>
5:13 pm - Friday April 18, 6713

እስክንድር ነጋ ኢትዮጵያዊው ማሃትማ ጋንዲ...!?!  ደረጀ ከበደ

እስክንድር ነጋ ኢትዮጵያዊው ማሃትማ ጋንዲ…!?! 

ደረጀ ከበደ

ማሃትማ ጋንዲ ጥቅምት 2 1869 ፖርባንዳር በተባለች የህንድ ግዛት ነበር የተወለደው። በጊዜው ህንድ በእንግሊዞች ቅኝ ስር ነበረች። ጋንዲ ተምሮ በህንድ ከፍተኛ ፍርድቤቶች ጠበቃ ሆነ። ሃብትና ክብር በእጁ ገባ። ነገር ግን ጥሪው ፍርድቤትና ዳኞች ፊት መሙዋገት እንዳልነበር ወዲያው አወቀና የውስጡን ጩሀት መስማት ጀመረ። የህሊናው እሪታ ለወገኖቹ ለህንድ ህዝብና ለሃገሩ ነፃነት ህይወቱን መሰዋት ነበር። ለመብትና ለነፃነት በሰላማዊ መንገድ ቅኝ ገዢዎችን መታገል የማሃትማ ጋንዲ ቁልፍ መለያው ነበር። ስልቱን በመጠቀም የህንድን ጭቁኖች ብቻ ሳይሆን በአለም ዙሪያ ነፃነታቸውን የተነፈጉ ሁሉ በሰላማዊ ተቃውሞ (peaceful protest) ነፃነታቸውን መጎናፅፍ እንደሚችሉ በተግባር ያሳያቸው ማሃትማ ጋንዲ ነው።
የኛው እስክንድር ነጋ ማህትማ ጋንዲን በብዙ ይመስለዋል። በቅርብ ያየሁት የእስክንድር ነጋ ኢንተርቪው በጣም ነበር ያስደነቀኝ።
“…ገድለን ሳይሆን በሞታችን እናሸንፋለን” አለ እስክንድር ነጋ። ምን አይነት ፅናት ነው? 
ጋንዲ ለህንድ ነፃነት የተዋጋው “በየቀኑ እየሞተ” ነበር። ጋንዲ ሃይማኖቱ ሂንዱ ሲሆን ለእስላሞችም ይሙዋገት ነበር። ይህንን ያልወደደ አንድ የሂንዱ አማኝ ነበር ጋንዲ በአንዲት ትንሽ ሰፈር ውስጥ ህዝቡን ሊያፅናና በሄደበት ተኩሶ የገደለው። ጋንዲ ሂንዱ ነበር የሞተው ግን ለሙስሊም ወገኑ በመሙዋገቱ ነበር።
እስክንድር ለብሄሮች ሁሉ ነው የታገለው የሚታገለውም፣ ዘጠኝ አስሬ የታሰረው፣ ልጁንና ባለቤቱን መስዋእት አድርጎ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እየጮሀ ያለው። ቤት ንብረት ላፍራ ሳይል፣ መጦሪያዬን ሳይል፣ በጠላቶቹ ላይ ሳይዝት፣ በፅናት ለህዝብና ለሃገር፣ ራሱን ዝቅ በማድረግና ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መጀመሪያ ወያኔን አሁን ደግሞ አቢይንና ኦነግን እየሞገተ ያለው።
 
ታዲያ ሁሉ በሰላማዊ መንገድ!!  የጋንዲ ልጅ አይደል!!  
እስክንድር ነጋ ለፖሊቲከኞችና ለጨቁዋኞች አይመችም። አይዘልፋቸውም፣ አይዘረጥጣቸውም፣ ስሜቱን ተቆጣጥሮ በአክብሮትና ሰከን ባለ መንገድ ጉዳዩን ያቀርባል። የተናገረውን በተግባር ያሳያል፣ ለራሴ ሳይል ለሌሎች ያካፍላል፣ እስክንድር ለማማትም አይመች፣ ለሃሜት መፅሄቶችም (Tabloid Megazines) ደባሪ ነው፣ ስራው ፊትለፊትና ቀጥተኛ ስለሆነ ስለሱ የሚቆፍሩም ቢኖሩ ሁልጊዜ ባዶ እጃቸውን ነው የሚወጡት። ኢትዮጵያዊው ጋንዲ!!
ይህን ሰው ነው አቢይ አህመድ ዋሽቶ ያሰረው። የሃሰት ምስክሮችን አሰልጥኖ በውሸት እንዲቀባጀሩበት እያደረገ ያለው። እስክንድር ነጋ ግን በቀልን አያውቅም። ዛሬ ከእስር ቢፈታ በሚቀጥለው ቀን ካቆመበት ነው የሚቀጥለው። ምክንያቱም እንደ ጋንዲ ጥሪውን በደንብ ያውቃላ። ትግል ለአስክንንድር እንደ አየሩ ጠባይ የሚለዋወጥ አይደለም፣ ዴሞክራሲ ወይም የክብር ሞት!!! እስከመጨረሻው!!
ሁለቱም መልካም ሰዎች  የሚመሳሰሉባቸውን ጥቂት ስብእናና አሰራሮች ጨምቄ ከዚህ በታች አቅርቤላችሁዋለሁ
1/ ሁለቱም በጣም የተማሩ ናቸው፣ ጋንዲ ጠበቃ ነበር፣ አክቲቪስት ነበር፣ የፖሊቲካ Ethicist ወይም በፖሊቲካ ዙሪያ ስላለው እሰራርና ሞራል የሚገደው ሰው ነበር። እስክንድርም በጣም የተማረ ሰው ነው። በአሜሪካን አገር በድህረምርቃ ደረጃ ያጠና ብሩህ ጭንቅላት የታደለ ሰው ነው።
2/ ሁለቱም ምቹ ኑሮ መኖር ሲችሉ ለህዝብና ለሃገር ብለው ከቅንጦት ይልቅ ዝቅ ያለ ኑሮን መረጡ።  ከሰፊው ህዝብ ጋር መኖር መረጡ። እስክንድር ከቤተሰቡ ጋር ቢያሻው ውጪ፣ አልያም በሃገሩ ላይ ምቹ ኑሮ መኖር በቻለ ነበር፣ ነገር ግን ለነፃነትና ለመብት እስርና እንግልትን አየ።
ፌስታሉን ይዞ በእግሩ አዲስ አበባን ሲያቁዋርጥ ሁልጊዜ በታላቅ ሞራል ነው
3/ የትግል ስልታቸው ከላይ እስከታች ተመሳሳይ ነው።ሁለቱም ትግላቸው ሰላማዊና አመፅ አልባ ነው። ማህተመ ጋንዲ ብዙ ጊዜ ይፆም ነበር፣ ብዙ ጊዜ ደህነትና ችግር ያለባቸውን ስፍራዎች እየሄደ ይጎበኛል። እስክንድርም ሰዎች ሲፈናቀሉ፣ ቤታቸው ሲፈርስ፣ በስፍራው መጀመሪያ የሚገኘው እሱ ነው። ያ ብቻ አይደለም የታከለኡማ አስተዳደር በከተማዋ ዙሪያ ያሉትን ቅርሶቻችንና እሴቶቻችንን ሲያፈርስና በምትኩ ሌላ ሲገነባ፣ እስክንድር ነጋ ወደስፍራው ይሄዳል፣ ጥያቄ ይጠይቃል። ለምሳሌ በመዲናችን የሞአ አንበሳ ዘእብነገደ ይሁዳ ሃውልት ሙጃ በልቶት ቆሻሻ ውጦት እስክንድር ባልደረባዎቹንና ጥቂት ፈቃደኞችን ይዞ ሄዶ ሲያፀዳ በፖሊሶች እንደተከለከለና እንዳስቆሙት ትዝ ይለኛል።
ጋንዲና እስክንድር የተግባር ሰዎች ናቸው። 
4/ ጋንዲ “BAPU” ማለትም የ”ህንድ የነፃነት አባት” የሚል ስያሜ የተሰጠው ለህንድ ወገኖቹ መብት ሳያቁዋርጥ ስለታገለ ነው። ይህ ሰው ተፅእኖው በአለም ሁሉ የተዳረሰ የሰላምና የእርቅ መላክተኛ ነው። ታላቁዋ ብሪታኒያን በሰላም ትግል ያንበረከከ ከመንጋጋዋ የህንድን ነፃነት ፈልቅቆ ያወጣና ለምድሩና ለህዝቡ የሰጠ ነው። የእኛው እስክንድር ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ደጋግሞ በእስር ተንገላቶአል፣ ህይወቱን፣ትዳሩን ሰውቶአል ስለዚህም “ታላቁ” እስክንድር እየተባለ ነው በአለም ዙሪያ ባሉ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ በፍቅር የሚጠራው። እሱ ግን ለዛ ብቁ ነኝ የሚል አንደበትም ሃሳብም የለውም። ተልእኮውም ለክብርና ለስልጣን እንዳልሆነ ከስራው ይታያል።
በመጨረሻም ከእልፍ የማህትማ ጋንዲ አባባሎች በእነዚህ በሁለቱ ላብቃ
“Love is the strongest force the world possesses.”
“The best way to find yourself is to lose yourself in the service of others.”
Filed in: Amharic