>

አማን ሚካኤል አንዶም … ለምን አሁናችንን ያስታውሱኛል? (አሰፋ ሀይሉ)

አማን ሚካኤል አንዶም … ለምን አሁናችንን ያስታውሱኛል?

አሰፋ ሀይሉ

(ታሪካዊ ምልሰት)
ጄነራል አማን ሚካኤል አንዶም – በጦሩ ዘንድ በነበራቸው ከፍተኛ ተቀባይነት፣ በዕውቀታቸው፣ በብስለታቸው፣ እንዲሁም ትውልደ ኤርትራዊ በመሆናቸው የኤርትራን ተገንጣይ ቡድኖች በሚገባቸው ቋንቋ አነጋግረው በማሳመን የሰሜኑን የሀገራችንን ችግር በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ይረዳሉ በሚል – በ1966ቱ አብዮት ወቅት – በመላው ኢትዮጵያ ከሚገኙ የበታችና መካከለኛ የጦር መኮንኖች ተውጣጥቶ ንጉሠ ነገሥቱን ከሥልጣን ያወረደው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ («ደርግ») – ሊቀመንበሩ አድርጎ ሾማቸው፡፡
የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ተደርገው የተሾሙትና በእንግሊዝ በህክምና ላይ ይገኙ የነበሩት የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ልጅ ልዑል አልጋወራሽ አስፋወሰን ሹመቱን እንደማይቀበሉና ወደ ሀገርቤትም እንደማይመለሱ ሲያሳውቁ፣ ጄ/ል አማን አንዶም የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔርም፣ የጊዜያዊው መንግሥት ሊቀመንበርም በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዚደንታዊ ሊሰኝ የሚችልን ሥልጣን አጣምረው የተቀዳጁ መሪ ሆኑ፡፡ ቀስ በቀስ ግን በደርጉ የበታች መኮንኖች ውሳኔዎች እጅጉን ይደነግጡ ጀመር፡፡
እርሳቸው መሪ ተብለው ተቀምጠው ሁሉ ነገር የሚወሰነው በእጅ ማውጣት ሆነ፡፡ ወታደራዊ ዲሲፕሊን የሌለበት የደቦ ዕድር ሆነባቸው፡፡ ያው የደቦ ፍርድ የቀኃሥን ሚኒስትሮችና የጦር መኮንኖች ማስረሸኑን ተከትሎ አማን ሚካኤል አንዶም ጭራሽ ከደርጉ ጋር ፊት ለፊት በአካል አልተያይም፣ አልነጋገርም አሉ፡፡ ወሳኝነቱን ስጡኝ አለበለዚያ ከናንተ ጋር ግንኙነቴን አቋርጬያለሁ አሉ፡፡ ጥበቃዎቻቸው ቀኑን ሙሉና ሌሊቱን በቤታቸው ቁጭ ብለው ዊስኪ በመጠጣት በብስጭትና በመብከንከን ብቸኝነትን መርጠው ያሳልፉ እንደነበር ሪፖርት ያደርጉ ነበር፡፡
የስልክ ንግግራቸው ተጠልፎ ሲሰማ – በጦር አመራር ሳይሆን በሎጂስቲክስ ሙያ የሰለጠኑትን እነ ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያምን ‹‹ዱቄት ሰፋሪዎች›› ብለው በመዝለፍ – ‹‹ከዱቄት ሰፋሪዎች ጋር አብሬ አልሰራም፣ ክብሬም፣ ዕውቀቴም አይፈቅድልኝም!›› ብለው መናገራቸው ታወቀ፡፡ በመጨረሻም – ደራሲ ማሞ ውድነህ ሙሉውን ንግግራቸውን ወደ ጽሑፍ በመገልበጥ ከመሞቱ በፊት ባሳተመው የህይወት ታሪክ መጽሐፉ ለታሪክ ከትቦ እንዳስቀመጠልን – ጄ/ል አማን ሚካኤል አንዶም በኤርትራ ስቴዲየም ተገኝተው ያደረጉት ንግግርም ታወቀ፡፡
በዚያ የአስመራው ስቴዲየም ንግግራቸው ‹‹እናንተ የሠለጠናችሁ ናችሁ፣ አንገዛም በሏቸው፣ ባርነትን አንሻም በሏቸው፣ ነጻነታችሁ በእጃችሁ ነው፣.. ›› እያሉ ኤርትራውያን እንዲገነጠሉ መቀስቀሳቸው የተቀረጸው ድምጻቸው ቀርቦ ተረጋገጠ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተጠራቅመው የቀረቡለት፡፡
እውነቱን ለመናገር ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርጉ ገና ሥልጣን ላይ ከመውጣቱ ራሱ የሾመውን ሊቀመንበር መልሶ ማውረድም ሆነ ሌላ አጉል ነገር ውሰጥ መግባት አልፈለገም ነበር፡፡ ጄ/ል አማን አንዶምን ደግሞ ደጋግሞ ቢለምናቸውና ቢያስለምናቸውም ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ በመጨረሻ ጄ/ል አማን ከሌላው ጦርሠራዊት መኮንኖችና ከቀኃሥ ታማኞች ጋር ተባብረው ደርጉን ራሱን ለማስመታት ከመንቀሳቀሳቸው በፊት እጃቸውን ይዞ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ደርጉ ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡
ብዙዎቸ እንዳይሆን የተመኙት፣ እና የተሳቀቁበት የማይቀረው የመጨረሻ ነገር መጣ፡፡ ጄ/ል አማን ሚካኤል አንዶም በመኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡ በታንክ ጭምር ተከበቡ፡፡ እጃቸውን እንዲሰጡ በድምጽ ማጉያ ተደጋጋሚ ጥሪ ተደረገላቸው፡፡ የጄኔራሉ መልስ ወደ አጥራቸው በሚቃረቡ ወታደሮች ላይ በመስኮታቸው በኩል ተኩስ መክፈት ነበር፡፡ ሁኔታው ለደርጉ በሬዲዮ መልዕክት ተነገረው፡፡ ሻለቃ መንግሥቱ ለደርጉ ያለውን ሁኔታ ‹‹ላይቭ›› አሳወቀ፡፡ እዚያው በዚያው የማያዳግም የመጨረሻ እርምጃ እንዲወሰድባቸው በአንድ ድምጽ ተወሰነ፡፡
የመቶ አለቃ ዳንኤል አነጣጥሮ ተኳሸ ጓዶች በቀድሞ ጄኔራላቸው ላይ ቃታ ሊስቡ ልባቸው እየተሸበረ ወደ ጄኔራሉ መኖሪያ ቤት ተጠጉ፡፡ እጃቸውን እንዲሰጡ፣ ወጥተው በሰላም ዘቦቹን እንዲያነጋግሩ ተጠየቁ፡፡ የእርሳቸው መልስ ተኩስ ነበር፡፡ እርሳቸው በመስኮት ሆነው እየተኮሱ፣ ግዙፍ የጦርሜዳ ታንኮች የቤታቸውን አጥር በረቃቅሰው፣ ግድግዳቸውን አፈራርሰው ገቡ፡፡ እና ቃላት ባልዋሉበት፣ ጥይቶች ብቻ በተነጋገሩበት አስከፊ ቀን፣ በቤታቸው ጨፈላልቀው ገደሏቸው፡፡ የበረሃው ጀግና፣ ልበሙሉው፣ ግርማ ሞገሳሙ፣ ጄ/ል አማን ሚካኤል አንዶም – የመጨረሻ የሞት ጽዋቸውን ሊቀመንበሩ አድርጎ በሾማቸው በደርጉ እጅ በዚሀ መልክ ተቀበሉ፡፡
ጄ/ል አማን ሚካኤል አንዶምን ሳስብ ከብዙ ነገሮቻቸው መሀል ብዙ ጊዜ ተነጥሎ ደጋግሞ የሚመጣብኝ – ከትውልደ ኤርትራውያን ተገንጣዮች ጋር ተነጋግረው ሰላምን ያመጣሉ ተብለው ሲታሰቡ – አስመራ ስቴዲየም ሄደው ያሰሙት ንግግር ነው፡፡ ጄኔራሉ ያን ንግግር ስለማድረጋቸው ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለውም፡፡ ማንም ሰው የማሞ ውድነህን መጽሐፍ ገዝቶ ቃል በቃል የተናገሩትን ማግኘት ይችላል፡፡
ግን የሚገርመኝ እኚህ የተከበሩ ጄኔራል – የፈለገውን ያህል ከደርጉ የበታች መኮንኖቻቸው ጋር ባይስማሙ – የፈለጋቸውን ያህል በሆነው ሁሉ ደስተኛ ባይሆኑ – እንዴት ያስታርቁናል ከተባሏቸው ከኤርትራ ገንጣዮች ብሰው – ነጻነታችሁን አውጁ እያሉ ሀገራቸውን የካዱ የጦር መሪ ሆነው ተገኙ? ለምን እንዲያ ማድረግ ፈለጉ? ከደቂቅነት እስከ ልሂቅነት ባደረሰቻቸው እናት ሀገራቸው ላይ ያደረባቸው ቅሬታ ወይ ቂም ምንድን ነበር? ብዙ ጊዜ መልስ የማላገኝለት ጥያቄ ነው፡፡
ደርጉ በእርሳቸውም ሆነ በማንኛውም ሌላ ሰው ላይ ከህግ ውጪ እርምጃ ስለወሰደባቸው እንደማንኛውም ለሀገር ሊጠቅም ይችል እንደነበረ ዜጋ ከልቤ አዝንላቸዋለሁ፡፡ ግን ደርጉ ብዙ ምክንያቶች እያሉት ከመጠን በላይ ታግሶና አስታምሞ እርምጃ የወሰደባቸው ሰው እንሆኑም እረዳለሁ፡፡ ይህ ማለት መሞት ይገባቸዋል ማለት በፍጹም አይደለም፡፡ ግን ሞታቸውን የጠሩት ራሳቸው መሆናቸውን ማወቅ ይቻላል ለማለት ነው፡፡
አሁን ታዲያ ኮ/ል አብይ አህመድን ሳይ ያ የጄ/ል አማን አንዶም ነገር በሩቁ ይመጣብኛል፡፡ ኮ/ል አብይ አህመድም የኦነግ ተገንጣዮችን በሚገባቸው ቋንቋ አናግሮ ሰላም ያመጣልናል ተብሎ ሲጠበቅ፣ ጭራሽ ከሀገሪቱ ሸሽተው ከየተደበቁባቸው ሀገራት ሁሉ ሰብስቦ አምጠቶ፣ ሀገሪቱ ላይ ፈትቶ ለቀቃቸው፡፡ ኦሮሚያ የምትባለውን ክልል እንደልባቸው መፈንጫና መደራጃ፣ ጦር መመልመያና ወታራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ አድርገው እንዲጠቀሙበት ወለል አድርጎ ለቆላቸው፣ ይኸው ሀገሪቱን በእርድና በደም ጎርፍ እያጥለቀለቋት ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ስም ሲጠራ በዓይኖቹ እንባ የሚያቀርረው አብይ አህመድ፣ ለምን ይህን ማድረግ መረጠ? ይገርመኛል፡፡ መልስ የለኝም፡፡
አብይ አህመድን ክፉ እንዲነካው አልመኝም፡፡ ከአብይ አህመድ ጋር ሲስተያዩ በምንም መስፈርት ከሚልቁት ከጄ/ል አማን አንዶም ጋር ማነጻጸርም እጅግ ከባድ ድፍረት እንደሆነም አውቃለሁ፡፡ ከእኚያ በወታደራዊ ብቃታቸው ከተከበሩትና በሙያም፣ በዕውቀትም፣ በልምድም ከአብይ ጋር የሰማይና የምድር ያህል ከሚራራቁት ከጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም ጋር፣ የኦህዴጉን ወዶገብ አብይ አህመድን ለማነጻጸር መሞከር ዝሆንና አይጥን ለማነጻጸር እንደመሞከር ያለ ነገር እንደሚሆንብኝም አውቃለሁ፡፡
ቢሆንም ግን ወያኔን ከመዲናችን ያስኮበለለው ህዝባዊ አብዮት፣ በኮ/ል አብይ አህመድ ላይ የጣለው ብርቱ የሰላም ተስፋና፣ በተግባር አብይ አህመድ ሀገሪቱን ወደየት እንደከተታት ስመለከት፣ የአብይ ነገሮች ሁሉ ወደ ጄ/ል አማን ሚካኤል አንዶም የክህደት መንገድ ያመሩብኛል፡፡ ደግሞ ደጋግሞ አብይ አህመድ አማን ሚካኤል አንዶምን ስለሚያስታውሰኝ – ይሄ ሬዞናንሱ – ገደል ማሚቶው ያስፈራኛል፡፡
አብይ አህመድ – እንደ አማን አንዶም – ኦነጎቹን አግባብቶ ወደ ሠላም ያመጣቸዋል ሲባል – የኢትዮጵያን ህዝብ ክዶ ኦነጎቹ ወደሚቃዡለት ቢሊሱማ ‹‹ነጻነት›› እየመራቸው ይሆን?? ኢትዮጵያ ዳግም ከ50 ዓመት በኋላ ይበጀኛል ባለችው መሪዋ ተከድታ ይሆን? አንድዬ ይወቅ፡፡
ከዚህ በፊት በመልክም ከሚመስለው ከልጅ መኮንን እንዳልካቸው ጋር አመሳስዬው እንደነበር አሁንም አልዘነጋሁትም፡፡ መኮንን እንዳልካቸውም ሊወድቅ አንድ ሐሙስ የቀረውን የዘውዱን ሥርዓት ለማትረፍ ታትሮ ያልተሳካለት የመጨረሻው ዘውዳዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር፡፡
አብይ አህመድም ከሥር ከመሠረቱ ነቅዞ በሕዝብ ኃይል ሊወድቅ የሚንገዳገደውን የኢህአዴግ ኦፓርታይዳዊ ሥርዓት በጠቅላይነት እየመራ ከአይቀሬ ሞቱ ለማትረፍ የሚጋጋጥ የመጨረሻው ኢህአዴጋዊ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡
ግን ከአማን አንዶማዊው አስፈሪ የክህደት ሃሳብ ጋር ሲስተያይ፣ ይሄ የኢህአዴግ መውደቅ አለመውደቅ ጉዳይ ብዙ የሚያስጨንቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ እስቲ ዕድሜ ይስጠንና ሁሉን ለማየት ያብቃን፡፡
«ሀገሬ እውር ናት ማየት የናፈቃት
እንባ ላብስ ያለ ዓይን እየሠረቃት»
     ( – ወጣት ገጣሚ ሕሊና ደሳለኝ)
ሀገሬ ሰላምሽ ይብዛ፡፡
አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic