>
5:13 pm - Sunday April 19, 1722

የኢትዮጵያ ልኂቃንን ውድቀት የሚያረጋግጠው ጦርነት...!!! (ብርሃኑ አበበ)

የኢትዮጵያ ልኂቃንን ውድቀት የሚያረጋግጠው ጦርነት…!!!

ብርሃኑ አበበ

ኢትዮጵያዊያን “ለምን ሌላ ዙር ጦርነት ውስጥ ልንገባ ቻልን?” የሚለውን ጥያቄ መጠየቅና የምር የሆነ ግምገማ ማድረግ ይገባናል፡፡ የረዥም ዘመን የአገረ መንግሥትነት ታሪክ ያለን አገር ሆነን ሳለ ለምን እስከ ዛሬ ድረስ ልዩነቶቻችንን በሰለጠነና ሥርዓት ባለው መንገድ፣ በውይይትና በድርድር መፍታት ሳይቻለን ቀረ? ለምን ዛሬም እንደ ትናንቱ ችግሮቻችንን ከውይይትና ድርድር ይልቅ በኀይል እንዲፈቱ ሆነ?
ለእኔ እንደሚታየኝ በዚህች አገር የፖለቲካ ፉክክር (contestation) የሚባል ነገር ኖሮ አያውቅም፤ አሁንም የለም፡፡ በአገራችን ትናንትም ሆነ ዛሬ ለሰለጠነ የፖለቲካ ፉክክር የሚሆን ምኅዳር አልነበረም፤ የለምም፡፡ ማንኛውም ዜጋ የፈለገውን ዓይነት የፖለቲካ አቋም ይዞ፣ ሌሎችን በማይጎዳና መብታቸውን በማይደፈጥጥ መልኩ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ፤ ከሕግና ከሥርዓት አፈንግጦ ሲገኝ ደግሞ በዚያው በተቀመጠው የጨዋታ ሕግ (ሥርዓት፡- ሕግ፣ ደንብ፣ መመሪያ ወዘተ…) መሠረት ተጠያቂ የሚሆንበትን ሥርዓት አልገነባንም፡፡ የቅርቡን እና አሁን ለገባንበት ቀውስ ምክንያት የሆነንን የሕወሓት ሁኔታ ብንጠቅስ፤ የሕወሓት አመራር ለሕዝቦች እኩልነት ታግያለሁ እያለ ነጋ ጠባ ቢናገርም የሕዝቦች መብቶች የሚረጋገጡበትን ሥርዓት ከመገንባት ይልቅ ይህን አጀንዳ ዋነኛ በሥልጣን ላይ መኖሪያ መሣሪያ አድርጎት ቆይቷል፡፡ የሕወሓት አመራር ስለ ብሔረሰቦች መብት መከበር እየለፈፈ እዚያው በዚያው ሕዝቦች በጥርጣሬ የሚተያዩበትን፣ ከዚያም እልፎ ውሎ አድሮ በመካከላቸው አለመተማመንና ጥላቻ የሚፈጠርበትን ሁኔታ ሲፈጥር የቆየ ቡድን ነው፡፡ ሕወሓት ለሰለጠነ የፖለቲካ ፉክክር ጨርሶ ባዕድ የሆነ ድርጅት ነው፡፡ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለምም የአገሪቱን የፖለቲካ ኀይሎች በዴሞክራሲያዊና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ጎራ ከፍሎ፣ የአገረቱ ህልውና ተጠብቆ ሊቀጥልና ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው ፀረ ዴሞክራሲያዊ ኀይሎች ከፖለቲካ መድረኩ ገለል ሲሉ ነው የሚል እጅግ አደገኛ ስትራቴጂ ሲከተን የኖረ ድርጅት ነው፡፡
የሕወሓት አክራሪ አመራር ሥልጣን ከመያዙ በፊትም ሥልጣን ይዞ ለ27 ዓመታት አገር ከገዛ በኋላም በነጻነት ማሰብ የማይችል፣ በከፍተኛ ሁኔታ በቡድን ስሜትና አስተሳሰብ የተበከለ፣ የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም ኅብረተሰብ ከደረሰበት ደረጃ አኳያ ራሱን እያስተካከለ መሄድ የማይችል ደካማ አመራር ነው፡፡ የሕወሓት አመራር፣ በተለይም አክራሪው ቁንጮ ቡድን ዛሬም እንደትናንቱ በስታሊኒስታዊ አስተሳሰብ የተለከፈ፣ የስታሊንን አስተምህሮ እንደ ማይከለስና ማይበረዝ ቅዱስ መጻሕፍት የሚያይ ኋላቀር አመራር በመሆኑ ነው በአገርና ሕዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል ሲያደርስ የኖረው፤ በማድረስ ላይም የሚገኘው፡፡
ይህ የሕወሓት ለሌሎች የፖለቲካ ኀይሎች ቦታ የማይሰጥ የአፈና ስትራቴጂ ውሎ አድሮ ሁሉም ኀይሎች በሕወሓት ላይ እንዲነሱ አድርጓቸዋል፡፡ የሕወሓት አመራር በተለይም በትጥቅ ትግል ያለፈው እና በዕድሜ የገፋው ኀይል ልክ የደርግ “አክራሪ ኮሚኒስቶች” እስከመጨረሻው ድረስ ከሶሻሊዝም ጋር ሲንገታገቱ እንደነበረው ይህም “አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ሞት!” ብሎ ቀጠለ፤ በዚህም ምክንያት ለውይይትና ድርድር የማይመች ሆነ፡፡ በሰለጠነ የፖለቲካ ፉክክር የማያምን አካል ሁልጊዜም ድርድርና ውይይት ውስጥ የሚገባው ሙሉ በሙሉ የእሱ አቋም ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ኀይል ለሰጥቶ መቀበል ባዕድ ነው፡፡
ይህ በተለይ ከ60ዎች ጀምሮ ስር እየሰደደ የመጣ ራስን ለሰጥቶ መቀበል ፖለቲካ ያለማስገዛት አካሄድ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ልኂቅ ዝቅጠት (degeneration) ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ እንዲያገኝ የሕወሓት አክራሪ አመራር መወገዱ በጣም አስፈላጊ መሆኑ የማያከራክር ቢሆንም፣ ችግሩ አገር ዐቀፋዊና ኅብረተሰባዊ መሆኑን መገንዘብ በጣም ያስፈልጋል፡፡
ዋናው ቁምነገር ግን የዝቅጠቱ ተጠቂ የሕወሓት አክራሪ አመራር ብቻ ሳይሆን ብዙሃኑ የአገራችን ልኂቅ መሆኑን እየጎመዘዘንም ቢሆን መቀበል ይገባናል፡፡ በሁሉም ጎራ ተሰልፎ ሲተጋተግ የሚውለው የአገራችን ልኂቅ ኢትዮጵያን የገጠማት ችግር ሌሎች አገሮችን ከገጠማቸው ችግር የማይበልጥ መሆኑን፣ በሰከነና በተጠና መልኩ መንቀሳቀስ ከተቻለ የዚህች አገር ችግሮች በቀላሉ መፈታት የሚችሉ ችግሮች መሆናቸውን የሚገነዘብ ልኂቅ አይደለም፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ እዚህ ግባ የሚባል ዕውቀትና ተሞክሮ የሌላቸው ለጋ ወጣቶች (አክቲቪስት በሚል ዘመን አመጣሽ ስም የሚጠሩ) መጫወቻ ሆናለች፡፡ ይህም ያለ ምክንያት የሆነ ነገር አይደለም፡፡ ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያ ልኂቃን ውድቀት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ልኂቃን ራሳችንን ኂስ ማድረግ ይገባናል፡፡ ሐቅ መራራ ብትሆንም እየመረረንም ቢሆን ሐቋን ተቀብለን ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ የምትወጣበትን መንገድ መቀየስ ይኖርብናል፡፡ የአገራችንን ዕጣ-ፈንታ ለእናውቅልሃለን ባይ ፖለቲከኞች ትተን ዘወር ማለት አይገባንም፡፡ የአገሬና የወገኔ ጉዳይ ያገባኛል፣ ይመለከተኛል ብለን መነሳት አለብን፡፡ ሁላችንም የዜግነት ኀላፊነታችንን ከምር ተቀብለን አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈልም ተዘጋጅተን አገራችንን ማዳን ይገባናል፡፡
Filed in: Amharic