>
5:13 pm - Thursday April 19, 1984

"አዲስ አበባ ላይ በርግጠኛነት የምናሸንፈው እኛ ነን!!!" (አቶ ገለታው ዘለቀ /የባልደራስ ፓርቲ የጽ/ቤት ኃላፊ)

“አዲስ አበባ ላይ በርግጠኛነት የምናሸንፈው እኛ ነን!!!”

አቶ ገለታው ዘለቀ /የባልደራስ ፓርቲ የጽ/ቤት ኃላፊ

 

የባልደራስ አጠቃላይ የምርጫ ዝግጅት ምን ይመስላል?
ባልደራስ ወደ ምርጫ ለመግባት ጥሩ ቁመና ላይ ነው ያለው፡፡ ጥሩ የሚባል የተብራራ ማንፌስቶ አዘጋጅተናል፡፡ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የተማሩ እና መልካም ሥነ-ምግባር ያላቸውን በቂ እጩዎችንም አዘጋጅተናል፡፡
በአዲስ አበባ ምን ያህል እጩዎችን ለከተማው መስተዳድር እና ለፓርላማው ታቀርባላችሁ?
በከተማው መስተዳድርም ሆነ በፓርላማው መቀመጫ ቁጥር ልክ እጩዎችን አዘጋጅተናል፡፡
የባልደራስ ዋነኛ አጀንዳዎች ምን ላይ ያጠነጥናሉ?
አንደኛው የአዲስ አበባ የመዋቅር ችግርን መፍታት ነው፡፡ ይኸውም በኢኮኖሚው ትልቅ አበርክቶ ያላት አዲስ አበባ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ቀመር በሚቀመርበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምንም ቦታ እንዳይኖራት ሆን ተብሎ እንደ አነስተኛ ከተማ እንድትታይ ነው የተበየነባት፡፡ እናም በምርጫው አሸንፈን እነዚህን ሁሉ እንዲስተካከሉ እናደርጋለን፡፡ በጥቅሉም ባልደራስ አዲስ አበባን ማዳን ኢትዮጵያን ማዳን ነው ብሎ ያምናል፡፡
ሌላው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የምንሰጠው ትኩረት ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው የመልካም አስተዳደር እጦት አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቱ ዘመኑን የሚመጥን የልማት አውታር እንዳይዘረጋ ዋነኛ እንቅፋት ሆኗል፡፡ ይህንን ለመቀየር ከሕዝባችን ጋር አበክረን እንሰራለን፡፡
ባልደራስ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ አበባ ላይ የሚያነሳውን ልዩ ጥቅምንም ሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ፍፁማዊ የባለቤትነት ጥያቄ የተቀየረውን አጀንዳ እንዴት ያየዋል?
በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ብሎ የሚነሳ የአንድ ቡድን የባቤትነት ጥያቄ አገር አፍራሽ ከመሆኑም በዘለለ በከተማይቷ ለሚኖረው ሰፊው ማህበረሰብ ክብር የማይሰጥ በጣም ስስታም እና ስግብግብ የሆነ አስተሳሰብ ነው፡፡
አዲስ አበባ የእኛ የኢትዮጵያውያን የጋራ ቤታችን ናት፡፡ ሁላችንም በጋራ እና በእኩልነት ልንኖርባት ይገባል፡፡ ስለዚህም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ አበባ ላይ በተናጠል የሚያሳየውን ልዩ ጥቅምንም ሆነ ወደ ፍፁማዊ ባቤትነት ያሸጋገረውን ፖለቲካ ምርጫውን በማሸነፍ ሙሉ በሙሉ እናመክነዋለን፡፡
የአዲስ አበባን ሕዝብ እንወክላለን ከማለታችሁ አኳያ ምርጫውን የምታሸንፉ ይመስላችኋል?
በሰራነው ጥናት እና በሄድንባቸው ክፍለ ከተማዎች እና ወረዳዎች በሙሉ ድጋፍ የነበረው ድጋፍ የሚያሳየን አዲስ አበባ እና ባልደራስ ሳይነጣጠሉ መዋህዳቸውን ነው፡፡ ባልደራስ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የአዲስ አበባን ብሶት በሰማው ልክ በማስተጋቦት እና የመታገያ አጀንዳ በማድረግ ሁሉንም ነዋሪ በእኩል ለማገልገል የገባውን ቃል እያከበረ ነው፡፡ ሕዝቡም ችግሬን ይፈታልኛል ብሎ የሚተማመንበት ፓርቲ እንደሆነ በተለያየ መንገድ ገልጾልናል፡፡
ከአብን ጋር የመሰረታችሁት ጥምረት በምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? በዋናነት ያጣመራችሁ ጉዳይ ምን ምንን ያካትታል?
ከአብን ጋር ብቻ ሳይሆን ከብዙ ብሔራዊም ሕብረ-ብሔራዊም ከሆኑ ፓርቲዎች ጋር ስምምነት ለማድረግ እየተወያየ ነው፡፡ ከአብን ጋር ያስማማን ዋነው የአዲስ አበባ የጋራ ቤትነት በተጨማሪ የብሔር ፖለቲካ በጋራ ቃልኪዳን እንዲፈርስ የመጀመሪያ ፈራሚዎች ነን የሚለው ነው፡፡ ጥምረቱ ያለበትን ደረጃ በተመለከተ በቅርብ ጋዜጣዊ መግለጫ ስለምንሰጥ እዛ ላይ በዝርዝር ይገለፃል፡፡
አዲስ አበባ ላይ እናንተን የሚገዳደረው ብልጽግና ነው ወይስ ኢዜማ?
እየተመፃደቅን ሳይሆን የህብረተሰቡን ስሜት ስናጠና አዲስ አበባ ላይ በእርግጠኛነት የምናሸንፈው እኛ  ነን፡፡ እዚህ መደምደሚያ ላይ  የደረስነው ሕዝቡ ባልደራስ ተስፋችን ነው የሚል አቋምና ስሜት እንዳለው በተለያየ መንገድ መግለፁን ገምግመን ነው፡፡
በኢትየጵያ ፍትሃዊ ሰላማዊ እና ነፃ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችሉ  ጠን ካራ የዴሞክራሲ ተቋማት አሉ ብላችሁ ታምናላችሁ?
አሁንም ቢሆን የመንግስት እና የፖርቲ መነጣጠልን እያየን አይደለም፡፡ ይሄ ደግሞ በምርጫው ላይ ተፅዕኖ ማምጣቱ አይቀሬ እንደሆነ ሁሉም ሰው የሚረዳው ነው፡፡ ፓርቲያችን ላይ የሚደረገው ጫናም ይህንን አያሳይም፡፡ ለምሳሌ የሱዳንን ወረራ የአንድ ብሔር የበላይነት መምጣትን የእነ እስክንድር ጉዳይን እና በመተከል የሚደርሰውን የዜጎች እልቂት በተመለከተ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ለጠየቅነው ጥያቄ የሰጡን መልስ የብልጽግናን አቋም የያዘ ነው፡፡ እናም እነዚህ ሁነቶች የከንቲባው ጽ/ቤት እና የብልጽግና ቢሮ የተለያዩ እንዳልሆኑ ያስረዳሉ፡፡
ለምርጫው በቂ ታዛቢዎች አዘጋጅታችኋል?
በቂ ታዛቢ ለመመደብ አየሰራን በመሆኑ በእርግጠኛነት እናዘጋጃለን፡፡
በምርጫው በብቃት ለመወዳደር የሚያችል የኢኮኖሚ አቅም አላችሁ ምንጫችሁስ ከየት ነው?
የባልደራስ አቅም በአገር ውስጥና በውጭ አገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡  እናም እነሱን ይዘን የማንሻገረው ወንዝ እና የማንወጣው ተራራ የለም፡፡
——
/
ከፍትሕ መጽሔት ጋር የነበራቸው ቆይታ /ቃለ-መጠይቅ
Filed in: Amharic