>

የጦርነት ትሩፋት፤ ትግራይ በአስከፊ የሰብአዊ ቀውስ ውስጥ  (ያሬድ ሀይለማርያም)

የጦርነት ትሩፋት፤ ትግራይ በአስከፊ የሰብአዊ ቀውስ ውስጥ 

ያሬድ ሀይለማርያም

በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት እንደ አገር ምን አተረፍን? ምንስ አጣን? ለደረሱት አስከፊ ጉዳቶችን ማነው ተጠያቂው? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን ለመመለስ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ያለውን ጠቅላላ ሁኔታ በቅጡ መመርመር እና ማጣራት ይጠይቃል። ጁንታ እየተባለ የሚገለጸው ነውረኛው የህውሃት ቡድን መደምሰስ ብቻውን የአገር ድል ሊሆን ይችላል ወይ? ‘አንድ ንጹ ሰው ከሚጉላላ አንድ ሺ ወንጀለኛ ቢያመልጥ ይሻላል’ የምትለዋ የጠቅላዩ የስልጣን መግቢያ ንግግር ዛሬ እንዴት ትታያለች? በእርግጥ አነጋገሩ የሕግ መርሆ መሰረት ከሆኑ አባባሎች የመነጨ ነው። ታዋቂው እንግሊዛዊው ዳኛ William Blackstone እንዲህ በሚለው አገላለጹ ይታወቃል፤ “[B]etter that ten guilty persons escape, than that one innocent suffer.” ይህ የሕግ መርህ በኃይማኖት መዛግብትም ላይ በሌላ መልክ ተገልጾ ታገኙታላችሁ። ታዋቂው እና የአሜሪካ ፈጣሪ አባት ተብለው ከሚጠቀሱት የፖለቲካ ፈላስፋው Benjamin Franklin ይህን መርህ ጠንከር አድርጎም “it is better a hundred guilty persons should escape than one innocent person should suffer.” ብሎ ይሟገታል።
ነውረኞቹን የህውሃት አመራሮች ባለፉት አሥርት አመታት ለፈጸሙት ግፍ እና ሰቆቃ በሕግ ተጠያቂ ማድረግ የዘገየ እርምጃ እንጂ ጥያቄ የሚነሳበት አይደለም። በተለይም ደግሞ በሰሜን ዕዝ ባለው የመከላከያ ሠራዊት አባልት ላይ የፈጸሙት አሰቃቂ የወንጀል አድራጎት ነውረኞቹ በሕግ ጥላ ስር የማዋሉን እርምጃ የግድ አድርጎታል። ይሁንና እነሱን ለመቆጣጠር የተሄደበት መንገድ ያስከተለውን ጉዳት በቅጡም በቅጡ መፈተሽ የግድ ይላል። ሕግ ለማስከበር ተብሎ የተገባበት ጦርነት በትግራይ ላይ ያስከተለውን አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በጥሩ ሁኔታ በተከታታይ እያወጣቸው ባሉ መግለጫዎቹ ላይ በዝርዝር ገልጿል።
በመጀመሪያ ለኮሚሽኑ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ያለኝን ታላቅ አክብሮት እና አድናቆት ለመግለጽ እወዳለሁ። በዚህ ፈታኝ እና ወቅታዊ በሆነ ጉዳይ ላይ ምርመራ ሰርቶ ሚዛናዊ የሆነ እሪፖርት የሚያወጣ እንዲህ ያለ ኮሚሽን መኖሩ የነጻ ተቋማትን አስፈላጊነት ይበልጥ አጉልቶታል። ኮሚሽኑ በማይካድራ በተፈጸመው የዘር ፍጅት፣ እንዲሁም በዳንሻና በሌሎች ሦስት ዞኖች የደረሰውን የጉዳት መጠን በዝርዝር በቅድሚያ ባወጣቸው ሁለት ተከታታይ መግለጫዎቹ አሳውቆናል። ስጋቱን እና መወሰድ ያላባቸውንም እርምጃዎች ጠቁሟል።
ዛሬ ባወጣው ሰፊ መግለጫ ደግሞ ኮሚሽኑ ትግራይ ላይ ያለውን አሳሳቢ የሰብአዊ ቀውስ፣ በጦርነቱ የደረሱ ጉዳቶችን እና በሥፍራው ተገኝቶ የታዘበውን ነገር ዘርዝሮ አቅርቧል። እጅግ አስደንጋጭ የሆኑ ነገሮችንም አካቷል። ባለማወቅም ሆነ በስሜታዊነት ክልሉ ውስጥ ያለውን ሰብአዊ ስንገልጽ የእኛን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ለመክተት የሞከራችው እና ስጋቱንም ውድቅ ለማድረግ ብዙ እርቀት የሄዳችው ወገኖቻችን እባካችሁ የኮሚሽኑን ሪፖርት ጊዜ ወስዳችሁ አንብቡት። ያ ካልሆነላችሁ በሪፖርቱ የተካተቱ እጅግ አሳሳቢ እና አስደንጋጭ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ከብዙ በጥቂቱ እነሆ፤
-ከመቀሌ፣ ከአይደር፣ ከአዲግራት እንዲሁም ከውቅሮ ሆስፒታሎች በተገኘ መረጃ መሰረት ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 108 (አንድ መቶ ስምንት) የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች ተፈጽመዋል።
– በመቀሌ እና የኢሰመኮ ክትትል ቡድን በተዘዋወረባቸው አካባቢዎች የሰብአዊ እርዳታ በማዳረስ ረገድ አበረታች እርምጃዎች ቢኖሩም፣ አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎቱ አሁንም አልተሟላም።
– ከሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች ወደ መቀሌ ከተማ የተፈናቀሉ ሰዎች የምግብ፣ የንጹሕ መጠጥ ውሃ እና የጤና አገልግሎት አቅርቦት እጥረት አለባቸው። በተለይም በሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ሁኔታ እና የጤና ተቋማት አገልግሎት መቋረጥ፣ ተጎጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች የህክምና እርዳታ ለማግኘት ረዥም የእግር መንገድ እንዲያደርጉ አስገድዷል።
– ኢሰመኮ በአይደር ሆስፒታል የሕፃናት ተኝቶ መታከሚያ ከፍልን በጎበኘበት ወቅት፣ ተኝተው በመታከም ላይ ከነበሩት 20 ከፍተኛ የአዕምሮ ጭንቀት እና ድንጋጤ (trauma) ታካሚ ሕፃናት መካከል 16ቱ በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። ከሕፃናቱ መካከል እጃቸውን፣ እግራቸውንና እና አይናቸውን ጨምሮ የአካላቸውን ክፍል ያጡ ወይም የተለያየ አይነት የአካል ጉዳት የደረሱባቸው የሚገኙ ሲሆን፣ በተለይ በሕፃናት ላይ  ለደረሱት ጉዳቶች አንዱ ምክንያት በመሬት ውስጥ “የተቀበሩ እና በሜዳ ላይ የተጣሉ ፈንጂዎች” የሚደርስ ጉዳት ነው።
– በአንዳንድ የሰሜን ምዕራብ እና የምሥራቃዊ ዞን የትግራይ ክልል አካባቢዎች የኤርትራ
መንግስት ወታደሮች መኖራቸው እና የክልሉ የቀድሞ ምዕራባዊ ዞን እና ሁለት የደቡባዊ ዞን
ወረዳዎች ከክልሉ መስተዳድር መዋቅር ውጪ ሆነው በአማራ ክልል አስተዳደር ሥር
መሆናቸው፣
– በትግራይ ክልል በነበሩ 10 ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ እስረኞች በሙሉ ከእስር ወጥተዋል፣ የእስረኞችን መረጃዎች የያዙ ሰነዶች ወድመዋል።
– በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች ውጊያ አለመቆሙ መደበኛ የኑሮ እንቅስቃሴዎችን መገደቡን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። በተለይም የመሰረታዊ ፍላጎት ሸቀጦች በአግባቡ እንዳይዘዋወሩ፣ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በሚፈለገው መጠን እንዳይንቀሳቀስ እና የእርዳታ ማጓጓዣ ትራንስፖርት
አገልግሎት በአግባቡ እንዳይጀምር እንቅፋት ሆኗል።
– በጦርነቱ ወቅት በተወሰኑ የጤና አግልግሎት ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱንና የጤና ባለሞያዎች ሞትን ጨምሮ በርካታ የክልሉ የጤና ተቋማት መዘረፋቸውን፣ እንዲሁም አብዛኞቹ አምቡላንሶች በክልሉ የጤና ቢሮ ስር ያለመሆናቸውን በቢሮው የተደረገ የዳሰሳ ጥናት ያሳያል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በመግለጫው መጨረሻ ላይ ያስቀመጣቸው የማሳሰቢያ ምክረ ሃሳቦች በቂ ትኩረት ያገኙ ዘንድ ለሰው ልጆች መብት እና ደህንነት የምትቆረቆሩ ሁሉ፤ ግፍን የምትጠየፉ ሰዎች እና ድርጅቶት ከኮሚሽኑ ጎን በመቆም ድምጻችሁን ልታሰሙ ይገባል።
Filed in: Amharic