>

የራሱን ሽንፈት የተነበየ አወዛጋቢው የሀገር መሪ (ይሄይስ አእምሮ)

የራሱን ሽንፈት የተነበየ አወዛጋቢው የሀገር መሪ

ይሄይስ አእምሮ (yiheyisaemro@gmail.com)

ሰዎች ስለሰዎች የእውነትም ይሁን የሀሰት ትንቢትን ይናገራሉ፡፡ አንዳንዶችም ስለራሳቸው የወደፊት ሁኔታ ምናልባትም ስለአሟሟታቸው የሚተነብዩ አይኖሩም አይባልም፡፡ የራሱን አሸናፊነት እንጂ ሽንፈቱንና ውድቀቱን የተነበየ ግን በበኩሌ አንድ ሰው ብቻ አውቃለሁ፡፡ እርሱም የኦሮሚያው ምክትል ጠ/ሚኒስትር  አቢይ አህመድ አሊ ነው፡፡

ወደሥልጣን እንደመጣ ህዝብን ያስገረመ አንድ ጥሩ ነገር ተናገረ፡፡ “መግደል መሸነፍ ነው” አለና አዳሜን በአግራሞት አስደመመ፡፡ “እንዲህ ያለ መሪ ከኢሕአዲግ ጉያ መውጣቱ የእግዜር ተዓምር እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም” ብለን ሁላችን ማለት ቢቸግርም ቢያንስ አብዛኞቻችን በደስታ ጮቤ ረገጥን (ኧረ እንዲያውም “በሱ የመጣ ባይኔ መጣ” ያልንም ነበርን)፡፡ አጅሬ አቢይ የተናገረው ትንቢት ወደራሱ መዞሩን ለመረዳት ግን እንደወያኔ ዘመን 27 ዓመት መጠበቅ ሳይኖርብን ከሦስት ዓመታትም እጅግ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ገሃድ እውነቱ ወጣ፡፡

አንድ የፐርሽያ ንጉሥ ነው አሉ፡፡ ከጎረቤት መንግሥት ጋር ይጣላል፡፡ ከጠቢባን ነቢያቱ መካከል በጣም ዝነኛ የሆነውን አንዱን ይጠራና “ከአንድ መንግሥት ጋር  ጦርነት መግጠም አስቤያለሁና ምን ይታይሃል? አሸንፍ ይሆን”? ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ነቢዩም “ንጉሥ ሆይ! አንድ ታላቅና ስመጥር መንግሥት እንደሚያጠፉ ይታየኛል!” ሲል ይነግረዋል፡፡ በዚህ ትንቢት ልቡ እንደኦህዲድ/ኦነጉ አቢይ አህመድ ያበጠው ንጉሥ “ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት” ብሎ በደርጉ አማርኛ ባለ በሌለ ኃይሉ ያን የጎረቤት መንግሥት ሊወር ይነሳል፡፡ ግን ብዙም ሳይፋለም የራሱ መንግሥት እንኩትኩቱ ይወጣና ንጉሡ እግር አውጭኙን ሸሽቶ አንዱ ሸጥ ውስጥ ይወተፋል፡፡ ዙፋኑና ክብሩም ከነቤተ መንግሥቱ በባላጋራው የጎረቤት ንጉሥ ይወረሳል፡፡ ይህ የተሸነፈ ንጉሥ እንደምንም ብሎ ያን ነቢይ ያገኘውና “ታላቅ መንግሥት ትጥላለህ አላልከኝምን? ምነው ጉድ ሠራኸኝ!” ብሎ በቁጭት ይጠይቀዋል፡፡ ነቢዩም የዋዛ አልነበረምና “ታዲያ ምን አጠፋሁ? ይሄውና የራስዎን ገናና መንግሥት ለሽንፈት አልዳረጉምን?” ይለዋል፡፡ እውነት ነው፡፡

አንዳንድ ትንቢት ቀጥተኛ ነው፡፡ አንዳንድ ትንቢት ደግሞ የግልብጥ ነው – በአተረጓጎም ስህተት ወደባለቤቱ ይዞራል፡፡ ፈረንጆቹ Self Fulfilling Prophecy የሚሉት ነገር አላቸው፡፡ በላይኛው አንቀጽ የተገለጸው ሞኝ ንጉሥ ያደረገውን ትንቢት-ነክ ሕፀፅ ዓይነት፡፡

ነገር አሳመርኩ ብሎ ራሱም በቅጡ ያልገባውን “መግደል መሸነፍ ነው” ብሎ የተናገረው  አቢይ አህመድ ተሸንፏል፡፡ ንግግሪቱ እርግጥ ነው ወርቅ ናት፤  ምንም እንከን አይወጣላትም፡፡ ችግሩ አተገባበሩ ላይ ነው፡፡ መናገር ደግሞ እንደማድረግ አይቀልም፡፡ ከነተረቱ “ለአፍ አቀበት የለውም” ይባላል፡፡ አቢይ ተቀባይነትን ለማግኘት ያኔ ያልቀባጠረው ነገር አልነበረም፡፡ ይሁንና ልጁ በማስመሰል እንጂ በጥበብ ባለመብሰሉ እየሆነና እያደረገ ያለውን ሁሉ ከመሆንና ከማድረግ የሚያግደው ምድራዊ ኃይል እስካሁን ሊገኝ አልቻለም፡፡ አሳዛኝ ሀገራዊ ክስተት፡፡ ሀገር ገደል ስትገባ ዝም ብሎ የማየት መጥፎ አጋጣሚ፡፡

ለማንኛውም አማራ የሚባል ዘውግ አለ ካላችሁ አማራ በሞቱ አሸናፊ ነው፤ ይህን ቋሚ እውነት መረዳት አስፈላጊ ነው – ሟች ምን ጊዜም አሸናፊ ነው – የዕዳ ቅራቅምቦውን ለገዳይ አስረክቦ ይህችን በወንጀለኞችና በኃጢኣተኞች የቆሸሸች ምድር ትቶ ወደቀጣዩ ዓለም ያልፋልና፡፡ እየሞተ የሚያሸንፍ ሕዝብ እንደ አማራ አላየሁም፡፡ አማራ ከሥልጣንም፣ ከሀብትም፣ ከሀገርም ከወጣና ከተሰደደ በትንሹ 30 ዓመት ይሆነዋል – ወደ ውጭ የተሰደደውን ትተን በሀገር ውስጥ ያለው አማራ ራሱ በሀገሩ ጉዳይ ባይተዋር ነው – የሀገር ውስጥ ስደተኛ፡፡ በአክራሪዎች አስተሳሰብና እምነት አማራ ከኢትዮጵያ የባለቤትነት መብት ተሰርዟል – ለመገደልና ለመፈናቀል ብቻ የተፈጠረ የነሱ መጫወቻ አሻንጉሊት መስሎ ሳይታያቸው አልቀረም፡፡ አሸነፍነው ያሉ የሁለት ነገዶች አክራሪ አባላት እየተፈራረቁ ይህን ከምኑም የሌለበትን አማራ እጃቸው በገባ ዱላ ሁሉ እንደ አህያ ይነርቱታል፡፡ እርሱም እነሱን ደስ ይበላቸው ከሚል አዘኔታ ይመስላል ዝም ብሎ ይቀጠቀጥላቸዋል፡፡ እነሱም አማራን በመግደልና በማሰቃየት እንዲሁም በማደህየት የሚረኩ አይመስሉም፡፡ የነሱ ችግር ይበልጡን ሥነ ልቦናዊ ነው፡፡ የአማራው ደግሞ እጅግ የተለጠጠ ሆደ ሰፊነት፡፡ ሆደ ሰፊነቱሞ የአማራን ጠላቶች እርር-ቅጥል ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይ አማራ ወደአማራነት ለመውረድ አለመቻሉ ይብሱን ያንገበግባቸዋል፡፡ የሞቱ መንስኤም አማራው አማራ ሆኖ እንደነሱ በመጥበብ በዘረኝነት የድንቁርና ካባ ተጀቡኖ አካኪ ዘራፍ አለማለቱ ነው፡፡ ዘረኝነት እንደሚያሳውር አብዛኛው አማራ ይረዳልና ወደዚያ አረንቋ አይገባላቸውም – የተወሰነ አዝማሚያ ቢታይም ቁጭት-ወለድና ጊዜያዊም ነው፡፡ አማራው የመረጠው የትግል ሥልት ታዲያ እየሞቱ ማሸነፍን፣ እየተሰቃዩ ጠላትን ማሰቃየትን ሆነ፡፡ ይህ የትግል ሥልት መጨረሻው ለሁሉም ግልጽ ባይሆንም ለአሁኑ ግን ፍቱን የማጥቂያ ዘዴ ይመስላል፡፡ ቤተ መንግሥትን ተቆጣጥረው በአማራ የሚበሳጩ ካሉ፣ ሀብትና ሥልጣንን ሁሉ በእጃቸው አስገብተው ሳለ ስለ አማራ በተሰበከላቸው የሀሰት ትርክት ሳቢያ በጥላቻ ተውጠው አማራነት እንቅልፍ የሚነሳቸውና የነሱን መኖር እንኳን የማያውቀውን፣ ከአድማስ ማዶ ሀገር እንዳለ የማይረዳውን ምስኪን አማራ በመጨፍጨፍና በማስጨፍጨፍ የሚረኩ የ8ኛው ሽህ ጭራቆች ከተፈጠሩ ጥፋቱ የአማራ ሣይሆን የአልጠግብ ባዮቹ የአክራሪ ኦሮሞዎችና እነሱን የፈጠሩት ሰሜነኞች ነው፡፡ በተበላሸ አእምሮ አገር አይተዳደርምና ፈጣሪ ይሁነን፡፡

እደግመዋለሁ – አቢይ አህመድና ሽመልስ አብዲሣ ተሸናፊዎች ናቸው፡፡ የሚገድሉት ሽንፈታቸውን ለመሸፈን ነው፡፡ በመሠረቱ አንድ ሰው ሌላውን ሰው የሚገድለው በሆነ ትልቅ ጉዳይ ሲጣላ ነው፡፡ በንግግር የማይፈታ ችግር ገጠመኝ ብሎ የሚያስብ ሰው ባላጋራየ ነው ያለውን በተመቸው መንገድ ይገድላል፡፡ መግደል በምንም መልኩ ትክክል ባይሆንም ይህ ዓይነቱ የታሰበበትም ይሁን ግብታዊ ግድያ ምክንያታዊ ነው፡፡ አንድን ሕጻን ወይም አንዲትን ሴት አማራነቷን እንኳን በውል ሳታውቅ ሕጻናቱንም ሴቲቱንም “አማራ ናቸው” ብሎ መግደል ግን ከመሸነፍም በላይ ነው፡፡ ይህ ስም የለሽ ዕኩይ ድርጊት ኅሊናን የመሳት ውጤትም ነው፡፡ ኅሊናውን የሳተ ሰው ደግሞ እንኳንስ ሀገርን ቤተሰቡንም መምራት አይችልም፡፡ መግባት ያለበት የአእምሮ ህሙማን የሚታከሙበት አማኑኤል ሆስፒታል ወይም ወደሱ ቅርንጫፎች ነው፡፡ በሉ ዘዴና ብልኃቱ ያላችሁ ሰዎች ወይንም ቤተሰብ የሆናችሁ እነዚህን ዕብዶች ከዚህም በላይ ብዙ ሳያጠፉን ወደ ጠበል ወይም ወደአእምሮ ህክምና ማዕከል ውሰዱልን፡፡ 

በነገራችን ላይ እነአቢይ በነሱ ቤት ጤነኞች ናቸው፤ በሽተኞቹ እኛ የምንቃወማቸው ነን፡፡ እንደንጉሡ የሚያጎነብሱ ቁጥራቸው የትዬለሌ መሆኑ ደግሞ ዕብዶቹን የልብ ልብ እየሰጠ ይበልጥ እንዲያብዱ ማድረጉ ልንቋቋመው ያልቻልነው ችግር ሆኗል፡፡ ይሄውና አለማየሁ ገ/ማርያም የተባለው ለሀገሩ ብዙ የደከመ ሰውዬ እንኳን  ከቢዮንሴ ቀጥሎ ለአቢይ አህመድ 46ኛው  ጽላት እንዲቀረጽለት ለፓትርያርክ ጽ/ቤት አመልክቷል ይሁን ሊያመለክት ነው እየተባለም አይደል? የጎፈነነ ስሜት ማለስለሻውን የዋዛ ንግግር ትተን ከምር ካየን ግን መጪው ጊዜ ጨለማ ይመስላል፤ ዳርዳርታው አያምርም፡፡ እግዜር ክፉን በሩቅ ያድርግልን እንጂ ሦርያና ሩዋንዳ፣ የመንና ሶማሊያ ወደኢትዮጵያ ሰተት ብለው እየገቡ ነው፡፡ እነአቢይ ከዚህ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕልቂት ምን እንደሚያተርፉ ካለቅንላቸው በኋላ እንደዕድል ሆኖ የሚተርፍ ሰው መኖሩ አይቀርምና የሚያየው ይሆናል፡፡

Filed in: Amharic