>
5:13 pm - Saturday April 19, 2656

«የጂሃድ አካዳሚ — የአይ ኤስ መነሻ»  (በጋዜጠኛና ደራሲ - ኒኮላ ሄመን) - አሰፋ ሀይሉ

«የጂሃድ አካዳሚ — የአይ ኤስ መነሻ» 

(በጋዜጠኛና ደራሲ – ኒኮላ ሄመን)
አሰፋ ሀይሉ

አንዳንዴ ያስቀኑኛል፡፡ እነዚህ የምዕራቡ ዓለም ጋዜጠኞች፡፡ ከሀገራቸው ወጥተው ሁለነገራቸውን ትተው በሰው ምድርና ህዝብ መሐል ለዓመታት ይኖራሉ፡፡ ጦርነት አመጽ መቅሰፍት አይበግራቸውም፡፡ ደፋሮች ናቸው፡፡ ስለ ራሳቸውና ስለ ዓለም በቂ ዕውቀት አላቸው፡፡ በዚያ ላይ የየተሠማሩበት ጉዳይ ምሁር ናቸው፡፡ አንጠርጥሮ-አዋቂዎች፡፡ ከዚህ ይበልጥ ደግሞ የተግባር ዕውቀታቸው፡፡ ያስደንቃል በእውነት፡፡ ፈልፍለው የሚዘግቡት ነገር ብዛቱ፡፡ አለማለቁም፡፡ ለየሀገራቸው እንዴት ያሉ ሳተና የመረጃ ምንጮች ሆነው እንደሚያገለግሉ ሳስብ ይደንቁኛል ያገር-ፍቅራቸው፡፡ የሙያ ፍቅራቸው፡፡ እና የህይወት-ዘመን ኮሚትመንታቸው! እነዚህ አስደናቂ ጋዜጠኞች ናቸው የዓለምን ትኩረት፣ ዕውቀትና ፖሊሲ በማያወላዱ መረጃዎቻቸውና ትንተናዎቻቸው ወዳሻቸው የሚያሠግሩት፡፡ /የኛ ሀገርስ ጋዜጠኞች? በጥያቄ ልለፈው፡፡/
ይሄ  ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ – ኒኮላስ ሄኒን – ጋዜጠኛ ብቻ አይደለም፡፡ በዓለማቀፍ ግንኙነት መስክ በትምህርቱ የገፋ፣ በዩኒቨርሲቲዎች እየተገኘ ልምድና ዕውቀቱን የሚያካፍል ምሁርም ነው፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ እነዚህንም ብቻም አይደለም፡፡ እንዲያውም ልዩ የሚያደርገው ከጉድ የተረፈ ሰውም መሆኑ ነው፡፡ ኒኮላስ ሄኒን ከ13 ዓመታት በላይ ለተለያዩ የምዕራብ ሚዲያዎች የውጭ ዜና ዘጋቢ ሆኖ በመካከለኛው ምስራቅ ሠርቷል፡፡ የኢራቅን ወረራ፣ የሳዳምን ሽሽትና ስቅላት፣ የሶሪያን አመጽና ጦርነት፣ የቱርክንና የኩርዶችን፣ የእስራኤልና ፍልስጥኤሞችን፣ ሌላም ሌላም የአካባቢውን አስከፊና አይረሴ ዜናዎች በየሥፍራው እየተገኘ ሲዘግብና ትንታኔዎችን ሲሠራ ኖሯል፡፡ በመጨረሻ በሶሪያ ራቃ ውስጥ በአይሲሶች (አይ ኤሶች) ቁጥጥር ሥር ባለ የጦርነት ወረዳ ውሰጥ ተፍ ተፍ ሲል ተገኘ፡፡ እና ለ10 ወራት ታሠረ፡፡ ማለትም አድራሻው ባልታወቀ ሥፍራ በአይ ኤስ ጂሃዲስቶች ታገተ፡፡
ከሄኒን ጋር አብረውት የታሰሩ የምዕራቡ ዓለም ሰዎች ነበሩ፡፡ አሜሪካውያን፣ እንግሊዛውያንና አንድ ራሺያዊ – ሁሉም በቪዲዮ ካሜራ ፊት እየተቀረፁ – በአይ ኤስ አራጆች አንገታቸው እየተቀላ ወደማይመለሱበት ዓለም ተሻግረዋል፡፡ እሱን ግን አንድዬ ቀንህ አልደረሰም ሲለው፣ ብዙዎችን ወደሞት የሸኙትን አጋቾቹን ልብ አራራለት፡፡ እና ወደ ሀገሩ በሰላም ተሸኘ፡፡ ያገሩ የፈረንሳይ መንግሥት በእርግጥ ዜጎቹን ያስለቀቀው ታዋቂ ሽማግሌ ልኮ፣ ሚሊዮን ዶላሮችን በምስጢር ከፍሎ (እርሱ በዚህ መጽሐፉ ላይ በግልጽ ባይለውም)፣ እና ተደራድሮ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ይሄን ጋዜጠኛ ጨምሮ ታሳሪዎቹን የለቀቁት አይኤሶች – ተደራዳሪውን ቄስ ግን አገቷቸው፡፡
ይሄ መጽሐፍ እስከተጻፈበት (እስከ 2015) ድረስም እኚያ ቄስ (ፓዎሎ) የደረሱበት አልታወቀም፡፡ ጋዜጠኛው በመጽሐፉ መጨረሻ ስለ እርሳቸው ውለታና አሳዛኝ አጠፋፍ የመታሰቢያ እንባውን አኑሮላቸዋል፡፡ ልብ ይነካል፡፡ ግን ፈጣሪ አንዳንዴም ሲያተርፍህ ዕቅድ አለው፡፡ ያን የእግዜሩን ዕቅድ ቶሎ ስትደርስበት እንዲህ እንደ ኒኮላስ ሄኒን ጉድ የሚያሰኝ መጽሐፍ ትጽፋለህ፡፡ እና ደረትህን ነፍተህ ትንቀሳቀሳለህ፡፡ ከዚህ በኋላ የፈለገ ያግተኝ፡፡ ብሞትም አይቆጨኝ፡፡ እያልክ፡፡ ደሞ ስትፈልገው እኮ ይሸሻል፡፡ ይሄ ሞት የሚሉት ሠላቢ፡፡ ስሙን ቄስ ይጥራውና!
ስለ አረቦችና እስላማዊው ዓለም፣ ስለ አካባቢው ጦርነትና ሠላም ምንጮችና ውጤቶች፣ ስለ እያንዳንዱ ሀገር የፀጥታ ቁጥጥርና የህዝቡ ኑሮ መታወክ፣ የሥልጣን አሰላለፎችና አምባገነናዊ፣ ጎጣዊ፣ ርዕዮተዓለማዊ፣ ሐይማኖታዊ፣ ቡድናዊ፣ ብሔራዊ፣ ሀገራዊ፣ ዓለማዊ፣ መንፈሳዊ፣ እና ድንበር ዘለል የሆኑ ብዙ ሻጥሮችንና ክፋቶችን በተለመከተ ጥልቅ መረጃውና ዕውቀቱ አለው የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ኒኮላስ ሄኒን፡፡ ደሞኮ ትህትናው ደስ ብሎኛል፡፡ አውቃለሁ እንዲህ ነኝ አይልህም፡፡ ራሱም አልልም ይላል ሲጀምር፡፡ ሌሎችን ነው የሚያመሰግነው፡፡ ለቃለመጠይቅ ስለተባበራችሁኝ፡፡ እውቀታችሁን ስላዋሳችሁኝ፡፡ ልባችሁን ከፍታችሁ ስለነገራችሁኝ፡፡ አመሰግናለሁ እያለ፡፡ ይህን መጽሐፍ ከጻፈ በኋላ ብዙ ሽልማቶች እንደተዥጎደጎዱለት ሳውቅ አልገረመኝም፡፡ ይገባዋል፡፡
የመጽሐፉን ርዕስ ‹‹የጂሃድ አካዳሚ›› ያለበትን ምክንያት መጽሐፉን አጋምሰህ ነው የምትደርስበት፡፡ እንደዚህ ጋዜጠኛ መረጃ ከሆነ፣ ብዙዎቹ የአይ ኤስ ‹‹አሸባሪዎች›› አንድ የሚያመሳስላቸው ታሪክ አለ፡፡ ያም እንደ ‹‹ካምፕ ቡካ››፣ ‹‹ጓንታናሞ››፣ ‹‹አቡግራዪብ››፣ ወዘተ.በመሳሰሉት የምዕራቡ (የአሜሪካ) ስመጥር የማሰቃያ እስርቤቶች ውስጥ የታሰሩ፣ ወይ በሌሎች የሶሪያና ኢራቅ ታዋቂ እስርቤቶች ታስረው የወጡ መሆናቸው ነው፡፡ እና ደራሲው ያናገራቸው የአይ ኤስ መሪዎች (እና ዌይስማንና ሐሰን የተሰኙ በጥምር ሥራቸውን ያሳተሙ የመካከለኛው ምስራቅ ተመራማሪዎች የጠቀሷቸው እማኞች) የሚናገሩት ነገር – እነዚያ እስርቤቶች – ለሁሉም ዓይነት አሸባሪ ኃይለኛ የመገናኛና መማከሪያ አዳራሽ ሆነው ማገልገላቸውን ነው፡፡
ከእነዚያ እስርቤቶች ጥብቅ አጥሮች በስተጀርባ ሆነው እየተማከሩ ነው ማለት ነው እንግዲህ ብዙዎቹ ‹‹አሸባሪዎች›› የረቀቁ የአይ ኤስ ሽብር ቡድን ዓላማዎችንና እንቅስቃሴዎችን የቀመሩት፡፡ አንዳንዶቹ ሲነግሩት ለጋዜጠኛው – እነዚያ እስርቤቶች ውስጥ መታሰራቸው – በመስክ ላይ ቢሆኑ ኖሮ ከሌላ ተቀናቃኝ አሸባሪ ወይም ከሚያሳድዷቸው መንግሥታት ሊሰነዘርባቸው ይችሉባቸው ከነበሩት ጥቃቶች አድኗቸዋል፡፡ በተለይ ‹‹ካምፕ ቡካ››ን ይጠሩታል፡፡ ብዙዎቹ በኩራት ካምፕ ቡካ ነበርኩ ነው የሚሉት፡፡ ልክ አንድ የአሜሪካ ሚሊቴሪ በኩራት – ‹‹ዌስት ፖይንት›› ነበርኩ፣ ወይ ‹‹ሳንድኸርስት›› ነበርኩ – እንደሚልህ ፡፡ ለአይ ኤሶች ደግሞ የአሜሪካኖቹ እስርቤት ‹‹ካምፕ ቡካ›› ታዋቂ የጂሃድ አካዳሚ ሆኖላቸው ነበር፡፡ አጃኢብ አሰኝቶኛል፡፡
እና በፍሬንች ጉያና ላይ አሸባሪዎች ብቻ የሚታሰሩት – ልክ እንደ አሜሪካኖቹ ጓንታናሞ ያለ ልዩና ጥብቅ፣ ከህገመንግሥታቸው የሰብዓዊ መብት ጥበቃ የህግ ማዕቀፎች ውጭ ሆኖ የሚታነፅ እስር ቤት ለማቋቋም የከጀሉትን የራሱን የፈረንሣይ መንግሥት ይመክራል ጋዜጠኛው፡፡ ሀሳባቸውን እርግፍ እንዲያደርጉት፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ ለአሸባሪ የተለየ እስርቤት መክፈት – ሌላ የጂሃድ አካዳሚን እንደ መክፈት ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ጓንታናሞ በኦባማ ሥልጣን ማብቂያ ላይ በይፋ መዘጋቱን የሰማሁ መሰለኝ፡፡)
ጋዜጠኛ ኒኮላስ ሄኒን – ብዙ መረጃዎችን እየፈተለ የሚያስረዳን ነገር – የመጀመሪያዎቹ የአሸባሪ መተላለፊያ ጎዳናዎች – ወይም ቀዳሚዎቹ ‹‹ጂሃዲስት ሃይዌይስ›› በመካከለኛው ምስራቅ የተከፈቱት – የኢራቅና የሌቫንት እስላማዊ ካሊፌትን እመሰርታለሁ የሚለው አይ ኤስ ከመመሥረቱም – የአልቃኢዳ የመካከለኛው ምሥራቅ ቅርንጫፍ ካሊፌት ክንፍ የሆነው ጃባት አል ኑስራ፣ ወይም እነ አህራር አሽ-ሻምና ኢዝላሚክ ፍሮንት፣ ሌሎችም ብዙ (ደራሲው ስምና ዝርዝር መረጃዎችን እየጠቀሰ የሚገልጻቸው) ጂሃዳዊ ቡድኖች በአካባቢው ላይ ከመመሥረታቸው ከዓመታት በፊት ነው፡፡
እንደ ደራሲው አባባል ‹‹ጂሃድ›› በእስልምና ያለው ትክክለኛ ትርጓሜ ‹‹ለተሻለ ህይወት መንፈሳዊ ጥሪህንት ተከትለህ አቅምህ የፈቀደውን መልካም ተግባር መፈጸም›› እንደሆነ ይናገራል፡፡ እና – የጂሃድን ቀና ትርጓሜ ቀይረው የደም ማፍሰስና የጠላት ማጥፋት፣ እና የሌላም የኃይል ተግባራት ሁሉ ማመካኛ ያደረጉት በየዘመኑ የመጡ መንፈሳዊ ቅዱስ ቃሎችን ለጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች ማሰባሰቢያነት ዓላማ ለመጠቀም የፈለጉ አስተምህሮቶች (ወይም እኩይ ሰባኪዎች) ናቸው፡፡ ይህ ሃሳብ በእርግጥ ከዚህ ቀደም በታሪቅ አሊ (‹‹ክላሽ ኦፍ ፈንዳሜንታሊዝምስ››) መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ ያገኘሁት ቢሆንም፣ በሌሎች ብዙ ድርሳኖች ላይ ግን ከዚህ በተቃራኒው ጂሃድ – በትክክልም የመካከለኛው ምስራቅ አሸባሪዎች እንደሚጠቀሙበት – ፅንፈኛ የጥፋት ጥሪን የሚያስተጋባ ዶክትሪን እንደሆነ ማንበቤንም አስታውሳለሁ፡፡ የደራሲውን ትህትና አስቀድሜያለሁ፡፡ ለእስልምና እምነት ተከታዮች ከመጠንቀቅ የተነሳ በብዙ ነገሮች ከመፈረጅ መንገድ እየራቀ የነገሮቹን በጎ ጎን ብቻ እየመረጠ የሚጽፈውን ነገር ሳላደንቅለት አላልፍኩም፡፡
ወዳነሳሁት ነጥብ ስመለስ – ደራሲው በብዙ መረጃዎች አስደግፎ የሚያስረዳን – ኋላ ላይ ምዕራቡን ዓለም ያንቀጠቀጠው ‹‹አይ ኤስ›› የተሰኘው የሽብር ቡድን መሠረቱን የጣለው ከመመሥረቱ 10 ዓመታት በፊት ነው፡፡ ያስጀመሩትም የመጀመሪያ ሰው ተቀማጭነታቸው በሶሪያ፣ ትውልዳቸው ኩርድ የሆኑ ‹‹ማህሙድ አቡ አል-ቃቃ›› (በእውነተኛ ስማቸው ‹‹ማህሙድ ጉል አግሃሲ››) የተባሉ ሼህ ናቸው፡፡ እኚህ ሼህ ሳዳም ሁሴን በአሜሪካው ጥምር ጦር ሊወረር ሲል – ለ20 ዓመት በተለያየ ውጊያ የተሰላቸ ጦሩ ወጥሮ እንደማይዋጋለት በመገንዘቡ – በዓለም ሁሉ ላሉ የእስልምና ተከታዮች በአሜሪካ ላይ የተቀደሰ ጦርነት (ጂሃድ) እንዲያካሂዱለት ጥሪ ሲያቀርብ – በጥሪው መሠረት ሊደርሱለት የተነሱ ናቸው፡፡ ወይም ተብሎ የታሰበው እንደዚያ ነበር፡፡ እንዴት አድርገው?
በሶሪያ የሚኖሩ ፈቃደኛ ጂሃዲስቶችን ከመላው ሶርያ በመመልመል – የሶሪያን ድንበር አሻግረው ወደ ኢራቅ ለማስገባትና በአሜሪካኖች ላይ ለማዝመት ነበር እቅዳቸው፡፡ እኚህ ሼህ ቀድሞውኑ – በሸሪዓ ህግጋት የሚተዳደር እስላማዊ መንግሥት በሶሪያና ኢራቅ መመስረት አለበት እያሉ የሚሰብኩ መንፈሳዊ አባት ነበሩ፡፡ የስብከት ካሴቶችና ሲዲዎቻቸው ከሶሪያ አልፈው እስከ ግብጽና ፓኪስታን፣ ኢራቅና አፍጋኒስታን ድረስ በስፋት የተሰራጩ ሰውም ናቸው፡፡ የዚህ ሰው ተጽዕኖ የቱን ያህል እንደሆነ የሚገባን – የተለያዩ ወደ አይ ኤስ እናቀናለን ብለው የሚያዙ ምዕራባውያን ወጣቶች፣ እና ለአይ ኤስ ተሰልፈው ሲዋጉ የተማረኩ ጂሃዲስቶች – ከብዙዎቹ ጋር ከተያዙ የግል ንብረቶች ውስጥ – እነዚያ የሼህ ማህሙድ አቡ አል-ቃቃ የእስላማዊ መንግሥት ስብከት ሲዲዎች መገኘታቸውን ጋዜጠኛው ሲነግረን ጭምር ነው፡፡ እንግዲህ ከስብከትም አልፈው በተግባር ገቡበት ማለት ነው፡፡
ሼህ ማህሙድ አቡ አል-ቃቃ የአይ ሲስን መሠረት የጣሉበት መንገድ ረቂቅና ሠንሰለታማ ነበር፡፡ በሶሪያ ውስጥ ያሉ – እና የሳዳምን ጥሪ ተከትሎ – ድንበር ተሻግረው በእስላማዊ የአጋርነት ስሜት ለመቆም የተነሳሱ ‹‹የሐይማኖት ፅንፍ የረገጡ›› ወጣቶችን ተቀብሎ የሚያስተናግድ በአሌፖ መስጊድ የሚተዳደር አንድ የእንግዳ ማረፊያ ተዘጋጀ፡፡ ያ ማረፊያ ከየመጡበት ተቀብሎ ያሳድራቸዋል፡፡ ከጥቂት ቀናት ቆይታ በኋላ ደግሞ – በኤፍራጠስ ሸለቆ አልፎ በሚጓዝ አውቶብስ አሳፍሮ፣ በራቃ እና ዴር ኤዝ-ዙር ከተሞች በኩል አሳልፎ፣ አቡ ከማል ወደሚባል ጠረፋማ ሥፍራ ያደርሳቸዋል፡፡ (በነገራችን ላይ በመጨረሻም ወደ ኢራቅ የሚገቡት ይህችን አቡ ከማልን ተሻግረው ነው)፡፡
የጂሃዲስቶቹ ጉዞ አቡ ከማል ላይ አይጠናቀቅም፡፡ ከዚያ ደግሞ በምስጢር የሚያገኟቸው የሼሁ አገናኞች አሉ፡፡ በእነርሱ አማካይነት በመኪና ተጭነው በአል-ቃይምና በሃዲታ አድርገው ወደ በደቡባዊ ፋሉጃህ ይወሰዳሉ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ እንደየምርጫቸውና ዕድላቸው – ከፊሎቹ በአል አንባር አውራጃ ወደሚገኙ ማሰልጠኛዎች ሲላኩ፣ የተቀሩት ደግሞ ከተወሰነ ቆይታ በኋላ የኢራቅን ድንበር ተሻግረው በአቡ ግራይብ ወይም አማሪያህ አውራጃዎች ወደሚገኙ ተመሳሳይ ካምፖች ይላካሉ፡፡
እንግዲህ በግዛታቸው የምታርፍ ወፍ ራሱ አትቀራቸውም የሚባሉት የሶሪያው በሽር አል-አሳድ ወታደራዊና የሥለላ ተቋማት እንዴት እኚህን ሼህ (ማህሙድ አቡ አል-ቃቃን) አልደረሱባቸውም? ያውም በግልጽ የሶርያን መንግሥት አስወግደን የሸሪዓ መንግሥት እንመሥርት እያሉ በአል-አሳድ ላይ አደጋ የሚጋብዝ የአመጽ ጥሪ እያስተላለፉ እንዴት አልተከታተሏቸውም? እንዴትስ ያለ በሽር አል-አሳድ ዕውቅና – በእነዚህ የሶርያ አካባቢዎች ሁሉ እንደልባቸው ጂሃዲስቶችን ማዘዋወር፣ ማሰልጠን፣ ማስታጠቅ፣ እና ድንበር እያሻገሩ ወደ ኢራቅ አስርገው ማስገባት እንዴት ቻሉ? ለምን ዝም አላቸው?
ልብ እንበል፡- ‹‹ለምን ዝም አላቸው?›› ነው እንጂ፣ ‹‹እንዴት አላወቀም?›› አይደለም ጥያቄው፡፡ አል-አሳድ እንኳን ይቺንና… የወፍ ወንዱን ያውቃል – የሚባልለት ዓይነት ሰላቢ ነው፡፡ ከልምዱም እንደታየው በአረመኔያዊ መንገድ ተቀናቃኞቹን ለመደፍጠጥ የሚያሳየው ርህራሄም የለም፡፡ መጠነ-ሰፊና ውስብስብ የስለላ መዋቅር ዘርግቷል፡፡ ኋላ በመጽሐፉ እንደምናገኘው – እንኳን ይህን ሽማግሌ ሼህ ይቅርና – በእነ አልቃኢዳና አይ ኤስ ውስጥ የራሱን ሰዎች በብዛት አስርጎ ለማግባት የተሳካለት ተንከሲስ ነው አል-አሳድ፡፡ እና ታዲያ አሁን – እንዴት ዝም አለ? ምናልባት በሽር አል-አሳድ ከተቀናቃኙ ከሳዳም ይልቅ – የአሜሪካ ጥላቻው በለጠበት? እያለ ይጠይቃል ጋዜጠኛው፡፡
ምናልባት አዎ፡፡ ግን ያ ብቻ አልተዋጠላቸውም የአካባቢውን (የጆርዳን፣ የአሜሪካ፣ የፈረንሣይ፣ የእስራኤል፣ የቱርክና የሌሎችም) በአካባቢው ያሉ ምስጢራዊ የስለላ ቡድኖች፡፡ ጋዜጠኛው እነዚህንም በስም በስማቸው እየጠራ ነው የሚነግረን፡፡ እና በመጨረሻ የጆርዳን የስለላ ሰዎች የደረሱበትንና ኋላ በሌሎቹ የተረጋገጠውን ምስጢር ያካፍለናል፡፡ ለካስ ሼህ ማህሙድ አቡ አል-ቃቃ – የበሽር አል-አሳድ ‹‹ማማለያ ወጥመዱ›› (ወይም በሥለላው ሰዎች አጠራር ‹‹የማር እንስራው››) ነበሩ፡፡
ሼህ ማህሙድ አቡ አል-ቃቃ በሶሪያ ምድር የሚገኙና – እስላማዊ የሸሪዓ መንግሥት ለመመሥረት ሲሉ መንግሥትን ለመፋለም ቆርጠው ለሚነሱ ጽንፍ-የረገጡ ጂሃዲስቶች ጥሪ በማቅረብ ከየግዛቱ እየመነጠሩ፣ እየለቀሙ፣ እያግተለተሉ ይሰበስብለታል – ለበሽር አል አሳድ፡፡ በማሰልጠኛ ካምፖች አስገብተው ስለ እያንዳንዱ ጂሃዲስት አቋም፣ የምሬት መጠን፣ የተግባር ዝግጁነት፣ ወዘተ. መረጃዎችን ለበሽር አል-አሳድ በምሥጢር ያቀብሉታል፡፡ በቋሚነት ማለት ነው፡፡ እና ሼሁ – ለአል-አሳድ እያገለገሉ የነበሩት ትውልዱን እንደ ማጣሪያ ወንፊት ሆነው ነበር፡፡ እውነት ከሆነ እንግዲህ – ሼሁ ልክ የሆነ የተላጠ ሽንኩርት በቅቤ ለቅልቀህ ከሩቅ እያሸተትካት ወደ ሽንኩርትህ ስትመጣልህ በወጥመድህ እንደምትይዛት የጓዳ አይጥ አድርገው ሲጫወቱበት ኖረዋል ማለት ነው የሶሪያ የአመጽ ኃይል ይሆናል ያሉትን ወጣት ሁሉ፡፡
አሳድ ለሥልጣኑ እጅግ የሚፈራቸውንና ዓለማዊ መንግሥቱን ለመጣል ብረት ታጥቀው ለመነሳት የቆረጡበትን እስላማዊ አክራሪዎች፣ በጂሃዲስት ስብከትና ጅንጀና አማካይነት እያማለሉ፣ ከያሉበት እየለቀሙ ያወጡለታል ሼህ ማህሙድ አቡ አል-ቃቃ፡፡ እና ጂሃዲስቶቹን አሰልጥነው፣ አስታጥቀው፣ ድንበር አሻግረው ወደ ኢራቅ ምድር እስኪያገቧቸው ድረስ በሽር አል-አሳድ በትዕግሥት አድፍጦ ይጠባበቃል፡፡ ያ የጂሃድን ጥሪ ተከትሎ ገሎ-ለመሞት ዝግጁ የሆነ ቆራጥ ወጣት ግን እንዳሰበው ኢራቅም፣ ጀነትም ሳይገባ – ለበሽር አል-አሳድ ገዳይ ስኳዶች ተላልፎ ይሰጣል፡፡ በመንገድ ይጠለፋል፡፡ እና የበረሃ ሲሳይ ሆኖ ይቀራል፡፡ ግፍ ነው በእውነቱ፡፡ አረመኔያዊ ግፍ፡፡ ኃይለኛ ማጣሪያ ግን ነው፡፡ ኃይለኛ ፊልተር፡፡ ከዚህ በላይ የስይጥንናን ደረጃ የተላበሰ – የቆረጡ ተቃዋሚዎችህን የምታስወግድበት ማጣሪያ ማሽን ከየት ይገኛል?
(ይህን ነገር ሳስብ – በኢህአዴግ ዘመን የትጥቅ ትግል እናደርጋለን እያሉ ጫካ ገብተው ወጣቶችን በመመልመል ለወያኔ-ኢህአዴግ ጥይትና ምርኮ አሳልፈው የሚሰጡ ነፃ-አውጪ ግንባሮች፣ የአርበኞች ግንባሮች፣ ወዘተ አይኖሩ ይሆን? የሚል ሀሳብ ድንገት ሽው ብሎኝ አለፈ፡፡ ክፋትን ለመኮረጅ መቼም ተወዳዳሪ የለንም – እና ይህ የማናደርግበት ምን ርህራሄ ኖሮን? አንድዬ ከክፉዎች የክፋት ሴራ ይጠብቀው እንጂ ህዝባችንን! ሌላ ምን ማለት ይቻላል?)
የሚገርመው ግን የሼሁ መጨረሻ ነው፡፡ በአንዷ ዕለተ-አርብ ወደ ሀገር-አማን ብለው ወደ መስጊድ ለጁምዓ እየሄዱ ነበር፡፡ ከዓይን እማኞች እንደተረጋገጠው፡፡ በመሐል አንድ ወጣት የሼሁን ስም ጠርቶ ሰላምታ አቀረበላቸው፡፡ እና ምላሻቸውን ሳይጨርሱ መሣሪያ መዝዞ በእሩምታ ተኩስ ሰውነታቸውን ወንፊት አድርጎት አመለጠ፡፡ ይህ መጽሐፍ እስከተጻፈበትም ጊዜ ያ የሼህ ማህሙድ አቡ አል-ቃቃ ገዳይ ማንነትና የገባበትም አልታወቀም፡፡ ኃላፊነቱን የወሰደ አካልም የለም፡፡
ጋዜጠኛው ግን ጥያቄውን አላቆመም፡፡ የሼህ አል-ቃቃ ገዳይ በፍጹም በሽር አል አሳድ ሊሆን አይችልም፡፡ ሌሎቹም ገና የሼሁን ምስጢራዊ ተግባር የተረዱበት ጊዜ ነበር ለማለት የሚያስችል ፍንጭ እንኳ አልተገኘም፡፡ እና ማን ሊገድላቸው ይችላል? ድንገት ለአሳድ ገዳዮች ተላልፎ ተሰጥቶ በተዓምር የተረፈ አንድ ጂሃዲስት ይሆን የተበቀላቸው? ማንም መልሱን የሚሰጠኝ አላገኘሁም – ብሎ ይደመድመዋል ታሪኩን፡፡ በጥያቄ፡፡
እኔ ደሞ ሌላ ጥያቄ ጨመርኩበት፡፡ ግምቱ እውነት ከሆነ ግን… ‹‹ስለት ድግሱን፣ ደባ ራሱን›› ማለት ይሄው ነው እንግዲህ አይደል? – የሚል ጥያቄ፡፡ የሆነ ሆኖ ግን እኚህ ሰው ናቸው የአይ ኤስን ‹‹የሽብር ቡድን›› ሀሳብና የመተላለፊያ ጎዳናዎችን ‹‹ጂሃዲስት ሃይዌይስ›› ቀይሰው ያለፉት፡፡ ምናልባትስ ይህ ሁሉ ውሸት ቢሆን? አላውቅም፡፡ አትፍረድ ነው ወንድሜ፡፡ ብዬ ብዬ በእግዜሩ ሥራ ደሞ ጥልቅ ማለት ይመረኝ? ሆሆይ…!
ደራሲው በአንዲት መጽሐፍ ለአንባቢ ያከማቸው የመረጃ፣ የዕውቀት፣ የልምድ መዓት ያስደንቃል ብዬአለሁ በመነሻዬ፡፡ ብዙ ሃሳቦች እየመጡብኝ የቱን እንደምመርጥ እየተቸገርኩ፣ እንደ ፊልምም እየጓጓሁ ነው ያነበብኳት ይቺን በመረጃ የታጨቀች ባለ 150 ገጽ መጽሐፍ፡፡ ቀኔን ፈጅታ፣ እንቅልፌንም ልትነጥቀኝ ለጥቂት ተረፍኩ፡፡ እኩለ-ሌሊት አለፈኝ፡፡ ግን ተመስገን አልኩ፡፡ መጽሐፏ አልቃለች፡፡ ሃሳቦቿ ግን ይቀጥላሉ፡፡ በሌላ ጊዜ፡፡ በአግራሞት ይሄ ከሞት-ተራፊ ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ ኒኮላ ሄመን ሽልማት ሲያንሰው ነው፡፡ ከፈረንሳይኛ ወደ እንግሊዝኛ የተረጎመለት ማርቲን ማኪንሰንም ምስጋና ይገባዋል፡፡ ሁለቱንም አመሰግኜ ተሰናበትኩ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ 
መልካም ቅዳሜ፡፡
Filed in: Amharic