>

“የትግራይ ህዝቡና ህወሓት አንድ ቢሆኑ ኖሮ ጦርነቱም እንደዚህ ባለ አጭር ጊዜ አይጠናቀቅም ነበር...!!!" (ኢንጅነር ግደይ ዘርዓጽዮን)

“የትግራይ ህዝቡና ህወሓት አንድ ቢሆኑ ኖሮ ጦርነቱም እንደዚህ ባለ አጭር ጊዜ አይጠናቀቅም ነበር…!!!”
ኢንጅነር ግደይ ዘርዓጽዮን

“የትግራይ ህዝብ ልጆቹን በትጥቅ ትግሉ ገብሮ ያተረፈው ነገር ቢኖር ጭቆና የፍትህ እጦት ፍርሃት ታፍኖ መኖርን ነው” ያሉት ኢንጅነር ግደይ “አሁን ህወሃቶች ህዝባችን ብለው ለተሸሸጉበት ምን ሰጡት ?ህወሓቶች የዘመናት ድርጊታቸው ለዚህ አሁን ላሉበት ውርደት ፣ሞትና መደበቅ ዳርጓቸዋል” ያሉት አቶ ግደይ፤ ህወሓቶች ከስልጣን በላይ የሚያስቀድሙት  ነገር ስለሌለ አሻፈረኝ ብለው እዚህ መሰል ጦርነት ውስጥ ገብተው መዋራዳቸውን አስታውቀዋል።
“ድርጅቱ ለትግራይ ህዝቡ ባዕድ መሆኑን ወይም ህዝቡ ከዚህ ቡድን ምንም እንዳልተጠቀመ የሚያሳየው ህዝቡ በዚህች ትንሽ ችግር የገባበት የኢኮኖሚ ቀውስ ነው፤ ለአጭር ጊዜ እንኳን ችግርን ተቋቁሞ ማለፍ የማይችል ህዝብን ነው ያተረፉት። እነሱ አመራር በነበሩበት ወቅትም ያን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈለላቸው ዜጋ በሴፍቲኔት ታቅፎ ነው ህይወቱን ለማቆየት ሲጥር የነበረው” ብለዋል።
ህዝቡና ድርጅቱ አንድ ቢሆኑ ኖሮ ጦርነቱም እንደዚህ ባለ አጭር ጊዜ አይጠናቀቅም ነበር ያሉት አቶ ግደይ ፣ ምክንያቱም ህወሓት አብዛኛውን ሰው አስታጥቃለች ነገር ግን ህዝቡ መሳሪያ ላስታጠቀኝ አካል እንኳን ብሎ አንዲት ጥይት ሳይተኩስ መሳሪያውን ማስረከቡን አመልክተዋል፡፡
የቡድኑ አመራሮች ሴራ በጣም ከባድ ነው፤ እርስ በርሳቸውም እየተባሉ እዚህ ደርሰዋል ። ይህ የመጠላለፍና የሴራ አካሄዳቸው እርስ በርሳቸው እያዳከማቸው እንደመጣ አይተናል። በመጨረሻም ድርጅቱ የደካሞች ስብስብ ሆኗል።
በተለይም አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ድርጅቱ ራሱን ችሎ መቆም ተስኖትም እንደነበር አመልክተው ፣ በዚህም አመራሮቹ ደካሞች እርስ በርሳቸው የሚፋጠጡና የሚጓተቱ ነው የሆኑት፤ ይህም የሴራው ውጤት በመሆኑ መጨረሻው በዛው አካሄድ መበላታቸውን አመልክተዋል።”
* አዲስ ዘመን የካቲት 05/2013
Filed in: Amharic