>
5:13 pm - Sunday April 20, 9806

የዘውግ ፖለቲካ ስረ-መሰረቶች...!!! (መስከረም አበራ)

የዘውግ ፖለቲካ ስረ-መሰረቶች…!!!

መስከረም አበራ

ሃገራችን ኢትዮጵያ የዘውግ ፖለቲካን ሙጥኝ ካለች እነሆ በሶስት አስርታትን አስቆጠረች። ለነገሩ የሃገራችን ታጋዮች የዘውግ ፖለቲካ የፍቅር ሊገድላቸው እየማለ ከለከፋቸው ወደ ግማሽ ምዕተ አመት ተቆጥሯል – የድንገቴው ደርግ በመሃል ገብቶ አስራ ሰባት አመቷን ባይወስድባቸው ኖሮ።
የሆነው ሆኖ የዘውግ ፖለቲካ ህገ-መንግስታዊ ማፅረግ ተሰጥቶት፣የሃገር ችግር ሁሉ የመፍትሄ ኪኒኒ ተደርጎ በግድም በውድም እንድንውጠው ተደርገናል። ይህ ሁሉ ሲሆን የዘውግ ፖለቲካው መመሪያ ድርሳን የስልሳዎቹ ጎረምሳ ፖለቲከኞች ብጣሽ ፅሁፍ አለያም የነመለስ ዜናዊ የ68 ማኒፌስቶ እልፍ ካለም የኦነግ እና ውላጆቹ እውነት ውሸቱ ያልተለየ ስሜት ያጀበው፣ጥላቻ ያነደደው የተበድየ ተረክ ነው።
 ይህ ጉዟችን በቢላዋ አስተራርዶናል፣እንደ ዝንጀሮ በድንጋይ ናዳ አጋድሎናል፣ ከገደል አፋፍ አወራውሮናል። ይህን ሁሉ የሆንንለት የዘውግ ፖለቲካችንን በተመለከተ ያለን እውቀት የሚቀዳው ከየዘውጋች ፖለቲከኞች እሳቤ ነው።  እነሱ ደግሞ ቢለዋ የሚያማዝዘንን “እውቀት” የሚያቀብሉን በብዛት ከስሜታቸው ቀድተው ነው። የእነሱ እውቀት እንደ ማር እንደወተት የሚጥመው ብዙ የሃገሬ ሰው እንዳለ አውቃለሁ።
 የዘውግ ፖለቲካን ነፍስም ሳይቀርለት እየወደደ ያለውም፣ከዘውግ ፖለቲካ መላቀቅ የሚፈልገውም ከፖለቲከኞች ንግግር ባለፈ የምሁራኑ አለም ስለዘውግ ፖለቲካ ምን ይላል የሚለውን ማወቅ እንዳለበት አጥብቄ አምናለሁ። አምኜም አልቀረሁም መዛግብትን አገላብጨ የተረዳሁትን በመፅሃፍ መልክ ለመሰነድ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ ሳደርግ አምስት አመት ሞላኝ።
 ለአንባቢ በመፅሃፍ መልክ ይዤ የምቀርበው ነገር መጀመሪያ እኔን እንዲያሳምነኝ ብዙ ደክሜያለሁ። ብዙ ድርሳናትን አንስቼ ጥያለሁ፣አካሌም አእምሮዬም እስኪዝል የቻልኩትን ሁሉ አድርጌያለሁ። በስተመጨረሻው እኔን ያሳመነኝን መፅሃፍ እነሆ ብያለሁ፨
ፖለቲካችንን እየዘወረ ስላለው የዘውግ ፖለቲካ እሳቤ መነሳት አለባቸው ብየ ያሰብኳቸውን ጭብጦች ለማካተት ሞክሬያለሁ። በአስር ቀን ውስጥ ከማተሚያ ቤት ወጥቶ ይደርሳችኋል። በጣም እንዳዘገየሁት ይገባኛል።ይህ የሆነው ግን ስለማከብራችሁ የማይመጥን ነገር ይዤ ላለመምጣት ነው
 መፅሃፉን  ከእኔ የተሻለ እውቀትና ልምድ አላቸው ላልኳቸው ሰዎች አስገምግሜያለሁ። መፅሃፉ እጃችሁ እስኪደርስ እነሱ በነግሩኝ አስተያየት ውስጥ የመፅሃፉን ጭብጥ እንድትገምቱ የነሱን አስተያየት አጋራችኋለሁ። ለዛሬ አንዱን ላጋራችሁ።
Filed in: Amharic