>

በፖለቲከኛ እስረኞች ላይ እየተፈፀመ ያለው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል![አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ]

Andinet partyየኢህአዴግ አገዛዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰብአዊ መብት በመጣስና ዜጎችን በማሰቃየት ወደር የሌለው ሆኗል። ስርዓቱ ለአገዛዜ ያሰጉኛል የሚላቸውን ንፁሀን የፖለቲካ አመራችን፣ ጦማሪያንና ጋዜጠኞችን ህገወጥ በሆነ መንገድ ክስ በመመስረት ማሰሩ ሳያንስ እነዚህን ዜጎች ሰብአዊ ክብራቸውን በመድፈርና ኢ-ሰብአዊ በሆነ ድርጊት እየፈፀመ በማሰቃየት ላይ ይገኛል።

ፓርቲያችን ይህንን ሕገ እየጠቀሰ ህገ-ወጥ ድርጊት የመፈፀም አካሄድ ፍፁም ከባህላችን ያፈነገጠ፤ ከአንድ ሀገር እየመራሁ ነኝ ከሚል ፓርቲ የማይጠበቅና በአስተሳሰብ ደረጃም የዘቀጠ እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልፀዋል። በዚህም ሳያበቃ የስርዓቱ ዱላ ሆኖ እያገለገለ ያለው የፀረ ሽብር አዋጁ እንዲሰረዝም በህዝባዊ ንቅናቄ ጠይቀናል። ሆኖም ግን ከገዥው ፓርቲ በኩል የተሰጠው ምላሽ አምባገነንነቱን አጠናክሮ በመቀጠል በዜጎች ስቃይ መደሰት ሆኗል።
በተለይም አንድነት ፓርቲ፣ አባላቱና አመራሮቹ የፖለቲካ እንቅስቃሲያቸውን ለመገደብ የፀረ ሽብር አዋጁ እየጠቀሱ ወደ ማጎሪያ መውሰድ የተለመደ ሆኗል። እነ አንዷለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮነን፣ አንዷለም አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ ሀብታሙ አያሌውና ሌሎችም በፖለቲካ እምነታቸው የተነሳ ወደ ማሰቃያ ስፍራ የተወሰዱ የአንድነት የቁርጥ ቀን ልጆች ናቸው።
ተይዘው ወደ ማዕከላዊ የተወሰዱት ወጣቱ ፖለቲከኛና የፓርቲያችን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌውና ም/የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ ማዕከላዊ በሚባለው የማሰቃያ ስፍራ አንድ ሰው ያደርገዋል ተብሎ የማይጠበቀው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እየተፈፀመባቸው እንደሆነ ፓርቲያችን ከተጨባጭ ምንጮች አረጋግጧል።
በተለይም አቶ ሀብታሙ አያሌውን ለአንድ ሳምንት የታሰረበት ክፍል ውስጥ እንዲፀዳዳ በማድረግና ለሶስት ሳምንታት ደግሞ ጨለማ ክፍል ውስጥ በማሰር የበቀል በትራቸውን እያሳረፉበት እንደሆነ አውቀናል። የስርዓቱ ጭካኔና አረመኔያዊነት ከኢትዮጵያዊ ባህል ያፈነገጠ ከመሆኑ ባሻገር ሀገርና ህዝብ የመምራት የሞራል ብቃት እንደሌለው ከዚህ በላይ ማረጋገጫ አይኖርም። አቶ ሀብታሙ እዚያው ላሉ የእስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች አቤት ቢልም ምላሹ ፌዝ ነበር።
አቶ ዳንኤል ሺበሺም በተመሳሳይ ሁኔታ ከከፍተኛ ዛቻና ስድብ በተጨማሪ የታፈነ ክፍል ውስጥ እንዲቀመጥ በመደረጉ በተደጋጋሚ ለተቅማጥና ለተለያዩ በሽታዎች መዳረጉን፤ ወደ መፀዳጃ ቤት እንዳይሄድም መከልከሉን ገልፆ ለፍርድ ቤቱ ቢያመለክትም ምንም ዓይነት ምላሽ አልተሰጠውም።
በአጠቃላይ በዚህ ክፉ ስርዓት ሺዎች በግፍ እየማቀቁ ይገኛሉ። ይህንን የበደል ዘመን ለማሳጠር እንዲቻልም ህዝቡ በቁጭት ለለውጥ እንዲነሳ ጥሪ እናቀርባለን። በተጨማሪም ለሰብአዊ መብት ልዕልና የቆሙ ድርጅቶች፣ የዴፕሎማቲክ ማህበረሰቡና በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑን እየገለፅን ይህንን ለማስቆም መታገል ወሳኝና ብቸኛው መፍትሄ እንደሆነ እናረጋግጣለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ (አንድነት) ፓርቲ
ጥቅምት 20/2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ

Filed in: Amharic