>
5:13 pm - Friday April 18, 4684

በአንድነት ፕሬዘዳንት የተመራ የልዑካ ቡድን የፖለቲካ እስረኞችን ጠየቀ [ፍኖተ ነፃነት]

በዛሬው ዕለት ወደ ቂሊንጦ የተዛወሩትን የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ወደ ስፍራው በማምራት አቶ ሀብታሙ አያሌውን፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺንና ሌሎችን የፖለቲካ እስረኞችን ማነጋገራቸውን ለፍኖተ ነፃነት ገለፁ፡፡

ወደ ቂሊንጦ የተንቀሳቀሱት የአንድነት ፕሬዘዳንት አቶ በላይ ፈቃዱ፣ የብ/ም/ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባዔ አቶ ፀጋየ አላምረው፣ የውጭ ጉዳይ ሃላፊው አቶ ዳንኤል ተፈራና ሌሎችን ያካተተው የልዑካን ቡድን የፖለቲካ እስረኞችን አግኝተው እንዳነጋገሯቸው፤ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈፀባቸውና እንዲሰቃዩ እንደተደረገ አረጋግጠዋል፡፡

አቶ ሀብታሙ አያሌው ለአመራሩ እንደገለፁት በማእከላዊ በእስር ላይ በቆዩባቸው አራት ወራት ከእስረኞች ተነጥሎ ለብቻው በጨለማ ክፍል ውስጥ እንደታሰረና ከሌሎች በተለየ ወደ መፀዳጃ እንዳይሄድ ይከለከል እንደነበረ፤ ከፍተኛ ድብደባ በተደጋጋሚ እንደተፈፀመበት ገልጧል፡፡

በተጨማሪም እንደተናገረው ምርመራ ያካሂዱበት የነበሩት ከፌደራልና ከደህንነት የሚመጡ ሲሆኑ ከሌሊቱ 6 ሰዓት እስከ 9 ሰዓት እያሰቃዩ ‹‹የግንቦት ሰባት አባል መሆንህን እመን፤ የፓርቲው ጠንካራ አመራር እነማን እንደሆኑ አውጣና የፓቲውን የፋይናንስ ምንጭ ግለፅ›› የሚሉ እንደነበሩ ተናግሯል፡፡

ወጣቱ ፖለቲከኛ ሐብታሙ አያሌው ታስሮበት የነበረው ክፍል ቀዝቃዛ በመሆኑና ወለል ላይ እንዲተኛ በመደረጉ ለእግርና ለተለያዩ በሽታዎች ተጋልጧል፡፡ አመራሩ አይቶ እንዳረጋገጠውም ሲመጣ እያነከሰና ተደግፎ ሲሆን አስቸኳይ ህክምና የማያገኝ ከሆነ ዘላቂ ለሆነ የአካል ጉዳት እንደሚጋለጥ ተናግሯል፡፡

ሐብታሙን ‹‹የግንቦት 7 አባል ነኝ ብለህ ፈርም›› በማለት በተደጋጋሚ እያሰቃዩ የጠየቁት ሲሆን ያልሆንኩትን ነኝ አልልም በማለቱ ቴክኒካል የሆነ የአካል ጉዳት እንደሚያደርሱበትና ጭንቅላቱንና አንገቱ ስር በመደብደብ ተዝለፍልፎ እንዲወድቅ መደረጉንና ‹‹እስቲ አንድነት ያስፈታህ!›› በሚል እንደሚዝቱ ለሉዑኩ ተናግሯል፡፡

በተያዘም ም/የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ የሆነው አቶ ዳንኤል ሺበሺ እንደ ሀብታሙ ሁሉ ተመሳሳይ በደል የተፈፀመበት ሲሆን ምንም አይነት ማስረጃ ማግኘት እንዳልቻሉ ሁለቱም ተናረዋል፡፡ እንደማስረጃ የቀረቡባቸው አንድነት ፓርቲ በህጋዊ መንገድ ያደረጋቸው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ያደረጓቸው ንግግሮችና ከጓደኞቻቸው ጋር ያደረጓቸው የስልክ ንግግሮች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

የፓርቱው አመራሮች እንዳረጋገጡት ትግሉ እስከ ለውጥ ድርስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ነውረኛ ድርጊትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ በሰላማዊ መንግድ እስከመጨረሻው ህገ ወጥነትንና፣ አንባገነንነትን መፋለሙ እንደሚቀጥል ለፍኖተ ነፃነት ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንም በንፁሃን ዜጎች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ድርጊት በማውገዝ ትግሉን እንዲደግፉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

Filed in: Amharic