>

...አጆሓ አጆሓ... (ሙሉአለም ገ/መድህን)

አጆሓ አጆሓ…!

ሙሉአለም ገ/መድህን

ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በኋላ ኤርትራ በእንግሊዞች የሞግዚት አስተዳደር ስር ለአስር ዓመታት (1934-1943) መመራቷ ይታወቃል፡፡ 
እንግሊዛውያኑ በዚህ ቆይታቸው ፖለቲካዊ ቅርጽ እንዲይዝ የደከሙለት አንድ ነገር ነበር። ይኼውም ሁለቱን ትግረኛ ተናጋሪ ሕዝቦች ከኢትዮጵያ በመነጠል እንደ ሀገር አንድ ሆነው እንዲቆሙ ለማድረግ የፖለቲካ ፕሮጀክት ዘርግተው ነበር፡፡ በተለምዶ ‘ትግራይ-ትግርኝ’ የሚባለው ማለት ነው።
በወቅቱ በእንግሊዞች ድጋፍ የተመሠረተው የኤርትራዊው ወልደአብ ወልደማሪያም ሊበራል ፕሮግረሲቭ ፓርቲ ‹የትግራይ-ትግሪኝ› አቀንቃኝ በመሆን ‘ሀገር የመመስረት’ ፕሮጀክት ለማስፈጸም ተልዕኮ ተሰጥቶት ነበር፡፡
በወቅቱ በንጉሡ አስተዳደራዊ ጥበብ የእንግሊዝ የሞግዚት አስተዳደር ቀርቶ፣ ኤርትራ በፌዴሬሽን ወደ ኢትዮጵያ ስትመለስ ፕሮጀክቱ የከሸፈ ቢሆንም አስተሳሰቡ ብልጭ ድርግም እያለ  ጨርሶ ሳይጠፋ ዘመናትን ተሻግሯል። በተለይም ‘ኢትዮጵያ ላይ ገዥነታችንን ያቆምን ቀን አደጋ ስለሚኖር ከሁዲሁ ፍኖታችን እናስተካከል’ የሚሉ የትህነግ ሰዎች ከሃሳቡ ርቀው አያውቁም ነበር።
ይህ ከሰባ ዓመት በላይ ያስቆጠረ አመለካከት፣ በነስብሃት ነጋ ባጀት መዳቢነት ‹በመረብ ኢንስቲትዮት› በኩል ድርጅታዊ ቅርጽ እንዲይዝ ሲሰራበት ቆይቷል። በዋናነት ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ ኢሳያስን ለማስወገድ የዚህ ጥምረት (የትግረኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ውስን ልሂቃን) መሰባሰብ ታምኖበት፣ ከኢፈርት እየተቆነጠረ ባጀቱ ይረጭ ነበር፡፡ በአፍሪቃ ቀንድ ጥናት ስም የውጭ ፈንድ ድጋፍም አይጠፋም ነበር። እንዴውም በዚህ ፕሮጀክት ዙሪያ አነ ማርቲን ፕላውት (እንግሊዛዊ መሆኑን ያስታውሷል) ሳይቀር አማካሪ ሆኖ መስራቱ ይነገራል፤ ሰውየው ተራ ጋዜጠኛ ብቻ አይደለም፤ ሚናው ከዚህ ያለፈ ነው።
በኢትዮጵያ ስቴት እምነት እያጣ የመጣው የድኀረ-መለሱ ትህነግ፣ በዋናነት የስብሃት ነጋ ክንፍ የትግራይ ትግርኝ ፕሮጀክት ኢሳያስን ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን በትኖ በዘላቂነት የመጠቃለል ምኞቱ  ነበረው።
ውለው ያደሩ የታሪክና የፖለቲካ ቅራኔዎቻቸው እንዲሁም የቀጣናው ተለዋዋጭ ባህሪ ታክሎበት ሁኔታዎች አልፈቀዱምና ፕሮጀክቱን ተስፋ  ቢስ የሚያደርግ ነገር ተከሰተ። ቀድሞውንም የኢትዮ-ኤርትራን የእርቅ ምዕራፍ በበጎ ጎኑ ያልተመለከተው ትህነግ፤ ሁለት ዓመት ተኩል የአስመራን መንግሥት ለመገልበጥ በነ ጀኔራል ኤፍሬም ስብሃት ላይ ሳይቀር የግድያ ሙከራ እስከ መሞከር ደርሶ ነበር። ኋላም የጥቅምት 24ቱ ታሪካዊ ዕብደቱ ኤርትራን ጎትቶ አምጥቶ ዳግም ደም ተቃቡ። በተለይም ትህነግ መደበኛ ጦርነት በመካሄድ ላይ በነበረባቸው ሳምንታት በሦስት የተለያዩ ቀናት ተከታታይ ሮኬቶችን ወደ አስመራ ማስወንጨፉ ታሪካዊ ቁርሾውን በማመርቀዝ ጥሉ ማህበረሰባዊ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎታል። ይህ ቅራኔ በቀላሉ የሚታረቅ አይደለም። ከምንም በላይ በጦርነቱ ወቅት በትግራይ የስደተኞች ካምፕ ተጠልለው ይኖሩ በነበሩ የኤርትራ ተወላጆች ላይ ትህነግ የፈጸመው ጭፍጨፋ እንደሕዝብ አዲስ ጠባሳ ፈጥሯል።
የዚህ ጠባሳ ውጤት ይመስላል ቁጥራቸው አናሳ ቢሆንም የትግራይ ትግርኝ ፕሮጀክት ደጋፊ የነበሩ በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ በጋብቻ የተሳሰሩ የሁለቱ ማህበረሰቦች፣ በጦርቱ የተነሳ ፍች እስከመፈጸም የደረሱት። ይህን ‘ማህበራዊ አመጽ’ በዜና አውታሮች ሲዘገብ እንደቀልድ ተመልክተናል። ይህ ተራ ዜና አይደለም! በዲያስፖራ ኮምዩኒቲ ደረጃ ከኢሳያስ አስተዳደር ጋር ቅሬታ አለባቸው የተባሉ ኤርትራዊያንን በማጥመድ ከትግራይ ዲያስፖራ ጋር እንዲጋቡ (የፖለቲካ ጋብቻ)  ብዙ የተሰራበት ማህበራዊ ትስስር ውሃ በልቶታል። በርካቶች ፍች ላይ ናቸው። ይህ ፖለቲካሊ ኪሳራው ወደ ቀጣዩ ትውልድ ጭምር የሚሻገር ነው።
በሌላ በኩል የትህነግ አስተሳሰብ ተሸካሚ የሆኑ የትግራይ ልሂቃን “ኢትዮጵያ ትፍረስ” የሚል አመለካከት ይዘው በድርጊት እየገለጹት ነው። “ከኢትዮጵያ ሕዝብ የሱዳን ሕዝብ ይሻለናል” ባይ ናቸው። ሱዳን ግን በቋንቋም ሆነ በባህል እንዲሁም በድንበር የምታዋስናቸው አይደለችምና ልፋፌው ቀቢጸ ተስፋነት ነው።
በምኞት ደረጃ ግን የሃሳቡ አቀንቃኝ የሆኑት ‹ትግራይ ትግሪኝ› ትግራይን ከኤርትራ ትግረኛ ተናጋሪዎች ጋር በማዋሃድ ሀገር የመፍጠር ፖለቲካዊ ግቡን ለማሳካት ጊዜው አሁን ነው የሚል ምኞት  ይዘው ቁጭ ብድግ ማለታቸውን አይተውም። በሳተላይት ጣቢያና በ Zoom meeting ‘ሶሊዳሪቲ’ ምናምን በሚል እየተፍጨረጨሩ ነው።
ለዚህም ይመስላል በሀገር ቤት እነ Ztseat Saveadna Ananya ከኤርትራ የደጋማው ክፍል ሐማሴኑን በመነጠል ሲያመሰግኑት የታየው። ያው ፖለቲካ መሆኑ ነው፤ ዛሬም የትግራይ ትግርኝ ፕሮጀክት ፍላጎት አለን እያሉ ነው።
በነዚህኞቹ ተስፈኞች በኩል ‹የታሪክ መሠረት› እንዲይዝ ጥረት ሲያደርጉበት የቆዩትን ይሄን ፕሮጀክት ከመቼውም ጊዜ በላይ ፍላጎታቸው ሊንር ቢችልም ጉዳዩ የአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው የሚሆነው፡፡ የኢሳያስ ተቃዋሚ ከሆኑት ከጥቂት ደገኛ ሽማግሌ ዲያስፖራዎች በስተቀር ወጣቱ ትውልድ ኤርትራዊ ማንነት ይዟል። በዲያስፖራው በኩል ሲሞከር የኖረው የፖለቲካ ጋብቻም፣ ከጦርነቱ ወዲህ መምከኑን እያስመሰከረ ነው። በርካታ ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ጎን ተሰልፈው ትህነግን ከማውገዝ አልፈው፣ ለሁለቱ ሀገራት እና ለአፍሪቃ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት ያላቸውን ቀናዒ ፍላጎት  አስመስክረዋል።
‹‹እኛ ሁለታችንም አግኣዚያን ነን›› የሚለው የጋራ ትርክት የፖለቲካ ፕሮጀክቱ የፕሮፖጋንዳ መስመር ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ቢሆንም፣ ዛሬ ሃሳቡ ገዥ አጥቷል።
ወትሮም ቢሆን እኮ! ኤርትራ የአፋር፣ ብሌን፣ ሂድራብ፣ ኩናማ፣ ናራ፣ ራሽዳ፣ ሻኦ፣ ትግረ እና ትግርኝ የሚባሉ የዘጠኝ ዘውጎች ሀገር በመሆኗ የነሱ ፕሮጀክት መሬት ላይ ቦታ ሊያገኝ አይችልም፡፡ የኤርትራ ቆላማው ክፍል በአመዛኙ የእስልምና እምነት ተከታይ በመሆኑ የትግራይ-ትግርኝን ፕሮጀክት በጽኑ ያወግዘዋል፤ ሃራም ነው!
የሳልሳዊ ወያነ ትውልድ እንደ ትህነግ አመጽን የትግራይ ጥቅም ማስከበሪያ አድርጎ ሊንቀሳቀስ የሚችልበት ዕድል ጨልሟል። በርግጥ በጦርነቱ ወቅት የደረሰውን ሰብዓዊ ቀውስ ከታሪክ በወረሰው አረዳድ ‘አዲስ የቅራኔ ምንጭ’ በማድረግ አመጽ ለመፍጠር ሊነሳ የሚችልበት ዕድል ጨርሶ የተዘጋ ባይሆንም፣ ወደ ኤርትራ ለመሸሽም ሆነ ከማዶ አጋር ለማግኘት የሚያስችል አሁናዊ ሁኔታ የለም፡፡  ሱዳን እንደሆነች ሙሉ በሙሉ በአማራ በኩል ነው ከኢትዮጵያ ጋር የምትዋሰነው።
አስመራ ላይ እግረ ረዥሙ ሰውዬ በሥልጣን ላይ ባይኖር እንኳ የትግራይ ትግርኝ ፕሮጀክት የተዘጋ ፋይል ነው!
ኤርትራ በኮንፌዴሬሽን ወደ ኢትዮጵያ ትመጣ ካልሆነ ያ የእንግሊዝ ምኞት ዘላለማዊ  ቅዥት ሆኖ ይኖራል!
[ያው በዚህ ጦርነት የእንግሊዝ መንግስትና ሚዲያዎቻቸው እንዲሁም ግብረ ሰናይ ድርጅት ነን የሚሉ የ MI6 ቅርንጫፎች የሕግ ማስከበር ዘመቻውን እንዴት አክፍተው እንደሳሉትና በጉዳዩ ላይ ጫና ለማሳደር እንዴት እንደተረባረቡ አይተናል፤ ‘ትግራይ ትግርኝ’ ባይሳካ እንኳ ‘ትግራይ ሀገር’ ትሁን ባይ ናቸው፤ የከረመብን ጩኸት ስለሰብዓዊነት ሳይሆን መሠረቱን ማህበረሰብ ላይ ያደረገ የፖለቲካ ቅራኔ ማቀጣጠያ ነው]
ይልቁንስ አሁን አሜኬላው ተነቅሏልና የኢትዮጵያና የኤርትራ ወዳጅነት በተቋማት ትብብር መሠረት እንዲይዝ ሊደርግ ይገባል። ይህ ተቋማዊ ትብብር የጋራ የየብስና የባህር ጦር እስከማደራጀት ሊደርስ ይችላል።
እናም የሳልሳይ ወያነ ትውልድ ለኢትዮጵያ መገበር ብቸኛ ምርጫህ ነው ልንለው እንገደዳለን፤ …አጆሓ አጆሓ…
ለሰፊው የትግራይ ሕዝብም ቢሆን በሀገረ-ኢትዮጵያ ጥላ ስር መቀጠሉ ነው የሚያዋጣው። ሌላው ቢቀር ኢትዩጵያ ሰፊ የገበያ ዕድል ነች!
Filed in: Amharic