>

ኦነግን እንደግብ ማስፈጸሚያ?  ሙሉአለም ገ.መድህን

ኦነግን እንደግብ ማስፈጸሚያ? 

ሙሉአለም ገ.መድህን

ልክ የዛሬ ዓመት (የካቲት/2012) የኦሮሚያ ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር ግርማ ገላን “ኦነግ ጫካ ካለው ሸኔ ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት አለው” ብለውን ነበር። 
 
ማገናዘቢያ
 
ይህ በኮሚሽነር ደረጃ የተነገረ ንግግር ነው። ኦነግ ደግሞ በ”ፓርቲ-ፖለቲካ” ህጋዊ ዕውቅና ተሰጥቶት አዲስ አበባ ጉለሌ ላይ ቢሮ ከፍቶ የሚንቀሳቀስ የ”ፖለቲካ” ድርጅት ነው። 
 
በኮሚሽነር ደረጃ እንደዚህ አይነት የአደባባይ ክስ ከቀረበበት በኋላም የኦነግ አመራሮች [በወለጋ፣ ጉጅና ቦረና ዞኖች ከሚንቀሳቀሰው የ ‘ሸኔ’ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተደረሰባቸው] በህግ ደረጃ ተጠያቂ ሲሆኑ አልታየም። ልብ አድርጉ ም/ኮሚሽነር ግርማ ገላን “ኦነግ ጫካ ካለው ሸኔ ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነት አለው” ካሉ በኋላ ከየካቲት እስከ የካቲት በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በማንነታቸው ተጨፍጭፈዋል። ለአብነት ባለፈው ጥቅምት አጋማሽ ላይ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ‘ጋዋ ቃንቃ’ በተባለ አካባቢ ‘ለስብሰባ ትፈለጋላችሁ’ ተብለው ከሁለት መቶ በላይ አማሮች በአንድ ጊዜ መጨፍጨፋቸው ይታወሳል። በወቅቱ መንግሥት 120 ብሎ ቢያምንም ቁጥሩ ከዚያ የሚሻገር ነበር፤ ከዚያ በኋላ በተከታታይ አማራ ተኮር ጥቃቶች ተፈጽመዋል። በሰሞነኛው (የካቲት 28-29) ጥቃት ብቻ ከሃምሳ በላይ ንጹሃን አማሮች ማንነታቸው ወንጀል ሆኖ ተገድለዋል። በዚህ ግድያ ህጻናት ጭምር ሰለባ ሆነዋል። 
 
ልብ አድርጉ! ‘ኦነግ ጫካ ካለው ሸኔ ሚስጥራዊ ግንኙነት አለው ያሉን የፖሊስ አመራሮች’ ዛሬም የስራ ኃላፊነት ላይ ናቸው። የኦነግ አመራሮችም አዲስ አበባ ውስጥ ይገኛሉ። ተጠያቂነት የለም! የአማራው ጭፍጨፋ ግን እንደቀጠለ ነው።  
 
በሌላ በኩል፣ እንደ አሜባ መበጣጠስ የታሪኩ አካል የሆነው [የዳውድ ኢብሳው] ኦነግ የውስጥ ክፍፍል ገጥሞታል። የኦነጉ ቃል-አቀባይ ቀጀላ መርዳሳ ከፍትሕ መጽሔት – Feteh Magazine  ጋር በነበረው ቆይታ  ሊቀመንበሩን ከማብጠልጠል አልፎ ክስ አቅርቦበታል። 
 
“ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላችሁ ይነገራል። እርስዎ ይቀበሉታል?” ተብሎ ሲጠየቅ፦ “ሊቀመንበሩ [ዳውድ ኢብሳ] ግልጽ የሆነ አቋም ካለመውሰዳቸውም በዘለለ፣ እዚህ እና እዚያ እየረገጡ የተደበላለቀ አካሄድን በምረጣቸው ነው” ሲል የዳውድ ኢብሳን ሚና ገልፆል። ‘እዚህ እና እዚያ መርገጥ’ ትርጉሙ ግልጽ ነው፤ ፖለቲካና የትጥቅ ትግልን ያጣቀሰ የኢህአፓ_ኢህአሠ ሞዴል እየተከተለ ነው ስለመሆኑ እየነገረን ነው። 
 
ለወትሮው በየወንዙ መማማል የማይሰለቸው ኦነጋዊ ኃይል፤ ዛሬ ደግሞ በየአደባባዮ በመካሰስ ላይ ነው። ይህኛው ክስ የሚለየው መስዋዕትነታቸው በሺህዎች ለደረሰው የአማራ ልጆች መቀጠፍ ምክንያት የሆነ መሆኑ ነው። ዳውድ ኢብሳ ጫካ ካለው ኃይል ጋር ግንኙነት አለው እየተባለ [በገዛ ጓዶቹ] እየተመሰከረበት፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ስም ባይጠቅሱም፦ ኦነግ [አመራሩ] ጫካ ካለው ኃይል ጋር ግንኙነት እንዳለው በአደባባይ እየከሰሱ በሕግ ደረጃ ተጠያቂ ማድረግ አልተቻለም። 
 
ለምን? 
 
ችግሩ ያለው የፖለቲካ አመራሩ ተጻራሪና ተጠፋፊነት ያለው የፖለቲካ ግብ ማስቀመጡ ላይ ነው።  የኦሮሞ ብልጽግና አመራር በዋናነት ክልሉን የሚመራው ኃይል አማራን ከክልሉ ማጽዳት እንደ ግብ አስቀምጧል። በአደባባይ ክስ እያሰማ በተግባር የሕግ ተጠያቂነትን የማያሰፍነው ኦነግ ሸኔ የግብ ማስፈጸሚያ መሳሪያው በመሆኑ ነው። 
 
በዘንድሮ ምርጫ ዳውድ ኢብሳና አጋሮቹ፣ በውስጠ-ፓርቲ ችግራቸው የተነሳ ከምርጫ ቦርድ ጋር ከገቡበት ችግር ጋር በተያያዘ የምርጫ ተፎካካሪ አይሆኑም፤ ያላቸው ዕድል ቀድሞውን ግንኙነት ከፈጠሩት የጫካ ኃይላቸው ጋር ሆነው የወለጋ ዞኖች ውስጥ በአማራው ላይ ጥቃት በማድረስ በቀውስ ውስጥ ዓላማቸውን ማስፈጸም ይፈልጋሉ።  
 
ይህ አማራን ዒላማ ያደረገ  ‘መንግሥትን የማስጨነቅ ሽብር ተኮር ጥቃት’ ፣ ክልሉን የሚመራው ኃይል እንደዕድል ቆጥሮታል። አማራን ከክልሉ ማጽዳት እንደ ግብ ያስቀመጠው ኃይል በወለጋ ዞኖች እየተፈጸመ ያለው አማራ ተኮር ጥቃት እንደመንግሥት ኃላፊነት ወስዶ ሊሰማው [የሕግ የበላይነትን ሊያስከብር] አይችልም። ስለሆነም ለነ አክቲቪስት ሽመልስ አብዲሳ ኦነግ ሸኔ የግብ ማስፈጸሚያ መሳሪያቸው ነው ብንል አልተሳሳትንም። በኦነግ መካከል ድንበር እንደሌለው ሁሉ፤ በኦነግና ክልሉን በሚመራው ኃይል መካከል የግብ ልዩነት የለም። ሁለቱም የአማራውን መጠቃት እንደ ግብ ማስፈጸሚያ ይጠቀሙበታል። 
 
አንድ ለመንገድ
 
ሦስተኛ ዓመቱን ባስቆጠረው የወለጋው የሽምቅ ውጊያ [አንዳንዴም መደበኛ ጦርነት] የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ አዛውንቶችን፣ ምሁራንን…ያስመረረ ሰብዓዊ ቀውስ ተፈጥሯል። ቅራኔው በመዋቅር ለውጥ እንጅ ከዚህ በመለስ አግባብ የሚፈታ አይመስልም። ከእንግዲህ ወለጋ ከቋንቋ ተዛምዶ ውጭ የሰልፍ ልዩነቱ ጎልቶ መውጣቱ አይቀሬ ነው። አማራን ያጸዳልናል ተብሎ ተፈትቶ የተለቀቀው ኃይል ለገዛ ማህበረሰቡ ስጋት ሆኖ ተገንቷል። የክልሉ መንግሥት ዳተኝነትም backfire አድርጎበታል። ሕዝብ ምሬት ውስጥ ገብቷል። አደጋው ለራሱ ለክልሉ መንግሥትም ነው። 
 
ወለጋ ‘ራሴን ችዬ ክልል ልሁን’ የሚልበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ወትሮም በአርሲ ይሁን በሐረርጌ የፖለቲካ ሙቀት የማይተኩስና የማይግል የራሱ ስሜት ያለው ነው። ዛሬ ቅራኔ ተጨምሮበት ያ የኖረ የኩምሳ ሞረዳ ሥነ-ልቦና ራሴን ልቻል ማለቱ ይጠበቃል። ከምንም በላይ መካነየሱስን አትርሱ! የዘንድሮ ፖለቲካ ዩኒቨርሲቲና ቤተ-እምነቶች ውስጥ እንደሚቦካ መርሳት ያስገምታልና!! 
 
መፍትሔ አለ?
 
የፖለቲካ አመራሩ ከሌሎች የማንነት ቡድኖች ጋር በተያያዘ ተጻራሪና ተጠፋፊነት ያለውን የፖለቲካ ግቡን አራግፎ ሊጥል ይገባዋል። ”ኦሮሚያን ቢያን ኬኛ! ኬሱማን ገቀልባ” (ኦሮሚያ የኛ ነች! መጤው ይውጣልን) የሚለው Nazism የፖለቲካ እሳቤ እናንተኑ መልሶ እንደሚበላችሁ አትጠራጠሩ። ክልሉ የመንግስትን መዋቅር እንዴትም መቆጣጠር የግድ በሚላቸው ጽንፈኛ የሃይማኖት ቡድኖች የሚጎተት አልፎም Salafi jihadi insurgencies, ሲፈትኑት እንደኖሩ ይታወቃል። 
 
ኦሮሞ ብቻውን ሊቆም እንደማይችል ወለጋ፣ አርሲ፣ ባሌና ሐረርጌ የታዩ አንጃዎችና ተጠፋፊ አሰላለፎች በቂ ምስክር ናቸው። ኦሮሞ ያለ ኢትዮጵያ ብቻውን መቆም እንደማይችል ሥልጣን ይዞ እንኳ በተግባር አይተነዋል። ይህን ሁሉ የማያቋርጥ ጭፍጨፋ በዝምታ በማየት አማራ የሌለባት ኢትዮጵያን መፍጠር ታስቦ ከሆነ ፍጹም ቅዥት ነው። አታስቡት! ሲያጠቁ መኖር ለናንተ ብቻ የተሰጠ ልዕለ-ኃይል አይደለም! ለመጤ ፍረጃችሁ ወራሪ የሚል የታሪክ ምላሽ እንዳለ አትርሱ።  እናም በጋራ የምንገነባትን ኢትዮጵያ ማሰቡ ይበጃል።  
~
ሁለተኛው መፍትሔ የተጠና ወታደራዊ ኦፕሬሽን  ነው። የክልሉ መንግሥት 31+ ዙር ልዩ ኃይል ያሰለጠነ ቢሆንም በክልሉ በዋናነት በወለጋ፣ ጉጅና ቦረና ዞኖች የዜጎችን ሠላምና ደህንነትን ማረጋገጥ አልቻለም።(ከፖለቲካ ሴራ የሚመነሱ ችግሮች እንደተጠበቁ ሆኖ) በአካባቢው የሰፈረው የመከላከያ ሠራዊትም በግዳጅ አፈጻጸም ዘላቂ ውጤት ማምጣት አልቻለም። አሁን ላይ ባለው ስምሪት የኃይል መሳሳት እንዲጋጠመ ይታወቃል። ስለሆነም ኦነግ ሸኔን የመደምሰስ ቁርጠኛ ፍላጎት ካለ ብሔራዊ የጸረ-ሽምቅ ግብረ ኃይል (National Counterinsurgency Task Force) በማቋቋም በተጠና ወታደራዊ ኦፕሬሽን በወራት ልዩነት የአካባቢውን ሠላምና ደህንነት ማስጠበቅ ይቻላል። ሙሉ ኃላፊነቱ የፌዴራሉ የጸጥታ ኃይል ሆኖ በየደረጃው ያሉ የክልሉ የጸጥታ አመራሮች የሚሳተፉበት የራሱ ‘አሀድ/Unit’ ያለው ስምሪት መስጠት ከተቻለ ኦነግ ሸኔ ታሪክ መሆን የማይችልበት ተዓምር የለም። ከዚህ ኦፕሬሽን ትይዩ ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት ያላቸው የኦነግም ሆነ የየትኛውም የፖለቲካ አመራሮች በሕግ ተጠያቂ ማድረግ ይጠበቃል።
***
ይህን ለማድረግ ‘መንግሥት’ መሆንን ይጠይቃል! 
ይህን አለማድረግ ደግሞ አናርኪስትነት ነው!!
 
የግርጌ ማስታወሻ
[ዳውድ ኢብሳ መደበኛ ስሙን ከፍሬው ወደ ዳውድ ሲቀይር በዓላማ ነበር። ጃዋር መሀመድ የሰፈሩ ሰው (የአርሲው) ከማል ገልቹ ፓርቲ እያለለት ኦፌኮን ሲቀላቀል በምክንያት ነበር። ያ ጥምረት ስድስት ወር ሳይሞላው ሜዳ ላይ ቀርቷል። መጨረቸው እግረ-ሙቅ የሆኑትን አትርሳ!! አባቴ ስሜት ሲንጠው በኖረው የኦሮሞ ፖለቲካ ‘ምክንያት’ ሆነ ‘ስሌት’ ቦታ የላቸውምና መለያየት ዕጣቸው ነው። መሰባሰቢያቸው የጋራ ጥላቻ እንጅ የፖለቲካ መርህ አይደለም!! 
 
እስካሁን ያነበብከውን እርሳውና አንድ ቁምነገር ብቻ ያዝልኝ፦ ኦሮሞ ያለ ኢትዮጵያ ብቻውን መቆም አይችልም! ልሂቃኑ ኢትዮጵያ ከሌለች አንድ ቀን አብረው ውለው አያድሩም።]
Filed in: Amharic