>

በታላቁ የዓድዋ ድል የተቋጨው የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ቅዠት (ዳንኤል አሰፋ)

በታላቁ የዓድዋ ድል የተቋጨው የአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ቅዠት

ዳንኤል አሰፋ

አውሮፓውያኑ አፍሪካን የመቀራመት ህልማቸውን የወጠኑት እ.ኤ.አ በ1884 ዓ.ም በርሊን ላይ ባደረጉት ጉባኤ ነው። ሆኖም ግን አፍሪካን መውረሩ የተጀመረው ከዛ ቀደም ብሎ እ.ኤ.አ በ1870 ዓ.ም ነበር። በዚሁ ዓመት አፍሪካን መውረር ሲጀምሩ ይዘውት የነበረው አስር በመቶ የሚሆነውን የአፍሪካን መሬት ብቻ ቢሆንም የቅኝ ገዢነታቸው አብቅቷል ተብሎ በሚታሠብበት ዘመን ማለትም እ.ኤ.አ በ1914 ዓ.ም ግን ዘጠና በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ መሬት በአውሮፓውያኑ ቁጥጥር ስር ነበር። በዚህ ዘመን ነፃ የነበሩት ሁለት የአፍሪካ ሀገሮች ኢትዮጵያና ላይቤሪያ ብቻ ነበሩ።
* ቅኝ የመግዛት ሃሳቡ መቼ ተወጠነ?
እ.ኤ.አ በ1884 ዓ.ም በፖርቹጋል ጥያቄ አቅራቢነት  የጀርመኑ መሪ ኦቶማን ቢስማርክ ሃያል ጉልበት ያላቸው ሃገራት በአፍሪካ ላይ ያላቸውን ማንኛውም ስምምነት እንዲያጠነክሩና ውዝግቦቻቸውንም እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበ። ጥሪ የቀረበላቸው ሃገራትም ኦስትሪያ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ፖርቹጋል፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም፣ ስዊድን፣ ብሪታንያ፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድ፣ ራሺያ፣ ስፔን፣ ቱርክና አሜሪካ ነበሩ።
ከእነዚህ አስራ አራት ሃገራት መሃልም ፖርቹጋል፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን በጉባኤው ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው እንዲሁም በወቅቱ አብዛኛውን የአፍሪካ ምድር የተቀራመቱ ሃገራት ነበሩ። ይሔንን እንዲያደርጉ ካስገደዷቸው ምክንያቶች ትልቁን ቦታ የሚይዘው በአውሮፓ ያለን የፖለቲካ የበላይነትን የመቆጣጠር ፍላጎት ነበር።
ይሄንን ለማሳየት ደግሞ አፍሪካን ጨምሮ በሌላው ዓለም ላይ ያላቸውን የበላይነት ማሳየት ዋነኛው መንገድ ሲሆን፤ ሌላኛው ምክንያት ደግሞ በአውሮፓ አዲሱን የካፒታሊስት ርዕዮተ ዓለም ተከትሎ እያደገ የመጣው ማህበራዊ ቀውስ (ረሃብ፣ ፍልሠት፣ ስራ አጥነት፣ የመኖሪያ ችግር ….) ነው።
እነዚህን ሁሉ ችግሮችን በቀላሉ የማስወገጃ ቁልፍ አፍሪካን በቁጥጥራቸው ስር ማድረግ መሆኑን በማመናቸው ነው ከላይ ያየናቸው አስራአራት ሃገራት በፓርቹጋል ጥሪ አቅራቢነት በጀርመን መሪነት አፍሪካ ባልተሳተፈችበት ጉባኤ አፍሪካን ለመከ’ፋፈል ከስምምነት የደረሱት። በስምምነታቸው መሠረትም በሚሽነሪነት፣ በ”ኃይማኖትን ልንሠብካችሁ ነው” ስም፣ በህክምና ሠጪነትና በመንገድ ቀያሽነት፣ በገዢዎች አማካሪነት ….. ስም ሠላዮቻቸውን በመላክ መውጪያ መግቢያዋን ካጠኑ በኋላ ቀስ በቀስ ወታደሮቻቸውን እየላኩ አፍሪካን መቆጣጠር ጀመሩ። “ስልጣኔንና ሃይማኖት እናስተምራችኋለን” የምትለው ማጭበርበሪያቸውን ያመኑት አፍሪካውያንም በገዛ መሬታቸው ከሠውነት እንኳን ወርደው የባርነት ኑሮን መግፋትን ተያያዙት።
* ቅኝ ግዛቱ እንዴት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ቻለ?
ቅኝ ገዢዎቹ አውሮፓውያን አፍሪካን በአጭር ጊዜ እንዲቀራመቷት ካስቻላቸው ምክንያቶች የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው አፍሪካውያን የየአካባቢው ገዢዎች መሀከል ለስልጣን የነበረ ሽኩቻ ነው። አውሮፓውያኑ ይሔንን የአፍሪካውያን ክፍተት በደንብ ነው የተጠቀሙበት። ቀድመው በላኳቸው ሚሲዮናውያን በኩል አንዱ አንዱን እንዲወጋ እያግባቡ፤ በጎን በኩል መሳሪያም እያቀበሉ እነርሱ ወደ ጦርነት ሳይገቡ አስቀድመው እርስ በእርስ እንዲጨራረሱ አደረጓቸው።
ሁለተኛው ምክንያት እ.ኤ.አ በ1895 ዓ.ም በዝናብ እጦት ተከስቶ የነበረው ከፍተኛ ረሃብና እርሱን ተከትሎ በመላው አፍሪካ የተቀሰቀሰው ከባድ የአንበጣ ወረርሽኝ እንዲሁም በአውሮፓውያኑ ወደ አፍሪካ እንዲገባ የተደረገው የከብት በሽታ እንስሳቱን ሁሉ መጨረሱ ነው። ይሔ ሁሉ ችግር የተደራረበባቸውና የሞራል ልሽቀት የደረሰባቸው አፍሪካውያን ብዙም ሳያስቸግሩ እጃቸውን ለአውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎቻቸው በቀላሉ ሠጡ።
ነጮቹ በግዛታቸው ግዜ ይጠቀሙበት በነበረው “Take the mind keep the body” (ሰውነቱን ተውና ሥነ ልቦናውን ቀማው) አይነት መንገድ መላው የጥቁር ህዝብ ነጮች የበላይ ናቸው፤ አይሸነፉም በሚል በሥነ ልቦና ተፅእኖ ስር ወድቀው እንዲቆዩና በኋላም የአድዋ ድል ላይ ነጭ ተሸናፊ ፍጡርም መሆኑ ታምኖበት ይደረጉ በነበሩ የነፃነት እንቅስቃሴዎች መነሻነት በፈረንጆች አቆጣጠር በ1960ዎቹ ነፃ እስኪወጡ ድረስ ህዝቡ ከነ ትውልዱ በመከራ ቀንበር ውስጥ ወድቆ… ከሰውነት ጎራ አስወጥተውት እንደ እንስሳ እየታየ በባርነት አመታትን ኖሯል።
ይሔ የቅኝ ገዢዎች ውጥን ኢትዮጵያ ላይ እንዴት ሊከሽፍ ቻለ? እንቀጥላለን
Filed in: Amharic