>

ʺአጤ ምኒልክ አሰመራት ሐብትና ፍቅርንም ተጓዘባት...!!!" (በታርቆ ክንዴ) 

ʺአጤ ምኒልክ አሰመራት ሐብትና ፍቅርንም ተጓዘባት…!!!”

በታርቆ ክንዴ 

 

*…. ምኒልክ ትናንት ነገሠ፣ ዛሬን አስቀድሞ ቀየሰ፣ ነገን አሻግሮ በጥበብ አለሰለሰ፡፡ ምኒልክ  ይመራል፣ ያሻግራል፣ ጥበበኛ ነውና በጥበብ ያኖራል፡፡ ሠርቶ ያኮራል፣ ተዋግቶ ሀገር ያስከብራል፣ ምኒልክ አንደበቱ ለፍቅር፣ ክንዱ ለክብር የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በጀግንነት የታወቀ፣ በጥበብ የረቀቀ፣ በመሪነት የተደነቀ፣ በግርማው ልብ የሚሰርቅ፣ በቁጣው መሬት ጋር የሚደባልቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን እንደ እናት እምዬ፣ እንደ አባትም አባየ ይሉታል፡፡ የጥቁር ዘመን ጨለማ በነበረበት፣ ነጭ ብቻ የምድር ገዢ በመሰለበት በዚያ አስቸጋሪ ዘመን ተገኘ፡፡ የሰው ልጅ የተገኘባት ኢትዮጵያ የሰው ልጅ እኩል ይሆንባት ዘንድ በተስፋ እየተጠበቀች ነበር፡፡ የኃያላኑን ክብር  የሚገረስስ፣ የጥቁሮቹን ማዕረግ የሚመልስ፣ በጥበብ የሚገሰግስ ታላቅ መሪ ይፈለግ ነበር፡፡ ጥቁሮች የተገኙባት አፍሪካ በወራሪዎች ተይዛለች፡፡ ተስፋና ምስክር የሆነችው ኢትዮጵያ ብቻ ቀርታለች፡፡ በተስፋዋ ምድርም ታላቁ ሰው ተገኘ፡፡ ዘመን ጠብቆ በክብር ተቀባ፡፡ በግርማም ነገሠ፡፡
ታላቅ ሀገር ይመራ ዘንድ ፈጣሪው መርጦታልና ታላቅ ነገርን ያደርግ ዘንድ ወደደ፡፡ ያለ መታከት ይሠራ ጀመር፡፡ ተቆጭ ያጡት ኃያላኑ ተስፋ የተጣለባትን ምድር በግፍ ረገጡ፡፡ ለቀኝ ግዛት ባሕር አቋርጠው መጡ፡፡ አባ ዳኘው አፈረ፤ አዋጅ አስነገረ፣ ፈረሱ ወደ ጣለት ግንባር ሰገረ፡፡ በዓድዋ ተራራዎች ላይም ተገናኘ፡፡ ኃያለኑ ተገረሰሱ፣ ጥቁሮች ከወደቁበት ተነሱ፡፡ በምሥራቅ የተገኘችው ሚስጥራዊት ሀገር እኩል የምታበራ ፀሐይ ወጣባት፡፡ ዓለም ሁሉ ተደነቀባት፣ አከበራት፤  ምኒልክ የሀገሩን ሥም ከዓድዋ ተራራዎች አናት ላይ ከፍ አድርጎ ፃፈው፡፡ የዓለም ሕዝብም አሻግሮ አነበበው፡፡
የጦር ሜዳውን ፍልሚያ በድል እንደጨረሰ ወደ ልማት ተመለሰ፡፡ አዳዲስ ጥበቦች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ይሻ ነበርና  የጥበብ በሮችን ማንኳኳት ጀመረ፡፡ ምኒልክ በዘመኑ ከሠራው ሥራ አንደኛው ባቡር ነው፡፡ የባቡር ሀዲድ ሥራውን ሀሳብ የወጠነው የሸዋ ንጉሥ በነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ ታዲያ ለመተግበር ጊዜ ያስፈልገው ነበርና ጊዜ እስኪደርስ ዘገየ፡፡ ጊዜው ደርሶ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ሆነ፡፡ የቀደመ ሀሳቡም ተንቀሳቀሰ፡፡ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት እንደሆነ ስለ ባቡር ጉዳይ ያነጋግርለት ዘንድ ሙሴ ሳቡሬን ወደ ፈረንሳይ ላከው፡፡ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ሙሴ ካርኔ ጋር እንዲነጋር፡፡
አውሮፓውያኑ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ የሚያስቡበት ዘመን ስለነበር የምኒልክ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ አላገኘም፡፡ ምንልክ ከፈርንሳይ መንግሥት የሚጠብቀው መልስ እየዘገየ በመሄዱ ለአማካሪው ሙሴ አልፍሬድ ኢልግ ከማንኛውም ድርጅት ጋር ተዋውሎ ሀዲዱን ለማሠራት የሚችልበትን ፈቃድና የሚዋዋልበትን የውል ዓይነት በማኅተም አትሞ ሰጠው፡፡
ስለሀዲድ መዘርጋት የሚያነጋግሯቸው ከበርቴዎች ሁሉ ʺየባቡር መስመር ቢዘረጋ ምን ጥቅም ይገኝበታል?” የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው የጥናት ውጤት ቀረበ፡፡ የጥናቱ ውጤትም ሀብቷ ባልተነካባት ድንግል ምድር ገብቶ ሥራ መጀመር አትራፊ እንደሚያደርግ ስላመላከተ ከበርቴዎቹ ተደሰቱ፡፡ ስለ ሀዲዱ መዘርጋት መልካም እንቅስቃሴ እንደነበር የዓድዋ ጦርነት ተነሳና ጉዳዩ ተቋረጠ፡፡ የእንግሊዝ መንግሥት የፈረንሳይን መንግሥት ለኢትዮጵያ የባቡር ሀዲድ መዘርጋት ፈቃድ እንዳይሰጥ አስጠንቅቆ ነበር፡፡  ሁለቱ ሀገራትም የምኒልክን እና የኢትዮጵያን ጥያቄ ወደ ጎን ትተው ስለራሳቸው ጥቅም ይዶልቱ ጀመር፡፡ የኢጣሊያንን ጥጋብ በዓድዋ አበረደው፡፡ በዓድዋው ድል የእንግሊዝና የፈርንሳይ መንግሥታትም ተደናገጡ፡፡
ከዓድዋው ድል መልስ ምኒልክ ጥያቄውን በድጋሜ አቀረበ፡፡ በኢጣሊያ ሽንፈት የተማረው የፈርንሳይ መንግሥት ጥያቄውን ለመመለስ ይሁንታውን ገለጠ፡፡ ከጅቡቲ ኢትዮጵያ የባቡር መሥመር ቢዘረጋ የሚስማማ መሆኑንም አስታወቀ፡፡ ይህ መሥመር የእንግሊዝን ጥቅም የሚነካ ነበርና የእንግሊዝ መንግሥት ተቃውሞውን አሰማ፡፡
ምኒልክ በዚህ ጊዜ ወዳጅ ለነበሩ ፈረንጆች ʺ…. ድሮም ኢጣሊያኖች አውከውኝ  ያው እንደሰማችሁት ዓድዋ ላይ ተገላገልን፣ አሁን ደግሞ እንግሊዞች አገሬ እንዳትሰለጥን የሚያደናቅፉኝ ከሆነ ሌላ የማደርገው ስለሌለኝ እንደ ዓድዋው ነው ማድረግ ያለብኝ፡፡ ፈረንሳዮችም ዘመዶቻቸውን እየደገፉ እኔን ባዕድ አድርገው ከጠሉኝ ላገሬ ስል ከእነርሱም ጋር እገጥማለሁ፡፡  ይህን ነገር እንዲያስቡበት እንደሚሆን አድርጉ፡፡.. ለየሰዎቻችሁም ንገሩ” አለ፡፡ የምኒልክ ንግግር አውሮፓውያን ጀሮ ዘንድ ደረሰ፡፡ የፈረንሳይ መንግሥትም ኢትዮጵያ የምትጠይቀውን ሁሉ በወዳጅነት እንደሚፈፅም ተናገረ፡፡
ችግሮቹ ታልፈው  በኅዳር 22/በ1890 ዓ.ም የባቡር ሃዲድ ዝርጋታው  በጅቡቲ ተጀመረ፡፡   የመጀመሪያው የባቡር ሀዲድ ሥራም ሐምሌ 15/1893 ዓ.ም ደወሌ ኢትዮጵያ ደረሰ፡፡ የባቡር ሀዲድ ዝርጋታው አያሌ ፈተናዎች ነበሩበት፡፡ በምኒልክ ጥበብ ችግሮቹ እየታለፉ ሥራው ቀጠለ፡፡ በታኅሣሥ 14/በ1895 ዓ.ም ድሬዳዋ ገባ፡፡ ድሬዳዋ በወረሃ ጥር ማለቂያ በ1890 ዓ.ም ነበር የተመሰረተችው፡፡ የሀገሬው ሰው ባየው ነገር ይገረም ጀመር፡፡ በግመልና በፈረስ የነበረው የበረሃ ጉዞ በአንድ ቀን ይደረስ ጀመር፡፡ ምን አይነት ንጉሥ  መጣ እየተባለ አድናቆቱ ከፍ እያለ መጣ፡፡ ምኒልክ ከጅቡቲ ድሬዳዋ በሚደርሰው የባቡር ሀዲድ ብቻ ረክቶ አልተቀመጠም፡፡ ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት ሀሳብ ወጠነ፡፡ በጥር 21/1900 ዓ.ም ተፈራረመ፡፡ ሥራውም ጀመረ፡፡ ማለፍ አይቀርም የማለፍ ዘመን መጣ፡፡  ምኒልክ በባቡሩ አዲስ አበባ መግባቱን ሳያይ አለፈ፡፡ የመጀመሪያው ባቡርም በ1909 ዓ.ም አዲስ አበባ ገባ፡፡
ምኒልክ ካሰመራት የፍቅር ዥረት ከፈሰሰባት ከተማ ድሬዳዋ ሄጄ ነበር፡፡ ባቡር ለድሬዳዋ ሀብት፣ በረከት፣ ፍፁም ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት፣ ሥራ ወዳድነት የሰጣት ወላጇ ነው፡፡ ድሬዳዋ ያለ ባቡር አትደምቅም፡፡ ከመቶ ዓመታት በላይ ባቡርን ያየችው ድሬዳዋ ዘመን ገፍቷት፣ የስልጣኔዋ መነሻ ባቡር ተዳክሞባት የቆዘመች ትመስላለች፡፡ በየጊዜው በባቡር የሚሄዱ ኢትዮጵያዊያን ናፍቆት የጎዳት ትመስላለች፡፡
ድሬዳዋ እምዬን የናፈቀች ትመስላለች፡፡ ባለውለታዋ ነውና ታስበዋለች፡፡ ከድሬ አዲስ አበባ በባቡር የሚሄዱበት የቀደመው መስመር ናፍቋቸዋል፡፡ ምኒልክ ባሰመረው መስመር ቡዙዎች ተጓዙበት፣ ሀብት አፈሩበት፣ ፍቅር ሸመቱበት፣ ዘመናዊነትን ኖሩበት፡፡ አሁን ግን የምኒልክ መስመር በረጅ መጓዝ አቁሟል ለምን እና እንዴት?  የሚለውን በቀጣይ ይዤ እመለሳሁ፡፡ ድሬዳዋንም በጋራ እንቃኛታለን እስኪዚያው ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡
ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክን በምንጭነት ተጠቅሜያለሁ፡፡ 
Filed in: Amharic