>

‹እኛ ነን እወቁን›› ብለው ፎቷቸውን የሚለጥፉ አራጆች ያሉባት ፤ እነሱንም አቅፋ-ደግፋ ሽፋን እየሰጠች  በሠላም የምታኖር ብቸኛ የዓለማችን ሀገር...!!! (አሰፋ ሀይሉ)

‹እኛ ነን እወቁን›› ብለው ፎቷቸውን የሚለጥፉ አራጆች ያሉባት ፤ እነሱንም አቅፋ-ደግፋ ሽፋን እየሰጠች  በሠላም የምታኖር ብቸኛ የዓለማችን ሀገር…!!!
አሰፋ ሀይሉ

 

መንግሥት ለህዝቡ ቆሞ ህዝብን ከወንጀል ፈጻሚዎች፣ እና ከአሸባሪዎች በሚከላከልበት በዓለም ላይ ባለ በማናቸውም ሀገር (ከኢትዮጵያ በስተቀር) በማናቸውም የፖለቲካ ምክንያት ንፁሃንን የሚያርዱ፣ የሚገድሉ፣ በንፁሃን ላይ ማናቸውንም የሽብር ተግባር የሚፈጽሙ ኃይሎች – በከፍተኛ ምሥጢር ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡ በጣት ከሚቆጠሩ መሪዎቻቸው በስተቀር በአደባባይም መልካቸውን ይዘው አይወጡም፡፡ 
 
ሌላ ቀርቶ በብዙ ሀገራት እንደልባቸው እየተሹለከለኩ መኖር የሚችሉ እንደ አይሲስና አልቃኢዳ ያሉ አክራሪ ጂሃዳዊ ቡድኖች እንኳ – የንፁሃንን አንገት ሲያርዱ በሚያሳዩባቸው ቪዲዮዎች – አራጆቹ መልካቸው እንዳይታወቅ ፊታቸውን በቡርቃ (በጨርቅ) ተሸፍነው ነው፡፡ የእንግሊዝና የአሜሪካ የሥለላ ድርጅቶች – ጂሃዲው ጆን በሚል ቅጽል የሚታወቀውን – እና ኋላ እንግሊዝ ውስጥ ያደገ እስላም መሆኑ የተረጋገጠውን – የአይሲስ አራጅ ማንነት ለማወቅ – የስንትና ስንት ወራት ድካም ነው የጠየቃቸው፡፡ ምክንያቱም በቪዲዮ እየቀረጸ አይሲስ ያገታቸውን ንጹሃን ሰዎች አንገት ሲያርድ ፊቱን ስለሚሸፍን፡፡ 
 
ይህ እንግዲህ የሚያሳየው – ህግ በሚከበርባቸው ሀገሮች – እና ለህዝቡ ደህንነት 24 ሰዓት የሚሠራ የፀጥታ ኃይል ባላቸው ሀገሮች – ንጹሃንን የሚያርዱ አሸባሪዎች – የቱንም ያህል አቅምና ዝና ቢኖራቸው – ምን ያህል ከህግ አስከባሪ አካላት ራሳቸውን ለመሰወር እንደሚጥሩ፣ ምን ያህል ዱካቸውን ላለመተው፣ መልካቸውን ላለማሳየት እንዲሚጨነቁ ነው የሚያሳየው፡፡ 
 
እኛ ሀገር ስትመጣ – እያገቱ ‹ሰልፊ› ፎቶ የሚነሱ የኦሮሞ አሸባሪዎችን ነው የምታገኘው፡፡ ቤተክርስትያን እያቃጠሉ ቪዲዮ እየቀረፁ በኦሮምኛ የሚነጋገሩ፣ ቤተክርስትያንን እያቃጠሉ መሣሪያቸውን ተሸክመው በደስታ ሲጨፍሩ በቪዲዮ ራሳቸውን ቀርጸው የሚልኩ አሸባሪዎች ናቸው እኛ ሀገር ያሉት፡፡ እኛ ሀገር ያሉት በግልጽ መንግሥት በሚቆጣጠራቸው ወረዳዎችና ዞኖች ውስጥ ገብተው፣ የፈለጉትን አርደው፣ የፈለጉትን ገድለው፣ የፈለጉትን አቃጥለው፣ ሰልፊ ፎቶ ተነስተው የሚለቁ አሸባሪዎች ናቸው ያሉት፡፡ 
 
በዓለም ላይ በታሪክ እንደ ኦሮሞ አሸባሪዎች – እንደ መንግሥት ባለሥልጣን መብቱና ጥቅሙ ተጠብቆለት ፎቶውን በአደባባይ እያስጣጣ የንጹሃንን ነፍስ ለማጥፋት፣ ለማረድ፣ ንብረት ለማውደም፣ ካህናትን ሳይቀር ለመጨፍጨፍ የደፈረ አንድም አሸባሪ አልሰማሁም፡፡ በዓለም ታሪክ እንዲህ ዓይነት እዩኝ ስሙኝ የሚል አሸባሪም፣ እዩኝ ስሙኝ የሚለውን አሸባሪ እጁን አጣጥፎ የሚመለከት መንግሥትም ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ 
 
ሌላ ቀርቶ የራሷ ማዕከላዊ መንግሥት በሌላት ሶማሊያ እንኳ አንዱ የጦር አበጋዝ በሚቆጣጠረው ክልል ውስጥ ሌላው አራጅ ገብቶ አሁን የኦሮሞዎቹ አራጆች በሚያሳዩት አይነት ዋልጌ ድፍረት ደረጃ እንደልቡ ሰውን እያረደ ሊቀጥል አይችልም በፍጹም! በመንግሥት አልባዋ በሶማሊያ እንኳ! 
 
በጦርነት ውስጥ ባለችው የመን፣ ወይ የዓለም አሸባሪዎች ከያሉበት ተሰባስበው በሚርመሰመሱባቸው ኢራቅና ሶሪያ ውስጥ – እንደዚህ ፎቷቸውን እየለቀቁ – እዩኝ እወቁልኝ ስራዬን የሚሉ አሸባሪዎች – በፍጹም አልተከሰቱም፡፡ ተደብቀው ሲያፈነዱ፣ አድፍጠው ጥቃት ሲሰነዝሩ፣ ወይም ጠፍተው ሲያጠፉ፣ ወይ ከተቆጣጠሩት አካባቢ እየተነሱ ውጊያ ሲያካሂዱ ነው እንጂ የሚታዩት – እንጂ እንዲህ እንደኛዎቹ የኦሮሞ አራጆች- መንግሥት በሚቆጣጠረው ሀገርና መንደር እየገቡ እንደፈለጋቸው አርደው ሰልፊ እየተነሱ የሚለቁበት ሽራፊ ዕድልም፣ ፍላጎትም፣ ድፍረቱም ጭምር የላቸውም፡፡ 
 
ምክንያቱም ቢታወቁማ – በስንት ምርመራና ክትትል – በየሀገራቱ የፀጥታ አካላት ብቻ ሳይሆን ፣በዓለማቀፍ የወንጀል መከላከል ተቋማት ደረጃ ነዋ የሚታደኑት፡፡ እና በህይወታቸው ላይ እንዲያ ዓይነቱን ቀልድ አይሞክሩትም፡፡ በአሁኑ ወቅት – በየትኛውም የዓለም ሀገር – ‹ክሪሚናል ፕሮፋይሊንግ› እና ‹የተማከለ የመረጃ ጥንቅር› (የወንጀለኞችን ማንነት የሚከታተል፣ የሚመዘግብና፣ የእያንዳንዳቸውን መረጃ የሚያደራጅ) ራሱን የቻለ የጸጥታ ተቋም እንደየሀገሩ ተጨባጭ ሁኔታ በስፋትና በጥራት ተደራጅቶ – በሁሉም መንግሥት ባለበት ሀገር ሁሉ ውስጥ ታትሮ ይሰራል፡፡ 
 
በእኛ ሀገር ላይ ብቻ እኮ ይመስለኛል – ቄሮንና ኦነግን፣ ሽመልስ አብዲሳንና ጃልመሮን፣ ወይ የኦነግ ሸኔን ኃይልና የኦሮሚያ ልዩ ኃይል የሚባሉትን እኮ ማንኛቸው የመንግሥት ማንኛቸው ፀረ መንግሥት እንደሆኑ በህሊና አመዛዝነህ ለመለየት እስኪሳንህ ድረስ – ባንድ ክልልና በአንድ ሀገር ውስጥ – አባራሪም ተባራሪም ሁሉም እኩል ተፈርቶ – ተደጋግፈውና ተፈቃቅረው ዘግናኝ የእርድ ተግባራቸውን ፈጽመው – የመታሰቢያ ፎቷቸውን በአደባባይ ሲለቁ – ተከባብረው በሠላምና በፍቅር ተቃቅፈው ሲኖሩ የምታገኘው፡፡ አንዳንዴ እነ ታዬ ደንደአ አቃፊ ነን የሚሉት ነገር ይሄንንስ ያጠቃልል ይሆን? ሁሉ እላለሁ በብስጭት፡፡ እንዴ? 
 
ምን ዓይነት ጊዜ ላይ ነው ያለነው? ምን እየተሠራ ነው? አራጆች ፎቷቸውን በየአደባባዩ በኩራት እየለቀቁ በግልጽ በሚፈነጩበት ሀገር ላይ እንዴት ነው ዜጎች መንግሥት አለን ብለን እጃችንን አጣጥፈን ቁጭ የምንለው? ምን እስክንሆን ድረስ ነው? የሞቃዲሾዋ ሶማሊያ ካለችበት ህግ-አልቦነት ሁኔታ የእኛ የሚለው በምኑ ነው? 
 
ኢትዮጵያውያን ሀገራችንን እንዲህ የወንበዴዎች መፈንጫ አድርገን አሳልፈን ሰጥተን በራሳችን ቤት እስኪመጣብን የማይሞቀን የማይበርደን ፍጡራን ሆነን የቀረነው ከመቼ ወዲህ ነው? በምን የተነሳ ነው? እንዴት ሀገር እንዲህ የወንበዴ መጫወቻ ሆና ንፁሃን እየታረዱ፣ ‹‹አራጆች እኛ ነን እወቁን›› እያሉ ከገዢዎቻችን እኩል ፎቷቸውን እየለቀቁ በሚኖሩባት ሀገር – መሪውን እያወደስን መኖር ቀሎን የተገኘነው? 
 
እንዴት የህሊና ደረጃችን፣ የኢትዮጵያዊነት ልካችን በዚህ ደረጃ ወርዶ ተዋርዶ ተገኘ? እጅግ እጅግ ያሳዝናል በእውነት፡፡ እንዴት ሀገራችንን ከአራጆች ጋር ተስማምተው ለሚኖሩ ለንጹሃን ህይወት ቁብ ለማይሰጣቸው ገዢዎች እንደ ፍጥርጥራቸው ብለን አሳልፈን ሰጠን? 
 
ወደድንም ጠላንም አንድ አምነን መቀበል ያለብን ነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያውያን መንግሥት አልባነትን እየተለማመድነው ነው፡፡ ግድ የሰጠን ግን አንመስልም፡፡ ምናልባት ሀገር ምድሩ ሁሉ የወንበዴዎች መፈንጫ ሆኖ፣ የያንዳንደችን ሠላማዊ ኑሮ ተናግቶ፣ እንደ ሶማሊያና ኮንጎ፣ እንደ የመንና ሶሪያ ሴቶች የምንልስ የምንቀምሰው አጥተን፣ የየቤታችንን ቴሌቪዥን እያወጣን በሽንኩርት ለመቀየር እስክንገደድ ድረስ – አንገታችንን አጎንብሰን መኖርን ብቸኛውና ዓይነተኛው የሕይወት መርህ፣ እኔ ነኝ ያለ የብልጠት ደረጃ አድርገን ቆጥረነው ይሆናል፡፡ ከሆነ ተሳስተናል፡፡ 
 
የዛሬ ኢትዮጵያውያን የተገኘንበት የዝቅታ ደረጃ ያሳዝናል በእውነት፡፡ ዛሬ ቁጭ ብለን የሰቀልነውን ነገ ቆመን ማውረድ እንደማንችል አጥተነው አይመስለኝም፡፡ ዛሬ በቸልታ የምንተወው ያገራችን መንግሥት-አልቦነት፣ ህግ-አልቦነት፣ ውንብድናና የንጹሃን እርድ – እና የፈለጉትን ያድርጉ በራሴ፣ በልጄ፣ በቤተሰቤ፣ በጓዳዬ ካልመጣ ብለን ጆሯችንንና ዓይናችንን የደፈንነው ነገራችን – ውሎ አድሮ በያንዳንዳችን ቤት ወደሚያንኳኳ በመንግሥት ወደ ተደገፈ ህጋዊ የሽብር ህይወት እንደሚዳርገን ካላሰብን ራሳችንን ደጋግመን መጠየቅ መጀመር ያለብን ሰዓት አሁን ነው፡፡ 
 
በሌሎች ሀገሮች አይደለም የሰው ነፍስ አጥፍተህ – የእንስሳት ነፍስን አላግባብ ብታጠፋ – ወንጀልንና ወንጀለኛን የሚከላከል ስንት የፀጥታ ሠራተኛ 24 ሰዓት ሙሉ ነቅቶ ይከታተላል፣ ወንጀለኛን ያሳድዳል፣ ሳይደርስ ያመክናል፣ ያመለጡትን ያሳድዳል፡፡ ሌሎች እንደኛው የሚያስብ አዕምሮና ለራሳቸው ክብር ያላቸው ህዝቦች ይህን ሲያደርጉ እያየን – እኛ እንዴት አስችሎን ተቀመጥን? በመንግሥታችን ላይ ብስጭታችንን የማንገልጸው ለምንድነው? ለህዝቡ ደህንነት የሚጨነቅና ከወንጀለኞች የሚከላከል፣ ከወንጀለኞች የሚታደገን፣ ወንጀለኞችን አሳዶ የሚይዝና የሚቀጣ መንግሥት አልፈለግንም ወይ ኢትዮጵያውያን?
 
ከቀን ወደ ቀን ባደባባይ ሰዎች እየታረዱ፣ አራጆቹም እኛ ነን እወቁልን ብለው ፎቷቸውን ባደባባይ እያስተዋወቁ፣ ዝም ብሎ የሚመለከት ‹‹መንግሥት›› ተሸክመን ለመቀጠል የመፈለግ ቁርጠኝነታችን ከምን የመነጨ ነው? ዛሬ አይተን እንዳላየን ማለፍን እንደ ትልቁ የኑሮ ብልጠት፣ እንደ ትልቅ በሠላም የመኖር ጥበብ ቆጥረነው ተቀምጠን ይሆናል፡፡ ነገ በሀገር በግለሰብ በህዝብ ደረጃ ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ አምነን ተቀበልነውም አልተቀበልነውም መንግሥት አልባነትን ጀምረነዋል፡፡ እየተለማመድነው ነው፡፡ አራጆቹ ፎቷቸውን ፊትለፊት እየለቀቁ እየነገሩን ያሉት ይህንኑ መልዕክት ነው፡፡ መንግሥት የላችሁም፣ በእኛ ቁጥጥር ሥር ናችሁ – ነው እያሉን ያሉት፡፡ 
 
‹‹እነሱ ደግመው ደጋግመው እንደሚሉት – ዓላማችን አጥፍተን እንጥፋ ነው – እና ጥያቄው እነሱ ይጥፉ ወይስ እኛ እንጥፋ ነው መሆን ያለበት – መልሱ የሚከብድ አይመስለኝም!›› ነበር ያለው ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም፡፡ አሁን ያለነው ኢትዮጵያውያን – እነሱ ይጥፉ ሳይሆን – እኛ እንጥፋ ብለን የመረጥን ነው የሚመስለው፡፡ እንግዲህ የሚጠብቀንን መንግሥት ለመፍጠርም ድፍረቱ ከሌለን፣ ራሳችንንም መጠበቅ ካልቻልን – አንድዬ እሱ ይሁነን ማለት ነው፡፡ ሌላ ምን ይባላል? 
 
የፈጣሪ ከህሊና ሽሽታችን ይመልሰን፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ከእውነት ሽሽታችን ያድነን፡፡ ከአድርባይነታችን፣ በእኔ ካልመጣ ለምን ዓለም አትጠፋም ከሚል ህመማችን፣ ጨርሶ ይማረን ፈጣሪ አምላክ፡፡ ነገን የምናስብበትን የሞራል ድፍረት ይስጠን አምላካችን፡፡ ለልጆቻችን ስንል የምንነሳበትን ልቦና ያኑርልን አምላካችን፡፡ ይህን ደጋግመን ማለት ያለብን ሰዓት ቢኖር አሁን ነው፡፡ ፈጣሪ ይታረቀን፡፡ ፈጣሪ ልቦና ይስጠን፡፡ ፈጣሪ አለሁ ይበለን፡፡ 
 
ሌላ ምን ይባላል?
Filed in: Amharic