>
5:13 pm - Thursday April 19, 2784

እንደምን ስለምንስ  ፈራን … ? ( አቶ ሙሼ ሰሙ)

እንደምን ስለምንስ  ፈራን … ?

     አቶ ሙሼ ሰሙ

ሁሉም ነገር እውነት እንዲመስል የሚፈለግበት፣ አንድም ነገር እውነት ያልሆነበትና ሁሉም  ዓይነት ቅጥፈት የተፈቀደበት ዘመን ላይ ደርሰናል። የሀገራች አሳሳቢ ጉዳይ “እያነቡ እስክስታ”  አየሆነ ነው ወይስ ፍርሃታችን ቅዠት ነው?!
በተለምዶ በስራም ይሁን፣ በፖለቲካ ወይም በማህበራዊ ጉዳይ ከማገኛቸው ሰዎች ጋር በተናጠልም ሆነ በቡድን ስለ ሀገራችን ስንወያይ፣ ልዮነት ቢኖረንም እንኳ በአብዛኛው ተስፋ የሞላበትና ራዕይን የሰነቀ መሆኑ የተለመደ ነበር፡፡  አሁን ግን ውይይታችን ከሰከነ፣ ምክንያታዊ ወይይት የራቀና ፈር የሳተ፣ በጣም ጨለምተኛ፣ በፍርሃትና በስጋት የተሞላ እየሆነ ነው፡፡ የሀገራችን መጻኢ አጣ ፈንታ ሲወሳ በርካታ ሰዎች ላይ የሚነበበው ትካዜ፣ ከአንደበታቸው የሚወጣው ምሬትና ተስፋ መቁረጥ የሚረብሽ ነው፡፡ እንዴት እዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ወደቅን?
ዛሬ  ጸጸት፣ ተስፋ መቁረጥና ጨለምተኝነት በኢትዮጵያውያን ዘንድ በስፋት የሚንጸባረቅ ዝንባሌ ነው፡፡ እንደ ዘንድሮ ፈርቼና ሰግቼ አላውቅም የሚለው ሕዝብ ከልሂቅ እስከ ደቂቂ፤ ከሀብታም እስከ ድሃ የዘለቀ ነው፡፡ አቅም አለኝ በሚለው ዘንድ የተያዘው ሩጫ ፓስፖርት ማደስ፣ ቪዛ መጠየቅ፣ የፕሌን ትኬት በመቁረጥ ከማይታየውና ካልተጨበጠው አደጋ ቀድሞ ለመሸሽና ለማምለጥ ይሆን? ሀገራችንን ምን ነካት? ሕዝባችንን ምን ነካው? በጥቅሉ ምን ተፈጠረ? ምን እየሁንን ነው? እንደ ቡድን ወይም እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ ህዝብ ለምን፣ ማንንና ምንን ነው የፈራው? እራሳችንን መመርመር ያለብን ጉዳይ እንዳለ ጮክ ብሎ እየተሰማኝ ነው፡፡
ስጋት ያለና ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ነገር ግን እራሳችን ከራሳችን እንዴትና ወዴት እናሸሻለን? ሸሽተንስ መጨረሻችን ምንድን ነው? ሀገር የሌለው ሕዝብና ስሩ የተነቀለ ዛፍስ አንድ አይደለም ወይ? ሞት ከተፈራስ በቁም መሞት ማለትስ ሀገር የፈረሰ እለት አይደለም ወይ? በፍርሃትና በስጋት ተሸብበን፣ ተሸማቅን፣ ከሽሽትና እርስ በርስ ከመወነጃጀል ውጭ እንዴት ሌላ አማራጭ አይኖረንም? ችግሩንስ ጥለንና ሸሽተን ለማን እያዋልነውና እያሳደርነው ይሆን? መወያየት፣ መደማመጥና መከባበር አቅቶን እራሳችን በቆሰቆስነው እሳት ሕዝብ ተላልቆ ሀገር ወድሞ፣ ሁሉም ነገር ፍርስራሽ ከሆነ በኃላ እንደ አዲስ ሕይወት ለመጀመር ከስደት ልንመለስ እያሰብን ይሆን? በድፍረት ልንነጋገርበት የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡
ለምን ፈራን? ለምንስ ሰጋን? ፍርሃቱን እንጋፈጠው ወይስ እንደፈራን እያሳሳቀ ይውሰደን?  በፍርሃትና ስጋት ተሸብበን እስከየት እንዘልቃለን? ያለ ስድብ ትዕቢትና ዘለፋ ስለ ሀገራችን መጻኢ እድል እንነጋገር።
Filed in: Amharic