>

አንቶኒ ብሊንከን ላብይ አህመድ አፍቀለጡ (መስፍን አረጋ)

አንቶኒ ብሊንከን ላብይ አህመድ አፍቀለጡ

መስፍን አረጋ


ያሜሪቃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አቶ አንቶኒ ክሊንተን “የኤርትራ ወታደሮች እና ያማራ ክልል ልዩ ኃይል ከትግራይ ምድር ባስቸኳይ ይውጡ” የሚል አስገዳጅ መግለጫ በቅርቡ በይፋ አውጠተዋል፡፡  ይህ መግለጫ በጦቢያ ሉዓላዊነት ላይ ዓይን ያወጣ ጣልቃገብነት ነው፡፡  ጣልቃገብነቱን የበለጠ ዓይን ያወጣ የሚያደርገው ደግሞ ያማራ ልዩ ኃይል “ትግራይን” ይልቀቅ ማለታቸው ነው፡፡

ባንቶኒ ብሊንከን ደረጃ ያለ የዲፕሎማሲ ሰው ይህን መሰሉን የሉዓላዊ አገርን –  ለዚያውም ደግሞ ያሜሪቃ አጋር የምትባልና ለሉዓዊነቷ እጅግ ቀናዒ በመሆኗ የምትታወቅ አገርን – ክብር እጅጉን የሚያዋርድ ኢዲፕሎማሲያዊ (undiplomatic) መግለጫ ለማውጣት የሚደፍረው፣ በመግለጫው ይዘት ካገሪቱ አመራሮች በተለይም ደግሞ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ከተስማማ ብቻና ብቻ ነው፡፡  ለዚህም ደግሞ አንቶኒ ክሊንተን መግለጫውን ከማውጣታቸው በፊት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በተደጋጋሚ መመካከራቸውን ማገናዘብ በቂ ነው፡፡

ስለዚህም ትልቁ ጥያቄ፣ ዐብይ አህመድ አንቶኒ ብሊንከንን እንደ አፈቀላጤ (proxy) ለመጠቀም የፈለገበት ምክኒያት ምንድን ነው የሚለው ነው፡፡  በተለይም ደግሞ አንቶኒ ክሊንተን ያማራ ክልል ልዩ ኃይል  “ትግራይን” ባስቸኳይ ይልቀቅ የሚል አስገዳጅ መግለጫ እንዲያወጡለት ዐብይ አህመድ ለምን ፈለገ የሚለው ነው፡፡   

ስልጣን ከያዘ በኋላ የወሰዳቸው ርምጃወች ከሞላ ጎደል ሁሉም በግልጽ እንደሚያመለክቱት፣ ዐብይ አህመድ የኦሮሙማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ (chief executive) ነው፡፡  የኦሮሙማ ዓላማ ደግሞ በጦቢያ ፍርስራሽ ላይ ያሁኒቷን ጦቢያን ከሞላ ጎደል ሁሉንም ክፍሎች እንዲሁም ከጎረቤት አገሮች የተወሰኑ ክፍሎችን የሚያጠቃል የኦሮሞ አጼጌ (Oromo empire) መመሥረት ነው፡፡  ዐብይ አህመድ የኦሮሙማ ሕልሙን ማሳካት የሚቸለው ደግሞ የሐብሻ ክልሎች የሚባሉትን ትግራይና አማራን በተደለሉ (convinced) ወይም በተታለሉ (confused) የኦሮሙማ ሎሌወች (puppets) የሚመሩ ገባሪ ክልሎች (vassal regions) ካደረጋቸው ብቻና ብቻ ነው፡፡   

አሁን ላይ ደግሞ ትግራይ በኦሮሙማ ሎሌወች የምትመራ የኦሮሙማ ገባሪ ክልል ስለተደረገች፣ የኦሮሙማ ሕልም እንዳይሳካ የቀረው አንድና አንድ ብቸኛ እንቅፋት ያማራ ክልል ነው፡፡  ስለዚህም ይህን ክልል የሚያጠናክሩ ማናቸውም ጅምሮች በማናቸውም መንገድ ከጅምራቸው መጨናገፍ አለባቸው፡፡          

የወልቃይትና የራያ ወደ ቀድሞ ቤታቸው ወደ አማራ ክልል መመለስ፣ ክልሉን በሁሉም ረገዶች የሁሉም ክልሎቸ የበላይ ኃያል (most powerful) አድርጎ፣ የዐብይ አህመድን የኦሮሙማ ሕልም፣ ሕልም ብቻ አድርጎ እንደሚያስቀረው ጥርጥር የለውም፡፡  ስለዚህም ወልቃይትና ራያ ወደቤታቸው እንዳይመለሱ ኦሮሙማውያን በጥፍራቸውና በጥርሳቸው ሳይቀር ቱልቀዳን (propaganda) እና ዲፕሎማሲን ጨምሮ በማናቸውም መንገድ ይሟሟታሉ፡፡   

በመጀመርያ ዐብይ አህመድ በትግራይ ያቋቋመው የኦሮሙማ ሎሌ አስተዳደር ከፍተኛ ዐባል በሆነውን ባቶ አብርሃ ደስታ አንደበት፣ ያማራ ልዩ ኃይል ከወልቃይትና ከራያ ካልወጣ ጦቢያ ትፈራርሳለች የሚል ዛቻ አይሉት ማስፈራሪያ አወጣ፡፡  ቀጥሎ ደግሞ ዛቻውን ከፍ ለማድረግ፣ ይበልጡንም ደግሞ በዘር ማጥፋት ወንጀል ልትከሰሱ ትችላላችሁ በሚል ዓይነት ገደምዳሜ (implication) ያማራ ክልል አመራሮችን በማስፈራራት ሽቁጥቁጥ እንዲሆኑለት ለማድረግ፣ ያብርሃ ደስታን ዛቻ ያሜሪቃው የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በገልጽ፣ በይፋና ባጽንኦት እንዲደግሙለት አደረገ፡፡         

አቶ ብሊንከን የኤርትራ ወታደሮች “ከትግራይ” ይውጡ ለማለት ያሜሪቃን ጥቅም የተመለከተ የራሳቸው ምክኒያት  ሊኖራቸው ይችላል፣ ይህን ሲሉ የጦቢያን ሉዓላዊነት ደፍረው በጦቢያ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡  ያብይ አህመድን እሽታ ሳያገኙ ግን በስማበለው (hearsay) ብቻ ተመርኩዘው ያማራ ልዩ ኃይልን በዘር ማጥፋት ወንጀል በመጠርጠር “ከትግራይ” ይውጣ እስከማለት ድረስ የጦቢያን ሉዓላዊነት ለመድፈር አይዳዳቸውም፡፡  

ያብዛኞቹ ያሜሪቃ መንግሥት አመራሮች (statesmen) ያለማቀፍ ፖለቲካ (international politics) እውቀት (expertise) መናኛ (nominal)  መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ምንም እንኳን አንቶኒ ብሊንከን ለተመደቡበት ኃላፊነት አዲስ ቢሆኑም፣ ኢትዮጵያን የተመለከተ ብርቱ – ለዚያውም ደግሞ አዋራጅ – መግለጫ ከማውጣታቸው በፊት፣ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዝርዝር ማብራሪያ (detailed briefing) እንደተሰጣቸው ይገመታል፡፡  በተለይም ደግሞ ባብይ አህመድ የብልጽገና ፓርቲ የኦሮሞና ያማራ አንጃወች መካከል ስለተጧጧፈው የሞት ሽረት ትግል በደንብ እንዲያውቁ ይጠበቅባቸዋል፡፡  እንዲህም ሆኖ ግን፣ ያማራ ክልል ልዩ ኃይል “ከትግራይ” ይውጣ የሚል መግለጫ አቶ ብሊንከን ሲያወጡ፣ ምናልባትም ሳያውቁት በጮሌው ዐብይ አህመድ በመታለል ከኦሮምያ ብልጽግና ጎን መቆማቸውን የተረዱት አይመስልም፡፡

       በውነትም ዐብይ አህመድ አፉና ምግባሩ ሐራምባና ቆቦ የሆኑ የኦነግ ኦቦ ነው፡፡  ባንደበቱ ኢትዮጵያን ቀን ከሌት እያወደሳት፣ በምግባሩ ግን ሳያሰልስ እንደሚያፈራረሳት ሁሉ፣ ላይ ላዩን ያማራን ልዩ ኃይል በጀግንነቱ እያሞገሰ፣ ውስጥ ውስጡን ግን ስሙን አጠልሽቶ በዘር ማጥፋት ወንጀል ሊያስከስሰው ከምዕራባውያን ጋር ይመሳጠራል፡፡ 

የብርሃኑ ጁላ ሠራዊት በስሙ እንጅ በግብሩ የኦሮሙማ ሠራዊት ስለሆነ፣ ራሷን ትግራይን ጨምሮ መላዋን ጦቢያን ከኦሮሙማ መቅሰፍት ለማዳን የቀረው አንድ ብቸኛ ኃይል የአማራ ልዩ ኃይል ነው፡፡  የቅርቡ ተጋድሎው በግልጽ ያረጋገጠው ደግሞ ይህ ያማራ ልዩ ኃይል – መሣርያው ነፍስ ወከፍ ብቻ ቢሆንም – ዐብይ አህመድ ሊያሰማራው የሚችለውን አስካፍንጫው የታጠቀን ማናቸውንም የኦሮሙማ ኃይል በቀላሉ መመከት እንደሚችል ነው፡፡  ስለዚህም ዐብይ አህመድ የኦሮሙማ ሕልሙን እንዳያውን (realize) እንቅፋት የሆነበትን ይህን ያማራ ልዩ ኃይል ማስወገድ የሚችለው፣ በዘር ማጥፋት ወንጅል አስከስሶ ምዕራባውያን ባለ በሌለ መሣርያቸው እንዲረባረቡት ካደረገ ብቻና ብቻ ነው፡፡  አንቶኒ ብሊንክን ያማራ ልዩ ኃይል “ትግራይን” ለቆ ይውጣ የሚል መግለጫ እንዲያወጡ የፈለገበትም ምክኒያት ሊሆን የሚችለው ይሄውና ይሄው ነው፡፡ 

 

Mesfin Arega

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic