>
5:13 pm - Monday April 20, 6703

አዲስአበቤ-Watch out 2 - ኤርሚያስ ለገሰ

አዲስአበቤ-Watch out 2

ኤርሚያስ ለገሰ

ብልፅግናን (ኦሮሙማን ጨምሮ) ከአዲስ አበባ ለማባረር በቅንጅት ለምትንቀሳቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች ሁለት ነገር ከግምት እንድትከቱ አሳስባለሁ፣
፩: የማሸነፊያ ግባችሁ ከሁለት ሶስተኛ(2/3ኛ) በላይ መሆን አለበት።
፪: የክፍለ-ከተማና ወረዳ የቀድሞ ህውሃት የአሁኑ ብልጽግና መንግስታዊ መዋቅር ለሚቀጥሉት አንድ አመታት (የአካባቢ ምርጫ እስኪካሄድ) ይቀጥላል። በመሆኑም ከወዲሁ የወረዳና ክፍለ-ከተማ ተመዳቢ ሻዶ ድርብ ካቢኔ ከዛሬ ጀምሮ ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
የአዲስ አበባ ክፍለ-ከተማ እና ወረዳ ሻዶ ካቢኔ ከወዲሁ የማዘጋጀት አስፈላጊነት፣
እንዳንድ አዲስአበቤዎች ይሄ ጉዳይ ግልፅ እንዳልሆነላችሁ እና ማብራሪያ እንድሰጥበት ጠይቃችሁኛል። አጀንዳው ወሳኝና ስትራቴጂክ ስለሆነ በተለያየ መንገድ በሰፊው እመጣበታለሁ። ለዛሬው መነሻ የሚሆን ላካፍላችሁ።
1ኛ፡- በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ በመሰረቱ በሁለት እርከን የሚካሄድ ነው። የመጀመሪያው <<አጠቃላይ ምርጫ>> የሚባል ሲሆን የፌዴራሉን ፓርላማ፣ የክልል ምክርቤት(አዲስ አበባን እና ድሬደዋን ጨምሮ) እንዲሁም ደቡብ ላይ የዞን ምክርቤት ጨምሮ የሚካሄድ ነው። ሁለተኛው <<የአካባቢ ምርጫ>> ተብሎ የሚጠራ ሲሆን አጠቃላይ ምርጫው ከተካሄደ ከአመት በኃላ በክልሎች ወረዳ፣ ቀበሌ፣ የከተማ አስተዳደር፣ ክፍለ-ከተማ ምርጫ የሚካሄድበት ነው።
2ኛ፡- ወደ አዲስ አበባ ስንመለስ የአሁኑ ምርጫ ለፓርላማ(23 ወንበር) እና አዲስ አበባ ክልል(138 ወንበር) የሚካሄድ ነው። በሌላ አነጋገር የቀድሞ ህውሃት መራሹ/ አሁን ኦሮሙማ መራሹ የክፍለ-ከተማና ወረዳ አስተዳደራዊ መዋቅር ለቀጣዩ አንድ አመት ሊቀጥሉ ይችላሉ።
3ኛ፡- ይበለውና የባልደራስ፣ አብን፣ መኢአድ ጥምረት የአዲስ አበባን ክልል ምክር ቤት (138 ወንበር) በአብላጫ ድምፅ አሸነፈ እንበለው። ይህ ከሆነ በጥምረት የሚፈጠረው የአዲስ አበባ መንግስት ለአንድ ዓመት ከብልፅግና የክፍለ ከተማና ወረዳ ካቢኔ ጋር ለመስራት ይገደዳል።ስለዚህ በየጊዜው የህዝብ ቅሬታ፣ የዕቅድ አፈፃፀም እንቅፋትና በሂደት የመፍረስ አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል። ስለሆነም ከወዲሁ በፍጥነት ህጋዊ ሻዶ የክፍለ ከተማና የወረዳ ካቢኔ  የማዘጋጀት ስራ መስራት ያስፈልጋል።
4ኛ፡- የክፍለ ከተማው ሻዶ ካቢኔ በእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ 15 በጥቅሉ 11×15= 165 ሻዶ የካቢኔ አባላት ከወዲሁ አዘጋጅቶ ለህዝብ ይፋ ማድረግ ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር እያንዳንዱ ፓርቲ 55 የሙሉ ጊዜ አመራር ማዘጋጀት አለበት።
5ኛ፡- ለእያንዳንዱ ወረዳ ሻዶ ካቢኔ 12 በጥቅሉ 100×12= 1,200 የሙሉ ቀን አመራር ከወዲሁ መዘጋጀት አለበት። በሌላ አነጋገር እያንዳንዱ ፓርቲ 400 የወረዳ ካቢኔ የሚሆኑ ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
#አዲስአበቤነት-ይለምልም!
#የአዲስአበባ-ግዛት-ይመለሳል!
Filed in: Amharic