>

ተጋላጭ ያደረገን የውስጥ ፖለቲካችን ነው...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ተጋላጭ ያደረገን የውስጥ ፖለቲካችን ነው…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

እኛ ለሰለጠነ ፖለቲካ ልባችንን ከከፈትን፣ 
* በጎጥ እና በማንነት ልዩነት መናቆራችንን ካቆምን፣
 * ልዩነቶቻችንን በዲሞክራሲያዊ መንገድና በውይይ ብቻ ለመፍታት ከቻልን፣ 
* ለዜጎች መሰረታዊ ነጻነቶች እና መብቶች መከበር በቂ ጥበቃና እንክብካቤ ካደረግን፣ 
* ሁሉም ዜጋ በእኩል ተከብሮና መብቶቹ ተጠብቀውለት የሚኖርባትን ኢትዮጵያን መፍጠር ከቻልን፣
*  የጋራ ብሔራዊ ራዕይ ኖሮን እሱን እውን ለማድረግ አብረን ከሠራን ሌላው ዕዳ ገብስ ነው
ኢትዮጵያ ጠላቷ ብዙ ነው። እኛም ለጠላቶቻችን እንመቻለን። ታሪካዊ ጠላቶቿ ሁሌም የሚበረቱት ውስጣችን ሲዳከም ነው። ኢትዮጵን ለማዳከም ለሚተጉ ሃይሎች ቀላሉ መንገድ የውስጥ ችግሮቻችን ላይ በርቀት ሆነው ገንዘብ እና እውቀታቸውን ማፍሰስ ብቻ ነው። ሁሌም ስንዳከም ይጠብቁና እንደ ጆፌ አሞራ ይከቡናል። ዛሬም እየሆነ ያለው ይሄው ነው። ከግብጽ እና ከሱዳን አንስቶ በሩቅ ያሉ ጏያላን ሳይቀሩ ኢትዮጵያን የመበታተን የቆየ አጀንዳቸውን ከመሳቢያቸው የሚስቡት በውስጥ ፖለቲካችን እርስ በርስ እየተባላን የተዳከምን የመሰላቸው ጊዜ ነው። የመሀል ፖለቲካችን ሰከን ሲል ደግሞ ዋና ደጋፊና አጋር ሆነው ይመጣሉ። ይሄ ዘመናችንን ሙሉ እንደ ጥላ ሲከተለን የኖረና ነገር ነው።
ነገሩ ‘ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁም’ እንዲሉ፤ የምንናቅ ሆነን ስንገኝ ይረባረቡብናል። ለዚህ መዳኑቱ የውስጥ ፖለቲካችንን እና ሰላማችን ላይ ተግተን መስራት ብቻ ነው። እኛ ለሰለጠነ ፖለቲካ ልባችንን ከከፈትን፣ በጎጥ እና በማንነት ልዩነት መናቆራችንን ካቆምን፣ ልዩነቶቻችንን በዲሞክራሲያዊ መንገድና በውይይ ብቻ ለመፍታት ከቻልን፣ ለዜጎች መሰረታዊ ነጻነቶች እና መብቶች መከበር በቂ ጥበቃና እንክብካቤ ካደረግን፣ ሁሉም ዜጋ በእኩል ተከብሮና መብቶቹ ተጠብቀውለት የሚኖርባትን ኢትዮጵያን መፍጠር ከቻልን፣ የጋራ ብሔራዊ ራዕይ ኖሮን እሱን እውን ለማድረግ አብረን ከሠራን ሌላው ዕዳ ገብስ ነው።
እርስ በርሳችን እየተናጨን፣ ፖለቲካችንን ጠልፎ በመጣል አዙሪት ቃኝተን፣ ከአገር በፊት ጎጥ አስቀድመን፣ ኢትዮጵያን በዘር ማጥፋትንና በሰው ስብእና ላይ ያነጣጠሩ ወንጀሎች የሚፈጸምባት አገር አድርገን፣ እርስ በርስ በግጭትና በጦርነት እየተጋደልን ባዳከምናት አገር ላይ የውጪ ጏይሎች ክርን ቢበረታ ምን ይደንቃል። ለኔ ዛሬም ትልቅ ስጋት የሚሆኑብኝ የውጪ ጠላቶቿ አይደሉም። የውስጥ ጉዳያችንን የያዝንበት መንገድ ነው። በእነገሌ ተደፈርን ብለን እምቧ ከረዬ ማለታችንን ትተን ለውጭ ጏይሎች ተጋላጭ እንድንሆን ባበቁን የውስጥ ጉዳዬቻች ላይ በቅን መንፈስና በጋራ ብንረባረብና ብንሰራ አሁን ካለንበት አጣብቁኝ በቀላሉ መውጣት እንችላለን። ዛሬም ፖለቲካችን በሸርና በክፋት የተሞላ ስለሆነ ህክምና ይሻል።
Filed in: Amharic