>

የG7 ሀገራት በመግለጫ በትግራይ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች  አሳስቦናል ብለዋል....!!! (አዲስ ዜና መረጃ)

የG7 ሀገራት በመግለጫ በትግራይ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች  አሳስቦናል ብለዋል….!!!
አዲስ ዜና መረጃ

የካናዳ ፣ ፈረንሳይ ፣ ጀርመን ፣ ጣልያን ፣ ጃፓን ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩኤስኤ የሚገኙበት የቡድን 7 ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ የትግራይን ወቅታዊ ጉዳይ በተመለከተ የጋራ መግለጫ አወጡ።
በመግለጫው የቡድን 7 ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ፣ በቅርቡ ሪፖርት የተደረጉ በትግራይ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች እንዲሁም የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ ጥሰት በጣም አሳስቦናል ብለዋል።
መግለጫው አክሎ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርስ ያለውን “ግድያ ፣ ጾታዊ ጥቃቶችን ፣ ያለ ልዩነት የሚፈጸም ከባድ ድብደባ እና በትግራይ ነዋሪዎች እና የኤርትራ ስደተኞች ላይ የሚፈጸመውን አስገዳጅ መፈናቀል” እንደሚያወግዙ ገልፀዋል።
ሁሉም ወገኖች የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ እና የሰብዓዊ መብቶችን እና ዓለም አቀፍ ህጎችን ማክበር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት ለእንዲህ ዓይነት ጥሰቶች ተጠያቂ መሆን ያለባቸውን ለመጠየቅ ላሳየው ቁርጠኝነት እውቅና የሰጠው መግለጫው መንግስት ቃሉን ተግባራዊ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በቅርቡ ጠ/ሚ ዐቢይ የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ይወጣሉ በሚል ያወጡትን መግለጫ በደስታ እንደሚቀበሉም መግለጫው ጠቁሟል፡፡ ይህ ሂደት በፍጥነት ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈጸም እንዳለበትም ነው የተገለጸው፡፡
የቡድን 7 ሀገራት ፥ “አመጽ እንዲቆም እና ትግራይን ጨምሮ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተቀባይነት ያለው እና ወደ ተአማኒ ምርጫ እና ወደ ሰፊ ብሔራዊ እርቅ የሚወስድ ግልፅ ፣ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሂደት እንዲፈጠር ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል።
Filed in: Amharic