>

በውድቅት ለሊት ወደ ቅራቅር የተደወለች  " ...ጦር መጣ ንቃ!"  ባይዋ  የስልክ ጥሪ...!!! (ሰይድ ደመቀ)

በውድቅት ለሊት ወደ ቅራቅር የተደወለች  ” …ጦር መጣ ንቃ!”  ባይዋ  የስልክ ጥሪ…!!!
ሰይድ ደመቀ

በፌደራል መንግሥቱና የትግራይን ክልል ያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው አለመግባባት እየተባባሰ ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም ላይ ወደ ወታደራዊ ግጭት ሲሸጋገር ቀዳሚ የውጊያ ቦታዎች የነበሩት ቅራቅርና ዳንሻ የተባሉት በአማራና ትግራይ ክልሎች መካከል የሚገኙት አዋሳኝ ስፍራዎች ላይ ነበር።
በፌደራል መንግሥቱ እና ትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር የነበረው ህወሓት መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ግጭት ያመራው ጥቅምት 24 2013 ምሽት የሕወሃት ኃይሎች የሰሜን እዝን ማጥቃታቸው ከተገለፀ በኋላ ነው።
ቀዳሚው ወታደራዊ ግጭት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ጠገዴ ወረዳ፣ ቅራቅር ከተማ ነበር የተከሰተው።
ግጭቱ በተቀሰቀሰ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በክልሉ የነበረ የስልክ ግንኙነት የተቋረጠ ሲሆን ለተወሰኑ ሳምንታት ከገለልተኛ ወገኖች ስለግጭቱ መረጃ ማግኘት ፈተና ሆኖ ቆይቷል።
በወቅቱ ከትግራይ ልዩ ኃይል በኩል ወደ ቅራቅር የሚደረግ ወታደራዊ እንቅስቃሴ መኖሩን የአካባቢው ጸጥታ ኃይል የተገነዘበው “በአንዲት ስልክ ጥሪ” ሰበብ መሆኑን የቅራቅር የፖሊስ አባላት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ድንገተኛዋ የስልክ ጥሪ
ጠገዴ ወረዳ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚገኝ ሲሆን ከተማው ቅራቅር ትባላለች። ከዚህ ወረዳ ቀጥሎ ደግሞ በትግራይ ክልል ስር ይተዳደር የነበረው ጸገዴ ወረዳ ይገኛል። ከተማውም ከተማ ንጉሥ ወይም ማክሰኞ ገበያ ይባላል።
ነዋሪዎች እንደሚሉት የቅራቅር ከተማ የትግራይና የአማራ ክልል የሚዋሰኑበት ስትሆን የሁለቱም ክልሎች የልዩ ኃይል ፖሊሶቻቸውን በከተማዋ አቅራቢያ ወደ ድንበር ላይ አስጠግተው ለብዙ ጊዜ አቆይተዋል።
ረዳት ኢንስፔክተር አሸብር ሲሳይ በትግራይ ክልል ውስጥ ይተዳደር በነበረው ጸገዴ ወረዳ ውስጥ የከተማ ንጉሥ ፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊ ነበር። ለ15 ዓመታት በፖሊስነት ካገለገለ በኋላ በነበረው ሁኔታ ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ ባለቤቱንና ልጆቹን ትቶ ወደ አማራ ክልል ማምራቱን ይናገራል።
ከዚያ በኋላ ኑሮውን በአጎራባቿ የአማራ ክልል ጠገዴ ወረዳ አደረገ። እዚያም ረዳት ኢንስፔክተር አሸብር በሙያው በወረዳው ፖሊስ ውስጥ የወንጀል መርማሪ በመሆን መሥራት ሲጀምር ቤቱን እሱ ወዳለበት ወደ ቅራቅር ከተማ እንዲመጡ አድርጎ ኑሮውን መምራት ቀጠለ።
በዚህ ሁኔታ ባለቤቱ ቤተሰቦቿን ለመጠየቅ በተለያዩ ጊዜያት ትግራይ ክልል ውስጥ ወደሚገኘውና የትውልድ ቦታዋ ወደ ሆነው ጸገዴ ወረዳ ንጉሥ ከተማ ታመራ ነበር። በጥቅምት አጋማሽ ላይም ባለቤቱ እህቷ በጸና ስለታመመች ለመጠየቅ ከሄደች ከቀናት በኋላ ያልጠበቀችው ነገር ተከሰተ። ማክሰኞ ምሽት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም።
እርሷ በእንግድነት በተገኘችበት አካባቢና በአቅራቢያው ባሉ ወታደራዊ ካምፖች ላይ ድንገተኛ የተኩስ ልውውጥ መከፈቱን ታስታውሳለች። ተኩሱ ከባድም፣ ያልተጠበቀም ስለነበር ሁሉም ሰው እጅጉን ደንግጦ ነበር። እሷም በዚህ ድንጋጤ ውስጥ ሆና ለባለቤቷ ደወለች።
“እዚህ በሚገኙ የመከላካያ ካምፖች ላይ ጦርነት ተከፍቷል። በዳንሻ በኩልም ተኩስ መጀመሩን ሰምተናል፤ እባካችሁ ራሳችሁን ጠብቁ” የሚል መልዕክት ከምሽቱ 5፡30 አካባቢ ከባለቤቱ መቀበሉን ኢንስፔክተር አሸብር ያስታውሳል።
ይህች የስልክ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት ስለመጀመሩ ለቅራቅር ከተማ ነዋሪዎች ያስታወቀች የመጀመሪያዋ ጥሪ ነች።
ከእንቅልፉ ተነስቶ በሚስቱ በኩል ግጭት መጀመሩን የሰማው ኢንስፔክተር አሸብር፣ ቀጣዩ ሥራው ይመለከታቸዋል ለሚላቸው አካላት ክስተቱን መንገር ሆነ። “በዚህም ምክንያት ወዲያውኑ ለማዕከላዊ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ እና ለአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ደውዬ ሁኔታውን አሳወቅኩ” በማለት የነበረውን ሁኔታ ያብራራል።
ተጨማሪ ማረጋገጫ ፍለጋ
አቶ ጌታቸው ሙሉጌታ የጠገዴ ወረዳ አስተዳዳሪ ናቸው። በአካባቢያቸው የሚያዩት ሁኔታ አስጊ እንደሆነ ቢገምቱም ጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም ግን ያልጠበቁት ሁኔታ መከሰቱን ያስታውሳሉ።
በወቅቱ ከጠኑበት ተቀስቅሰው ጦርነት መጀመሩን ሲሰሙ፣ ከተጨማሪ ሰው ስለክስተቱ ለማረጋገጥ መረጃው ይኖረዋል ብለው ከሚያምኑት ሰው ደውለው ማጣራት ነበረባቸው። ይህንን ያረጋግጡልኛል ብለው ያሰቡት ደግሞ በምዕራብ ዕዝ የ5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አዛዥ ብርጋዲየር ጀኔራል ሙሉዓለም አድማሱን ነበር።
ጄነራሉም “ነገሮች ተበላሽተዋል፤ እናንተም ላይ ጥቃት ሊፈጸምባችሁ ስለሚችል ራሳችሁን ተከላከሉ” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ይናገራሉ።
ወዲያውም “በየቤቱ ያረፈውን የአካባቢውን ሚሊሻና ታጣቂ ቤት ለቤት እየሄዱ እንዲቀሰቅሱ ለአባላቶቻቸው ትእዛዝ ሰጥተው፣ እየመጣ የነበረውን ጥቃት ለመከላከል ቦታ ቦታ ማስያዝና ማሰማራት እንዲሁም ተጨማሪ ኃይል ከአጎራባች ወረዳዎች ለማምጣት ጥረት ተደረገ” ሲሉ አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የጠገዴ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ጀምበሩ ሙሉ፣ ከኢንስፔክተር አሸብር ባለቤት የደረሳቸው የስልክ ጥሪ አስቀድሞ “ኃይል ለማደራጀት ጠቅሞናል” ሲሉ ይናገራሉ።
የባልደረባቸው ሚስት ስልክ ባትደውል ኖሮ “ውጤቱ ሊቀየር ይችል ነበር” ያሉት ዋና ኢንስፔክተር ጀምበሩ፣ ከስልክ ልውውጡ በኋላ በአካባቢው ያለውን ኃይል ለመከላከል ማዘጋጀት እንደቻሉ ያስታውሳሉ።
ቀራቅርን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተደረገ ውጊያ
ከእኩለ ሌሊቱ በኋላ በከተማዋ አንድ ወገን ተጀመረ የሚሉት ተኩስ ለሁለት ሰዓታት ያህል የቆየ ነበር። ከሌሊቱ 9፡30 አካባቢ ሲሆን ከከተማዋ ወጣ ብሎ በሚገኘው የቅራቅር ትምህርት ቤት አካባቢ ዋናው ጦርነት እንደተጀመረ በወቅቱ የአማራ ልዩ ኃይልን ይመሩ ከነበሩት አዛዦች መካከል አንዱ ዋና ሳጅን ማናለኝ ወርቄ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እናም “ከሌሊቱ 9፡30 ሲሆን ለጥቃት የመጣው ኃይል ካሉበት አካባቢ የውሻ ድምጽ ሰማን፤ ያ የውሻ ጩኸት ወደ እኛ እየመጡ መሆናቸውን አመላካች ነበር” ያሉት ዋና ሳጅን ማናለኝ፣ ወዲያውኑ ኃይላቸው እንዲዘጋጅ ማዘዛቸውን ያስታውሳሉ።
በጠገዴ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የስምሪት ኃላፊ የሆኑት አስር አለቃ ዋኘው፣ እንዳሉት ከዚያ በኋላ ውጊያው ለረጅም ሰዓታት መቀጠሉን ያስታውሳሉ።
“በጦር ዝግጅት የተሻሉ ቢሆኑም ቀድመን ቦታ ይዘን ስለነበር ለመከላከል አልተቸገርንም። ቅራቅር በወታደራዊ አተያይ ገዢ መሬት ስለሆነች፣ የቡድን መሣሪያ ለማስቀመጥ ሲባል ቀድመው ለመያዝ አቅደው ነበር” ብለዋል።
አካባቢው ኃይል ከአቅራቢያ ከተሞች በመጡ ታጣቂዎች እየታገዘ “ያለምግብና ውሃ” ለሰዓታት ከተማዋ እንዳትያዝ ውጊያው መቀጠሉን ያስታውሳሉ።
ጥቅምት 24/2013 ከምሽቱ 5፡30 ላይ በረዳት ኢንስፔክተር አሸብር ባለቤት የተደረገችው የስልክ ጥሪ ስልክ በኋላ የተጀመረው ግጭት፣ እስከ ቀኑ 11 ሰዓት 30 ቀጥሎ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ተችሏል።
ሕይወት እንደቀድሞው
በተከታዩ ቀንም ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ከተማ ንጉሥን በመያዝ ወደ ሌሎች አካባቢዎች መሰማራታቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፖሊስ አባላት ይናገራሉ።
ከዚህ በኋላ በትግራይ ኃይሎች በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት መካከል የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ፣ ውጊያው በሌሎች አካባቢዎች ቀጥሏል።
ምንም እንኳን ቅራቅር የመጀመሪያው ግጭት ቢካሄድባትም ከአንድ ቀን በኋላ ህይወት እንደ ቀድሞው እንደቀጠለ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በፌደራሉ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈፀማቸው ከተገለፀ በኋላበኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የአገሪቱ ሠራዊት እርምጃ እንዲወስድ ማዘዛቸውን ተከትሎ ለሳምንታት የቆየ ወታደራዊ ግጭት ተካሂዷል።
መንግሥት “ሕግን ማስከበር” ያለው ወታደራዊ ዘመቻም በሦስተኛ ሳምንቱ የትግራይ ክልል ዋና ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ ማብቃቱ ቢነገርም የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ሌሎች የረድዔት ድርጅቶች ውጊያው ቀጥሏል በማለት ሪፖርት አውጥተዋል።
የፌደራል መንግሥት በበኩሉ በአሁኑ ጊዜም በሕግ ተፈላጊ ናቸው የተባሉ የህወሓት አመራሮችን ለመያዝ ክትትል እተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
Filed in: Amharic