>

የትግራይ ህዝብ የስቃይ ምክንያቶች ሁሉ ከጉያው ተፈልፍለው "እንታገልልሃለን" እያሉ በስሙ ከሚምሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች  የመነጩ ናቸው ሰዒድ ደመቀ

የትግራይ ህዝብ የስቃይ ምክንያቶች ሁሉ ከጉያው ተፈልፍለው “እንታገልልሃለን” እያሉ በስሙ ከሚምሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች  የመነጩ ናቸው
ሰዒድ ደመቀ

በዘረኛ የፖለቲካ ቅኝት ዳንኪራ ደንክሮ እያስደነከረ የትግራይን ህዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ህብረ ሪትም ያስፈነገጠ ቡድን እንደ ህወሃት ያለ ማንም የለም፡፡
የዘረኝነት ጦሱ  የማታ ማታ “ታግዬ ነጻ አወጣሃለሁ” ሲል ላታለለው ምስኪን ህዝብም ተረፈ፡፡የአማራን ህዝብ ከገዛ መሬቱ እና ርስቱ በማሰደድ ሚሊዮኖችን አፈናቀለ፡፡
በዘር ማጽዳት ጭፍጨፋ ተከታታይ ዘመቻዎች በጅምላ እየገደለ ሲቀብር የኖረው ህወሃት በስተመጨረሻም የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊትን በጅምላ መግደል የክህደቱን ጫፍ አሳየ፡፡
ለዚህ ወንጀሉ አጸፋ በተሠጠው የኃይል እርምጃ ጎሮሮው ተበጠሠ፤ እሱ በመዘዘው ሠይፍ የራሱ አንገት ተበጠሰበት፡፡ ከአማራ ገበሬዎች በኃይል የወሰዳቸው መሬቶች እና በባርነት ወለል ላይ አንጥፎ ሲጨቁናቸው የነበሩት አማራዎችም  ነጻ ወጡ፡፡
ይሁን እንጂ ትላንት ህወሃት በአማራ ህዝብ እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ እና የሀገር ክህደት ወንጀል ለማውገዝ አንደበታቸው ዱዳ የሆነባቸው የባይቶና እና የአረና አመራሮች ቅንጣት ታክል ሐፍረት ሳይሰማቸው ፤ ነጻ የወጡትን የአማራ ገበሬዎች ለዳግም ባርነት ተላልፈው ካልተሠጡን እያሉ ዱብ እንቅ ማለት ጀምረዋል፡፡
ፓርቲዎቹ፡- ይባስ ብለው በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ ቀውስ ከሌሎቹ ክልሎች ውስጥ ከተፈጠሩት ቀውሶች የበለጠ አሳሳቢ እንደሆነ በማጓጓን ፤ ግድያ፣ ዘረፋ በሴቶች ላይ የደረሰው ወሲባዊ ጥቃት፣ መፈናቀል እና ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የግዝፈታቸውን ያህል አልተነገሩም እያሉ በሐሰተኛ ወሬዎች የሀገር ገፅታን ማጠልሸት የሙሉ ግዜ ስራቸው ሆኗል፡፡
በህወሀት ቁምጣ ውስጥ ገብተው በአማራ ክልል የተያዙ አካባቢዎች ሕገ መንግስቱን ተከትሎ መቋጫ እስኪበጅለት ድረስ በትግራይ ክልል መስተዳደር ስር ሊቆዩ ይገባል አይናቸውን በጨው አጥበው ጠይቀዋል።
በህወሀት ጫማ ላይ የቆሙት እነዚህ ፓርቲዎች የስም እንጂ የግብር ለውጥ የሌላቸው መሆናቸውን ተግባራቸው ገልጦታል፡፡
ህወሃት ጥሎት ከሄደው ጦስ በቅጡ ያላገገመውን የትግራይን ህዝብ ከድጡ ወደ ማጡ ለመክተት በህወሃት የዘር ፖለቲካ ቅኝት በአዲስ ጥርስ መደንከር ጀምረዋል፡፡ ዜማቸውም መሬት….መሬት … የሚል ብቻ ሆኗል፡፡
ይህን በአልጠግብ ባይ አዛውንቶች ደራሲዎች ተደርሶ በማያድጉ ቅርብ ወራጅ የባይቶና እና የአረና ተወካይ አቀንቃኞች እየተዜመ የሚገኘውን “የመሬት ይመለሥልኝ ነጠላ ዜማ ” በአንክሮ ያደመጠው የአማራ ክልል መንግሥት፤ በክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ አማካይነት “ከዚህ ቀደም በሕወሓት ቡድን በግዳጅ የተያዙና ነፃነታቸውን የተቀሙ ነዋሪዎችን  ነጻ አወጣን እንጂ ከትግራይ ክልል የወረርነው መሬት የለም ” ሲል ምላሽ ሠጥቷቸዋል፡፡
ሀቁም .ይሄው ነው!
Filed in: Amharic