>
5:13 pm - Sunday April 19, 9187

ያፄ ይኩኖ አምላክን ማንነት ለመቀየር የተነዛው ውሸትና ዓላማው ....!!! (ልጅ ተድላ መላኩ)

ያፄ ይኩኖ አምላክን ማንነት ለመቀየር የተነዛው ውሸትና ዓላማው ….!!!

(ልጅ ተድላ መላኩ)

*…. “ያፄ ይኩኖ አምላክ የእናቱ አባት አዛዥ ጫላ የሚባሉ ናቸው”  ብለው የዋሹት አዛዥ ክላ የሚለውን ሥም ወደራሳቸው የጎሳ ስም ቀይረው መኾኑን ግእዙን እንደወረደ በማየት ማወቅ ይቻላል። በግእዙ ስለ አዛዥ ክላ ስምና ማንነት የተጻፈው እንዲህ ይነበባል…!
 
ያፄ ይኩኖ አምላክን ታሪክ የዜና መዋዕል ጸሐፍትና የታሪክ ተመራማሪዎች በተገኘው ተአማኒ ማስረጃ አስተካክለው የሰነዱትም ቢኾን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ታሪክን የጎሳ ማንነታቸው ንብረት በማድረግ ዓላማ የተነሳሱ ዋሾች “አንድነትን ለመስበክ ነው” በሚል ሽፋን ሕዝብን ከእውነተኛ ታሪክ ለማለያየት መጽሐፍ እየጻፉና በየ ሚድያው እየቀረቡ የሥነ ልቡና ጥቃት በመሰንዘር ጉዳት እያስከተሉ ከርመዋል። በዚህም ምክኒያት  ሕዝባዊ ንቃተ ሕሊናንና ሥነ ልቡናን ለመታደግ ሐሰታቸውን የመናድ ሥራ ለነገ የሚተው አልኾነም።
እንደ ምሳሌ፣ በዘመኑ በምድሩ ላይ እንኳ ያልነበረውን የጎሳቸውን ማንነት ለኢትዮጵያ ነገሥታት ለመስጠትና ታሪኩን በጎሳ ማንነታቸው ተብትበው ባለቤቱን ከሥነ ልቡናው
 ለመንሳት  ሲሉ “አንድ ነን” በሚል ለምድ የነገሥታት ሁሉ አባት (ላለፉት ሰባት መቶ ዘመናት) የኾነውን ያፄ ይኩኖ አምላክን እውነተኛ ማንነት አጥፍቶ ለመቀየር የሄዱበትን ያፈጠጠ እውሸታዊ ርቀት ማስተዋል ይቻላል። እንደ ዣን ዶሬስ ያሉ ሥመ ጥር ዓለም አቀፍ አርኪዮሎጂስቶችና የታሪክ ተመራማሪዎች እንኳ አፄ ይኩኖ አምላክን “ዐምሓራ ልዑል” እና “ዐምሓራ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት” እያሉ በታሪካዊ ያጠናን ዘዴ (historical method) እውነተኛ ማንነቱን የገለጹትን ታሪካዊ ገፅታ ሞኝ-አያፍር ዋሾቹ  የቤተሰቡን ሥም በጎሳቸው ሥሞች በመቀየር እንደ አዋጅ በየ ንግግራቸው ሲያስተጋቡት ተስተውለዋል።
ወደ ፍሬው ነገር ስንመጣ፣ “ያፄ ይኩኖ አምላክ የእናቱ አባት አዛዥ ጫላ የሚባሉ ናቸው”  ብለው የዋሹት አዛዥ ክላ የሚለውን ሥም ወደራሳቸው የጎሳ ስም ቀይረው መኾኑን ግእዙን እንደወረደ በማየት ማወቅ ይቻላል። በግእዙ ስለ አዛዥ ክላ ስምና ማንነት የተጻፈው እንዲህ ይነበባል:
“ወእምዝ ሖረ ተስፋ ኢየሱስ ወበጽሐ ምድረ ሠገራት ኀበ ሀሎ አሐዱ ብእሲ ሊቀ ዘስሙ አዛዥ ክላ በመካን እንተ ትሰመይ መኮነኛ፣ ወኀደረ ተስፋ ኢየሱስ ውስተ ቤተ ዝንቱ ባዕል ወተራከበ በፈቃደ አምላክ ውስተ አሐቲ እምቅኑያት።”
የግእዙን ጥቅስ ያወጣሁበት ቀዳሚ ምንጭ  ይህ ነው: “Actes de Iyasus Mo’a abbé du couvent de St-Étienne de Hayq”, p. 23, Volumes 259-263, (published in 1965).
 ግእዙን ወደ ዐምሓርኛ ስንመልሰው:
[ፃዲቁ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ያፄ ይኩኖ አምላክን አባት ተስፋ ኢየሱስን ዙፋን ላንተ ሳይኾን ለልጅህ  ነው የሚመለሰው(ዳዕሙ ለወልድከ)ብለውት] “ከዚያም ተስፋ ኢየሱስ ጉዞውን ቀጥሎ መኮነኛ በምትባል ቦታ የወታደር አለቃ የኾነና አዛዥ ክላ የተሰኘ ሰው ወዳለበት ሠገራት ወደ ተባለ መሬት ሄደ” ይላል። ያዛዥ ክላ ሥም በዚህ መልክ ተጠቅሶአል።
 ዋሾች ያፄ ይኩኖ አምላክ አያት (የእናቱ አባት)” አዛዥ ጫላ ነው የሚባሉት” ብለው ፍጹም ውሸት የሚናገሩት በብራናው ላይ ያለው ያፄ ይኩኖ አምላክ አባት ተስፋ ኢየሱስ እርሱን ከመውለዱ በፊት የሄደበትንና ይኩኖ አምላክን የምትወልድለትን ሴት ያገኘበትን  የጦር አዛዥ ነው። የዚህ ስሙን የመቀየር ውሸት ዋናው ዓላማ አንድነትን ለመስበክ በሚል ሽፋን ይሁን እንጅ አፄ ይኩኖ አምላክ የነገሥታቱ ሁሉ አባት ስለኾኑ ነገሥታቱን  በውሸት የጎሳቸውን ማንነት በመስጠት በጎሳ የታሪክና የማንነት ውርሻ ለማድረግ ታልሞ ነው። እውነታውን መናገር ግዴታ የኾነውም ለዚህ ነው።  ምን ይህ ብቻ። ያፄ ይኩኖ አምላክን እናት፣ እምነ ጽዮንን፣ “ስሟ ጊፍቲ ነው” ብለው ዋሽተው ጽፈዋልና ልብ ይባል።
 ሥዕል – አፄ ይኩኖ አምላክና ፃዲቁ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ
Filed in: Amharic