>

የኦሮሞ ፓርቲዎች አድማ ትርፍና ኪሳራ...!!! (በፍቃዱ ኃይሉ)

የኦሮሞ ፓርቲዎች አድማ ትርፍና ኪሳራ…!!!

በፍቃዱ ኃይሉ

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እስካሁን ቢያንስ 8209 የምርጫ ተወዳዳሪ ዕጩዎች መመዝገባቸውን አሳውቋል። ከነዚህ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከፍ ያለ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያላቸው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ማለትም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አንድም ዕጩ አላስመዘገቡም። ከዚህ ቀድሞ በተደጋጋሚ መንግሥት ዕጩ ሊሆኑላቸው የሚችሉትን ሰዎች እንዳሰረባቸውና ጽሕፈት ቤት እንደዘጋባቸው ገልጸዋል። እንደፓርቲዎቹ ከሆነ ከምርጫው የወጡት ተገፍተው ነው።
ለመሆኑ የእነዚህ ፓርቲዎች ምርጫው ላይ ላለመሳተፍ መወሰን ትርፍና ኪሳራ ምንድን ነው?
ያለመሳተፍ አድማ
ልደቱ አያሌው በቅርቡ ከሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “በሰላማዊ ትግል ለሚያምን ፓርቲ ወይም የፖለቲካ ሰው ምርጫ አንድ የመታገያ መድረክ ነው… [ምርጫ] ለሰላማዊ ታጋይ ጦር ሜዳው ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። ፖለቲከኛው እንደተናገሩት በምርጫ ወቅት ፓርቲዎች የሚዲያ ትኩረት ያገኛሉ። በገዢው ፓርቲ የሚደርስባቸውንም አፈና ለብዙኃን ለመናገር መድረክ የሚያገኙበት ጊዜ ነው። የሕዝብ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ተገደው ኮታ እንዲሰጧቸው ይደረጋል። የክርክር መድረኮች ላይ ተገኝተው “የተሻልን ነን” የሚሉበትን ፖሊሲ የማሳየት ዕድል አላቸው። ጊዜያዊም ቢሆን ዕጩዎቹ ያለመከሰስ መብት ስለሚያገኙ በተወሰነ ደረጃ የተሻለ የፖለቲካ ቅስቀሳ ነጻነት ያገኛሉ፤ የአደባባይ እና የአዳራሽ ስብሰባ ለማድረግ ከምርጫ ወቅት የተሻለ ዕድል የለም። ሁለቱ ፓርቲዎች ከምርጫው ራሳቸውን ሲያገልሉ ከቀድሞ የከፋ ችግር ገጥሟቸው ይሆን ይህንን የሰላማዊ ጦር ሜዳ ረግጠው የወጡት? ወይስ፣ የተሻለ ትርፍ ታይቷቸው ነው?
የአድማው ኪሳራ
ኦነግ ከ1987ቱ ምርጫ ረግጦ መውጣቱ ኦነግን እንደ ድርጅት፣ የኦሮሞ ሕዝብን ትግልም እንደ ትግል አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፎበት ከርሟል። ኦነግ በድጋሚ በዚህ ምርጫ አለመሳተፉ ፈረንሳዮች ‘ዴ ዣቩ’ እንዲሉ ያለፈው ነገር ዳግም እንዳይከሰት ስጋት የሚያጭር ነገር አለው። የሆነው ሆኖ፣ ኦነግ በኦሮሞ ሕዝብ ትግል ውስጥ የአስኳል ሚና ይኑረው እንጂ የምርጫ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ አያውቅም። ስለዚህ ምርጫው ውስጥ አለመሳተፉ ውስጥ የልምድ ማጠር ጉዳይ ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ኦነግ በውስጣዊ የመሰንጠቅ እሰጣገባ ውስጥ መሆኑም የአደባባይ ምሥጢር ነው። በርግጥ ድርጅቱ ለእዚህ የውስጣዊ ችግሩም ቢሆን ተጠያቂ የሚያደርገው የገዢው ፓርቲን አፈና አልያም ጣልቃ ገብነት ነው።
በተቃራኒው፣ ኦፌኮ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ፣ እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከመዋሐዳቸው ጊዜ አስቀድሞ ባሉት ባለፉት የምርጫ ሒደቶች ሁሉ ተሳትፏል። ኦፌኮ በምርጫዎቹ በሚሳተፍባቸው ጊዜያት በተለይም በ2007 ምርጫ ወቅት በርካታ አባላቱ በእስር የሚገኙ የነበረ ቢሆንም ከመሳተፍ አልተቆጠበም። ከምርጫ 97 በኋላ ፓርቲው አንዳንድ ቦታዎች ላይ ምርጫው ተጭበርብሯል የሚሉ ቅሬታዎች ቢኖሩትም፣ ከነቅሬታው የተመረጡት ፓርቲ አባላቱ ፓርላማ ገብተው እየተሟገቱ ለአምስት ዓመታት ቆይተዋል። ዘንድሮ ላለመሳተፍ የወሰነው ካለፈው የበለጠ አፈና ገጥሞት ይሆን?
አንዳንድ የኦሮሞ አክቲቪስቶችን “ከበፊቱ የከፋ አፈና አለ ይሆን?” ብዬ ጠይቄ ነበር። ያገኘሁት መልስ “አዎ” የሚል ነው። የሚሰጡት ምክንያት “ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ላይ የጎላ ሕዝባዊ መነቃቃት አልነበረም። ስለዚህ አፈናው የሚያተኩረው ዋና ዋና የፖለቲካ አመራሮችን በማሳደድ ነበር፤ አሁን ግን ብዙኃን የሆኑት ወጣቶች ሁሉ በመነቃቃታቸው እና ዝንባሌያቸው የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን የመምረጥ ስለሆነ ኦሮሚያ ላይ አፈናው ከፍቷል” የሚል ሆኖ አገኘሁት። ነገር ግን እነዚህም ቢሆኑ መሳተፍ ካለመሳተፍ የተሻለ ነው የሚል አስተያየት አላቸው።
ኦፌኮም ይሁን ኦነግ በእስር ላይ የሚገኙትን ታዋቂ ፖለቲከኞቻቸውን አልፎ አልፎ ከመጥቀሳቸው በስተቀር የታሰሩባቸውን አባሎች ሥም ዝርዝር ቀርቶ ቁጥራቸውን እንኳን በይፋ ተናግረው አያውቁም። የተዘጉባቸውን ቢሮዎች ቁጥር ቦታም እንዲሁ አሳውቀው አያውቅም። ይህም በትግላቸው ላይ ግልጽነት የጎደለው ጥያቄ እንዲያነሱ እና ተጠርጣሪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
ይሁንና አክቲቪስቶች ከዚህ ቀደም ትዊተር ላይ ባደረጉት ዘመቻ ከ174 በላይ ዕጩ የመሆን ዕድል ያላቸው የኦሮሞ ፖለቲከኞች መታሠራቸውን ሲናገሩ ነበር። በኦሮሚያ 178 ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት እና 537 ለኦሮሚያ ጨፌ የሚሆኑ በድምሩ 715 ዕጩዎች ያስፈልጋሉ። አንድ ፓርቲ ክልላዊ መንግሥት ለመመሥረት ቢያንስ 267 ወንበሮችን ማቅረብ አለበት። ስለሆነም በዚህ ቁጥር የምናስመዘግበው ዕጩ የለንም ማለት አያስኬድም። ነገር ግን ዋነኛው ትግል አንድም አባልም ቢሆን በታሰረበት ሁኔታ ፓርቲዎቻቸውን ወደ ፖለቲካ ውድድር አይገቡም የሚል ክርክር ከሆነ ሊያስኬድ ይችላል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ምኅዳሩ በራሱ ያጋደለ ስለሆነ እና አሸናፊው ከወዲሁ የታወቀ ስለሆነ ተሳትፏችን ከአጃቢነት የዘለለ አይሆንም የሚልም ከሆነ ሊያስኬድ ይችላል። ነገር ግን አሁንም የልደቱ አያሌውን ንግግር ዋቢ አድርገን የጠቀስነውና አጋጣሚውን ለትግል መጠቀም በሚለው ሚዛን ክርክሩ ውኃ አያነሳም።
በሌላ በኩል ኦነግ እና ኦፌኮ “የአንድነት ኃይሎች” ብለው ለሚጠሯቸው ብልፅግና ፓርቲ እና ምናልባትም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) መድረኩን ጥለው መውጣታቸው፣ ለርዕዮተ ዓለም ተቀናቃኞቻቸው ትልቅ ዕድል ነው የሚሆነው። በተለይም ደግሞ ረግጦናል ለሚሉት ብልፅግና ቀላል መንገድ አድርገውለታል። ምክንያቱም ኢዜማ ዝቅተኛ ተሳትፎ የሚያደርገው ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሲሆን፣ ዕጩ የሚያቀርብባቸው ወረዳዎች ከ67 (በድምሩ 201  አይበልጡም። ስለሆነም ብልፅግና ያለምንም ፈተና ክልሉን ለቀጣዩ አምስት ዓመታት እንዲመራ መንገድ ተጠርጎለታል።
ትርፉ ምንድን ነው?
ኦፌኮ እና ኦነግ ከምርጫው ተሳትፎ መውጣታቸው ኦሮሚያ ውስጥ ተቀባይነት ያለው ተቃዋሚ እንዳይኖር በማድረግ ክልሉ ውስጥ የሚቋቋመው መንግሥት፣ ጨፌው፣ እንዲሁም ፌዴራሉ ላይ የሚመሠረተው መንግሥት ተቀባይነት እንዲያጣ ለማድረግ ያለመ ይመስላል። ብቸኛው ትርፍ ሊሆን የሚችለውም ይኸው ነው።
እንደአቀዱትም አሁን ኦሮሚያ ውስጥ በብሔር የተደራጀ ብቸኛው ተቃዋሚ ድርጅት የኦሮሞ ነጻነት ንቅናቄ (ኦነን) ነው። ኦነን ደግሞ እስካሁን ያስመዘገባቸው ዕጩዎች ቁጥር 4 ብቻ ነው። ይህ ምርጫ ቢያንስ ካለፉት ሁለት ምርጫዎች የተሻለ ተጠባቂ ነበር። ካለፉት ሁለት ምርጫዎች የተሻለ ነጻ ይሆናልም ተብሎ ይጠበቃል።
የኦነግ እና የኦፌኮ ዓላማ ምርጫዎቹ ካለፉት ሁለት ምርጫዎች የተሻሉ እንዳልሆኑ ማሳየት ከሆነ እምብዛም የሚሳካ አይሆንም፤ ነገር ግን እንደተጠበቀው ውድድር የበዛበት እና ‘ማን ያሸንፍ ይሆን?’ ተብሎ በጉጉት የሚጠበቅ አይሆንም። ይህ ደግሞ እነርሱ ቢሳተፉም የሚቀየር አይመስልም። በአሁኑ ጊዜ በጉጉት እና በፍርሐት የሚጠበቀው ምርጫው በሰላም ይጠናቀቅ ይሆን ወይስ ነውጥ ይኖር ይሆን የሚለው ብቻ ነው። አንዳንዶች የኦነግ እና ኦፌኮ አለመሳተፍ ውጥረቱን ስለሚቀንስ ግጭት ይቀሰቀሳል የሚለውን ስጋትም ይቀንሰዋል እስከማለት ደርሰዋል።
በዚህ መልኩ ትርፍ እና ኪሳራውን አመዛዝነን መደምደሚያ ለመስጠት ብንሞክር በተለይም ለሰላማዊ ትግል ከሚኖረው አበርክቶ አንፃር የኦፌኮ እና ኦነግ ምርጫው ላይ ማደም ኪሳራው ያመዝናል።
Filed in: Amharic