>

እኛ እና ዓለም - ምን እናድርግ? - ምንስ አናድርግ?  (አሰፋ ሀይሉ)

እኛ እና ዓለም – ምን እናድርግ? – ምንስ አናድርግ? 

አሰፋ ሀይሉ

— ‹‹የጎሳዎች ቅርጫት›› በሆነች ሀገር፣ ጎሳዊ አጀንዳን የተሻገረ ሀገራዊ ፖለቲካን ማምጣት የሚሞከር ነው?
ለመሆኑ ከጥንታዊ አደረጃጀት ያልተላቀቁ ጎሳዊ ማኅበረ-ሰቦች በአንድ ሀገር ውስጥ በዝተው የመገኘታቸው እውነታ – ዘመናዊ ሀገራዊ አስተዳደርና ዘመናዊ የዜጎች ፖለቲካዊ ሥርዓት እንዳይመሠረት እንቅፋት ይሆናል ወይ? አሁን በጎሳዊ ‹ፖለቲካዊ› አጀንዳዎች ተወጥሮ እየተርገበገበ ያለውን መንግሥታዊ የአስተዳደርና ፖለቲካ ሥርዓታችንን – በሀገራዊ የጋራ ጉዳዮችና ርዕዮተ-ዓለማዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ወደሚያውጠነጥን ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት ከፍ ማድረግስ ይቻለናል? ለመሆኑ እንደኛ ባለች ከ60 በላይ ጎሳዎች ከነ80 ቋንቋቸው በሚርመሰመሱባት ‹‹የጎሳ ቅርጫት›› ሀገር ላይ፣ ከጎሳዊ አጀንዳዎች የተላቀቀ ሀገራዊ የፖለቲካ አውድን ለማምጣት መከጀል የሚሞከር ነው? ሀገሪቱ በጎሳ ማኅበረሰቦች ተሞልታ ሳለ፣ እንዴት የሀገሪቱ ፖለቲካ ከጎሳዊ ማንነት የዘለለ ሀገራዊ ገጽታንና ማንነትን ሊላበስልን ይችላል?
ብዙዎች እንደሚያስረዱት የተለያዩ ቋንቋዎችን የሚናገሩ፣ የተለያዩ ባህሎችን የተላበሱ፣ በተለያዩ ጎሳዎችና ነገዶች የተከፋፈሉ፣ እንዲሁም በተለያየ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የዕድገት ደረጃዎች ላይ የሚገኙ ማኅበረሰቦችን የያዘች ሀገር፣ ብዙ የጋራ ነገር ያላቸውን አንድ ወጥ የሆነን ማኅበረሰብ ከምትመራ ሀገር ይልቅ ፈተናዋ ብዙ ነው፡፡ ብዙ ‹‹ቻሌንጆች›› ይጠብቋታል፡፡ (በእርግጥ ይህ ማለት አንድ ‹‹ኔሽን›› ነን የሚሉ ህዝቦች የፈጠሩት ሀገር ሁልጊዜም ሀገራዊ ፖለቲካው የተሳካና አልጋ ባልጋ ይሆናለታል ማለት እንዳልሆነ የብዙ የዓለም ሀገራትን ሁኔታ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡)
ብዙ ዓይነት ጎሳዊ ማኅበረሰቦችን ያቀፈች ሀገር ብዙ ‹‹ቻሌንጆች›› ይጠብቋታል ብለናል፡፡ ይህ ማለት ግን የብዙ ጎሳዎች መናኸሪያ የሆነች ሀገር ፖለቲካ እንደ ጎሳዎቹ ብዛት የተበጣጠቀና ሺህ ቦታ የተሰነጣጠቀ መሆን አለበት ማለት አይደለም፡፡ በተቃራኒው – ብዙ ጎሳዎችን በውስጧ ያቀፈች ሀገር ፖለቲካ – ከሌላው ወጥ ማኅበረሰቦችን ካቀፉ ሀገራት በበለጠ – እርስ በእርስ ከሚያለያይና ከሚከፋፍል ፖለቲካ ይልቅ – ሁሉንም በአንድ ጥላ ሥር የሚያሰባስብ፣ የተለያዩትን ማኅበረበሶች ወደ አንድነት የሚወስድ፣ ብዙዎቹን በጋራ አግባብቶና አስማምቶ ሊያኖር የሚችል፣ አብሮነትን የሚያቀላጥፍና፣ የጋራ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትና ሀገራዊ ትስስርን ሊያመጣ የሚችልን – የጋራ ሀገራዊ ፖለቲካ (a politics based on commonalities) ለመፍጠር ትገደዳለች፡፡ ብዙዎች ሀገራት ያደረጉት ይሄንን ነው፡፡
ለምሳሌ ህንድን እንውሰድ፡፡ በህንድ ወደ 650 የሚጠጉ ጎሳዎችና ከ20 በላይ ቋንቋዎች የሞሉባት ሀገር ነች፡፡ የህንድ ጎሳዊ ማኅበሰብ ብዛት በትንሹ ከእኛ 10 እጥፍ ይልቃል ማለት ነው፡፡ ያ ብቻ አይደለም፡፡ በህንድ ማህበረሰብ ውስጥ ለረዥም ዘመናት የዘለቀ ህዝቡን በኑሮ ልዩነቱ፣ በዘሩና ቀለሙ፣ በመተዳደሪያ እንጀራውና በመሳሰሉት ነገሮች ላይ በመመስረት የበላይና የበታች ብሎ የሚደለድል ‹‹caste system›› አለ፡፡
ከፍተኛ አክብሮትና ማዕረግ ከሚቸራቸው ከ‹‹ጃቲስ›› ካስቶች አንስቶ እስከ የመጨረሻው ሰብዓዊ ክብራቸው እስከተገፈፈባቸው ‹‹ሃሪጃንስ›› ድረስ – በህንድ ውስጥ 3,000 ካስቶች፣ እና 25,000 ልዩ ልዩ ንዑስ-ካስቶች በአንድ ሀገር ጥላ ውስጥ ተዳብለው ይኖራሉ፡፡ ህንድ በህገመንግሥቷ ልማዱን እስክትከለክል ድረስ – ሃሪጃኖችን ለፅዳት ሠራተኛነት ራሱ የሚቀጥር የመንግሥት ቢሮ አልነበረም፡፡ ሰዎች ሊነኳቸው እንኳ ስለሚፀየፏቸው ‹‹Untouchables›› (‹‹አይነኬዎቹ››) በሚል ስም ይጠሩ ነበር፡፡ በእነዚህ ሁሉ የጎሳ፣ የቋንቋና የካስት ልዩነቶች ሳቢያ በህንዳውያን ህይወት ውስጥ ከፍ ያለ የጎጠኝነት እና የጎሰኝነት መንፈስ ተንሰራፍቶ ይኖር እንደነበር ከብዙ ስለህንድ ከጻፉ የታሪክ፣ የማኅበረሰብና ፖለቲካ ምሁራን የምንረዳው ሀቅ ነው፡፡
በዚያ ላይ ሐይማኖትም አለ፡፡ ብዙዎቹ ህንዶች ሂንዱዎች ቢሆኑም፣ ሌሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች፣ ክርስትያኖችና ሲዩኮችም አሉ፡፡ ህንድ ከእንግሊዞች ነፃ በወጣች ማግስት ሁለት ቦታ የበታተናት ዋናው ምክንያት ሐይማኖት ነው:: ሂንዱ የሚበዛባት ህንድ ሙስሊም ከሚበዛባት ፓኪስታን ጋር ሁለት ቦታ ተከፈለች፡፡ ቀጥሎ ደሞ ምስራቃዊዋ ፓኪስታን በህንዶች እገዛ ከምዕራቡ ፓኪስታን ተገነጠለችና ሌላ ሶስተኛ ሀገር ሆነች – ባንግላዴሽ፡፡ በሀይማኖት የተከፋፈለችው ህንድ፣ ለምን በጎሳዎቿና ካስቶቿ ልክ 10ሺህ ቦታ ሳትበታተን ቀረች? ያልን እንደሆነ ምክንያቱ አንድና አንድ ነው፡፡ ያም የህንድ ፖለቲካ ከመነሻው ጀምሮ 650 ቦታ ከተሰበጣጠረው ጎሳዊ ማንነቶቿ ከፍ ብሎ፣ እንደ ትልቅ ሀገራዊ ጥላ ሆኖ በሀሳብ የተለያዩ ማህበረሰቦቿን እንዲያሰባስብ፣ በርዕዮተ ዓለም እንዲያገናኝ ተደርጎ የተቃኘ መሆኑ ነው፡፡
ሳስበው ያም ቢሆን የፈጣሪ እርዳታ ጭምር ሳይታከልበት የተሳካ ይመስለኛል፡፡ ብዙዎች እንደሚሉት ህንዶች ከአንድ ጎሳ በላይ ተሰሚነት ያላቸው ታላላቅ የፖለቲካ ሰብዕናዎችን ለማግኘት መታደላቸው ከብዙ ጥፋት ታድጓቸዋል፡፡ ይህን ሳስብ ለራሳችን አዝናለሁ፡፡ በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር መስፍን በመጽሐፋቸው ‹‹ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የትልቅ ሰው ድርቅ መቷታል›› ብለው ሲያዝኑ ነበር፡፡ እንግዲህ ፕ/ር መስፍን ህንድ ሀገር ኖረው ተምረው ታሪኳን ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰው ናቸው፡፡ ለእኛ ጋንዲና ማንዴላ የለንም ብለው ማዘናቸውን ከልብ እረዳላቸዋለሁ፡፡ ምናልባት እግዜሩ እኛንም ካገዘን መፍጠር እንችል ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል?
ወደ ቁምነገሩ ስንመለስ – ገና ከጅምሩ የነበሩት የህንድ የፖለቲካ መሪዎችና እንቅስቃሴዎች በተቻለ መጠን በህንዶች ነጻነትና መንፈሳዊ ሰብዕና ላይ ያተኮሩ፣ በቻሉት መጠን የጎሳ ማንነትን የተሻገሩ፣ እና ታላላቅ ራዕይ ባላቸው ሰዎች የሚመሩ ነበሩ፡፡ ፕራቪ፣ ራሽክሪያ ሳንግ፣ ወዘተ የሚባሉ የህንድ ቀደምት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የነጻነት ዘመኖቹ እነ ጋንዲና ኔህሩ ያቆሙት ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ፣ እና በእኛ 80ዎቹ ውስጥ የተመሰረተው ህዝባዊ ፓርቲ (‹‹ባህራቲያ ጃናታ››)፣ እና ሌሎችም ቀደምት የህንድ የፖለቲካ ቡድኖች – ምንም እንኳ የየራሳቸው ዝንባሌ ቢታይባቸውም – ገና ከጅምሩ የአጠቃላዩን ህንዳውያን ማንነትና ዘርፈ-ብዙ ባህል ዕውቅና ሰጥተው – ነገር ግን ከጎሳ አስተሳሰብና ከጠበበ የአንድ ወይም የሌላ ነገድ ወኪልነት ከፍ ብለው የተገኙ ነበሩ፡፡ አሁንም ናቸው፡፡
የሚገርመኝ በህንድ ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባት የተሰለፉት ፖለቲከኞች ብቻ አይደሉም፡፡ ሌላ ቀርቶ በየዓመቱ እስከ 2,000 የሚደርሱ አዳዲስ ፊልሞችን በ20ውም የተለያዩ የህንድ ቋንቋዎች እያመረተ ለገበያ የሚያቀርበው በዓለም ግዙፉ የህንዶች የፊልም ኢንደስትሪ – ቦሊውድ – ጭምር ራሱን የቻለ የጋራ ህንዳዊነትን መፍጠሪያ ታላቅ የሀገራዊ ፕሮሞሽን (ፕሮፓጋንዳም) ኢንደስትሪ ሆኖ አገልግሏቸዋል፡፡ እያገለገላቸውም ነው፡፡ የህንዶች ሁሉም ነገር፡፡ ሙዚቃው፡፡ የቁንጅና ተወዳዳሪው፡፡ የሚበሉት ሩዝ፡፡ የጋንጊስ ወንዛቸውና ወርቃማዋ ላማቸው ሳትቀር – እያንዳንዱን ሀገራዊ ነገር ህንዶች – ህንዳዊነትን ለመገንባት ይጠቀሙባቸዋል፡፡ እንዲህ ነው እንጂ ዜጋ ማለት፡፡ ሀገሩን የሚወድ፡፡ ለሀገሩ የጋራ ማንነት ያለውን ሁሉ የሚሰጥ፡፡ ያለውን ሀብት ሁሉ የሚጠቀም፡፡
በእርግጥ የህንዳውያኑን ሀገራዊ ብሔራዊ መነሳሳት አነሳን እንጂ – ሁሉም ነገር አልጋ-በአልጋ ሆኖላቸዋል ማለታችን እንዳልሆነ ግልጽ ነው – በዓለም የመጀመሪያ ተርታ ያሉ ቱጃሮችም፣ በዓለም የመጨረሻዎቹ ድሆችም የሚገኙት በዚያችው በህንድ ሀገር ነው – የሠማይና የምድርን ያህል የተራራቀው የኑሮ ልዩነትና የተንሰራፋው ሀገራዊ ሙስና – የህንዳውያኑን ህልውና እየተፈታተኑት ነው፡፡ በሀገራዊ ጉዟቸው ውስጥ ህንዶቹ ሀገራዊ መከራም፣ የእርስበርስ ጦርነትም፣ መበተንም አልገጠማቸውም ማለት እንዳልሆነ ከላይ ያልነው ነው፡፡ በብዙ ሀገራዊ መበጣጠሶችና መቆራቆሶች ተፈትነዋል ህንዶቹ፡፡ እስከዛሬም ድረስ፡፡
ግን ከእነ 650 ብሔሮቻቸው፣ ከእነ 20 ቋንቋዎቻቸው፣ ከእነ 3ሺህ ካስቶቻቸው፣ ከእነ 25ሺህ ሰብ-ካስቶቻቸው፣ ከእነ 4 ግዙፍ ሐይማኖቶቻቸው – ይኸው ሁሉንም ነገራቸውን የህንድን ሀገራዊ ብሄርተኝነት እንዲገነባላቸው አሰልፈው፣ በታላቋ የ‹‹ሂንዱስታኒዎች›› ምድር የጋራ ባንዲራቸውን ከፍ አድርገው እያውለበለቡ – በጋራና ኃላፊነት በተሞላበት ሀገራዊ ፖለቲካቸው ሥር ዜጎቻቸውን አሰባስበው አስጠልለው – ቢሊዮን ህዝባቸውን መግበው፣ ከሌሎች የዓለማችን ቢሊዮን ህዝቦች ጋር ይወዳደራሉ፡፡
እኛ ሀገር በአሁኑ ወቅት እየተቀነቀነ እንዳለው የጎሳ ሥርዓት – እና በዘርፈ ብዙ አቅጣጫዎች ሆን ተብሎ እየተሠራበት እንዳለው ህዝብን ከህዝብ፣ ጎሳን ከጎሳ፣ ነገድን ከነገድ፣ ቋንቋን ከቋንቋ የማናቆርና የማለያየት እኩይ መንግሥታዊ ተግባር – በሕንድም በጎሳዎቿ ብዛት ልክ የሚቀነቀን ከፋፋይ የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓት ቢነግሥባት ኖሮ – ያለጥርጥር ህንድ ገና ድሮ 500 እና 600 ቦታ ተሰነጣጥቃ – ዛሬ የደረሰችበት ሀገራዊ የአንድነት፣ የሥኬትና የህልውና ደረጃ ላይ እንደማትደርስ ሁሉም የዓለም ምሁር አስረግጦ የሚናገረው እውነት ነው፡፡
ከህንዶች ደግሞ ወደ አንዲት ሌላ የብሔሮች ጎተራ ወደሆነች ሀገር እንሻገር፡፡ ወደ ፓፓዋ ኒው ጊኒ፡፡ በፓፓዋ ኒው ጊኒ ከ350 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች አሉ፡፡ (የእኛን 60 ብሔሮች በስድስት እጥፍ የሚያስከነዱ ብሔሮች ማለት ነው)፡፡ ፓፓዋ ከጎሳዎቹ ቁጥር በላይ አንዱ አካባቢ የሚነገረውና ሌላው አካባቢ የሚነገረው ቋንቋ በአንድ ጎሳ ውስጥ ራሱ የሚለያይባትም ሀገር ነች፡፡ በዚህ የተነሳ ከ800 በላይ ቋንቋዎች የሚነገሩባትም የጉድ ሀገር ነች ፓፓዋ ኒው ጊኒ፡፡
ከ800 በላይ ቋንቋዎች!! በዓለም ላይ አንደኛ ያደርጋታል፡፡ ይህን ስናስብ እንዴ? ፈጣሪ ባቢሎንን የገነባው በፓፓዋ ይሆን እንዴ? ብለን መጠርጠራችን አይቀርም፡፡ የእኛን 80 ቋንቋዎች አስብና የእነሱን 800 ቋንቋዎች አስብ፡፡ እነሱስ ጋር ‹‹አማርኛ አንናገርም! በአማርኛ እንዳትገበያዩ›› የሚሉ ደናቁርት ፖለቲከኞች ይኖሩ ይሆን? አላውቅም፡፡ የሚኖሩ አይመስለኝም ግን፡፡ ‹‹ዲዳክሽን›› የሚባል ተጠየቃዊ ትንተና አለ አይደል? ከውጤቱ ተነስተህ፣ ምክንያቶቹን መናገር የምትችልበት? እና እንዲያ ዓይነት ፖለቲካ ቢኖራት ኖሮ – ትንሿ ፓፓዋ በጥላቻ ተባልታና ተበታትና ወደ ምንምነት ትቀየር ነበር – የሚል አመለካከት አለኝ፡፡
የፓፓዋ ፖለቲካ ከእነዚህ እጅግ ብዙ ጥንታዊ ስብስቦች ጎሳዊ መቆራቆዝ ከፍ ብሎ በዘመናዊ ሥርዓት የተቃኘ ሀገራዊ መልክ ያለው ነው፡፡ ፓፓዋ ኒው ጊኒዎች እርስ በርስ መሳሪያ አማዝዞ ያጫረሳቸው የመበላላት ፖለቲካ እስካሁን አልገጠማቸውም፡፡ ፓፓዋ ኒው ጊኒዎች ልክ እንደ ትልልቆቹ አውስትራሊያና ካናዳ እስከዛሬም በእንግሊዟ ንግሥት ኮመንዌልዝ ውስጥ ተጠቃልለው የሚኖሩ ህዝቦች ሆነው፣ በራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ ሀገር የሚመሩ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንድ ጎሳ ወኪል አይደለም፡፡ የዚህ ጎሳ ታሪክ ሰርቶ ያሳያችኋል፣ የዚህ ጎሳ ይውደም፣ የዚህ ጎሳ ይለምልም ሲል ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ ተጠሪነቱ ለሀገሪቱ ህዝብ እና ለክብርት ንግሥቲቱ ብቻ ነው፡፡ የፓርላማው አባላት በሀገሪቱ በተዘረጋው የምርጫ አካባቢ ተመርጠው የመጡ ናቸው፡፡
በየትኛውም ዓለም የፖለቲካ ካርታ ከምርጫ ካርታ የተለየ እንደሆነ ልብ ማለትን ሳንረሳ፣ በፓፓዋም ወኪሎቹ ከተለያየ ብሔርና ብሔረሰብ አካባቢዎች ተመርጠው የሚመጡ መሆናቸውን ልብ እንበል፡፡ ተቺዎች ግን ፓርላማው በጎሰኝነት ችግር የተበሳበሰ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ መንግሥቱ ደግሞ የተወካዮቹን ድምጽ ለማግኘት በሙስና መዓት ስለሚያጥለቀልቃቸው – ሕዝቡ የተቸገረው በወኪሎቹ ጎሰኝነት ሳይሆን – በወኪለቹ የሙስና ንቅዘት ነው፡፡ በማለት ያሄሳሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ፓፓዋ ኒው ጊኒዎች እንደኛ በብሔር ብሔረሰብ በመባላት ችግርም፣ ጎሳና ጎሳን አለያይቶ በሚያባላ የፖለቲካ ሥርዓትም አይታሙም፡፡
‹‹ቶክ ፒሲን›› የተባለው ከእንግሊዝኛ ጋር የተቀየጠ ሀገርኛ ቋንቋና፣ ‹ሂሪ ሞቱ› የተሰኘ ቋንቋቸው ከንግሥት ሀገር እንግሊዝ ቋንቋ ጋር ተዳብለው 350 ብሔሮችና 850 ቋንቋዎች ያሉትን የፓፓዋ ዥንጉርጉር ህዝብ – አንዱን ካንዱ አግባብተው –  ከጠባብ የጎሳና የቋንቋ ጉሮኖዎች ወጥቶ – ከፍ ያሉ ሀገራዊ አጀንዳዎችን በሚያቀነቅን የፖለቲካ ድባብ – በአንድ የጋራ ሀገር ጥላ ሥር – በሠላም ሠርተው በልተው ስማቸውን አስጠርተው ያድራሉ፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮ – ቀደም ብዬ እንዳልኩት – ፓፓዋ ገና ድሮ ሕዝቦቿን አለያይታና አበላልታ ወደ ብዙ ቀበሌዎች በተበተነች ነበር፡፡
በአፍሪካችንም ውስጥ – ብዙ ጎሳዎችን በውስጣቸው የያዙ ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች አሉ፡፡ እነዚህ ሀገራት ግን ለሀገርና ማህበረሰብ ዘመናዊ የዕድገት ጉዞ የግድ አስፈላጊ መሆኑን ተረድተው – አምባገነናዊም ይሁን ነፃነት የሰፈነበት – ከጎሳና ከነገድ የወረደ የማንነት መሰባሰቢያ ጥላ ከፍ ያለ መሰባሰቢያ የሚሆን ሀገራዊ ፖለቲካ የሚቀነቀንበትን – ‹‹ዘመናዊ›› የፖለቲካ ሥርዓትን ለመገንባት ሲቧትሩ እናገኛቸዋለን፡፡
ብዙዎቹም ከጥቂት የጎሳቸው መብት በብዙሃኑ ተጨፍልቆብናል ከሚሉ አናሳ-ጎሳዎች አመጽ በስተቀር ሀገራዊ ፖለቲካ አራማጆቹ ህዝባቸውን በሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የሚያንቀሳቅስላቸው ከወረደ የጎሳ አተካሮ ከፍ ያለ ፖለቲካን መፍጠር ተሳክቶላቸው እናገኛለን፡፡ የአናሳ ማህበረሰቦችን መብት የማክበር ጉዳይ በእርግጥ ከሀገራዊ ፖለቲካ ድርቅ በበለጠ፣ በአፍሪካችን ካለው ዝቅተኛ የዲሞከራሲ ልምምድ ጋርም ይገናኛል፡፡ ሆኖም በብዙዎቹ በቅኝ በተገዙ የአፍሪካ ሀገሮች (የእኛዋን ኤርትራን ጨምሮ) በጎሳና በጎጥ ሳይሆን – ንጥር ባሉ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ዙሪያ የተዋቀሩ በትክክል ‹‹የፖለቲካ ፓርቲ›› ለመባል የሚበቁ ፓርቲዎች የተፈጠሩት ዛሬ ላይ አንዳልሆነ ልብ እንበል፡፡ ገና በ50ዎቹና 60ዎቹ ውስጥ፣ ገና ከግማሽ ክፍለዘመን በፊት፣ በአንዳንዶቹ ከዚያም በጣም ቀድመው የጀመሩት ልምምድ ነው፡፡ እኛም ባጭር ባይቀጭ ከአብዮቱ ማግስት ጀምረነው ነበር፡፡ የነካነው ሁሉ አይባረክላችሁ ብሎ የረገመን ይኖር ይሆን? እላለሁ አንዳንዴ በቁጭት!
ይሄ ሁሉ የሆነው በአጋጣሚ አይመስለኝም፡፡ አንድም ሌላው ዘመናዊው ዓለም የደረሰበትን የነፃነትና የማህበራዊ ዕድገት መሠረቶች በማስተዋል ነው፡፡ በሌላም በኩል እርስ በርስ ተከፋፍሎ በኋላቀር የጎሳና የነገድ (ወይም የብሔርና ዘውጌ) ጠባብ መንገኝነቶች ላይ ተቸንክሮ የቀረ ማህበረሰብ – አንድ ላይ ቆሞ የጋራ ሀገርን ለመገንባት እጅግ አስቸጋሪ እንደሚሆንበት እነዚህን አፍሪካውያን ወንድሞቻችንን እርስ በእርስ ከፋፍለው፣ አጠላልተው፣ አለያይተው፣ አናክሰው በገዟቸው አስከፊ አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎቻቸው ሥር ሆነው ካሳለፉት ረዥምና አስከፊ ተሞክሮ በተግባር ቀምሰው ስላረጋገጡ ጭምር ነው፡፡ ሌላ ቀርቶ ከእነዚህ በባርነት የተገዙ አፍሪካውያን ዘመዶቻችን እንኳ አንሰን – በዛሬው ዘመን ላይ – በተበሻቀጠ የጎሳ ፖለቲካ እየታመስን ሀገራችንን ወደ ኋላ 50 ዓመት መጎተታችን ህሊና ላለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የብስጭት ምንጭ ሊሆን የተገባና አንገት የሚያስደፋ ሀገራዊ ውርደታችን ነው፡፡
ወደ ቻይና ደሞ እንሻገር፡፡ በ20ኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ ላይ ቻይናን ከክዊንግ ሥርወመንግሥት ያላቀቃትና 50 ዓመት የዘለቀውን የጎሚንዳንግ ሀገራዊ ፓርቲ የመሠረተው (እና በሚገርም ጨዋነት ከቂንግ ዳይናስቲ ሥልጣን ማብቃት በኋላ አዲስ የተፈጠረውን የቻይና ሪፐብሊክ በጊዜያዊ ፕሬዚደንትነት ለ4 ወራት ቆይታ መርቶ ለተከታዩ መሪ ያስረከበው፣ እና ከኮሚኒስቶቹ በፊት የነበረውን አንጋፋውን የቻይና ብሔራዊ ፓርቲ ጎሚንዳንግ ፓርቲ የመሠረተው) የዘመናዊት ቻይና ቀደምት መሪ ሱን ያት ሰን – በወቅቱ ቀዳሚ የሪፐብሊኩ አጀንዳ አድርጎ ካቀረባቸው ነገሮች ዋነኛው የቻይናን ማህበረሰብ ከታጠረበት የጎሳና የነገድ ባህላዊ አደረጃጀት፣ አኗኗርና አስተሳሰብ አላቅቆ በጋራ ሀገራዊ አመለካከቶች ዙሪያ እንደገና ማዋቀርን (Social Reconstruction ማካሄድን) ነው፡፡
የሚገርመው ነገር ጎሚንዳንግን ከሥልጣን ለማስወገድ የሚሊዮኖችን ህይወት የቀጠፈ መራር ጦርነት ያደረጉት ፀረ-ኢምፔሪያሊስትና ፀረ-ፊውዳሎቹ የቻይና ኮሚኒስቶች እነ ማኦ ዜዶንግም በበኩላቸው – እንኳን መንግሥት ሆነው ይቅርና – ገና መንግሥት ሳይሆኑ ከቻይና መንግሥት ነጻ ባወጧቸው ግዛቶቻቸው – ትክክለኛ ሆኖ ያገኙት ቁልፍ አጀንዳ – ያንኑ ሱን ያት ሰን ሲያቀነቅነው የነበረውን ባህላዊ ማህበረሰባቸውን በህዝባዊ ሀገራዊ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ ማበልጸግንና እንደ አዲስ ማደራጀትን ነው – ያው የተለመዱ የማርክሳዊ ነገሮችን ጨማምረውበት ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ይሄ ጎሰኝነትን ከመንግሥታዊ ፖለቲካዊ ሂደት ማራቅ እና ህዝቡን በሀገራዊ አስተሳሰቦች ሥር የማደራጀት አስፈላጊነት የቀኙም የግራውም የቻይና ኃይሎች የዛሬ 100 ዓመትና፣ የዛሬ 50 ዓመት ያስተዋሉት ተመሳሳይ ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን ማለት ነው፡፡ ይሄን ስናይ ለመሆኑ ስለራሳችን ምን ይሰማናል?
አሁንም ወደ አፍሪካችን እንመለስ፡፡ እና በዘመናቸው የተጨበጨበላቸውን የአፍሪካ ቀደምት የነፃነት አባቶችን እንይ፡፡ ለምሳሌ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ብንወስድ – ኃይለሥላሴ ደግመው ደጋግመው የሚናገሩት የነበረው – ‹‹አዲስ ዓይነት የሰው ልጅን ህብረትን፣ አዲስ ዓይነት ሰብዓዊ አስተሳሰብን የሚያቀነቅን ሀገራዊ ማህበረሰብን የመፍጠርን አስፈላጊነት›› ደግመው ደጋግመው ሲያንጸባርቁና ለዚያም ዓላማ በአህጉርም በሀገርም ደረጃ ተግተው ሲሰሩ ነበር ያሳለፉት ዘመናቸውን፡፡ የትናንትና የዛሬ የጎሳ አስተሳሰብ ሰባኪዎች ምንም አሉ ምን – ቀኃሥ በጊዜያቸው በተግባር የደረጉትና የጣሩትም ያን ከጎሳና ብሔር የተሻገረ ሀገራዊ ማንነት በትውልዱ ለመፍጠር ነበር፡፡
የጋናውን ክዋሜ ንኩሩማህን ብንመለከት ደግሞ፣ ለምሳሌ ንኩሩማህ የሚታወቀው አፍሪካ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የሚሊቴሪ አንድነት ፈጥራ እንደ አንድ ኃያል አህጉር ሆና መውጣት ትችላለች አሊያ ግን እስከመቼውም ከተደቀነብን ዳግመኛ ቅኝ ግዛት አንወጣም እያለ የሚሰብክ ባለታላቅ ራዕይ መሪ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ንኩሩማህ አፍሪካን አንድ ለማድረግ ከመነሳቱ በፊት ግን ሀገሩን ጋናን አንድ ማድረግ እንዳለበት ጠፍቶታል ወይም ቀላል መስሎ ታይቶታል መሰለኝ፡፡ ንኩሩማህ የጋና መሪ ሆኖ 10 ዓመታት ሥልጣን ላይ ቆየ፡፡ ግን የጋናን ፖለቲካ ወደ ዘመናዊነት አቅጣጫ ንቅንቅ ሊያደርገው አልቻለም፡፡ ለጋናውያን ሀገራዊ ትሩፋትን ያመጣልኛ ብሎ የጠበቀው ፓርላማ በጎሳና ጎሳ ተከፋፍሎ እየተባላ ስንዝር ሊያስኬደው አልቻለም፡፡
ንኩሩማህን ብንወስድ በጊዜ ሂደት የታየው የንክሩማህ ይበልጥ አምባገነን፣ ይበልጥ ሃሳቡን በግድ ተግባሪ ወደመሆን የመሸጋገሩን መራር ሃቅ ነው፡፡ የዲሞክራሲና የነጻነት ሰባኪው ንኩሩማህ፣ በብሔር ኃይሎች ተሞልቶ አላሰራ ያለውን ፓርላማ ለመሻገር ያለመበት መንገድ ህገመንግሥቱን ቀይሮ ራሱን የህይወት ዘመን የጋና ፕሬዚደንት ብሎ መሰየም ነበር፡፡ ግን ራሱን የሕይወት ዘመን ፕሬዚደንት ብሎ ሰይሞ ሁለት ዓመት ሳይሞላው ነው በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣኑ ተጎትቶ የወረደውና ሀገሩን ጥሎ የተሰደደው፡፡ ይሄ የአፍሪካችን ሀገራዊ የጎሳ ክፍፍል ሥርዓት ሌላ ቀርቶ እንደ ንኩሩማህ ያሉትን ዓለም ያደነቃቸውን የነጻነት ሃዋርያት እንኳ ራዕያቸውን ተግባራዊ እንዳያደርጉ አንቆ እንደያዛቸው፣ እና እንዴትስ አድርጎ እንደለወጣቸው ማየትና መረዳት ይቻላል፡፡
የጊኒውን ሴኩ ቱሬን ደግሞ እንይ፡፡ ሴኩ ቱሬ እጅግ የሚደነቅ ዘመናዊ አስተሳሰብን የተላበሰ ፈረንሳይ ለአፍሪካ ካበረከተቻቸው ብርሃናማ መሪዎች አንዱ እየተባለ በጊዜው የሚሞካሽ ባለብዙ ራዕይ የነጻነት ዘመን መሪ ነበር፡፡ ግን የጠበቀው ቀርቶ የጠላው ወረሰው፡፡ ጊኒ በጎሳና በነገድ ተከፋፍላ እንደተመኘው አላራምድ አለችው፡፡ እሱም ራሱን ከዲሞክራትነት ወደ ለየለት ፈላጭ ቆራጭ አምባገነንነት አሸጋግሮ ነው የፖለቲካ ጉዞውን ያሣረገው፡፡
ቀደም ብለን ወዳነሳናት ደቡብ አፍሪካ ደግሞ እንውረድ፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን በአይምሬና አስከፊ የውጭ ኃይሎች ሥር ተቀጥቅጠው መገዛታቸው እርስ በርሱ የተከፋፈለውን ጎሳዊ ማንነታቸውን አቻችለው በአንድ ሀገራዊ ብሎም ከፍ ባለ አፍሪካዊ የነፃነት አጀንዳ ሥር እንዲሰባሰቡ የራሱን እገዛ አበርክቶላቸዋል፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን ሌላ ቀርቶ ራሱን ከጎሳና ዘውጌ አጥር ከፍ አድርጎ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግስ (ANC) በሚል ስም ያደራጀው የእነማንዴላና ሲሱሉ ፓርቲ እንኳ – የቱንም ያህል ከዘር ልክፍት የጸዳ ሀገራዊ ስምና ዓላማ ቢያነግብምና፣ በዘመናዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ፕሮግራም አስቀምጦ ለመንቀሳቀስ ቢመኝም – የፓርቲው ሥረ መሠረት ግን በዘር ላይ የተመሠረተ (ፀረ-ነጭ-ፀረ-አፓርታይድ የጥቁሮች ድርጅት) በመሆኑ – እስካሁኗ ቅጽበት ድረስ – አፍን ሞልቶ ዘመናዊና ነፃ የፖለቲካ ፓርቲ ነኝ እንዳይል ሆ እንከን ሆኖበታል፡፡ ኤኤንሲ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የምርጫ ቀን ሲደርስ ነጮች ጥቁሮችን በውሻ የሚያስነክሱበትን ቪዲዮ እየለቀቀ የጥቁሮችን የምርጫ ካርድ የሚሰበስብ ካሳለፈው የፀረ-ነጭ ዘረኛ ፕሮፓጋንዳ አሁንም ያልተላቀቀ ቡድን ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
እና አይደለም የዘር ፖለቲካን እንደ ትክክለኛ መርህና የመደራጃ ሀሳብ ቆጥረን ለተገኘነው ለእኛ ይቅርና፣ የጎሳና የዘርን አደረጃጀት እርግፍ አድርገን ትተነዋል ብንልና ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓትን እናምጣ ብንል፣ አሊያም በዘር መደራጀትን ህገወጥ አድርገን ብንነሳ እንኳ ያለፍንበት ጎሳዊ የዘር አደረጃጀት ታሪካችን (Our past tribal legacies) በአሁኑና የወደፊቱ ዘመናዊ የፖለቲካ ጉዟችን ላይ የራሱን ትልቅ ጠባሳና አሉታዊ አሻራ እንደሚያሳርፍብን ከደቡብ አፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ አይተን የምንማረው አብነት ነው፡፡
እንደ ስንብት የዚምባብዌውን ሮበርት ሙጋቤን ላንሳ፡፡ ሮበርት ሙጋቤ ገና ከመነሻው ነው የቅኝ ገዢዎቹን አፓርታይዳዊ የፖለቲካ አደረጃጀት ሃሳብ በፅኑ የተቃወመው፡፡ እስካሁንም ሬከርዳቸውን ማየት በሚቻል ቪዲዮዎች ሙጋቤ በተደጋጋሚ ለዓለም ያሳውቅ የነበረው ከጎሳ ክፍፍል ከፍ ያለ የጋራ ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓትን ስለመመስረት ነበረ፡፡
‹‹እኛ እርስ በእርሳችን ነጭና ጥቁር ተባብለን፣ ሾናና ካራንጋ፣ ማንዪካና ዜዙሩ፣.. እየተባባልን ተከፋፍለን፣ ዘመናዊቷን ዚምባብዌን መፍጠር አንችልም – ነጮቹ እናንተ ጥቁሮች የራሳችሁን ፖለቲካና የራሳችሁን አስተዳደር መሥርቱ – እኛም በራሳችን እንወከልና በልዩነታችን ተስማምተን በየራሳችን እንተዳደር ይሉናል – ሁሉም ጎሳ እየተነሳም እንዲያ ይለናል – ነገር ግን የተከፋፈለ ቤት አንድ ላይ አይቆምም – እኛ የምንመኛትና የምንፈልጋት ዚምባብዌ ከዘርና ክፍፍሎች በላይ የሆነችና ሁሉም ያቅሙን የሚያዋጣባት በጋራ የተባበረ ክንዳችን የምትገነባዋን ዚምባብዌን ነው›› – እያለ ነበር የሚናገረው የ7 አካዳሚክ ዲግሪዎች ባለቤት የነበረው ሮበርት ሙጋቤ፡፡ ምን ዋጋ አለው? ለመሆኑ ዚምባብዌ ሙጋቤ ከመነሻው ያሰባትን ያህል ተሻግራለች ወይ? እንዲያ ዓይነት ሀገራዊ ዘመናዊ ራዕይ የነበረው ሰውዬስ እንዴት የታወቀ አምባገነን ሊሆን በቃ? እነዚህን ደጋግሞ መጠየቅና ትምህርት መውሰድ የኛ ፈንታ ነው፡፡
በመጨረሻ ግን ‹ዞሮ ዞሮ ከቤት› እንዲሉ የሁሉም ዙረታችን ማጠንጠኛ የራሳችን ሀገርና የራሳችን ሕዝብ ነውና – የማጠንጠኛችን መዳረሻ ወደሆነችው ወደ ውዲቱ ሀገራችን እንመለስ፡፡ ወደ ራሳችን እንመልከት፡፡ እና የሀገራችንን የፖለቲካ እንቆቅልሽ ለመፍታት እንሞክር፡፡
ከእኛ ቁጥራቸው በብዙ እጥፍ በሚያስከነዱ ጥንታዊ ጎሳዎች ከጫፍ እስከ ጫፍ የተዥጎረጎሩ ብዙ የዓለማችን ሀገሮች – የተጣባቸውን ጥንታዊ ጎሳዊ አስተሳሰብና ጋርዮሻዊ ክፍፍል፣ አሊያም መነካከስና መበጣጠስ የሚነዷቸውን ጎሳዊ ጦሶች – ባላቸው አቅምና ችሎታ ሁሉ ታግለው ካሸነፉ – እና ከጎሳዊ መበላላቶች ከፍ ያለ የሁሉም ዜጋ የሆነ ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓትን መዘርጋት ከተሳካላቸው – እኛስ ይሄን ለማድረግ የሚያተን ምንድነው?
ለመሆኑ በሀገራችን የተዘገራው ጥንታዊ ጎሳዊ የፖለቲካና አስተዳደር ሥርዓት ‹አርቴፊሻል› ነው ወይስ ተፈጥሯዊና እውነተኛ? በትክክል እየሆንን ያለነው ምንድነው? ምን እናድርግ? ምንስ አናድርግ?
( …/ይቀጥላል)
Filed in: Amharic