>
5:13 pm - Wednesday April 19, 7544

በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከአብን የተሰጠ መግለጫ...!!!

በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከአብን የተሰጠ መግለጫ…!!!

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በሰሜን ሸዋ ዞን በአጣዬና አጎራባች አካባቢዎች የጥላቻ ኃይሎች በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጦርነት በሕዝባችን ላይ መክፈታቸውን አረጋግጧል። በዚህም ምክንያት የበርካታ ወገኖቻችን ሕይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል እንዲሁም ከፍተኛ ንብረት ወድሟል።
ጥቃቱ የተከፈተውና እየተፈፀመ ያለው በመሀል የአማራ አካባቢዎች ሲሆን ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ሲፈፀሙ የነበሩ ጥቃቶች ቀጣይ ክፍል ሆኖ በተለይ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚኒሻ የትሕነግን አሸባሪ ኃይል ለመመከት፣ ሕዝቡን፣ ክልሉንና አገሩን ለመከላከል ወደ ክልሉ ምዕራባዊና ደቡባዊ ግዛቶች በሰፊው መንቀሳቀሱን ተከትሎ መሆኑ ብዙ ነገር ይገልጣል።
አብን ቀደም ብሎ መረጃው በደረሰው ወቅት ጉዳዩን በቅርበት በመከታተልና ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በማሳሰብ አጥፊዎቹ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት አፋጣኝ እርምጃ ተወስዶ የሕዝባችን ሰላምና መረጋጋት እንዲረጋገጥ ጠይቋል፤ አሁንም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ ይገኛል።
ስለሆነም ጥቃቱ በተከፈተበትና በሌሎች ቅርበት ባላቸው አካባቢዎች የምትገኙ ወገኖቻችን በተለይም ወጣቶች የተለያዩ የጥፋት አጀንዳ ባላቸው አካላት ሕዝቡን ለማሸበር ታስበው ከሚለቀቁ ሐሰተኛ መረጃዎች በመቆጠብ፣ ከመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበርና ውስጣዊ አንድነታችሁን በማጠናከር ለሕዝባችን ደኅንነት መረጋገጥ የበኩላችሁን ሚና እንድትወጡ አብን ያሳስባል።
የአማራ ክልል መንግስትና ገዢው «የአማራ ብልፅግና» የአመራሩን ውስጣዊ አንድነት ከመቸውም ጊዜ በላይ በማጠናከር፣ ለሰርጎ ገቦችና ሴረኞች እንዲሁም አገራችን ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ አበክረው የሚሰሩ የውጭ ኃይሎችና ሚዲያወች በከፈቱት የተቀነባበረ ፕሮፖጋንዳና ወከባ ሳይንበረከክ በሕዝባችን ላይ በየአቅጣጫው የተከፈተውን ዘር ተኮር ጥቃት በብቃት መመከት እንዲችልና ለዚህም ሁሉንም የአማራ ኃይሎች ከጎኑ የማሰለፍ የማስተባበር ሚናውን በቁርጠኝነት እንዲወጣ አብን ታሪካዊ ጥሪውን ያቀርባል።
በአሁኑ ጊዜ የፌደራሉ መንግስት ከበዛ ቸልተኝነት፣ ከታዳሚነት አልፎ አመራሩና መዋቅሩ ለጽንፈኛ ኃይሎቹ በምሽግነትና በድጋፍ ሰጭነት እያገለገለ መሆኑ የተረጋገጠና በራሱ በመንግስት በተደጋጋሚ የታመነ ኃቅ ሆኗል። ስለሆነም መንግስት አገርንና ሕዝብን ወደፊት አንድ እርምጃ ማሻገር ቢሳነው እንኳ ላልተቋረጠ የኋሊዬሽ እንሽርት ዳርጎ ለመቀጠል ያለውን ፍላጎት ደጋግሞ እንዲያጤነው በአፅንኦት እንጠይቃለን።
በተለያዩ አካባቢዎች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀሙትን ዘር ተኮር ጥቃቶች በዘላቂነት ማስቆም ካልተቻለና በአጥፊዎቹ ላይ የማያዳግም እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ በቀጣይ ግንባር ቀደም የአገር ኅልውናን አደጋ ላይ የሚጥል ችግር መሆኑ እንደማይቀር ያለንን ስጋት ለመግልፅ እንወዳለን።
Filed in: Amharic