>
5:13 pm - Saturday April 19, 0521

የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት 4ኛ ህልፈተ-ዓመት ሲዘከር! (አሰፋ ሀይሉ)

የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት 4ኛ ህልፈተ-ዓመት ሲዘከር!

አሰፋ ሀይሉ
(Remembering Prof. Richard Pankhurst – 4 Years of Rest in Peace!)

እኚህ ድንቅ የታሪክ ምሁር፣ ታላቅ የኢትዮጵያ ወዳጅና ባለውለታ – ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት – በህይወት ከተለዩን እነሆ 4 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ የዛሬ 4 ዓመት ልክ በዛሬዋ ዕለት February 16, 2017 (የካቲት 9/ 2009 ዓ.ም.) ነበር የተለዩን፡፡
የሪቻርድ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ፍቅር በዘር የተላለፈ እስኪመስል ድረስ እጅግ የሚደንቅ ተዓምር ያለው ነው፡፡ የሪቻርድ ፓንክረስት ሴት አያት Emmeline Pankhurst በ20ኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ ላይ በእንግሊዝ የሴቶችን የመምረጥ መብት የማስከበር ንቅናቄ (UK suffragette movement) የመሩና ለእንግሊዛውያን ሴቶች ፖለቲካዊ ነጻነትን ያቀዳጁ ታላቅ ዓለማቀፋዊ ክብርና ዝናን ያተረፉ የሴት አርበኛ ነበሩ፡፡
በ1928 ዓ.ም. የጣልያን ፋሺስቶች 40 ዓመት በሙሉ በበቀል ሲዘጋጁ ኖረው ኢትዮጵያን ሲወርሩ፣ እና በመርዝ ጋዝና የአውሮፕላን ቦምቦች፣ በእሳትና በዘመናዊ ጦርመሣሪያዎች ግማሽ ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን በግፍ ሲጨፈጭፉ – እና ብዙው የነጩ ዓለም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለፋሺስቶቹ ዘረኝነት የተሞላበት ወረራ ድጋፉን ሲቸር – የሪቻርድ ፓንክረስት እናት Sylvia Pankhurst በእንግሊዝ ምድር ሆና – ዓለም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲሰለፍና የኢትዮጵያውያንን ጭፍጨፋና ወረራ እንዲያስቆም – ሙሉ ጊዜዋን ሰጥታ – የኢትዮጵያ ወዳጅ ጋዜጣ እያሰራጨች፣ ህዝብን በመንገድ ሁሉ እያስቆመች ስትጮህና ስትቀሰቅስ የነበረች ብቸኛ የኢትዮጵያውያን የእውነትና የሀቅ ድምጽ ነበረች፡፡
ያን አይረሴ ድምፅ ወደፊት ኢትዮጵያን የሚል የኢትዮጵያ ባለአደራ ትውልድ ሲነሳ በጥልቅ አጥንቶ የሚዘክረው በአውሮፓ ምድር ያለማቋረጥ የተሰማ የኢትዮጵያ የነጻነት ድምጽ ነበር፡፡  ይህች ሲልቪያ ከነጻነት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልላ መጥታ ታላቅ ሀገራዊ ሥራዎችንም አበርክታለች፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ የነርሶች ማሰልጠኛ፣ የልብስ ስፌት ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ወዘተ ዘመናዊ ትሩፋት የጎበኛቸውን ሀገራዊ ተቋማት ለመክፈት በሚያደርጓቸው ጥረቶች ሁሉ ሲልቪያ ፓንክረስት ቀኝ እጃቸው ነበረች፡፡ ለኢትዮጵያ ይጥቀሙም አይጥቀሙም እንደ ሜይትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፣ እንደ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ፣ እንደ ፀጋዬ ገብረመድህንና ሌሎችን ቁጥራቸው የበዙ ኢትዮጵያውያን የጥበብ ሰዎችን ከልጇ ሪቻርድ ሳትነጥል በቤቷ አሰባስባ አርዓያ ያለው ወላጃዊ ድጋፍ እየቸረች ያሳደገቻቸውና የደገፈቻቸው ወይዘሮም ነበረች፡፡
የሪቻርድ ፓንክረስት እናት ሲልቪያ ፓንክረስት በዓለማቀፍ ደረጃ ስመጥር የሆነውንና በኢትዮጵያ ላይ የተካሄዱ ብዙ ምሁራዊ ጥናቶችን ያስተባበረውን የኢትዮጵያ ጥናት ወዳጆች ማህበርን ካቋቋሙ ግንባር ቀደም ሰዎች መካከል አንዷ ነበረች፡፡ ስለ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፣ ስለ ኢትዮጵያውያን ባህል ብዙ ጽሑፎችን በብዙ ዓለማቀፍ መጽሔቶችና ጆርናሎች ላይ ያሳተመች የኢትዮጵያ የህይወት ዘመን ወዳጅ ነች፡፡ መካነ መቃብሯ በሥላሴ ካቴድራል መግቢያው ላይ አርፎ – ኢትዮጵያን ለሚወዱ ሁሉ ስለ ሀገር ፍቅር አስታዋሽ ሆኖ ይኖራል፡፡
እና እኚህ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የበቀሉት ከእንደዚህ ለሰው ልጅ መብት፣ ብሎም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን  ታላቅ አክብሮትና ፍቅር ካደረባቸው ድንቅ ቤተሰቦች መሐል ነው፡፡ ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት ለኢትዮጵያ ያደረጉትን ምሁራዊ አበርክቶት ለማወቅ የፈለገ ቢኖር ዛሬውኑ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ቤተመጻሕፍት ይሂድና በሪቻርድ ፓንክረስት የታተሙ በኢትዮጵያ ላይ ያተኮሩ ከ60 በላይ (ይሄ እኔ በዓይኔ ያየሁት ነው) የምርምር መጽሐፎቻቸውን ይመልከት፡፡
በበኩሌ ብዙ ስለ ኢትዮጵያ የደከሙ፣ የለፉ፣ ሕይወታቸውን የሰጡ ምሁራንን አውቃለሁ፡፡ የብዙ ሰዎችን ሥራዎችም ለማየት ዕድሉን አግኝቼያለሁ፡፡ በዚህች በኢትዮጵያ ምድር ግን እንደ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት መላ ህይወቱን ሰጥቶ እጅግ በርካታ የምርምር ሥራዎችን አሳትሞ፣ ሀገራችንን ለራሳችን ለኢትዮጵያውያንና ለዓለም አሳውቆ ያለፈ ሰው ግን አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ 10 ፐርሰንቱ የሪቻርድ ፓንክረስትን ግማሹን እንኳ ሥር ቢያነብና ቢረዳ፣ አሁን እያዳከርንበት ያለነውን በዘር ተከፋፍለን የምንቧጨቅበትን የወረደ የኢትዮጵያዊነት የዝቅታ ታሪካችንን ለመቀየር ይነሳ እንደነበረ በግሌ በሙሉ ልቤ አምናለሁ፡፡
ይህ ሁሉ እንግዲህ ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት የእንግሊዝን ሙዝየሞች ደጅ ጠንተው ወደ ሃገራችን ያስመለሱልንን ጥንታዊ ቅርሶች፣ የአክሱም ሃውልትን ከኢጣልያ ለማስመለስ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር አብረው የወጡትን የወረዱትን ሁሉ ሳይጨምር ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ በተለያየ መልክ እያገዙ በእግሩ አቁመው ያስኬዱት SOFIES (Society of Friends of Institute of Ethiopian Studies) ብቻ በባለፉት 50 ዓመታት ተግባራቱ ኢትዮጵያን ለራሳችንና ለዓለም በማሳወቅ ያደረገው ተግባር ራሱ እንኳን በዚች ቁንጽል ጽሑፍና ዕውቀት፣ በሰፊ ጥናትና ዳሰሳ ራሱ በአንድ መጽሐፍ የሚያልቅ ገድል አይደለም፡፡ ፕ/ር ሪቻርድ ከምርምር ሥራዎቻቸው ውጭ ለኢትዮጵያ ያበረከቷቸውን አስተዋፅዖዎች በዚህች የመታሰቢያ ጽሑፍ ተነስቶ የሚያልቅ አይደለምና መልካም ተግባሮቻቸውን ብቻ በጥቅሉ አስታውሰን ብናልፋቸው ይሻላል ብዬ በጥልቅ ምስጋና ብቻ ልለፈው ላሁኑ፡፡
ደግሞ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ብቻ አይደሉም፡፡ እንዳልኩት መላ ቤተሰባቸው ነው ሁለመናውን ለኢትዮጵያ ሰጥቶ የምናገኘው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች በአውሮፕላን ጉዞዎች መሐል ታዋቂውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ‹ሠላምታ› መጽሔት የገለጠ – ነፍሳቸውን ይማርና የሪቻርድ ፓንክረስት ባለቤት የነበሩትን የ Rita Pankhurstን ኢትዮጵያን የተመለከቱ፣ የኢትዮጵያን ሴቶች፣ የኢትዮጵያን አመጋገብ፣ ባህል፣ የቡና ሴረሞኒ፣ የባህል አልባሳት፣ ወዘተ የተመለከቱ ጽሑፎች ሳያገኝ አይከድንም፡፡ የሪታ ፓንክረስት ህይወት ያለፈው ከባለቤታቸው ሪቻርድ ፓንክረስት ሞት 2 ዓመት በኋላ ይመስለኛል፡፡
ፓንክረስቶች ያረፉበትን የመቃብር ሥፍራ በዓይኑ ማየት እና የኢትዮጵያን የፍቅር መንፈስ ከእነርሱ መቅዳት የፈለገ ሰው – በሥላሴ ካቴድራል መካነ መቃብር ሄዶ ቢያየው ብዙ የሚሰማው፣ የሚገባው፣ የሚማረው ነገር እንዳለ አምናለሁ፡፡ ይገርመኛል በእውነት፡፡ እኚህ የፓንክረስት ቤተሰቦች የዚህች እፁብ ድንቅ ሀገራችን የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ነገር የዘር ልክፍት ሆኖባቸዋል ማለት ነው? እያልኩ እስክገረም ድረስ ነው የሚደንቁኝ፡፡
የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ልጅ – አሉላ ፓንክረስትም ደግሞ አለ፡፡ እሱማ እዚሁ ኢትዮጵያ ተወልዶ፣ ኢትዮጵያዊት ሴት አግብቶ፣ ልጅ ወልዶ ከብሮ እዚሁ እየኖረ ያለ የፓንክረስቶችን የኢትዮጵያዊነት ፍቅር በልቡ አንግቦ የአያት ቅድመአያቶቹን አደራ እየተወጣ ያለ የኢትዮጵያ ወዳጅ ነው፡፡
ገና የሶሺዮሎጂ ትምህርቱን በድህረ-ምረቃ እያጠና (በተማሪ አቅሙ) 54ሺህ ብር የሚያወጣ የእኛን ቅርሶች በኦዲዮቪዥዋል መንገድ ቀርጾ ለማስቀመጥ (ቢጠፉ ቢሰወሩ ቢቃጠሉ እንኳ ለትውልድና ለታሪክ ለምርምር እንዲቆዩ አስቦ) ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም በሥጦታ ሲያበረክት በቦታው ነበርኩ፡፡ በእውነት በሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር በጀት ያለው ዩኒቨርሲቲና፣ በቢሊዮን ብሮች በጀት ያላት ሀገር ይህን ሳያስቡ – ይሄ የፕ/ር ሪቻርድ ልጅ አሉላ ፓንክረስት አስቦ አደረገ፡፡ በወቅቱ በእሱ ምግባር ልቤ ተነክቶ፣ በእኛ በራሳችን ደግሞ አዝኜ ነበር ከአዳራሹ የወጣሁት፡፡
ይህ አሉላ ፓንክረስት የአርበኞችን ልብስ ለብሶ፣ ጭንቅላቱን በኢትዮጵያ ባንዲራ አስሮ፣ የማሞ ውድነህን ‹‹አሉላ አባ ነጋ›› ግጥም፣ በሚገርም ኢትዮጵያዊ የጀግንነት መንፈስ በቃሉ አጥንቶ በመድረክ ያቀረበበትን ቪዲዮ ተመልክቼ እንባዬን መቆጣጠር ሁሉ ተስኖኝ ነበር፡፡
በአንድ ወቅት በሀገረ እንግሊዝ የለንደን ከተማ ባቡር ውስጥ ከፊቱ የተቀመጡ ሁለት ኢትዮጵያውያን ሴቶች አጋጥመውት – ስለሆነ ሰው እያወሩ – ከኋላ መቀመጫ ላይ ሆኖ ‹‹ውሸታም!›› ይላቸዋል፡፡ ዞር ብለው ያያሉ፡፡ ባቡሩን የሞላው ፈረንጅ ብቻ ነው፡፡ ‹‹በስመአብ!››  ብለው አማትበው አሁንም ወሬያቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ወሬው ሲያልቅ እየተከተለ ‹‹ውሸታም!›› ይላቸዋል በሹክሹክታ፡፡ ሴቶቹ ቀልባቸው ተገፍፎ እምዬ ማርያምን ሲጠሩ – አሉላ ሳቁን መቆጣጠር አቅቶት እየሳቀ በአማርኛ ያዋራቸዋል፡፡ ለንደን ላይ አግኝቶ ስላፈራቸው ኢትዮጵያውያን ወዳጆቹ ሲናገር ነው ይሄ፡፡ ገጠመኙ በሳቅ ይገድላል፡፡ የቀልድ፣ የጨዋታ አዋቂነቱ ሁሉ ገርሞኛል፡፡ ከእኛ እንደ አንዱ ነው፡፡ የፓንክረስቶች የትውልዱ ባለአደራ – አሉላ ፓንክረስት! እኛ ያላከበርነውን ስምና ታሪክ – ፓንክረስቶች ለልጃቸው መጠሪያነት ማዋላቸው ራሱ – ለገባው ትልቅ መልዕክት ነበር! አሉላ ፓንክረስትን ከነቤተሰቡ ፈጣሪ አብዝቶ እንዲባርከው እመኝለታለሁ፡፡
ሰው በሥራው እንጂ፣ በመንፈሱ እንጂ፣ በአስተሳሰቡ እንጂ፣ በአካሉ ዘለዓለማዊ ሆኖ አልተፈጠረም እንግዲህ፡፡ እና መሞት ለማንም አይቀርም፡፡ እኚህ ታላቅ የኢትዮጵያ አባት – ታላቅ የኢትዮጵያ ምሁር – ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትም – በመጨረሻ ሰው ናቸውና በሚወዷትና መላ ህይወታቸውን በሰጡላት የኢትዮጵያ ምድር – ልክ የዛሬ አራት ዓመት – በመካከላችን አረፉ፡፡
የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን ነፍስ፣ በመካከላችን መኖርን ብቻ ሳይሆን በመካከላችን ማረፍን መርጠው አካላቸውን በዚህች ድንቅ ኢትዮጵያዊ ምድራችን ያሳረፉትን የፓንክረስትን ቤተሰቦች ነፍስ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ አምላክ – ሠላሙን፣ እረፍቱን፣ ሐሴቱን በአፀደ ገነቱ አብዝቶ ይስጥልን!
የፓንክረስቶችን ፈለግ የሚከተል፣ በኢትዮጵያ ፍቅር ሁለመናው የሚነድድ፣ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ትውልድን ያምጣልን የኢትዮጵያ አምላክ፡፡
የተሰጠንን እንድናውቅ፣ ያለንን እንድንጠቀምበት፣ በጠላቶቿ ፊት ጸንተን እንድንቆም የምንችል ያድርገን ፈጣሪ የኢትዮጵያ አምላክ፡፡
Professor Richard Pankhurst – a lifetime friend of Ethiopia – a University professor and researcher – 1927-2017 – May Almighty God bless his soul in peace in Heaven.
አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic