>
5:13 pm - Sunday April 20, 0577

ስለ ሻዕቢያ የማስበውን አንድ ሳላስቀር አውጥቼ ስናገር — ከድሮ እስከ ዘንድሮ!  (አሰፋ ሀይሉ)

ስለ ሻዕቢያ የማስበውን አንድ ሳላስቀር አውጥቼ ስናገር

ከድሮ እስከ ዘንድሮ!

 አሰፋ ሀይሉ

በሻዕቢያ የመገንጠል ጦርነት ወቅት አብሯቸው በውጊያ መስክ የነበረው አሜሪካዊ ጋዜጠኛና ደራሲ ዳን ማኮኔል ‹‹ከፈተናዎች ባሻገር›› ብሎ በእንግሊዝኛ ያሳተመላቸውን የኤርትራ የነጻነት ትግል ገድል ከዚህ ቀደም አስነብቤያሁ፡፡ ዳን ኮኔል በመጽሐፉ ካሰፈራቸው ራሱ በዓይን ከተመለከታቸው እማኝነቶች መካከል ሻዕቢያ ከምጽዋ ወደ አስመራ የሚወስደውን የትራንስፖርት መስመር የቆረጠበት ኦፕሬሽን አንዱ ነው፡፡
ይህ የሻዕቢያ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ጥቅምት 6 ቀን 1970 ዓ.ም. ላይ (በጎርጎሮሳውያን ካሌንደር October 16, 1977) የተከናወነ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በምጽዋ ላይ ለሰፈረው ጦር ስንቅና ትጥቅ የሚያመላለስበትን ብቸኛ መተላለፊያ ለመዝጋትና ምጽዋንና አስመራን በኃይል ለመቆጣጠር በረዥሙ ያለመው የሻዕቢያ የሽምቅ ሠራዊት፣ በዚህች ዕለት ከፈጸማቸው ነገሮች መካከል ዳን ኮኔልን እጅግ ያሰቀቀው አንድ ነገር አለ፡- ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ወታደሮችን አስከሬን ከየወደቁበት ሰብስቦ ጋዝ አርከፍክፎ ያቃጠለበት ዘግናኝ ተግባር!
እነዚያ ኢትዮጵያውያን ጦር አሰልፎ ሊወጋን የሚነሳ ሠራዊት ይመጣብናል ብለው በህልማቸውም በእውናቸውም አልጠረጠሩም፡፡ ባልጠረጠሩበት የሻዕቢያ ደፈጣ ተዋጊዎች ለረዥም ጊዜ ዝግጅት የተደረገበትን ድንገተኛ (‹‹መብረቃዊ››) ጥቃት ሠንዝረው አንድም ሳያስቀሩ ኢትዮጵያኑን ወታደሮች ወደ ሞት ሸኟቸው፡፡ በውትድርና የውጊያ ህይወት ውስጥ መግደልና መሞት ያለ ነው፡፡ ሻዕቢያ ግን የኢትዮጵያን ሠራዊት በመግደል ብቻ የረካ አይመስልም፡፡ ሬሳቸውን ጋዝ አርከፍክፎ አቃጠለው፡፡
የሰውን ልጅ አካል፡፡ የሰው ልጅን ሥጋ፡፡ የሰው ልጅን አጥንት፡፡ እንደ ከብት ሥጋ አንጨርጭሮ መጥበስ፡፡ ማቃጠል፡፡ ከቃጠሎው በኋላ መልካቸው የማይለይ ጥቁር በእሳት የተንጨረጨሩ አካሎች አካባቢውን ሞልተውት አሞሮችን ይጠባበቁ እንደነበር ይናገራል የዓይን እማኙ ጋዜጠኛ፡፡ እንዴ? እንዴት ዓይነት ጥላቻ ነው? እንዴትስ ዓይነት እብደት የተጸናወታቸው ሰዎች ነበሩ? እጅግ እጅግ እጅግ ይገርመኛል፡፡
አሜሪካዊው የሻዕቢያ ጋዜጠኛ ዳን ኮኔል ምክንያት ከመደርደር አልቦዘነም፡፡ ሻዕቢያዎች የኢትዮጵያን ወታደሮች ሬሳ ያቃጠሉት ከሬሳው ብዛት የተነሳ በሞቱት አስከሬኖች ብስባሽ በአካባቢው ላይ ወረርሽኝ እንዳይቀሰቀስ በመፍራት ነው ይለናል፡፡ በሞላ ሀገርና ምድር ለምን ቆፍረው አልቀበሯቸውም? ለሚለው የዳን ኮኔል መልስ ‹ጊዜውና ዕድሉ አልነበራቸውም› የሚል ግርድፍ መልስ ነው፡፡
እንዴ? ሺህ ጦር አሰልፎ፣ መንገድ ሰብሮ፣ የሰበረውን አካባቢ በጠላት ጦር እንዳይያዝበት ለወራት ተቆጣጥሮ የሚጠብቅ የታጠቀ ኃይል – እንዴት ነው የሞቱ ወታደሮችን ለመቅበር ጊዜና ዕድሉን የሚያጣው? የኢትዮጵያውያንን ወታደሮች ጋዝ አርከፍክፎ ያቃጠለውና፣ የአካባቢው አውሬ የሰው ልጅን የጎድን ጥብስ እየዘነጠለ ድግሱን እንዲበላ የተወው ሻዕቢያ፣ ያስጨነቀው የበሽታ መቀስቀስ ከሆነና ጊዜ ካልነበረው፣ የራሱንስ የሞቱበትን ተዋጊዎች አስከሬን ከኢትዮጵያውያኑ ጋር ቀላቅሎ ጋዝ አርከፍክፎ አቃጥሏል? ለምን አላቃጠለም? እና ለጅብና ለአሞራ ትቶ አልሄደም? እጅግ ያሰቅቃል እንዲህ ደረጃ ደርሶ የነበረ የጥላቻ እብደት ስለ እውነት፡፡
በቅርቡ በሞት የተለየን የወቅቱ አውደ ውጊያዎች ደራሲ ታደለ ቴሌ ሳልቫኖ ‹‹አይ ምፅዋ›› በሚል መጽሐፉ – በመጽሐፉ የፊት ሽፋን ጭምር በፎቶሾፕ አስደግፎ እያሳየ፣ በምጽዋ ላይ ዳግመኛ የሻዕቢያ ወታደሮች የኢትዮጵያ ወታደሮችን አስከሬን ከምረው ቤንዚን አርከፍክፈው ሲያቃጥሉ በዓይኑ በብረቱ የማየቱን እማኝነት እንደሰጠ አልዘነጋሁም፡፡ በወቅቱ መጽሐፉን ተሽቀዳድመው ካነበቡት ሰዎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ብሆንም ግን – በፍጹም ልቤ ላምነው ተቸግሬ ነበር፡፡ ምክንያቴ የታደሰ ቴሌ ሳልቫኖን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባቴ ነበር፡፡
ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ በሻዕቢያ ላይ ከባድ ጥላቻና ነዲድ ስሜት እንዳለው ከመጽሐፎቹ አይቶ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያን ከገንጣዮቿ እጅ ለማዳን ከሻዕቢያ ጋር አንገት ለአንገት ሲተናነቅ የኖረ ወታደር፣ እና ተናንቆም አቅም አንሶት ዓይኑ እያየ የተሸነፈ ሰው፣ በአካል የሚያውቀውን ሻዕቢያን ቁጥር-አንድ የኢትዮጵያ ጠላት አድርጎ ቢቆጥርና ያንንም ቢጽፍ ሊገርም አይገባም፡፡ አይገርመኝም፡፡ ምናልባትም የጻፈው ነገር እውነቱን ይሆናል፡፡ ግን ከዚህ ዓይነት ሰው የሚሰጥን ምስክርነት ደግሞ እጠራጠረዋለሁ፡፡ በጥላቻ ኃይል ብዙ የተጋነኑ ነገሮች፣ እና ብዙ ፕሮፓጋንዳ የተቀላቀለባቸው ትርክቶች ሊነገሩ ስለሚችሉ፡፡
አሁን ግን ከሻዕቢያ ጋር አብሮ በበረሃ ኖሮ፣ ሻዕቢያን ለዓለም ያስተዋወቀው፣ የመጀመሪያውን የሻዕቢያ ታሪክ ለዓለም ያሳተመላቸው እና በበኩሌ ‹‹ቆዳው ነጭ የሆነ አሜሪካዊ ሻዕቢያ›› ብዬ ብጠራው ምንም ቅር የማይለኝ ዳን ኮኔል፣ ያንኑ ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ ሲነግረኝ አላምን ያልኩትን እውነት፣ ደግሞ በዓይኑ አይቶ ከመዘገበው ማስታወሻው አውጥቶ – ያውም መጽሐፉ ከመታተሙ በፊት የሻዕቢያ መሪዎች ረቂቁን ደጋግመው አይተው አርትዖት እንዲሠሩበት ማድረጉን የሚናገረው ይኼው ደራሲ – ደግሞ ሲነግረኝ ግን – የእውነታው ንዝረት፣ የጥላቻው ልቀት፣ የወገኖቼ የነደደ አካል፣.. ዓመታትን አልፎ ውስጤን አመመኝ፡፡ አንገበገበኝ፡፡ አንገፈገፈኝ፡፡
ግን ለምን? ያን የሚያህል ጥላቻ! ያን ያህል ግዙፍ ጥላቻ! ከጥላቻም የከፋ አረመኔያዊ ጥላቻ! ለምን? ጥላቻ! ጥላቻ! ጥላቻ! ከጥላቻ ጋር ወደፊት! – ይህ ይመስለኛል ባለፍንበት የሀገራችን አሰቃቂ ታሪክ ደግመን ደጋግመን የምናገኘው ጉልህ በደም የተጻፈ መፈክር! ይህ ነገራቸው ነው በተለያየ ጊዜ ኢትዮጵያን ጠልተው የተነሱትን ሻዕቢያን፣ ወያኔንም ሆነ ኦነግን የሚያመሳስልብኝ አንድ የጋራ አቋም፡፡
ሻዕቢያ በወታደራዊው (በመጨረሻው ለሀገሩ አንድነት በተዋደቀው) የኢትዮጵያ መንግሥት መውደቂያ ዓመታት ላይ፣ ከሠራዊቱ በጡረታ የተሰናበቱ ‹‹አባት ጦሮች›› ዳግም ወደ ሠራዊቱ ተቀላቅለው ወደ ኤርትራ እንዲዘምቱ መደረጋቸው ይታወቃል፡፡ አባት ጦሮች እንዲዘምቱ ሲደረጉ ከመካከላቸው በሻዕቢያ የተማረኩ ነበሩ፡፡ በዚያው ወቅት በጦሩ ውስጥ የነበረ የሥጋ ዘመዴ በኤርትራ ምድር ስለዘመቱት ስለ እነዚያ የኢትዮጵያ ‹‹አባት ጦሮች›› በአንድ ቆየት ያለ ጨዋታ መሐል ሲያወጋኝ ሻዕቢያ በአባት ጦሮቹ ላይ ምን እንደፈጸመባቸው በዓይኑ ያየውን የነገረኝንም አልረሳሁትም፡፡
ሻዕቢያ የማረካቸውን ‹‹አስራ ሁለት አባት ጦሮች፣ በየአንድ አንድ ሜትር ርቀት በቁመታቸው ልክ ጉድጓድ ካስቆፈራቸው በኋላ፣ በቆፈሩት ጉድጓድ ጭንቅላታቸውን ብቻ አስቀርቶ እስከ አንገታቸው ቀብሮ፣ በጭንቅላታቸው ላይ የፈላ ዘይት ለቀቀባቸው››፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሥፍራው ሲደርሱ ያጋጠማቸው ‹‹እንደ ጥቅል ጎመን በመሬት ላይ የተተከለው የአባት ጦሮቹ ጭንቅላት ተበለሻሽቶና አውሬ ገጣጥቦት›› ነበር፡፡ ለማሰብም እኮ የሚከብድ የሆረር ፊልም እኮ ነው በእውን የተሠራው በዚህች ሀገር ላይ፡፡ በሆረር ፊልም ላይ ራሱ የማናገኘውን ዓይነት ጥላቻ ነው እኮ ከዚህች ምድር የበቀሉ የገዛ ወገኖቻችን በተለያዩ የታሪክ አጋጣዎች በገዛ ወገኖቻቸው በኢትዮጵያውያን ላይ ዘርግፈው ያሳዩን፡፡
በእርግጥ የኢትዮጵያስ የየወቅቱ ወታደር በማረካቸው ሻዕቢያዎች፣ ወይም ወያኔዎቹና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ባላንጣ ኃይሎች ላይ ምን ዓይነት ዘግናኝ ድርጊት ፈጽሞባቸው ይሆን? የሚለውን አልፌው ነው፡፡ የተፈጸማባቸው ምን እንደሆነ ወይም ምን ሊፈጸምባቸው እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ቢሆንም ያ ብቻውን ከጤነኛ አዕምሮ ይፈልቃሉ ተብለው ለማይጠበቁ ብዙ ሠይጣናዊ ድርጊቶች ማስተባበያ ሊሆን አይችልም፡፡ የሌሎች በስህተት መነከር፣ ያንተን ስህተት ልክ ሊያደርግልህ አይችልም፡፡ Others’ wrong cannot make your wrong right! ሚዛኑ ይኸው ነው፡፡
የወቅቱ ገንጣዮች ‹‹ደርግ›› ፈጸመብን ስለሚሉት ብዙ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች ነግረውናል፡፡ ሀገሩን ለመቁረስ የተነሱ ኃይሎችን ለምን ተዋጋ ብለው የመክሰስ የሞራል አቅሙ የሚኖራቸው አይመስለኝም፡፡ ዛሬ ቤኒአሚሮች ወይም ቢለኖች፣ ወይም የየትኛውም የኤርትራ ክፍል ያለ ህዝብ ሀገሩን ገንጥዬ የራሴን ሀገር ልመሥርት ቢል፣ ሻዕቢያ ከደርግ መንግሥት በበለጠ ብቃትና ፍጥነት ድምጥማጣቸውን ለማጥፋት እንደሚነሳ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ጦርነት የብዙ ዘግናኝ ክስተቶች ምንጭ ቢሆንም ግን – እስካሁን የኢትዮጵያ ወታደር ከቀረቡበት ትርክቶች ውስጥ ጋዝና ቤንዚን እያርከፈከፈ የራሱን ዜጎች በየሜዳው ከምሮ ያቃጥል ነበር የሚል ውንጀላ አንድም ጊዜ ላይ አልሰማሁም፡፡ ይህን ስል አሁን እንዳይጽፉ ሰጋሁ፡፡
ብቻ ግን ያ ጥላቻ አልፎ፣ ጊዜ ጊዜን፣ ሰው ሰውን፣ አቋምም አቋምን ሲተካ፣ ከሁላቸውም ውስጥ ያ ዓይነቱ ለከቱን ያጣ ጥላቻና የደም ስካር የወለደው እብደት ቀስ በቀስ ከልባቸው የወጣላቸው ይመስለኛል፡፡ ጊዜ የማያለዝበው ምን ነገር ይኖራል? ግን ደግሞ ሻዕቢያዎችም አልፈው፣ ወያኔዎችም አልፈው፣ ተረኛው ኦነግና በተለያየ ስም የሚያሰማራቸው ደም አፍሳሾች ደግሞ የሚፈጽሟቸውን እጅግ ዘግናኝ ድርጊቶች አሁን በዚህ ዘመንም ላይ እያየን ነው፡፡ አንዳንዴ ሳስበው እነዚያ የኢትዮጵያ ጥላቻዎች ዳግም ነፍስ ዘርተው በመሐላችን እየጨፈሩ እንዳይሆኑ ያጠራጥረኛል፡፡
የወያኔ-ኢህአዴግ መንግሥት በውድቀት አፋፍ ላይ ደርሶ ከላይ ከታች በተወጠረበት፣ እና የሰው ልጅ ሞትና ዋይታ የነገሠባቸው አስፈሪና ዘግናኝ የመርዶ ዜናዎች ከያቅጣቸው በሚሰሙበት የዛሬ ሶስት አራት ዓመት ገደማ – በመስክ ሥራ ግዳጅ ወደ ሻሸመኔ አዋሳ መስመር አቅንቼ ነበር፡፡ ሻሸመኔና አካባቢዎቹን ጨምሮ እስከ አዋሳ ድረስ በአጊአ (የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ) ኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ሥር ሆነው በምሽት ሠዓት ዕላፊ ሥር ውለው ነበር፡፡ እኔና ባልደረቦቼ ስንሄድ ገና የእሳቱ ጭሶች ከየተቃጠሉ መኪናዎች ላይ አልበረዱም ነበር፡፡ እዚህም እዚያም የፈሰሰው ደም አልደረቀም፡፡ የሰዎች ፊት ለሚመለከታቸው ሁሉ ‹‹ሥጋት›› የሚባለውን ቃል በአካል በአምሳል ያሳብቁ ነበር፡፡
አዋሳ መግቢያ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፌዴራል መከላከያ ሠራዊት ፈስሷል፡፡ በተላላፊ መንገደኞችና ተዘዋዋሪዎች ሁሉ ላይ – ሴት ነሽ ወንድ ነህ ሳይባል – ጅምላ ማመናጨቅና ፍራቻ የቀላቀለበት ክብረ ነክ ብርበራና ማዋከብ ይደረጋል፡፡ ሻሸመኔን እንደምንም አለፍን፡፡ የሀገረ ማርያም መተላለፊያ ተዘግቷል፡፡ እንደገባሁ መረጃ አገኘሁ፡፡ ከሰዓታት በፊት በጥቂት ኪሎሜትሮች ርቀት ‹‹ቄሮ›› ብሎ ራሱን የሚጠራው (እና ኋላ ኦህዴድ እኔ ነኝ ያደራጀሁት ብሎ ያመነው) የኦሮሞ ወጣቶች የታጠቀ ቡድን አካባቢው ላይ በማሸመቅ፣ አስራ ስምንት የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በድንገተኛ ከበባ ገድሏል፡፡ ገደሎም አልበቃውም፡፡ አስከሬናቸው እስኪበጣጠስ ድረስ በገመድ አስሮ መንገድ ለመንገድ በሞተር ሳይክል እየጎተተ ውሏል፡፡ ያንን ተከትሎ፣ ቄሮዎቹን ለመበቀል በሥፍራው የደረሰው የመከላከያ ሠራዊት – ባገኘው ወጣት ላይ እየተኮሰ በመግደልና በማቁሰል ንዴቱን እየተወጣ ነው፡፡
ይህና ሌላም ብዙ መረጃ ተነገረኝ፡፡ በሰዉ ሁሉ ላይ ውጥረት ነግሷል፡፡ መንግሥት የሚፈርስበትና የእርስ-በርስ እልቂት የሚጀምርበት የሆነ የፍርድ ቀን አዋጅ የታወጀ ይመስል በሁሉም ሰው ላይ ፍርሃት ነግሶ አየሁ፡፡ ፍርሃት ጩኸትን ይቀንሳል፡፡ የሁሉም ሰው ንግግር ቮልዩም ወደ ሹክሹክታ ደረጃ ወርዶ ነበር፡፡ ያየሁት የሰማሁት ሁሉ ሰብዓዊ ልብን ያርዳል፡፡ ሰውነትን ያስጠላል፡፡ አካልን ያንዘረዝራል፡፡ እንቅልፍ ይነሳል፡፡ ያ አሁን የምናገርለት ከ40 ዓመት በፊት የታየው የሻዕቢያ ጥላቻ አይደለም፡፡ ያ 40 ዓመት ሙሉ ሀገር ምድራችንን ያመሰው የወያኔ ጥላቻም አይደለም፡፡ ምናልባት ውጤቱ ይሆን? ዛሬ አሁን ላይ በኦነግና ተከታዮቹ ላይ አድሮ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን እያደማ ያለው መንፈስ ከዚያ ካለፍነው ዘመን አስደንጋጭ መንፈስ ጋር አንድ ነው፡፡
ምንጩ ምን ይሆን? የአንዱ ክፋት ሌላውን እያከፋው? ጥላቻ ጥላቻን እየሞረደው? የአንዱ የጥላቻ መንፈስ በሌላው ላይ እየተጋባ? – ወይስ ከመጠን ያለፈ ቁጥራችንን ለመቀነስ በየ40 ዓመቱ ብቅ የሚል የማልቱሲያን የእርስ በእርስ እልቂት ክስተት ይሆን? ወይስ በጭቆናና አፈና ከመጠን በላይ ሞልቶ የገነፈለ የሰዎች የእምቢተኝነት ስሜት መውጫ ቀዳዳ አግኝቶ ሲገነፍል እንዲህ ከቁጥጥር ውጭ ወደሆነ የማይታመን አውሬያዊ ተግባር ይመራ ይሆን? ወይስ እንደ ሩዋንዳ ሲወርድ ሲወረድ ሲንሸራሸር የኖረ ጥላቻና ቂም ባንድ ጀንበር እንደ እሳተ ገሞራ ከየሰዉ ሁሉ ላይ ገንፍሎ ሀገሩን እያጥለቀለቀ ነው? ምን ይሆን ምክንያቱ? ምክንያቱ ብዙ ነው፡፡ ወይም ምክንያቱን በትክክል ማወቅ አልቻልንም፡፡ ይመስለኛል፡፡
መድኃኒቱን በትክክል ያላወቅንለትን ተዛማች በሽታ በጉያችን ታቅፈን እያስታመምን ለመጓዝ በመገደድ ውስጥ ግን፣ የምንደርስበትን የመጠፋፋት መጨረሻ አለማሰብ ይሻላል፡፡ ‹‹የሞቱት የታደሉ ናቸው›› (“The dead are fortunate”) ብሎ ነበር ሼክስፒር፡፡ በእርሱ ዘመን ለንጉሥ የገቡትን መሐላ አፈረሱ፣ ቀኖና አረከሱ የተባሉ 300 ጳጳሳት ከያሉበት ተለቅመው በየዛፉ ላይ የመሰቀላቸውንና ለቀናት ለአሞሮች እንደ ቋንጣ ድግሥ የመቅረባቸውን ጭካኔ በህይወት ኖሮ ለሚመለከተው በህይወት ላለው ሰው አዝኖ ነው ያን ያለው፡፡
አንዳንዴ – እነዚህን ሁሉ ጥላቻ-የወለዳቸው ኢትዮጵያዊ ትንግርቶች ሳይወድ በግድ ከሚያየውና ከሚሰማው እና ወደ ጥፋቶቹ ሳይወድ በግድ ፈጻሚም ሰለባም ለመሆን ከሚጣደው የዛሬው በሕይወት ኗሪ ወገን ይልቅ፣ እነዚያ ያመኑበትን ላመኑበት ኖረው በደህና ጊዜ ያረፉ፣ የተገላገሉ፣ ይህን ሳያዩ ወደማይመለሱበት ዓለም የተሸኙ የቀደሙ ወገኖቻችን ምንኛ የታደሉ ናቸው? እላለሁ አንዳንዴ፡፡ የእውነት!? ያሰኛል አንዳንዱ ነገር! አንዳንዴ!
የቆየም ሆነ ያልቆየ የታሪክ እማኝነቶቻችንን አንስቼ የምናገረው የተረሳ ቂምን ለመቀስቀስም፣ ያገረሸ ቂምን ለመለኮስም አይደለም፡፡ ከ40 ዓመት በፊት ጋዝ በኢትዮጵያን ላይ ጋዝ አርከፍክፎ ባቃጠለው በሻዕቢያ ላይ፣ አሁን እርግማን ለማውረድም አስቤ አይደለም፡፡ ግን ታሪክ ራሱን ይደጋግማልና፣ በአንዱ ባንማር ምናልባት ከድግግሞሹ መማር እንችል እንደሆነ ብዬ ነው፡፡ ምናልባት የሆንነውን ሁሉ ደግመን አስጣጥተን ስናየው አንድ መፍትሄ ወለል ብሎ ይታየን ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል?
በበኩሌ ያለኝ ዓለማዊ ምልከታ በዚህች ዓለም ላይ ለውጥ የማይጎበኘው ምንም ነገር እንደሌለ ያረጋግጥልኛል፡፡ Nothing is impervious to change! ማንም ሳይለወጥ በዚያው ተገትሮ እንደዚያው እንደነበረ የሚቆይ የለም፡፡ በዚያው ባለበት ተቸንክሮ የሚኖር የሰው ልጅ አስተሳሰብም የለም፡፡ የሰዎች አቋም ይለወጣል፡፡ ነባራዊ ሁኔታዎች ይለዋወጣሉ፡፡ ሰዎች ለነባራዊ ሁኔታዎች የሚሰጧቸው ምላሾችም ከጊዜና ከሁኔታ ጋር ይለወጣሉ፡፡
ከዚህ አንጻር ሳስበው – በግሌ አመለካከት – ከሻዕቢያ ማግስት የተወለደው በሻዕቢያ አዛውንት የሚተዳደረው የአሁኑ የሀገረ ኤርትራ ሠራዊት – በሻዕብያ ‹‹የትግል›› ዘመን ሰፍኖ የቆየው የኢትዮጵያ-ጥላቻ ትርክትም ሆነ ተግባር – ከውስጡ ተንጠፍጥፎ ወጥቶለታል ብዬ ማመን እፈልጋለሁ፡፡ የሻዕቢያ አቅምም፣ አቋምም፣ ነባራዊ ከባቢያዊ ሁኔታም፣ ለሁኔታዎቹ የሚሰጠው ምላሽም፣ ሆነ ዓለማዊ አመለካከቱና አሠራሩ – እንደማንኛውም የዚህች ዓለም ነገር ሁሉ – ባለበት ሊቆም አይችልም፣ ተለውጧል፣ ተቀይሯል ብዬ ማመን እፈልጋለሁ፡፡ ስለፈለግኩና ስለተመኘሁ ብቻ ግን አይደለም፡፡ እውነታውም የሚመሰክረው ይህን ይመስለኛል፡፡
ቢያንስ የራሳችን ኢትዮጵያዊ ትውልድ በፍርሃት ቆፈን ተሸብቦ፣ በአይምሬ ገዳይ ገዢዎች ማሰቢያ አዕምሮውና ሰውነቱ እግር-ተወርች ተጠፍንጎ፣ ከከተማ እስከ ገጠር፣ ከምሁር እስከ ወታደር እየተንቀጠቀጠ – ለወያኔና ጭፍሮቹ አሜን ብሎ ሰግዶ እየተዛ በሚኖርበት አሳዛኝ የታሪክ ወቅታችን ላይ – ራሱ በአምሳሉ ጠፍጥፎ የፈጠረውን ወያኔን – በሚያውቅበት የጥይት አለንጋ ለማነጋገር የደፈረና፣ እስኪበቃው ገርፎ፣ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ፣ ልኩን ያስገባው – ሌላ ማንም ሳይሆን – ራሱ ወያኔን ከጭቃ ጠፍጥፎ ፈጥሮ በኢትዮጵያ ላይ የለቀቀብን ሻዕቢያ ይመስለኛል፡፡
ሻዕቢያ ወያኔን የተጋፈጠው በአካል ብቻ አይመስለኝም፡፡ በርዕዮትም ነው፡፡ የዘር ትብታብሽ ለአካባቢው መርዝ ነው! ብሎ በአደባባይ አውጆ – ከነነገዳዊ ፍልስፍናሽ ሰነፈጥሽኝ፣ በቃሽኝ፣ ብሎ በልበ ሙሉነት ጥርት ያለ ርዕዮቱን አንግቦ ወያኔን የተጋፈጠው – ሌላ የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም፡፡ ማንም ጀግና አይደለም፡፡ ሻዕቢያና ሻዕቢያ ብቻ ነው! ጦር ለሰበቀ ጦር ሰብቆ፣ ጦር በጦር እንደሚመለስ በተግባር ያስመሰከረ ማንም ሌላ ኃይል አይደለም፡፡ ሻዕቢያና ሻዕቢያ ነው! ይህን ስል ግን በወያኔ የዕድሜ ልክ የአጥፍቶ-ጠፊነት አቋም ምክንያት በአሁኑ ወቅት በየዕለቱ የሚፈሰው የንጹሃን ወገኖቻችን ሞት ውስጤን አያቆስለኝም እያልኩ አይደለም፡፡
በአንድ ሰው ዕድሜ ያየሁትን የሻዕቢያን ለወቅቱ የሚመጥን በተግባር የታየ ለውጥ ስመሰክር – በወያኔ ላይ ዘማች ነኝ ብሎ የኢትዮጵያን መንግሥት የተቆጣጠረው የኦሮሙማው ኃይል ከወያኔ ያነሰ የኢትዮጵያ ጥላቻ ያነገበ ኃይል ነው እያልኩ አይደለም፡፡ ወያኔን የሚያስከነዱ ባንዳዊ ስሌቶቹን ከልቤ የሚቀበል ህሊና ኖሮኝም አይደለም፡፡ ታሪክ በህይወት አቆይቶ እንዳየው ስላደረገኝ ስለ ሻዕቢያ ተገዳዳሪ ጀግንነት ስናገር ለትግራይ ህዝብ ዘለዓለም ዓለሙን ጦርነትና ጥይት ይገባዋል እያልኩ አይደለም፡፡ ለኤርትራም ህዝብ ዘለዓለም ዓለሙን የጥይት አረር ሲጨስበት እንዲኖር ተመኝቼ ቸይደለም፡፡
ከኦቶማን ዘመን፣ እስከ ፋሺስት፣ ከወያኔ-ሻዕቢያ ዘመን እስከ አሁን ድረስ የትግራይ ህዝብ የዘወትር ቀለብ ጥይት፣ ሞትና ዋይታ መሆኑ እጅግ ልቤን ያደማዋል፡፡ የኤርትራ ህዝብ ከረዥም የእርስ በእርስ ደም አፋሳሽ ጦርነት ወጥቶ፣ ደግሞ ደጋግሞ ወደ ሌላ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ የመግባቱ አሳዛኝ ዕጣ ፈንታ ከልቤ ያሳዝነኛል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በርሱ ከመጋደልና ከመደማማት አለመውጣቱ እስከ ህልፈተ ሞቴ ያስቆጨኛል፡፡ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር መደፈር ሁለመናዬን የሚቆረቁረኝ ሰው ነኝ፡፡
ከፋፍሎ ሊገዛን የመጣ የውጭ ቅኝ ገዢ ጠላት ብቻ በሚያደርገው ልክ፣ ኢትዮጵያውያንን ሺህ ቦታ ከፋፍሎና ዘነጣጥሎ የኢትዮጵያን አንድነት በመቆራረጥ፣ እንዲህ አሁን እንደምናየው የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የማንም መጫወቻ ሆኖ መቅረቱ የሚያንገበግበኝ ሰው ነኝ፡፡ ዛፎች አልቀው እንቧጮዎች ዋርካዎች መሆናቸው ያንገበግበኛል፡፡ ኢትዮጵያ ከጠበበ የጎጥ አስተሳሰብ ባልወጡ ሚጢጢ ሰዎች እጅ መውደቋ እስከ ወዲያኛው ያስቆጨኛል፡፡
ነገር ግን በዚህ ሁሉ መካከል ሻዕቢያ – ከኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በድንበር ተከለለም አልተከለለም፣ በሀገር በሰፈር ተለየም አልተለየም፣ ራሱን የቻለ ባንዲራ አውለበለበም አላውለበለበም፣ የዓለም ጉልበተኞች ለራሳቸው ጥቅም ግልቢያ እንዲያመቻቸው የቀረፁትና የሚያበጃጁት ዓለማቀፍ የአገዛዝ ሥርዓት ተፋለሰም አልተፋለሰም፣ ሻዕቢያ ከ40 ዓመት በፊት ኢትዮጵያውያንን ጋዝ እያርከፈከፈ ሲያቃጥል የነበረ የአንድ ዘመን አሸማቂ ይሁንም አይሁንም – አሁን ግን – አሁን – ለእኔ – ሻዕቢያ – እምቢኝ ለኢትዮጵያ ብሎ በተግባር በሙሉ ልብ የተነሳ – የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጅ መሆኑን ያስመሰከረ – ታሪክ የማይረሳው የኢትዮጵያ ጀግና ሆኖብኛል፡፡
አሁን ሻዕቢያ እያደረገ ያለውን ኢትዮጵያን የመገላገል ተግባር – እስኪያስደነግጠኝ ድረስ፣ የሻዕቢያን መለወጥ ማመን እስኪሳነኝ ድረስ፣ ገርሞኝ አላባራ ያለ፣ እና በከፍተኛ ጥርጣሬና ሥጋት ውስጥ ሆኜ ያየሁት የማይታበል እውነት ነው፡፡ የወያኔን ናዚ ሽማግሌዎች ታግሶ አይቀጡ ቅጣት የቀጣልን ሻዕቢያ – በተብረከረከ ትውልድ ፊት ቀጥ ብሎ በጀግንነት መቆምን በተግባር ያሳየን ሻዕቢያ – የድሮውን ሃጢያቱን በታላቅ የቅድስና ተግባር እንዳጠበልን እቆጥረዋለሁ፡፡ በግሌ የሻዕቢያ ያለፈ ቁስል ወጥቶልኛል፡፡ ከሻዕቢያ ላይ ቀረኝ የምለው ነገር የለኝም፡፡ የሻዕቢያ ጠላትነት ከውስጤ ወጥቶልኛል፡፡ በቀሪው ዘመኔም በሻዕቢያ ላይ ላስበው የምችለው ኩነኔ የለም፡፡
ኢትዮጵያውያን በፍርሃት ርደው በተገኙበት፣ እምቢኝ ብሎ በልበሙሉነት ተሰልፎ ወያኔን ድባቅ የመታው ሻዕቢያ ምስጋና ይገባዋል! ሻዕቢያ ወደደም ጠላም፣ እኛ ወደድንም ጠላንም፣ ሻዕቢያም ሆነ ኤርትራዊ ትውልዶቹ – ከእናት ኢትዮጵያ አብራክ የወጡ፣ የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ታሪክ በደማቁ የመሰክረልን እውነት ይህ ነው፡፡ እንደ እኔ ሻዕቢያን የኢትዮጵያ ወዳጅ ይሆናል ብለን ለማሰብ ላልፈለግን ሰዎች ሁሉ – ታሪክ በተግባር እየመሰከረልን ያለው እውነት ይህንን በይፋ የተገለጠ እውነት ነው፡፡ ሻዕቢያ በኢትዮጵያ ላይ ፈጥሮ የላከባትን የወያኔን ዘረኛ ኃይል ቀንዱን ሰብሮ በፊታችን አሳይቶናል፡፡ ሻዕቢያ የቁርጥ ቀን ባለውለታችን ነው፡፡ እናመሰግናለን፡፡
ዕድሜ መስታወት ነው፡፡ እስካሁን ብዙ አይተናል፡፡ መኖራችን ካልቀረልን – ያቆየንና – ገና ነገ የሚያመጣውን ብዙ ታሪክ ደግሞ እናያለን፡፡ በጀግኖች ብቻ የሚጻፍ ገና ያልተወራረደ ቀሪ ኢትዮጵያዊ ታሪክ አለ፡፡ ያን ታሪክ መጻፍ ለአሁኑና ቀጣዩ ኢትዮጵያዊ ትውልድ የተሰጠ አደራ ነው፡፡ ፈጣሪ እናት ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ በቁርጥ-ቀን አለሁሽ ብለው ከጎኗ የቆሙ ጀግኖቿንም፡፡
_____________________
Image: a page (pp. 139) from Dan Connell’s book, “Against All Odds – A Chronicle of the Eritrean Revolution”, 1997, paper back edition with a new afterword aon the postwar transition, The Red Sea Press, Inc.
Filed in: Amharic