>

ዘውግ(ብሔር) ሳይንሳዊ  መሰረት የሌለው ምናባዊ ነው!!! መጽሀፍት ለሁሉም

ዘውግ(ብሔር) ሳይንሳዊ  መሰረት የሌለው ምናባዊ ነው!!!

መጽሀፍት ለሁሉም

እንስቷ የፖለቲካ ተንታኝና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ  መስከረም አበራ  ኢትዮጵያን በሚንጣት የዘውግ ፖለቲካ ዙሪያ ጥልቅና ፈር ቀዳጅ  ያልተጠበቀ ስራ ይዛ በመምጣቷ ትልቅ አክብሮት ይገባታል!!!
  ———————–
    በገጽ 7 ላይ ‘ በዓለም ላይ ” ባሉ ዩኒቨርስቲዎችና ማዕከሎች ውስጥ  በክብር የሚቀመጥ …ለአጥኝዎችና ለተመራማሪዎች ሊቀርብ የሚገባ የእውቀት ምንጭና የማሕበረሰባዊ ጉተራ ነው ” በማለት የገለጡት “የችካጎ ሃርፐር የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ፣ የዲፓርትመንት ኃላፊ እና የቪዥን ኢትዮጵያ መስራች ፕሬዘዳንት የሆኑት ዶክተር ጌታቸው በጋሻው በተጋነነ መንገድ ምስክርነት ሲሰጡ ለገበያ ማሻሻጫ መስሎኝ  ነበር  … ዳሩ ግን መስከረም ከገንዘብና ከዝና ርቃ በዚህ ዘመን ከአንድ ቆራጥ ኢትዮጵያዊ አርበኛ የሚጠበቀውን እንዳደረገች የምንረዳው መጽሐፉን በእርጋታ ስናነበው ብቻ ነው ።
     ————
      ብሔርን ፣ ዘውግን ፣ዘርን ፣ማንነትን ፣ነገዳዊነትን ጎሳን በተለይም  ከሶሾሎጅ እንጻር ከስር መሰረቱ በጥልቀት በአመክንዮና በመረጃ ስተነትነው ለተመለከታት ሰው መስከረምን ከማሕበራዊ ሚዲያ በሳል ንግግሯ ባሻገር በተየ መንገድ እንዲመለከታት ታስገድደዋለች ።
    ———
    ማንነትን በቋንቋ ፣በባሕል ፣በዘውግ ፣በመደብ ፣በሃይማኖት…መወሰን ሳይንሳዊ መረጃ የሌለው ስሁት የፖለቲካ  ጨዋታ መሆኑን በአመክንዮና በመረጃ ትተነትናለች ገጽ 83  ሃገራችንን እየፈተናት ያለው ሰዎችን በዘውግ የመከፋፈል  ፖለቲካዊ ጽንሰ ሃሳብ  ሳይንሳዊ ማስረጃ የሌለው ተለዋዋጭ ምናባዊ  የፖለቲከኞች ፈጠራ እንደሆነ በአመክንዮ ትተነትናለች ። ገጽ 93
    የዘውግ ፖለቲካ በአፍሪካ  እንዲመሰረት ፣እንዲደራጅና እንዲያድግ  በማድረግ ክፋት የሰሩት የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች እንደሆኑ በዝርዝር በመረጃ  ትናገራለች ።
   ————–
   ኢትዮጵያን እንደ ሃገረ- መንግስት  ያቆሟት አእማዳት የሰሎሞን ስርወ መንግስት ርዕዮት ፣ የኢትዮጵያ ኦ.ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የአማርኛ ቋንቋ  ናቸው በማለት በተለይ የዘውዱ ስርዓትና ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከአማራ ሕዝብ ጋር ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለዬ ግንኙነት እንደሌላቸው ትተነትናለች ።  ከገጽ 255 እስከ 306
  ———-
    የዘውግ ፖለቲካን ጽንሰትንና እድገትን  በኢትዮጵያ  በዝርዝር  የተነተነችበት መንገድ ልዩ ነው ። የዘውግ ፖለቲካ በመጀመሪያ በሚሽነሪዎች ተጀምሮ እንዴት ጣሊያኖች እንደቀመሩት እንግሊዞች እንዴት እንዳሳደጉት እና የኢትዮጵያ ተማሪዎች ደግሞ እንዴት  እንዳፋጠኑት ከዘረዘረች በኋላ በሕወኃት ፣ በሻቢያና በኦነግ መሬት ላይ እንዴት እንደወረደ በግልጽ የታሪክ ፍሰት ተንተነዋለች ።
   ———
    የዘውግ ፖለቲካን ይዞ ዲሞክራሲን እገነባለሁ ማለት እንደማይቻል እና በዘውግ (በብሔር) አስተዳደር ውስጥ  እውነት ፣ፍትህ ፣ አመክንዮ ፣ መብት ፣ ዲሞክራሲ ወዘተርፈ እንደሌለና በጊዜው መላ ካልተበጀለት አደገኛ እንደሆነ በብዙ ቦታዎች ላይ ከዓለም ተሞክሮዎች  በማምጣት ትመክራለች ።
   ————–
  በመጨረሻም  በገጽ 406   እዲህ ትላለች “ሃገራችን የፖለቲካ አካሄዷን ከዘውግ ወደ ሕዝብ… ከፍ ካላደረገች ዲሞክራሲን መገንባት አትችልም ብቻ ሳይሆን እንደ ሃገረ መንግስትም የመቀጠል እድሏም ፈተና ውስጥ ይገባል  ። ይህ ፈተና ደግሞ ሁሉንም የሃገሪቱን ዜጋ ሊያሳስበው ይገባል” በማለት መጽሐፉን ትጨርሳለች ።
    ——-
 የሃሳብ ድግግሞሽ ፣ ከበድ ያለ ወደ አካዳሚያዊ ያደላ አጻጻፍ   እና በታሪክ ደረጃ በተለይም በኢትዮጵያ ኦ.ተዋህዶና በሰሎሞናዊ ስርወ መንግስት ዙሪያ ያቀረበቻቸው ታሪኮች የታሪክ ምንጭና ሳይንሳዊ ትንተናዎች ይቀራቸዋል። Yosef Fiseha  የሰጣቸውንም አስተያየቶችንም እጋራለሁ ።
     የኢትዮጵያን አሁናዊ ውስብስብ የግራ መጋባት የፖለቲካ ዝቅጠት መንስኤ የሆነውን የዘውግ ፖለቲካን እኩይነት ማስረዳትና የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ ከጊዜያዊ መፍትሄ ጎን ለጎን ለሚቀጥለው ትውልድ ጥቅሙ ብዙ ነው ።
     መስከረም አበራ ይኸንን ፈር ቀዳጅ መጽሐፍ ስላበረከትሽልን እናመሰግናለን!
*   *  *
“የዘውግ ፖለቲካ ስረ- መሰረቶች” የተሰኘውን  መፅሃፌን Book for ALL እንደሄሰው። በጣም አመሰግናለሁ
Filed in: Amharic