>

ወይ አዲስ አበባ !!! .ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ 

ወይ አዲስ አበባ !!!

.ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ 

አዲስ አበባ የየትኛውም አካል ጠባብ አስተሳሰብና የዘረኝነት ሰንኮፍ አብቅላ የማሳደግ ምቹ ገፅ ሳይኖራት ዘመናትን አስቆጥራለች ። ዘረኛው መለስ ዜናዊ እንኳ ከደደቢት ዋሻ ታቅፎት የመጣውን ክፉ የዘረኝነት መንፈስ አዲስ አበባ ላይ ዘርቶና አብቅሎ  ፍሬ ለመሰብሰብ አልቻለም ። አ/አ ከሁሉም የሐገሪቱ ክፍል ዘረኝነትን ከማብቀልና ከማፋፋት አኳያ ምሕዳሯ ጭንጫ ነው ።
ዘረኝነት ፣ ጎሰኝነት ፣ አክራሪ ሐይማኖተኝነት እና ” የኔ ብቻ! ” መንፈስ ለአዲስ አበባ አሜኼላ ነው ። ከርክሰትም የከፋ ጥይፍ ነው ። ዝቅ ያሉ ዘረኞችና የብዙሃን ውክልና የሌላቸው እንዲሁም በጠባብ ቅርጫት ራሳቸውን ያጨቁ ወገኖች ሁሉ ለነሱ ዝቅ የማለት ምክንያት የሆነውን የዘረኝነት መርዝ አዲስ አበባ ላይ በመድፋት፤ …በአካታችና በአቃፊነት የደመቀቺውን ይህቺን ወብ ከተማችንን ሊያጠለሿት ይዳክራሉ ።
.
አዲስ አበባ ከ100 ሚሊየን በላይ የሆነው ኢትዮጵያዊ ቅድመ-እናትና አባቶቹ እንዲሁም ሃያቶቹ ጥሪታቸውን ፣ ባሕላቸውን ፣ እምነታቸውን ፣ ማንነታቸውን ፣ ወዛቸውን ያፈሰሱባትና በእነዚህም የአበውና እመው እሴቶች አማካይነት በልፅጋ የኖረች የጋራ ፍሬያችን ናት ። አዲስ አበባ የበለፀገቺው  ከከርሰ-ምድሯ በተዛቀ አለያም ከሰማዯ በዘነበ ወርቅ ፣ አልማዝና ነዳጅ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሐያቶች ላባቸውን ጠብ አርገው ባፈሩት ሐብት ነው ፤ ከዚህ በመነሳት አ/አበባችን  የሁሉም ሕዝብ የተጋድሎ ፣ የሐብትና የታሪክ አሻራ ውጤትም ናት ። ከዚህ አልፎ መላው ኢትዮጵያውያን ለአፍሪካና ለአለም ያበረከቷት የፖለቲካና የዲፕሎማሲም ማእከል ናት ። ማንም ነጠላ ብሄር ተነስቶ ” ለአዲስ አበባ እዚህ ደረጃ መድረስ ምክንያት እኔ ብቻ ነኝና ፤ …. የብቻዬ ንብረትም ነች ” ማለት አይችልም ። አዲስ አበባም ሆነ አዲስ አበቤነት ስሪታቸው ውሕድ ፣ ሕብርና የወል ነው ።
.
አ/አ ከ80 በላይ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች መንፈስ ፣ ተግባርና እውነት ፈትሎ የሸመናት የኢትዮጵያውያን የጋራ ብሄራዊ ጥበብ ስለመሆኗ አሁን ያለው ገፅታዋ መስካሪ ነው ። ለዚህም ነው ወያኔ በአዲስ አበባና በአዲስ አበቤነት ላይ 27 አመት ሙሉ ዘረኝነት ቢዘራም በሚፈልገው መጠን ፍሬ ለመሰብሰ ያልቻለው ። የተገመደችበት የጥበብ ክርና ውህድ ማሕበረሰቧም በቀላሉ ሊተለተል ያልቻለው ትስስሩ ጥብቅና ጥልቅም በመሆኑ ነው ።
” እኔ አ/አበቤ …. ወገንተኝነት አይዘኝም ፤ ብሄርተኝነት አይገድበኝም ፤ የፍቅር እጄ በየአቅጣጫው እንደጨረር የተዘረጋ ነው ። ያገኘሁት ሰው ወገኔ ነው ፤ ….. የተወለድኩት ከአንድ እናትና አባት ይሁን እንጂ ያደኩት በብዙዎች እጅ ነው ። ….. በአማራ ፣ በኦሮሞ ፣ በትግራይ ፣ በሐረሪ ፣…… የጉርብትና እናት እጅ አድጌአለሁ ። ….. በሌላም የጉርብትና አባት እንዲሁ ። ‘ ተጎራባች አባት ከየት ? ‘ ቢባል ፤ ከሲዳማ ፣ ከኩናማ ፣ ከድሬ ፣ ከቡሬ ፣ ከኤርትራ ፣ ከጎርጎራ ፣ ከጎንደር ፣ ከሐረር ፣ ነው ። ….. እኔ አ/አበቤ ያደኩት በደቦ ነው ። ወገንተኝነቴ ተቀይጧል ፤ አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ አይሆንልኝም ። …. እኛ አ/አበቤዎች ….. ሁሉም ኢትዮጵያውያን ባእድ ሳያደርጉ አሳድገውናል ። ….. ሌጣውን የመጣ …  ብሄር ከተፈጥሯችን ጋር ይቃረናል ።  እኔ …. በአስተዳደጌ ውስጥ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ” እጅ እላፊ ” አለብኝ ። – በማጉረስም ፣ በመቆንጠጥም ። ” ይላል ፣
.
እንግዲህ አ/አበባም ሆነ አ/አበቤነት ተቦክተው የተጋገሩት ፣ ተደርተው የተሸመኑት ፣ ተጠርበው የተዋቀሩት ፣ ተነድፈው የተፈተሉት ፣ ነጥረው/ቀልጠው/ የተቀረፁት ይኸው አለማየሁ ገላጋይ በገለፀው ሂደትና አይነት ጭምር ነው ። …… ለዚህም ነው ፤ ” አ/አበባና አ/አበቤ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የመዋጮ ሕንፀቶች ናቸው  ” የሚባለው ። ለዚህም ነው አንድ ዜጋ ከየትም ተነስቶ ወደ አ/አ ሲመጣ ፤ ከሌላኛው ቤቱ ወደ ሌላኛው ቤቱ እንደሚመጣ የሚሰማው ። አንድ ዜጋ ከየትም የሐገሪቱ ክፍል ተነስቶ ወደ አ/አ ሲመጣ ……..” ከተማዬ ” እያለ በጉጉት ሊረግጣት የሚጓዘው ፤ የሐያቶቹ ፣ …. መንፈስ ፣ ጉልበት ፣ እውቀት ፣ እምነት የተከላት ከተማ እንደሆነች ስለሚያምን ነው ። የአባቶቹ ሁለንተናዊ ማንነት አዲስ አበባን በመፍጠሩ ምክንያት የሱም ሐብት እንደሆነች ስለሚያስብም ነው ። ደግሞም ትክክልም ነው ።
.
ዛሬ ከግራም ከቀኝ ” አ/አ የኔ ብቻ ናት ” የሚሉት ወገኖች … አ/አበባን ከመላው ኢትዮጵያውያንና ከዚያም ወርደው ከነዋሪዎቿ ነጥለው ነው ። የአዲስ አበባ ባለቤቶች የአሁኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሳይሆኑ የዛሬ 100 አመት አካባቢ የነበሩት ፊንፊኔያውያን ናቸው አይነት መከራከሪያም እያቀረቡ ነው ። ከዚህ እምነታቸውና ትርክታቸውም ተነስተው በዚህ የስልጣኔ ዘመን  የአዲስ አበባን ነዋሪ  በወክልና አለያም በቅኝ  ሊገዙት እየተጉረመረሙ ነው ። ” መሬቱ የአባቶቼና የሐያቶቼ ነውና ፤ እኔ ልጃቸው ሰፍሬ በምሰጥህ የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚና የአስተዳደር መዋቅር ትኖራለህ ! ” አይነት አዋጅ እያወጁም ነው ። ይህ አዋጅና አግላይ እምነታቸው እስከየት ሊጓዝ እንደሚችል ግን ለወደፊቱ የሚታይ ነው ።
ምንጭ:- “.መለያየት ሞት ነው ” ከሚለው መፅሐፉ ……
Filed in: Amharic