>
5:13 pm - Sunday April 19, 7142

ሁሉንም ወይም ምንም!" ፈውስ የሚያስፈልገው የኢትዮጵያዊያን የዜሮ ድምር አስተሳሰብ...!!! (ብርሃኑ አበበ (ዶ/ር))

‘ሁሉንም ወይም ምንም!”

ፈውስ የሚያስፈልገው የኢትዮጵያዊያን የዜሮ ድምር አስተሳሰብ…!!!

(ብርሃኑ አበበ (ዶ/ር))

 

* … የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከዚህ የዜሮ ድምር አስተሳሰብ ካልተፈወሰ እና ካልዘመነ ማናችንም ነጻ እንወጣም፡፡ ለልዩነት ቦታ መስጠት፣ ኢትዮጵያ የሁሉንም ልጆቿን አስተዋጽዖ እንደምትፈልግ ከምር መቀበል፣ ይብዛም ይነስም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአገሩ አስተዋጽዖ ሊያደርግ እንደሚችል ማመን ያስፈልጋል፡፡ ዕብሪትና መታበይ የውድቀት መሠረት ነው!
 
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል “ሁሉንም ወይም ምንም” በሚል መንፈስ የተቃኘ ለዴሞክራሲ ግንባታ እጂግ አደገኛ የሆነ ባህል ነው፡፡ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር ወይም ሁሉንም ነገር ማጣት የተለመደ የፖለቲካ ታሪካችን አካል ነው፡፡ አሁንም ከዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ፈቀቅ አላልንም፡፡
ባህሉ የእኛ ብቻ ባህል አልነበረም፡፡ ዛሬ ዴሞክራሲያዊ ናቸው የምንላቸው ብዙዎቹ የዓለማችን አገሮች እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብና አሠራር ነበራቸው፡፡ አገረ-መንግሥቱን የተቆጣጠረው ቡድን ከሚያስበው ውጪ ያሰበ አካል፣ እሱ ካስቀመጠው ውጪ የተለየ ነገር ያደረገ አካል ከባድ ቅጣት የሚቀበልበት ባህል በብዙ አገሮች የነበረ ነው፡፡ አውሮፓ ውስጥ ምን ያህል አፈና እንደነበር፣ የተለየ ሐሳብ የሚያራምዱ ሰዎች እንዴት ያለ ቅጣት ይደርስባቸው እንደነበር፣ የነበረውን ጥብቅ ሳንሱር ወዘተ… ታሪክ የመዘገበው ሐቅ ነው፡፡ ሁሉንም መጠቅለል የተለመደ ነገር ነበር፡፡ በጊዜ ሒደት በብዙ ትግልና መስዋዕትነት ነው ሁሉንም የመጠቅለል ባህልና አሠራር እንዲቀር የተደረገው፡፡ ከብዙ ትግልና መስዋዕትነት በኋላ ነው ሥልጣን ልጓም የተበጀለት፡፡ ይህ አገረ-መንግሥቱን እና አገረ መንግሥቱን የሚመራውን አካል (መንግሥትን) የማዘመን (Civilizing the State) ሒደት ምዕራባዊያን ለዓለም ያበረከቱት ትልቅ አበርክቶ ነው፡፡
የአገራችን ፖለቲካ ግን አሁንም ኋላቀር ነው፡፡ የፖለቲካ ተፎካካሪዎችን በጠላትነት መፈረጅ፣ በጠላትነት ከመፈረጅም አልፎ ስትራቴጂ ነድፎ ተፎካካሪዎች እንዲጠፉ መሥራት የተለመደ ያልተሻገርነው የፖለቲካችን ነቀርሳ ነው፡፡ ሌሎች አገሮች የፖለቲካ ፉክክር የሚደረግበትን ሜዳ እና የጨዋታውን ሕግ ሥርዓት ባለው መልኩ ሲያዘምኑት እኛ አሁንም በጨዋታው ሕግም በመጫወቻ ሜዳው ሁኔታም እንደነበርን አለን፤ ፈቀቅ አላልንም፡፡
ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ መውሰድ ከጊዜ በኋላ ሁሉንም ነገር ማጣትን እንደሚያስከትል ከቀዳማዊ ኀይለሥላሴ መንግሥት አልተማርንም፡፡ ቀዳሚ ኀይለ ሥላሴ ለተቀናቃኞቻቸው ቦታ ቢተው ወይም ከጊዜ ጋር አብረው ቢሄዱ ኖሮ ለበርካታ ዓመታት ደክመው የገነቡት ሥርዓትም፣ የእሳቸው ክብርና ስምም፣ እሳቸው፣ ልጆቻቸና ያገለገሏቸው ባለሥልጣኖቻቸውም በዚያ ደረጃ መከራ ባላዩ ነበር፡፡ ሁሉንም መጠቅለል ሁሉንም ማጣትን አስከተለ፡፡
ዐፄ ኀይለ ሥላሴን በፈላጭ ቆራጭነት ፈርጆ ብዙ ሲዘምር የከረመው የደርግ እጣ-ፈንታም ተመሳሳይ ነው፡፡ ደርጋዊያኑም ሁሉንም ተፎካካሪያቸውን በኀይል ፀጥ አሰኝተው አገሪቱን በብቸኝነት ለመግዛት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ ለውይይት ቦታ አልነበረም፡፡ ለልዩነትና ለሰጥቶ መቀበል ቦታ አልነበረም፡፡ ሁሉንም እኛ ብቻ እንያዘው፤ እንጠቅልለው ተባለ፡፡ ሆኖም ይህ ስግብግብ አስተሳሰብ ሄዶ ሆዶ ሁሉንም ማጣትን አስከተለ፡፡ አይነኬ ይመስሉ የነበሩት የደርግ መሪዎች እየተለቀሙ ወህኒ ቤት ወረዱ፣ የሥርዓቱ ቁንጮና አንዳንድ ዕድል የገጠማቸው ተከታዮቻቸው ደግሞ አገር ጥለው ተሰደዱ፤ “ፈረጠጡ” ይሏቸዋል አንዳንዶች፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለመዘመኑ ምክንያት ኢሕአዴግም በዚያው በተለመደው የሁሉንም ልጠቅልለው አባዜ ተለክፎ ተፎካካሪዎቹን ሁሉ በሽብርተኝነት እየፈረጀ ሲያስር፣ በንጹሐን ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈፅም፣ ለሥልጣኔ አስጊ ናቸው ያላቸውን ሁሉ ሲያሳድድ ከረመ፡፡ ሁሉንም እኛ ብቻ እንብላው አሉ፡፡ ሆኖም እንዲያ ልክ በሌለው እብሪት ተወጥረው በአገርና በሕዝብ ላይ ተነግሮ የማያልቅ በደል ያደረሱ ሰዎች ዛሬ የት እንዳሉ እያየን ነው፡፡ ወደፊት የሚሆነውን ደግሞ አብረን እናያለን፡፡
አሁንም ከዚህ አደገኛ በሽታ አልተፈወስንም፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የያዘውም በተቃራኒ ጎራ የተሰለፈውም ሁሉም የዚህ የመጠቅለል በሽታ ሰለባ ነው፡፡ የለውጡ ብቸኛ ባለቤት እኔ ነኝ እየተባለ የሚዘመረው፣ እከሌ የተባለውን ቡድን ያደራጀነው እኛ ነን፤ ተነስ ስንለው የሚነሳ ቁጭ በል ስንለው የሚቀመጥ በእኛ ትዕዛዝ ነው እየተባለ የሚነገረው ሁሉ የዚህ በሽታ ምልክት ነው፡፡ የዚህ አካባቢ ብቸኛ ወኪል እኔ ነኝ እየተባለ በግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ጥላሸት የሚቀባው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከዚህ የዜሮ ድምር አስተሳሰብ ካልተፈወሰ እና ካልዘመነ ማናችንም ነጻ እንወጣም፡፡ ለልዩነት ቦታ መስጠት፣ ኢትዮጵያ የሁሉንም ልጆቿን አስተዋጽዖ እንደምትፈልግ ከምር መቀበል፣ ይብዛም ይነስም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአገሩ አስተዋጽዖ ሊያደርግ እንደሚችል ማመን ያስፈልጋል፡፡ ዕብሪትና መታበይ የውድቀት መሠረት ነው፡፡ “Hubris Kills” ይላሉ ሮማዊያን፡፡
Filed in: Amharic