>

ኢትዮጵያ  በአረቦች እና በአፍሪቃ መሀል      (ጋዜጠኛ ስለ አባት ማናዬ)

ኢትዮጵያ  በአረቦች እና በአፍሪቃ መሀል!

     ጋዜጠኛ ስለ አባት ማናዬ 

የአፍሪቃ ቀንድ? ወይስ የአረብ ቀንድ?  አዲሱ የአፍሪቃ ቀንድ ስጋት የወደብ ቅርምት‼

  
የአፍሪቃ ቀንድ በሚባለው ቀጣና ውስጥ የሚገቡት አገሮች ላይ ሙሉ ስምምነት የለም። ብዙ ጸሐፍት ሱዳንን እና ኬንያን አይጨምሩም።አንዳንዶቹ ሱዳንን ይጨምሩና ኬንያን ያስውጣሉ፡አንዳንዶቹ ደግሞ ኡጋንዳንም ይጨምራሉ። ሁሉም ምንም ተጨባጭ ምክንያት የላቸውም። ኢትጵያዊው ሊቅ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ለዚህ ችግር መፍትሄ ሊሆን ይችላል በሚል በአውሮፓዊያኑ 1999  የአፍሪቃ ቀንድ ግጭት  እና ደህንነት(THE HORN OF AFRICA CONFLICT AND POVERTY)በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ አንድ ሀሳብ አቅርበዋል።
በአፍሪቃ ቀንድ ካሉ ሀገራት ጋር ሁሉ የመሬት ድንበር ያላት ኢትጵያ ነች።ከኤርትራ፣ከሱዳን፣ደቡብ ሱዳን፣ከጂቡቲ፣ከሶማሊያ እና ከኬንያ ጋር ትዋሰናለች። በዚህም እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ኢትጵያ የአፍሪቃ ቀንድ እምብርት ነች። ከዚህ በመነሳት ከኢትጵያ ጋር የድንበር ግንኙነት ያላቸው ሀገራት ሁሉ የአፍሪቃ ቀንድ አካል ናቸው ማለት ይቻላል ባይ ናቸው።
አንጋፋው የጂኦግራፊ ምሁር  ሌላም  ልናስተውለው የሚገባ ነገር እንዳለ በዚሁ መጽሐፋቸው አስገንዝበውናል። ኢትጵያ፣ኤርትራ፣ጂቡቲና ሶማሊያ ከአፍሪቃ ቀንድ ውጭ ካሉ ሀገራት ጋር የድንበር ግንኙነት የላቸውም። እነዚህ አገሮች ሙሉ በሙሉ የአፍሪቃ ቀንድ አገሮች ናቸው ። በአንፃሩ ሁለቱ ሱዳኖች እና ኬንያ ከአፍሪቃ ቀንድ ውጭ ካሉ አገሮች ጋር የድንበር ግንኙነት አላቸው። በዚህ ምክንያት ይላሉ ፕሮፌሰር መስፍን ሁለቱ ሱዳኖች እና ኬንያ የአፍሪቃ ቀንድ አካልንታቸው በከፊል ብቻ ነው። የአፍሪቃ ቀንድ በቆዳ ስፋት ከአፍሪቃ 16 ነጠብ 4 በመቶ ይሆናል።በሕዝብ ቁጥርም 18 በመቶ ያህል ነው። በስፋት ሃያ እጥፍ የብሪታንያን፣17 እጥፍ የጣሊያንን፣9 እጥፍ ፈረንሳይን ያክላል። በሕዝብ ቁጥርም ቢሆን ከእያንዳንዳቸው ይበልጣል። ከአስሩ የአፍሪቃ ቀንድ አባል ሀገራት ውስጥ የባህር በር የሌላቸው ሁለቱ ብቻ ናቸው።
አሳዛኝዋ ኢትጵያ እና የትናንቷ ደቡብ ሱዳን። ከጎረቤት ብዛትና ዓይነት ጋር አብሮ መታየት ያለበት ዋና ጉዳይ የውስጥ የአስተዳደር ነው። መጥፎ አስተዳደር በሁለት ምክንያት ጉዳትን ሊያደርስ ይችላል። አንደኛ ከድንበር ማዶ ያለው አስተዳደር ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ኑሮ የተሻለ መሆኑ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን፣የዜግነትን ክብርና ኩራት እየተሸረሸረ ልብንና ታማኝነትን ይከፍላል። ሁለተኛ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች  የቋንቋ ወይም የሃይማኖት ዝምድና ሲኖራቸው መጥፎ አስተዳደር ሁኔታውን እያባባሰ የዜጎችን ልብ ያሸፍታል።
ስለዚህም የድንበሩን ቀዳዳ ከሚያሰፉትና ከውጭ ለሚገባ ጉዳት ከሚያጋልጡ ነገሮች አንዱ ብልሹአስተዳደርነው።
የአፍሪቃ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ አዲስ ራስ ምታት እና የአረቦች መሻኮት‼
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያውቃት ትንሽ ሀገር ግን በነዳጅ ሀብታም መሆኗን ነው። እኛ ኳታር እንላታለን ። የሀገሬው ሰው እና አረቡ ዓለም ደግሞ ቀጠር ይላታል። ስሟ አያጣላንም ፡ኳታር እያልን እንጥራት። የዚች ትንሽ  ሀገር(በቆዳ ስፋቷ ነው) ስሟ መናኘት የጀመረው በአቋቋመችው ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ነው ። አል ጀዚራ ። አል ጀዚራ ከወላጅ እናት ድርጅቱ ቤን የመገናኛ ብዙሃን ኩባንያ ራሱን ችሎ የተቋቋመው ህዳር1 በአውሮፓዊያኑ 1996 የዛሬ 25 ዓመት ገደማ ነው። በኤሚሮች የነዳጅ ዶላር እየታገዘ አሁን ላይ ከፍተኛ ተሰሚነት  አግኝቷል። በተለይ በአረቡ ዓለም ። የካታሩ ኤሚር ሼህ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ላለፉት ዓመታት በአረቡ ዓለም ከፊት ለፊት መታየት ጀምረው ነበር። እርሳቸው በየሀገራቱም አስታራቂ እና አሸማጋይ በመሆን ሱዳን ዳርፉር ድረስ ዘልቀዋል። ይህ የዱሀ አካሄድ ግን ለሪያድ ሰዎች ፈፅሙ የሚዋጥ አልሆነም። እኛ የቅዱሳን ቦታዎች መገኛ የእስልምና እምብርት ሆነን እንዴት ትናንት ተመስርታ ያለ አቅሟ መዝለል ጀመረች በሚል የሳወዲ ሼሆች እና  አልጋወራሾች እና ንጉሶች በቅናት ንዴት ተቃጠሉ። ይባስ ብሎ ኳታር የሙስሊም ወንድማማቾችን መደገፏ የካይሮን ሰዎች እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን አልጋወራሽ ታበሳጭ ጀመር። በሪያድ ገና በወወጣትነታቸው የአልጋወራሽነት መንበረ ስልጣንን የተጎናፀፉት ልዑል አልጋወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን እነዚህን ሁነቶች አገጣጥመው በኳታር ላይ ሁሉን አቀፍ ማዕቀብ ጣሉ ። በእርግጥ የበጋ መብረቅ ሆኑባት ነው የሚባለው። የሰኔ ወር ለኢትጵያዊያን ለምስራቅ አፍሪቃ አባል ሀገራትም የክረምት መባቻ ነው። ለኳታር ግን ሰኔ 5 2017 የበጋ መብረቅ ሆኖ ብቅ አለ።ነፍስ ውጭ ነፍስ ገቢ የሚያስብል ማዕቀብ ወረደባት።
የባሀረ ሰላጤው የጋራ ምክር ቤት  አባላት እና የኳታር ቀውስ ተዘማች ተፅዕኖ በአፍሪቃ ቀንድ‼
የባህረ ሰላጤው የጋራ ምክር ቤት አባል ሀገራት በአፍሪቃ ቀንድ መራኮት የጀመሩት በእርግጥ ከዛሬ አራት ዓመት በፊት አስቀድሞ ነው።የእኔ የሚሏቸውን የዚህ ቀጣና ሀገራት መንግስታት  እና መሪዎችን በገንዝብ ዲፕሎማሲ(Cash Diplomacy) እየደለሉ የራሳቸውን ዘላቂ ጥቅም ለማደላደር ርብራብ ሲሰሩ ባጅትዋል።በተለይ ኳታር ወደ አፍሪቃ ቀንድ የገባችው በሁለት መንገድ ነው ።በአሸማጋይነት እና በሰላም አስከባሪ ስም።አሸማጋይነቷን በዳርፉር ግጭት የሱዳንን ተፋላሚ ሃይለት ለማሸማገል በፔትሮዶላሯ ተማምና ገብታ ነበር።በሰላም አስከባሪነት ስም ደግሞ ኤርትራ እና ጂቡቲ በሚወዛገቡባቸው ደሴቶች ላይ ወታደሮቿን እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ አስፍራ እንደነበር የሚታወስ ነው።አዳዲስ የአገዛዝ ለውጥ እና የአረብ አብዮት የፈጠረው የሕዝብ ተቃውሞ መነሳሳት ያሳሰባቸው ሼሆች እና ኤ ሚሮች መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ወደ ውስጥ የሚመለከት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን ማስቀጠል አልፈለጉም።ቢያንስ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን በመከለስ ከውስጥ ወደ ውጭ እንዲመለከት በማድረግ በአረብ አብዮት ልቡ የሸፈተውን ዜጋቸው በተስፋፊ ፖሊሲያቸው የተስፋ ዳቦ መጋገር ጀምረውለታል።ይኽው የተስፋ ዳቦ የሚጋገርበት ቀጣና ደግሞ የእኛው ምስራቅ አፍሪቃ በተለይም የአፍሪቃ ቀንድ ነው።አሜሪካ የሚገኘው የሀሳብ አፍላቂ ተቋም ወይም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መማክርት ብሩኪንግ ኢስቲቲዩሽን የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካ እሽቅድድም(RED SEA RIVALARIES፡THE GULF,THE HORN, AND THE NEW GEOPOLITICS OF THE RED SEA.JUNE 2019) በሚል የሰራውን ጥናት ሰኔ 2019 ይፋ አድርጎ ነበር። የዚህ ጥናት ተሳታፊ የአፍሪቃ ቀንድ እና የቀይ ባህር ፖለቲካ ቤተኛ ነኝ የሚሉት ዛች ቬርተን፡የአፍሪቃ ቀንድ በወደብ እና በጦር ሰፈር ግንባታ ፖለቲካ   እየታመሰ መሆኑን በርካታ ማጣቀሻዎችን በማስቀመጥ ሀሳባቸውን በጥናቱ ላይ አካተዋል።
አዲሱ የአፍሪቃ ቀንድ ስጋት የወደብ ቅርምት እና የጦር ሰፈር ግንባታ እሽቅድድም‼
አሁን ላይ ምስራቅ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው የወደብ ቅርምት እና የጦር ሰፈር ግንባታ እሽቅድድም ከአረቦች እስከ ሃያላን ግብግብ ውስጥ እንዲጠመዱ አድርጓቸዋል። በተቃራኒው ወደብ አልባዎቹ ኢትጵያ እና ደቡብ ሱዳንን ጨምሮ የቀጣናው ሀገራት የበይ ተመልካች በሚመስል መልኩ አረ በህግ አምላክ ከማለት ተቆጥበዋል። የአውሮፓዊያኑ 2009 ላይ ጂቡቲ ውስጥ የጦር ሰፈር የነበራቸው ሀገራት ሁለት ነበሩ፡አሜሪካ እና ፈረንሳይ። ዛሬ ላይ ከአስራ አንድ ዓመታት በኋላ በጂቡቲ ከግማሽ ደርዘን በላይ ሀገራት የጦር ሰፈራቸውን ገንብተዋል።ያውም ተቀናቃኞች ሳይቀሩ። በርካታ የባህረ ሰላጤው የጋራ ምክር ቤት አባላት ወደ አፍሪቃ ቀንድ መምጣት የጀመሩት በወደብ ፖለቲካ ናው።በተለይ የኳታር እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኩባንያዎች ከሶማሊያ እስከ ጂቡቲ ከኤርትራ እስከ ሱዳን ተሻኩተዋል። ዲፒ ወርልድ የወደብ ግንባታ አልሚ ኩባንያ በዚህ ፉክክር ስሙ ፊት ለፊት ይመጣል። ከ2014 ነሃሴ ወር ጀምሮ ደግሞ የቱርክ የወደብ አልሚ ኩባንያዎችም ወደ ሶማሊያ ገብተዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በአፍሪቃ ቀንድ‼
መካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪቃ ቀንድ ተመሳሳይ በሆኑ የሃይማኖት፣የታሪክ፣የንግድ እንዲሁም የሕዝብ እንቅስቃሴ ተጽዕኖ ምህዋር  ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። ለቀይ ባሕር  ያላቸው ቅርበት፣ታሪክ፣ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ውርሶች፣ንግድ፣የገንዝብ ልውውጦች እንዲሁም የሰዎች እንቅስቃሴ (ስደትን ጭምሮ) እና የደህንነት ጉዳዮች የአፍሪቃ ቀንድ እና መካከለኛው ምስራቅን በጥብቅ የሚያቆራኟቸው ናቸው። ሦስቱ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች ማለትም ክርስትና ፣እስልምና እና አይሁድ እምነቶችም የሁለቱ አካባቢዎች መጋመጃዎች ናቸው። አቡዳቢ እና አልጋወራሽ መሃመድ ቢን ዛይድም የዚህ ሁነት ተጋሪዎች እና መሪዎች ናቸው። አቡዳቢ በአሁኑ ወቅት በአፍሪቃ ቀንድ የባህር ወደብ ግንባታ እና አስተዳደር፣አምራች ኢንዱስትሪ ግንባታ፣ እንዲሁም እርሻ ላይ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ እያፈሰሰች ነው። በስደት ኤምሬትስ ውስጥ ሚኖሩ የአፍሪቃ ቀንድ አባል ሀገራት ዜጎች ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ (ሪሚታንስ)ወደ ትውልድ ሀገራቸው እየላኩ ነው። በተደጋጋሚ በአቡዳቢ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዙርያ ጥናት ያደረጉት ዶክተር መሃሪ ታደለ ማሩ  የኤምሬቶች የአፍሪቃ ቀንድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምሰሶዎችን በአራት ይከፍሏቸዋል። ንግድ፣ቱሪዝም፣ፀረ ሽብር ዘመቻ እና ኢራን በአካባቢው የጎላ ድርሻ እንዳይኖራት ማድረግ የሚሉ መሆናቸውን አስፈረዋል። በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውስጥ የእስልምና እምነት የሀገሪቱን ፖሊሲዎች እንደሚመራ መንግስታዊ አስተምህሮት(doctrine)አይወስድም። ከዚህ በተቃራኒው ሌሎች የባህረ ሰላጤው ሀገራት ሳውዲ አረቢያን በመከተል የሸሪዓ መር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎችን ያራምዳሉ። የኤምሬቶች ማኅበራዊ እና የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ሉላዊነትን ይከተላል። ሀገሪቱ የግብርና ምርቶችን ከአፍሪቃ እና ከተቀረው ዓለም በመሸመት ብሎም በፋብሪካ ምርት ሂደት በማስግበት እና በማሸግ ለዓለም ገበያ በመሸት የአምራች ኢንዱስትሪዎች መገኛ ማዕከል ለመሆን ትሻለች።
አቡዳቢ  እያደገ ከመጣው የኳታር የዓለም አቀፍ ንግድ እና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ጋር ፉክክር ውስጥ ነች።ኳታር በ2022 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫን የምታዘጋጅ ስትሆን ኤምሬቶች ደግሞ የዓለም የንግድ ኤክስፖን ታስተናግዳለች።

 የኤምሬቶች የወደብ ፖለቲካ‼

አሰብ ፦ ኤርትራ‼
ኤምሬቶች ወደዚህ የወደብ ጥገና እና አዲስ ወታደራዊ የጦር ሰፈር ግንባታ ለመምጣታቸው የወዲያው ሰበብ ያደረጉት መጋቢት 2015 በይፋ የተጀመረውን እና የተቀላቀሉትን  የየመንን ጦርነት ነበር።ከዚህ አኳያ የሳወዲ አረቢያው ንጉስ ቢን ሳልማን ከኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ባደረጉት ረዥም ድርድር ለ30 ዓመታት በሊዝ በመፈራረም ፤ኤምሬቶች የጦር ሰፈር እየገነቡ ነው።አሁን ላይ በአሰብ የሚገኘው የአቡዳቢ የጦር ሰፈር ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖች ማዘዣ(UAV)፣የጦር ጄቶች እና ሌሎች ወታደራዊ ቁሳቁሶች ይገኙበታል።ዋና ተልዕኮው ተብሎ የተቀመጠው በየመን ኢራን ከምትደግፋቸው ሃውቲዎች ጋር  እየተደረገ ባለው ጦርነት የአየር ሃይል ድጋፍ ለመስጠት የሚል ነው።
በርበራ ፦ ሶማሊ ላንድ‼
ዲፒ ወርልድ(DP World)ኩባንያ በበርበራ ወደብ መሳተፍ የጀመረው የዛሬ አራት ዓመት በአውሮፓዉያኑ 2016 ላይ ነው።የወደቡን 51 በመቶ ድርሻ በመግዛት።በዚህ የወደብ ግንባታ ላይ ሶማሊ ላንድ 30 በመቶ ፣ኢትጵያ 19 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ። ዲፒ ወርልድ በሶስት የግንባታ ምዕራብ 442 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ ላመድረግ እቅድ  አውጥቶ ወደ ስራ ገብቷል ። የመጀመሪያው ምዕረፍ ወደ መጠናቀቅ ተቃርቧል። በበርበራ ወደብም የተወሰነ ክፍሉን ለወታደራዊ ጦር ሰፈርነት አብዛኛውን ለንግድ መውጫ መግቢያነት የሚውል ነው። የዚህ ወደብ ፖለቲካ ኤምሬቶችን ከሶማሊያ መንግስት ጋር በጣልቃ መግባት ጉዳይ ውዝግብ ውስጥ አስገብቷችዋል።
ቦሳሶ ፦ፑንትላንድ‼
~~~~\\\~~~
በሌላኛው የሶማሊያ ራስ ገዝ አስተዳደር ፑንትላንድ የሚገኘው የቦሳሶ ወደብ ግንባታም የአቡዳቢ እጅ የረዘመበት ነው። በዚህ ወደብ ግንባታ  ኤምሬት በ2017 ላይ መሳተፍ ጀምራለች።ዲፒ ወርልድ ወደብ ገንቢ እና አስተዳዳሪው ኩባንያ ነው በቦሳሶ የወደብ ፖለቲካም የሚዋኘው።ኤሚሮች የቦሳሶን ወደብ ያሰቡት ለወታደራዊ አገልግሎት ነው። በዚህ ጉዳይም አቡዳቢ እና ሞቃዲሾ እየተወዛገቡ ነው። የየመንንሶኮትራ፣ፔሪም፣ኤደን ፣ሙካላ፣ሺሂር፣ሞካሃ፣ሆዴዳህ ወደቦችን በበላይነት ተቆጣጥራ ከየመን አጋሮቿ ጋር እያስተዳደረች ነው።
ኳታር እና የአፍሪቃ ቀንድ የወደብ ፖለቲካዋ‼
ሱዋኪን ፡ሱዳን -በ2018 ጸደይ ወቅት ላይ የኳታር ኤሚሮች ወደ ሱዳን መመላለስ አብዝተው ነበር። በዚያ ሲመላላሱ ደግሞ ብቻቸወን አልነበሩም።የቱርክን ሰዎች የአንካራን ፖለቲከኞች የኢስታንቡልን ነጋዴዎች ጭምር ይዘው እንጂ።በዚህ ወቅት ዱሃ እና ካርቱም የሱዋኬን ደሴትን በአንድ አቅጣጫ በመጀመሪያው ምዕራፍ በ500 ሚሊዮን ዶላር ለማልማት ተስማሙ።ግንባታው በዚያው ዓመት 2018 ተጀምሮ 2020 ዘንድሮ ይጠናቀቃል ቢባልም እስካሁን ድረስ የተጀመረም አይመስል።በአርግጥ ስምምነት ፈራሚው ሰው የቀድሞው የካርቱሙ ሰው አልበሽርል ተሰናብተዋል።
ሆብዮ ፡ሶማሊያ -በሰሜን ምስራቅ ሞቃዲሾ በምትገኘው የሆብዮ ከተማ አቅራቢ አዲስ ወደብ ለመገንባት የኳታር መንግስት ከሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት ጋር ታህሳስ 2018 ላይ ተፈረርሟል።ሳውዲ አረቢያም ጂቡቲ ላይ የጦር ሰፈር ለመገንባት እቅድ ይዛለች ።ኤርትራ ውስጥ የመግባትም ፍላጎት አላት ።የ30 ዓመቱ የአሰብ ፖለቲካ እርሷንም ስለሚያካትት።
ኢትጵያ በአረቦች እና በአፍሪቃ መሀል‼
አረቦች ኢስያም አፍሪቃም አህጉሮቻቸው ናቸው። አረቦች በምዕራብ ኤስያ ይኖራሉ፡በሰሜን አፍሪቃም ይኖራሉ። ስለዚህ አረቦች የሁለት አህጉሮች ህዝቦች ናቸው ማለት ይቻላል። ኢትጵያ አፍሪቃዊ አገር ብትሆንም ከቀይ ባህር ማዶ ኤስያ ከሚኖሩት አረቦች ጋርም ሆነ ከቀይ ባህር ወዲህ በአፍሪቃ ከሚኖሩት አረቦች ጋር የቆየ ጥንታዊ ግንኙነት አላት። የናይል ወንዝ እና ቀይ ባህር የእስያን እና አፍሪቃን አረቦች ከኢትጵያ ጋር ያነካካል። በአፍሪቃ ውስጥ የኢትጵያ አቀማመጥ(geographical positioning ) ከአረብ አገሮች ጋር ትይዩ እና የተቀራረበ ነው።የአፍሪቃ ቀንድ ሳንካ አሁንም ልክ እንደ ኢትጵያ የሚገኝበት ክፍለ አህጉራዊ አቀማመጥ ነው።የስዊዝ ቦይ እንደ አውሮፓዊያኑ 1869 ሲከፈት ፣ቀይ ባህር የዓለም የንግድ መስመር አንዱ የደም ስር ሆነ።በዚህም ልዕለ ኃያላኑ ሀገራት በአካባቢዎች አገሮች አልፈው የመርከብ መተላለፊያ መስመር ጸጥታ ጉዳይ ያገባናል ባይ ሆኑ።በክልሉ የጂኦ ፖለቲክስ ፍላጎት እና ርኩቻም በተቀያየረ ቁጥር የዚያኑ ያህል ሁኔታዎች ይለዋወጣሉ።በአውፓዉያኑ አቆጣጠር በ1950ዎች የስዊዝ ቦይ ቀውስ እና የቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት፣እንደገናም በ1970ዎች የዐረቦች እስራኤል ጦርነት አፋፍ ላይ በደረሰበት ወቅት የልዕለ ኃያላኑ ፉክክር በአፍሪቃ ቀንድ እና በየመን ላይ ከባድ ውጥረት አድርሶ ነበር።
 
ቁርስ ያልሆነው ዳቦ የሰንዓ ፎረም‼
ከባህር ጂኦ ፖለቲካ አንፃር ካየነው ሀገራችንን ሦስት ወደ ኋላ አንድ ወደ ፊት አይነት ጉዞ ላይ ትገኛለች።በጥንታዊያን የአክስማዊያን ሥልጣኔ ዘመን እስከ ኤደን ባህረ ሰላጤ ድርሻ የነበረን ሰዎች ዛሬ ከቀይ ባህር ፖለቲካም ርቀት ይሄው ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጠርን።ዛሬ ላይ የባህር በርን እንደ ብሄራዊ ደህንነት አጀንዳ ሳይሆን እንደ ሸቀጥ የቆጠረው ቡድን ከመንበር ስልጣኑ የተገረሰሰ ቢሆንም ጥሎት ያለፈው የታሪክ ጠባሳ በተለይ ከወደብ ፖለቲካ አኳያ ከሞት በኋላም ሀጥያቱ የሚሰረይለት አይመስልም።የባህርን በር አስወስዶ እንደ መሿለኪያ አዲስ ተስፋ ለመፍጠር በቀይ ባህር አለን ለማለት አንድ ጅማሮ ይፋ ተደርጎ ነበር።በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ገፋፊነት የቀጣናው ሀገራት አስተባብሮ አንድ ፎረም ተመስርቶ ነበር ።የሰንዓ የትብብር ፎረም።ይህ ፎረም 1996 ዓመተ ምህረት ነበር ሱዳን ፣የመን እና ኢትጵያ በጋራ የመሰረቱት።ፎረሙ የታሰበውን ዓላማ ሳያሳካ ተበተነ ።ምን አልባትም ያ ፎረም እንደታሰበው ተጠናክሮ ክፍለ አህጉራዊ ድርጅት ወደ መሆን ቢሸጋገር ኖሮ ዛሬ ላይ በቀይ ባህር አሁናዊውን ትርምስ  ባልተፈጠረ ነበር።ለታሪክ እማኝ ይሆን ዘንድ የሰንዓ የትብብር ፎረምን የፀደቀበት አዋጅ ተያይዞ ቀርቧል።
ኢትጵያን ያገለለው አዲሱ ሰንዓ ፎረም የቀይ ባህር ትብብር መድረክ‼
የቀይ ባህር ፎረም ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሰረተው 2018 በሳወዲ አረቢያ አነሳሽነት እንደሆነ ይነገራል።የውሃ ጂኦ ፖለቲካ ተንታኞች እንደሚናገሩት ከሆነ ግን ሀሳቡ የሪያድ ሳይሆን የካይሮ ነው።ስውር ዓላማውም ኢትጵያን እስከ መጨረሻው ከቀይ በህር ጂኦ ፖለቲካ የማራቅ እና ከበባ ስሜት ውስጥ የማስገባት አባከሳዊ ስሌት ነው።አሁን ያ የቀይ ባህር ፎረም እነ ዮርዳኖስን ሁሉ አካቶ ወደ ቀይ ባህር የትብብር መድረክነት2019 ላይ አድጓል።ኢትጵያ ከረፈደም ቢሆን የግብፅን ሴራ ለማክሸፍ እየተጓዘችበት ያለው መንገድ ክፍለ አህጉራዊው ተቋም ኢጋድ ለቀይ ባህር እና ለኤደን ባህረ ሰላጤ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረጉ ላይ ነው።አህጉራዊው ተቋም የአፍሪቃ ህብረትም ቢሆን ለወሳኙ የባህር ፖለቲካ ትኩረት መስጠት የጀመረው ከብዙ  ትችት በኋላ ነው።አዲስ አበባ በተለይ በእነ ካይሮ የሚመራውን የቀይ ባህር የትብብር መድረክ በአንክሮ መከታተል ይገባታል። እየተሻሻለ ባለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ትኩረት የተሰጠውን የባህር ሃይል እና ወደብ የማግኘት አካሄድን ከወረቀት ወደ መሬት ማርድ ግድ የሚላት አስራ አንደኛው ሰዓት ላይ ነች።ከዚህ አኳያ ስናየው እኛ ያለንበት ቀጣና በእርግጥ የአፍሪቃ ቀንድ ወይስ የአረብ ቀንድ አያስብልም ትላላችሁ ?ቀጣይ የኃያላኑ ዳግም ወደ አፍሪቃ የመመለስ ተዛማች ተፅእኖ እና በኢትጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ሊያመጣው የሚችለው ስጋት ዙርያ  እመለሳለሁ ቸር እንሰብት።
Filed in: Amharic