>
4:11 pm - Thursday January 24, 7585

‹‹ሰላም ነን›› - [ በጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ]

ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ወ/ጊዮርጊስና ጦማሪ ናትናዬል ፈለቀ
*****ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ …ከጠበቃቸው ጋር ተገናኝተዋል *****

በቂሊንጦ ዞን ሶስት ታስረው የሚገኙት ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ አስማማው ወ/ጊዮርጊስና ጦማሪ ናትናዬል ፈለቀ ሙሉ ነጭ ቲሸርት ለብሰው ከጠያቂዎች ጋር የሞቀ ጨዋታ ይዘው ነበር – ዛሬ ከሰዓት በኋላ፡፡
ነጩ ቲሸርት ሰላማዊ መሆናቸውን እየገለጹ ያሉበት መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ በቅርቡ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት መሰል አለባበስ ሁሉም (ሌሎች ጓደኞቻቸውን ጨምሮ) ላይ ይታይ ነበር፡፡ ዛሬ ጠዋትም ፍርድ ቤት ቀርበው ተለወጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡

Zone 9 bloggers & Journalists 04.11.2014እነተስፋለም ስሜታቸው በጣም ተረጋቶ በተለያዩ ሚዲያ እና ሀገር ተኮር ጉዳዮችን አንስተው ከእኛ ከጠያቂዎች ጋር ሲወያዩ ደስ ይሉ ነበር፤ ምንም እንኳ እስራቸው ቢያሳዝነንም፡፡
በጨዋታቸው መካከል አስቂኝ ቀልድ ጣል ማድረግም ጀምረዋል፡፡ ለቀልዱ ልማድ እዚህ እስር ቤት ብዙ ቀልድ አዋቂዎች መኖራቸውን በምክንያትነት ያነሳሉ፡፡ ሦስቱም አብረው በአንድ ዞን መታሰራቸው ይበልጥ ወንድማማችነታቸውን እንዳጠናከረው በአንክሮ የተመለከታቸው በቃላሉ ይረዳል፡፡ ስለታሰሩበት ጉዳይ ከማንሳት ይልቅ በሀገሪቷ ላይ እየተደረጉ ያሉ ነገሮችን ይበልጥ ለማወቅ ከመሻታቸው የተነሳ ጥያቄ ወዲያው ወዲያው ይጠይቃሉ፡፡ ባላቸው መረጃ ላይ ተንርሰውም ተጨማሪ መረጃ በትኩረት ይጠይቃሉ፡፡ (የተስፋለም ጽሑፍን ብቻ ሳይሆን ቃላትንም ኤዲት የማድረግ ልምዱ አሁንም አብሮት አለ፡፡) አሁንም በሀገራቸው ጉዳይ ያገበናል ባይነታቸው እንዳለ መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡ የጋዜጠኝነት ሙያ ፍቅር እና ውስጣዊ ልክፍት እስር እንደማይገታውም ላውቅ ችያለሁ፡፡ ባለፈው ሳምንት ዓርብ ዕለት ከወዳጄ አቤል አለማየሁ ጋር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን (ወደዝዋይ ከመዘዋዘሩ አንድ ቀን ቀደም ብሎ)፣ ጦማሪያን አቤል ዋበላ እና ዘላለም ክብረትን በዚሁ ቂሊንጦ እስር ቤት ዞን አንድ በጠየቅናቸው ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነበረው፡፡ በዚህም የሀሳብ ልውውጡ ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር በተያያዘ እና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ ነበር፡፡
ዛሬም በዞን ሁለት ተገኝቶ ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉንና ጦማሪ አጥናፍ ብርሃኔን መጠየቅ የቻለው ወዳጄ እዩኤል ፍስሐ፣ መሰል ውይይት እንደገጠመው አጫውቶኛል፡፡
…..ሰሞኑን በሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ከአራት ወራት የማዕከላዊ እስር በኋላ ወደቂሊንጦ እስር ቤት የተዘዋዘሩት የአንድነት ፓርቲዎቹ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ እንዲሁም ከሰማያዊ ፓርቲ አቶ የሺዋስ አሰፋና ከአረና ፓርቲ አብርሐ ደስታ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በዚሁ እስር ቤት ከጠበቃቸው ጋር ተገናኝተው በክሱ ጉዳይ ላይ መነጋገራቸውን ማወቅ ችያለሁ፡፡
ሀብታሙ እና የሺዋስ በዞን ሦስት ከእነ ተስፋለም ጋር ሲሆኑ አብርሃ ደስታ ከበፍቄ እና አጥናፍ ጋር፣ እንዲሁም ዳንኤል ሺበሺ በዞን አንድ ከዝነ ዘላለም ክብረት ጋር ይገኛሉ፡፡
በመጨረሻም እነተስፋለም ‹‹ሰላም ነን›› የሚል ሰላማዊ ቃላቸውን ከነገሩኝ በኋላ ‹‹ቻው አይዟችሁ!›› ብዬ ተለይቻቸዋለሁ፡፡
ፈጣሪ ብርታትና ጥንካሬ ይስጣቸው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Filed in: Amharic