>

⁽⁽አቃፊነቱን⁾⁾ አየነው ፤ ⁽⁽ወንድማማችነቱ⁾⁾  ወዴት አለ?!? (አንሙት አብርሃም)

⁽አቃፊነቱን⁾⁾ አየነው ፤ ⁽⁽ወንድማማችነቱ⁾⁾  ወዴት አለ?!?

አንሙት አብርሃም

አማራ ተብሎ በተካለለው ክልል የሚኖር ኦሮሞ በቀበሌ ምክርቤቶች ፤ በዞን ምክርቤት ፣ በከተማ ፣ በወረዳ ፣ በክልል እና በፌደራል ምክር ቤቶች ተወክሏል ፡ ይወከላል፤ አማራ እንዲሁ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ይወከላል ፤ አገው ከቀበሌ እስከ ፌደራል ይወከላል፣  አርጎባና ሌላውም ሁሉ ማነህ ሳይባል በምርጫ ስርዓት ከቀበሌ እስከ ፌደራል ምክር ቤቶች ይወከላል። ወንድማማችነት እንዲያ ነው።
በኦሮሚያ የሚኖረው አማራ ፡ ከሐረሪ፡ ከቤጉ ፡ ከጋምቤላና አፋር እንዲሁም ከሲዳማ ክልሎች ሕዝብ ድምር ይልቃል። ብዙ ወረዳዎች ብዙ ከተሞች አማራና ኦሮሞ ለዘመናት አብሮ የሚኖርባቸው ናቸው!
ሁለ-አገሩ የሆነው የጉራጌ ማህበረሰብ እና ሌሎችም ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ሰፋ ያለ አብሮነት አላቸው።
የኦሮሞን ሕዝብ በአብሮነት የሚያመሰግን ሁሉ ፣ መዋቅራዊ አካታችነት ሲጓደል ነገሩ መጓደሉን ሊረዳ የግድ ነው።
በወንድማማችነት እሳቤ ውስጥ አንዱ ቤተኛ ሌላው ባይታወር ተደርጎ አይታይም። ወንድማማችነትና አካታችነት ጉዳይ አይመርጥም❗
የሕዝብ ወንድማማችነት እና እኩልነት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ እንጂ በፖለቲካዊ ውክልና የሚበልጥና የሚያንስ ፣ የሚወስንና የሚወሰንለት ካደረገነው ጎደሎ ነው።
እኩልነትና ፍትሐዊነትን የሚገድፍ ወንድማማችነት የእውነት ወንድማማችነት አይደለም!
ተጋብቶ የተዋለደን ፣ ነግዶ የሚገብርን ፣ የሚያስተምር የሚያክምን ፣ ለዘመናት ክፉና ደግ አብሮ ያሳለፈን ደምና ከጥንት ቆጥረህ በፖለቲካ ካገለልከው ወንድማማችነት እንዴት ያለ ነው?
ዜግነትን እና ሰውን ማዕከል ማድረግ የሚፈልግ ድርጅት ፤ ፍትሐዊነትንና እኩልነትን መርህ እንዲሆን የሚፈልግ አመራር ፣ ወንድማማችነትን ማንበር የሚመኝ ስርዓት በዘመናት ዑደት አብሮ በመኖር አብሮነትን ካረጋገጠ ሕዝብ መካከል ለይቶ የፖለቲካ መብት አይሰጥም።
ፅንፈኛ ብሔርተኝነትንና ዘረኝነትን የሚኮንን ድርጅት አመራር ፣ የብሔር ፖለቲካ በኢትዮጵያዊ ዜግነት ማቀራረብና የአገር አንድነትን የሚመኝ ኃይል ፣ ዘረኝነት አገር ያጠፋል የሚል የአገር አመራር ፣ ከብሔር አደረጃጀት ወጥተን የሁሉም የጋራ ድርጅት ነን የሚል ድርጅት፣  ብሔር መርጦ የምርጫ ወኪል አይመርጥም ፡ ማንነትን ለይቶ የምክር ቤት እጩ አያቀርብም።
ባለቤትና ባይታወር በሚያደርግ የሕዝብ ውክልና ፣ አግላይ  የመምረጥና መመረጥ መብት አያደርግም።
አማራ የሚገኝ ኦሮሞ እየተወከለ ኦሮሚያ የሚገኝ አማራና ጉራጌ ወዘተ ሳይወከል ወንድማማችነት ስም ብቻ ነው።
ያ ከሆነማ ወንድማማችነት ንግግር ብቻ ነው!
⁽⁽አቃፊነት⁾⁾ በአግላይነት የተሸፈነ ተረት ነው። ማካተትንና መወከልን የሚጠላ ⁽⁽አቃፊነት⁾⁾ ፣ በብሔር የሚለካና የሚመዝን ፖለቲካ ወንድማማችነትን ያረክሰዋል።
Filed in: Amharic