሚጠራቀመውና የሚለማው እያንዳንዱ የሚጠቅመውንና የሚጠቀምበትን በያለበት ለማምረት እድል ሲያገኝና እርስ በርሱ የምርት ልውውጥ ማድረግ ሲችል መሆኑን የምጣኔ ሃብት ሊቃውንት ያስገነዝቡናል። ጥቂቶች ሃብታሞች የሆኑበትና ብዙኃኑ የደኸዩበት አገር ለማደግ በእጅጉ ይቸገራል። ይህ ደግሞ ያለምክንያት ሳይሆን አብዛኛው በእጁ ላይ ንብረት ኖሮት አምራችና ሸማች ካልሆነ በሀገር ውስጥ ተንቀሳቃሽ ሃብት ስለሚጠፋ ነው። የእነ አዳም ስሚዝ (Adam Smith) ኢኮኖሚያዊ ንድፈ ሃሳብ (The invisible hand) የሚያስታውሰንም ይኸውን እውነታ ነው – የአንዲት ሀገር ዜጎች በያሉበት በየግላቸው የሚችሉትንና የሚፈልጉትን በርትተው እያመረቱ ሲጠቀሙና በገበያ ላይ ሲለዋወጡ ድንገት ሳያውቁት በድምሩ የሀገራቸውን ሃብት ይፈጥራሉ። ስለሆነም የግለሰቦች ከአምራችነትና የልውውጥ ኡደት ውጭ መሆን ጉዳቱ በቀጥታ የሀገር ጉዳት ነውና ይህን ሚስጥር ሁሉም ሊያውቀውና እጅ ለእጅ ሊይያያዝና ሊረዳዳ ይገባል።
በሌላ በኩል ደግሞ በየደረጃው ግንባር ቀደሙንና ፋና ወጊውን ትውልድ የሚመለከተው ችግር ነው። ማንኛውም አገር – በተለይም ደግሞ ታዳጊ አገሮችን አስመልክቶ- ወደፊት ለሚያደርገው ግስጋሴ የተማረው የህብረተሰብ ክፍልና በዘመናዊ የሥራ መስኮች የተሠማራው ህብረተሰብ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ይህ የህብረተሰብ ክፍል ነው ሕዝብን በመወከልና በማስተባበር እርስበርሱ ተወያይቶና ታግሎ ቋሚ ሥርዓት ሊያማክል የሚችለው። አገርን መሠረቱ ጽኑ በሆነ ሥርዓት ላይ ለመገንባት በዚህ የህብረተሰብ ክፍል መካከል መግባባትና መቻቻል የግድ ይላል። በኃይል እየተሸናነፈና ቀንቶት የድል ባለቤት በሆነ ጉልበታም ሰላምና ዕድገት አይገኝም፤ ከተገኘም ጊዜያዊ እንጅ ዘላቂ አይሆንም። በሀገራችን እስካሁን በታዩ ብዙ የታሪክ ገጠምኞች ይህ ታሪክ ተረካቢ ትውልድ በየእርከኑ ያካሄደው ተጋድሎውና መስዋእትነቱ ሳያንሰው መለኛ የመሆን ድክመት ግን በጉልህ ተንጸባርቆበታል ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። እንዲወጣለት የሚፈልገው ትልቁ እጣ አገሩን ሰላምና ዕድገት ማጎናጸፍ ሆኖ እያለ በጋራ አገር ጉዳይ ላይ ጠርዝና ጠርዝ እየያዘ ሲሳሳብ አክርሮ እየበጠሰ፤ የሀገር ጉዳይ የእያንዳንዱ ዜጋና የሁሉም ሕዝብ ጉዳይና የጋራ መገለጫ አይደለ ይመስል መግባባትን አሳንሶ መሸናነፍን እያጎላና እያስቀደመ፤ ዜጎች በየግላቸው ያላቸው አመለካከትና ፍላጎት የተወሳሰበና የበዛ መሆኑ እየታወቀ እኔ የያዝኩትና የታየኝ ብቻ ነው ትክክል በሚል ግትርነት ራሱን ከብዙሃኑ እየነጠለ፤ ከሀገሪቱ ታሪክና ሥሪት ጋር በማይዋህድ ሃሳባዊ ፍላጎትና አቋም እየተቃኘ፤ ከተጨባጭና አጣዳፊ የሕዝብ ፍላጎትና የአገር ጉዳይ  ውጭ እየባዘነ፤ — በአጠቃላይም እንዲያሻግር በሚጠበቀው ፈር ቀዳጅና መሪ በሆነው ትውልድ መካከል መልኩና ዓይነቱ ለበዛውና ውጥንቅጡ ለወጣው የሀገራችን ጉዳይ እርስ በርሱ ተደማምጦና ተሳስቦ ሃሳብን ማቀራረብና ማቻቻል ስለተሳነው እስካሁን ባለው አካሄድ ሕዝብና አገርን ከድህነት፤ ከኋላ ቀርነትና ይህን መሠረት አድርጎ በረሃብና ስደት ከሚከሰት ብሔራዊ ውርደት ለማላቅቅ መፍትሄ ሊያገኝለት አልተቻለውም።
ሲጠቃለልም፤ ‘አገር እንዴት፤ ትግል እንዴት’ ብለን ስንዳውር በበኩላችን የታዬን ይኸው ነው – ሀገር ለያንዳንዱም ለሁሉም እኩል ነች። እንደ ግለሰብ የእያንዳንዱ ዜጋ ፍላጎትና ጥቅም ሊለያይ ይችላል። የሁሉም አንድነት ግን በወል ማንነቱ (በዜግነቱ) ይገለጻል። የመሪዎችና ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች ሚና የእያንዳንዱን ዜጋ ጥቅምና ፍላጎት ማሰብና መደመር የሚገባቸው ሲሆን የማይወዱት የተለየ እይታና አካሄድ ቢኖር እንኳ በብዙሃኑ ፍላጎት ላይ በአመጽና በጉልበት እስካልተነሳ ጊዜ ድረስ ሌላ መካተት የሚገባው የአገርና የሕዝብ ባህርይ ነውና በአገር የመፍትሄ እቅፍ ውስጥ መካተት ይኖርበታል። በሌላ በኩልም በተለያየ መንገድ ለሕዝብ የተሻለ መጻኢ እድል የሚስያቡና የሚታገሉ ሁሉ የዜጎችን ልብ ገዝቶ በጋራ ለማሰለፍና ብሎም አስፈላጊውን ውጤት ለማግኘት የእርስ በርሳቸው መግባባትና መቻቻል መሠረታዊ የሆነውን ያህል በሌላው ገጽ ደግሞ የሚያስቡላቸውና የሚታገሉላቸው ዜጎች በግልና በጋራ ያላቸውን የትሥስር ግማድ ጠንቅቆ ማወቅና ሊረዱት፤ ሊዳሥሱትና ሊጨብጡት በሚችሉት ግብዓት ላይ በተግባር ተግቶ መገኘት አስፈላጊ ይሆናል።
Filed in: Amharic