>

ታጠቅ ታጠቅ. . .  ምን ጊዜም ታጠቅ!   (አቻምየለህ ታምሩ)

ታጠቅ ታጠቅ. . .  ምን ጊዜም ታጠቅ!  

አቻምየለህ ታምሩ

ጦርና ወሬን ድል ነስተው፣ ለሀገራቸው ሊፈጽሙ ያሰቡትን አስደናቂና ዘላቂ ዓላማ አንግበው ሲያደርጉ የኖሩትን ተጋድሎ ጨርሰው፣ ታሪክ ቀይረውና የዘላለም ስም ተክለው ያለፉት ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ “እጄን ለጠላት ከመስጠት ራሴት በገዛ እጄ ብገድል ይሻለኛል” ብለው መቅደላ ላይ ሕይወታቸውን በማሳለፍ ትግላቸው የፈጸሙት ከዛሬ 153 ዓመታት በፊት በዛሬው እለት ሚያዚያ 7 ቀን 1860 ዓ.ም. ነው። ዘላለማዊ ክብር የማይጠፋ ሥራ ሰርተው ላለፉት ንጉሠ ነገሥትና አብረዋቸው ለወደቁ  ጀግኖች ሁሉ ይኹን!
አሁን የምንገኝበት አይነት ተመሳሳይ ዘመን ያጋጠማቸው  አርበኛው ሠዓሊ አገኘሁ እንግዳም በ1928 ዓ.ም. በጻፉት አስደማሚ ግጥማቸው የዐፄ ቴዎድሮስን መንፈስ እንዲህ ጠርተውታል. . .
በግራ በቀኝህ ጠላት መቶብሀል፣
በፊትም በኋላ ደመኛ ከቦሀል፣
በል ተነሣ ካሳ ባንተ ያምርብሀል፤
አሁንም ሙትልኝ ታጠቅ እንደገና፣
መቼም መች አይገድህ ሞት በጅህ ነውና።
ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያትም “ቴዎድሮስ” በተሰኘው ቲያትራቸው እንዲህ ቋጥረው ነበር. . .
ሱሪህ አረንጓዴ ጐራዴህ ባለ ወርቅ፣
በጣም አምሮብሃል አንተ ብቻ ታጠቅ፤
አባትና እናቱ ያላንድ አልወለዱ፣
አባ ታጠቅ ካሣ ያው አንዱ ያው አንዱ። (ያ ወንዱ)።
አጤ ቴዎድሮስ የጀግንነት ብቻ ሳይሆን የርህራሄም አባቱ ነበሩ…!!!
ከእለታት በአንዱ ቀን አጤው በአለቃ ገብረሃና ድርጊት እጅግ ተናደዱ። ሲወጡ ሲገቡ የአለቃን ሾርኔ መቋቋም አቃታቸው። እሳቸው ሲበዛ ቁጡ ነበሩና ለቧልት ልባቸው እምቢ አለ። በዚህም ተማረው አለቃን ከፊታቸው ገለል ማድረግ ፈለጉና “አንተ ሰው… ወይ ቀልድህን ተወኝ አልያ እኔ ከማልገዛው አካባቢ ሄደህ ኑር፤ ካሁን በሗላ እንዳላይህ፤ አሻፈረኝ ብለህ ግዛቴ ውስጥ ብትገኝ ግን አይቀጡ ቅጣት እቀጣሃለሁ!” ብለው አለቃን አሰናበቷቸው።
አለቃም “እንግዲህ አጤው የማይገዙት ጎንደር የለ፥ ጎጃም የለ፥ ወሎ፥ ሸዋ የለ  ታዲያ ወዴት እሰደዳለሁ?” ብለው ደሴ አካባቢ ዘጌ ደሴት ላይ መኖር ጀመሩ። እዚያ መኖራቸውን ያዬ አንድ እሾማለሁ፥ እሸለማለሁ ያለ አቃጣሪ ተማሪያቸው ይህንኑን ሊናገር ወደ አጤው ገሰገሰ። እንደደረሰም ለንጉሱ እንዲህ ብሎ ተናገረ፦
“ንጉሥ ሆይ፦ በእኔ ግዛት ውስጥ እንዳላይህ ያሉት ወንበዴኮ ዘጌ ደሴት መኖር ከጀመረ 8 አመት አልፎታል” አለ።
ንጉሡም “ማነው እሱ?” ብለው ጠየቁ።
“አለቃ!”
“አለቃ ማ?”
“አለቃ ገብረሃና!”
ይህኔ ንጉሡ በመናደድ ወታደሮቻቸውን ጠርተው አለቃን ካለበት ይዘው እንዲያመጧቸው አዘዙ። አለቃም በወታደሮች ተይዘው ንጉሡ ፊት ቀረቡ። ይሄኔ አጤ ቴዎድሮስ ያን አቃጣሪ ተማሪ “በል አሁን መምህርህን ክሰሳቸው” አሉት።
ተማሪውም ቀጠለ “በግዛቴ እንዳላይልህ ያሉት ወንበዴ ዘጌ መኖር ከጀመረ 8 አመት አልፎታል” አለ።
አጤውም በመገረም “አሁን እኔ ከመምህርህ በልጨብህ ነው ይሄን የምትነግረኝ? ሲሆን ሲሆን መደበቅ ነበረብህ? እንዳውም የእሳቸውን ቅጣት አንተ ትቀጣለህ” ብለው አርባ ጅራፍ ከፈረዱበት በኌላ “አለቃ በግዛቴ እንዳላይልህ አላልኩህም?”
“ጃንሆይ በጎንደር፥ በጎጃም፥ በወሎ፥ በሸዋ ግዛቱ መሬቱ ሁሉ የእርስዎ ቢሆንብኝ ወደ ደሴቱ ሄጄ ከውሀው ተጠግቼ መኖሬ ነበር … !”  ቢሏቸው ጃንሆይ በሀዘኔታ አንገታቸውን ሰበር አድርገው “በል ባሻህ ኑር!” ብለው አሰናበቷቸው።
ንፍስህን ይማረው ጃንሆይ!
Filed in: Amharic