>

ኦነግ የእጩ ማቅረቢያ ቀኑ ይራዘምልን  አለ...!!! - አቶ ቀጀላ መርዳሳ የኦነግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ

ኦነግ የእጩ ማቅረቢያ ቀኑ ይራዘምልን  አለ…!!!
– አቶ ቀጀላ መርዳሳ የኦነግ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ
(ኢ ፕ ድ)

ድርጅቱ በምርጫ ለመሳተፍ ፍላጎት ቢኖረውም በውስጥ ችግር ምክንያት ሀገራዊ ምርጫው ላይ ለመሳተፍ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ማድረግ አለመቻሉን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀጀላ መርዳሳ አስታወቁ። ምርጫ ቦርድ ችግሩን ግምት ውስጥ በማስገባት ቀኑን ቢያራዘምልን ሲሉ ጥሪ አቀረቡ።
አቶ ቀጀላ መርዳሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ ባለፉት ስምንት ወራት የፓርቲው አመራሮች በውስጥ ጉዳይ ተጠምደው ነበር ፡፡ ጉዳዩ እልባት ሳያገኝ ምርጫው መድረሱ ለምርጫ በሚደረገው ዝግጅት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አሳድሯል።
አንድ ፓርቲ መንቀሳቀስ የሚኖርበት እንደ ፓርቲ ነው የሚሉት አቶቀጀላ፣ የፓርቲው አመራር ከአባላቱ ጋር በጋራ ለምርጫ መዘጋጀት ሲኖርበት በማፈንገጡ የተነሳ የምርጫ ዝግጅት ማድረግ አለመቻሉን አመልክተዋል።
ይህን የውስጥ ችግር በመፍታት ወደ ምርጫ ዝግጅት ለመግባት የተደረጉ ጥረቶች አለመ ሳካታቸውን የተናገሩት አቶ ቀጀላ፣ የፓርቲውን ችግር ለመፍታት የምርጫ ቦርድ ሁለት ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄዶ እንዲፈታ ለማመቻቸት ያደረገው ጥረት በሊቀ መንበሩ እንቢተኝነት ሊሳካ አለመቻሉን አስታውቀዋል።
አንድ ወጥ የሆነ አመራር በሌለበት ወስኖ ወደ ተግባር ለመግባት አስቸጋሪ እንደሚሆን ያመለከቱት ኃላፊው ፣ ያሉትን ችግሮች እንደሰለጠነ ሰው ቁጭ ብሎ ለመነጋገርም በተለያዩ አካላት ማለትም በምርጫ ቦርድ፤ በሀገር ሽማግሌዎች፤ በሃይማኖት መሪዎች፤ ውጭ ሀገር በሚኖሩ ቀደም ሲል የአመራርነት ቦታ ላይ የነበሩ አባላት ጨምሮ አሁን በምክር ቤት ደረጃ አማካሪ በሆኑት ግለሰቦች መሞከሩን ገልጸዋል ።
ለሰላሳና አርባ ዓመታት በተለያዩ የአመራር እርከኖችና አባልነት ላይ የነበሩ ሰዎችን በፓርቲው ውስጥ እውቅና መስጠት አለመፈለግ፤ የጋራ ችግሮችን ለመፍታት ተነሳሽነት ማጣት የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን ጠቁመው ፣አሁን በየቦታው የሚገኙ አባላትን፤ የሥራ አስፈፃሚና የማእከላዊ ኮሚቴ አባላትን በማወያየት መደረግ የሚገባውን ነገር ለማድረግ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የመጀመሪያው እርምጃ የሚሆነውም ድርጅቱ እንደ ድርጅት እንዲቀጥል ማድረግ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ቀጀላ ፣ ይህን ማድረግ ሲቻል ለምርጫ ዝግጅት በማድረግ ለምርጫው ለመድረስ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
አሁን ተወዳዳሪ እጩ ማቅረቢያ ጊዜ ሰሌዳ ሊገባደድ በተቃረበበት እና የጋራ አመራር በሌለበት ሁኔታ ማን ምን ቦታን ወክሎ ይወዳደር? የት የት ቦታስ መወዳደር ይኖርብናል? የሚሉ ጥያቄዎችን የሚመለሱ ሥራዎች ሊሰሩ አለመቻላቸውን ያስረዱት አቶ ቀጀላ፣አሁን አባሎችን በማወያየት ከምርጫ ተሳታፊነት ላለመውጣት የመጨረሻ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ያፈነገጠው አመራር ቢሮዎችን መዝጋት፤ ጥቃቅን ነገሮችን እያነሳ ፓርቲው ለሁለት እንዲከፈል እያደረገ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ቀጀላ፤ የአቅም ማነሰ፤ የፀጥታ ችግር፤ እርስ በእርስ አለመስማማት ችግሩን ያባባሰው መሆኑንም ጠቁመዋል።
Filed in: Amharic