>

የነገድ ‹‹ፖለቲካ›› Vs. ሀገራዊ ፖለቲካ  (አሰፋ ሀይሉ)

የነገድ ‹‹ፖለቲካ›› Vs. ሀገራዊ ፖለቲካ 

አሰፋ ሀይሉ

የድሮ ቅኝ ገዢዎች፣ ተገዢዎቹን ማኅበረ-ሰቦች በትምህርት እንዳይገፉ፣ እንዳያነቡ፣ በዕውቀት ነክ መስኮች እንዳይሰማሩ፣ እና ለህዝባቸውም የአዕምሮ መነቃቃትን እንዳይፈጥሩ ይከለክሉ ነበር፡፡ እነርሱ የሚያውቁትን ተገዢዎቹ እንዳያውቁ ነው፡፡ ራሳቸውን ነጻ እንዳያወጡ፣ እነሱ የደረሰቡት ደረጃ እንዳይደርሱ፣ እንዳይፎካከሩ፣ እንዳይቀድሙም ተጨንቀው ነበር፡፡ የሚያሳዝነው አሁን በቅኝ ተገዢዎች የነጻነት ዘመን በሚባልበት ወቅት ላይ ሆነን እንዲህም እያማናቸው፣ አሁንም የምናገላብጠው የእነርሱን የዕውቀት ትሩፋቶች መሆኑ ነው፡፡ ብዙ የእነርሱን የሥልጣኔ ቱሩፋቶችስ እናግሰብስ የለ? ዕውቀታቸው ለእድገታችን የሚጠቅመን ከሆነ የታባቱንስና፡፡ ለማን ደቼ እንተወዋለን? ከልካይ የለብን ባሁን ዘመን! ካገኘነው አንምርላቸውም!
በዓለም ላይ አሉ የተባሉ የሶሺዮሎጂ ጥናቶችን፣ የፖለቲካና ማህበራዊ ሳይንስ ምርምር ሥራዎችን፣ በህግና ዲሞክራሲ ርዕሰጉዳዮች ላይ የተጻፉ ምሁራዊ ጥናቶችን፣ እና ሌሎችም አሉ የተባሉ የመንግሥት አስተዳደር ድርሳናትን አግኝተን ለማንበብ እንሞክር፡፡ ብዙ የአፍሪካችንንና የሌሎችንም ታሪኮች አጥብቀን እንመርምር፡፡ እና አንድ ነገርን አበክረን እንጠይቅ፡- እኛ ኢትዮጵያውን፣ ወይም እኛ አፍሪካውያን ጎሳዊ ማንነታችንን ከሚገባው መጠን በላይ አላራገብነው ይሆን? በጥንታዊ ጎሳዊ ማኅበረሰቦችና አስተሳሰቦች የተገነባ ባህላዊ ማንነትን የተላበስን ሕዝቦች ብንሆንም፣ ነገር ግን ጎሳዊ ማንነታችን ከሁሉም የእኛነታችን መገለጫዎች ልቆ፣ ሌላውን ዘመናዊ ነገራችንን ሁሉ ሸፍኖ ተገኝቶብን እንደሆነና እንዳልሆነ ከነምክንያቶቹ በጥንቃቄ እንፈትሽ፡፡ ምናልባት ብዙ መልሶችን እናገኝ ይሆናል፡፡
በበኩሌ ከሁለት አሰርት ዓመታት በፊት ገደማ በጥናት የደረስኩበት አንድ ደፋር ድምዳሜ ነበረ፡፡ ደፋር ያሰኘኝ ከወቅቱ ጋር የሚስተሃቀር ስለነበረ ነው፡፡ በግሌ ብዙ ዋጋም ከፍዬበታለሁ፡፡ ነገር ግን እስካሁንም ድረስ ያን አቋም የሚያጠናክርልኝ እንጂ የሚቀይርልኝ ምክንያት አላገኘሁም፡፡ ደጋግሜ የምናገረው የጠራ እውነት መሆኑን ስለማምንበት ነው፡፡
በሀገራችን እየተተገበረ ያለው የብሔር ‹ፖለቲካ› (Tribal Politics) እጅግ ኋላ ቀር የሆነ የሰው ልጅ የማህበረ-ሰብ አደረጃጀት ላይ ተመሥርቶ የተቀመረ የመሆኑ፣ እና ይህ ነገራችን ለወደፊቱም በአስሳሰብ ላይ የተመሰረተ ሁሉንም ዜጋ ያማከለ ሀገራዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዳይዳብር እንቅፋት የሚሆን የዘመናዊ ዲሞክራሲ ነቀርሳ የመሆኑ እውነታ ነበር፡፡ የዘር ፖለቲካ በተፈጥሮው ፍትህን ለሁሉም ለማዳረስ ለሚሹና ለሚችሉ የሀገሪቱ ዜጎች የመንቀሳቀሻ ሜዳውን የሚያሳጣ፣ የሀገር አስተዳደር በአንድ ወገን አቀንቃኞች ብቻ እንዲሞላ የሚያደርግ፣ እና ዓለም በኋላቀርነቱ አንጓጦና አንቅሮ የጣለው የአስተዳደር ዓይነት መሆኑንም ጭምር አስምሬ አልፌ ነበር፡፡ አሁን 19 ዓመት ሆነው፡፡ ጽሑፉ በ150 ገጾች ተተይቦ አሁንም በእጄ ላይ ይገኛል፡፡ ለወቅቱ አበርክቶት ያልቸረ ጥናት፣ ታሪክ ብቻ ነውና ለታሪክ አስቀምጬዋለሁ፡፡ የራሴን በዚሁ ልቋጨውና ከሌሎች ወደቀሰምኩት እውነት ደግሞ ልሸጋገር፡፡
ባሳለፍኳቸው በርከት ያሉ የሥራ ዓመታት በየረገጥኩበት የሚሆነውን ለማስተዋል ብዙ ሞክሬያለሁ፡፡ በርከት ያሉ ሊቃውንት በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ የጻፏቸውን ድርሰናትም ለማገላበጥ በብዙው ጥሬያለሁ፡፡ እና የሚገርመኝ ነገር ወደ ተቀራራቢ ድምዳሜ የሚወስደኝ እንጂ ከላይ የገለጽኩትን እውነት የሚቃረን ነገር ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ብዙዎቹ የሚናገሩት ይህ በደም ትስስር፣ እና በቋንቋ አንድነት፣ አሊያም በሰውነት ገጽና ተክለቁመና ምስስሎሽ፣ አሊያም ከሌላው የተለየ ባህልን ወይም ሐይማኖትን ወይም አበላልን፣ ለቅሶን፣ ጎጥን ወይም መግባቢያ ቋንቋን በመጋራት የተነሣ የሚፈጠረው ይህ የሰዎች ስብስብ – ጎሳ፣ ብሔር፣ ነገድ፣ ዘውጌ፣ ወዘተ ብለን የምንጠራው – በዘመናዊው የሰው ልጅ የእድገት ደረጃዎች ውስጥ ከተፈጠሩ የሰው ልጅ ስብስቦች ሁሉ – እጅግ ኋላቀሩ (Primordial ወይም Primal) የሚባለው ኋላቀር የሰው ልጅ አደረጃጀት ሥርዓት የመሆኑን ያፈጠጠ ሃቅ ነው፡፡
ይህ ዓይነቱ ነገዳዊ ወይም ጎሳዊ የሰውልጆች ስብስብ (ወይም ማኅበረ-ሰብ) ማንም ሰው አቅዶና አስቦ ይሁንልኝ ብሎ የሚፈጥረው ሳይሆን፣ በጊዜ ሂደት እንዲሁ የሚፈጠር፣ ሆነ ተብሎና ታስቦ ሳይሆን ለደመነፍሳዊነት ባጋደለ የሰው ልጅ አብሮ የማዝገም ዝንባሌ የተነሳ በሚፈጠር – የሰው ልጅ ጋርዮሻዊ ስብስብ ነው፡፡
ከጥንታዊ አንግሎ ሳክሰኖች እስከ ጥንታዊ ግሪኮች፣ ከሰሜን አሜሪካ ቀይ ህንዶች እስከ ደቡብ አሜሪካ ጥንታዊ ነገዶች፣ ከካሪቢያን እስከ ኤዢያ ፓሲፊክ፣ ከአፍሪካ እስከ አንታርክቲካ ድረስ – ቁጥራቸው እጅግ በበዛ የሰው ልጅ ጥንታዊ ነገዶችና ማህበረሰቦች ላይ አያሌ የምርምር ሥራዎችና ሳይንሳዊ ጥናቶች ተካሂደዋል፡፡ ብዙ ጥናቶች የሚያሳዩት የእነዚህ ጥንታዊ ማህበረሰቦች በደምና በሥጋ የተሣሰረ አደረጃጀትና ጥንታዊ ማህበራዊ ሥሪት፣ ምንም እንኳ ለዘመናት የነገዶቹን ህልውና ለመጠበቅ ያገለገለ ቢሆንም፣ ዘመናዊነትን ያልተላበሱ እና በጊዜ ሂደት መሻሻል የማይችሉ ብዙ እንከኖችን ይዞ የቀጠለ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ጥንታዊ ባህላዊ የማህበረብ ስብስቦች የራሳቸው የሆኑ ብዙ መልካም እሴቶች እንዳሏቸው ጥርጥር ባይኖረውም በብዙ መልኩ ለለውጥና ለዘመናዊ ዲሞክራሲያዊ አሰራር ዝግ ናቸው፡፡
ጥቂቶቹን ለመግለጽ ለምሳሌ ብዙዎቹ ከነገዱ ውጭ ያለን ሌላን ሰው ወደ ስብስባቸው የሚቀበል ማንነት የላቸውም፡፡ በእጅግ ጥቂቶቹ አብነቶች ሌላውን ሲቀበሉም እንኳ የሰውን ልጅ የአስተሳሰብና የማንነት ነጻነትን የሚገፉ ብዙ ጎሳዊ መስፈርቶችን አሟልቶ ብቻ ነው፡፡ በአባሎች ጥያቄና ይሁንታ የሚቀየር የጎሳ ቀኖና የለም፡፡ እንኳን የማህበረሰቡን እሴቶች ጥያቄ ማስገባት ይቅርና ቀላል የምንለውን የግንባር ጭረት ወደ ታፋዬ ይዛወርልኝ የማለት መብት ያለው የጎሳ አባል የለም፡፡ በወንዱ ፋንታ ሴቷ መሪ ትሁን ብሎ መጠየቅ እንደመዘባረቅ ይቆጠራል፡፡ የግለሰቦች ነጻነት ብዙውን ጊዜ እጅግ የታፈነ ነው፡፡ ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር በአስተሳሰብም ሆነ በጋብቻ መጣመር አጥብቆ የተከለከለ አሊያም በጥብቅ የሚወገዝ ድርጊት ነው፡፡
እነዚህ የጎሳ ስብስቦች ሐይማኖቴ የግሌ ነው አይባልባቸውም፡፡ ብዙ ጊዜ በጎሳው ወይም ነገዱ አባላት የሚቀርቡ ሃሳቦች በጎሳው ተሰሚነት ባለው አንድ ሰው ፍላጎትና ሀሳብ ይለመጣሉ፣ ወይም ይደፈጠጣሉ፡፡ እና ሌላም ከዘመናዊ ማህበረሰቦችና የፖለቲካ ማህበሮች የሚቃረን ብዙ ዝግ ነገር አላቸው፡፡ እነዚህ ጎሳዊ ስብስቦች ለዘመናዊው ‹‹ፖለቲካ›› ብለን ለምንጠራውና ‹‹ፖለቲካ ፓርቲ›› ብለን ለምንጠራው አስተሳሰብና ተሞክሮ እጅግ የራቁ የሰው ልጅ ስብስቦች ናቸው፡፡ ይሄ አባባል ጎሳችን ዲሞክራሲያዊነትን ተላብሷል ብለው ለሚያምኑትም ጭምር የሚሰራ ነው፡፡
ለመሆኑ ዓለም ባለፈባቸው የሀገር ምስረታ ታሪኮች ውስጥ እነዚህ ጥንታዊ ማኅበረ-ሰቦች በዘመናዊው የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ የነበራቸው ሚና ምን ነበረ? ከዘመናዊው የሀገር አስተዳደር ጋር ምን ዓይነት ግንኙነትና ፋይዳ ሲኖራቸውስ ነው የሚታዩት? የሚሉትን ጥያቄዎች ያነሳን እንደሆነ – ለአቀራረብ እንዲመች በሚል የተከፈሉ በጥቅሉ ሶስት ዓይነት ጥንታዊ ማህበረ-ሰቦች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡
አንደኛው በቀደመው የቅድመ-ቅኝ ግዛት እና የቅኝ ግዛት ዘመን ተሞክሮ የታየ የግንኙነት ዘዬ ሲሆን – ያም አንድም እነዚህን ጎሳዊ ማንነቶች ለዘለዓለሙ እንደማይቀየሩ የቅኝ ተገዢዎቹ ‹‹ያልሠለጠኑ›› ማንነቶች በመቁጠር – በቅኝ ገዢዎቹ አስተዳደር ውስጥ የሀገሬውን ስሞታ እንዲያቀርቡ (ይበልጡኑ ደግሞ የቅኝ ገዢዎቹን ትዕዛዛት ለሀገሬው እንዲያደርሱ) የየጎሳው ተወካዮች የተሰሚነት (የወሳኝነት ሳይሆን የመደመጥ) ሚና ተሰጥቷቸው ለታዛቢነት በቀረበ ሚና በገዢው የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ የሚወከሉበት የግንኙነት አሠራር ነው፡፡
ይህ ‹ሎካሉ› (የሀገሬው ሰው) ሰው ምን ይፈልጋል? የሚለውን ነገር ለማወቅ ቅኝ ገዢዎች ያስተዋወቁት የየዘውጉን ወኪሎች በመንግሥት ዕውቅና ሰጥቶ (ጥቅምና ስልጣኖችን ቸሮ ጭምር) የሚሉትን የመስማት ዘይቤ – ጉዳዩን በጥልቅ ባጠኑ ምሁራን ከሚተችባቸው ነጥቦች አንዱ – የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ይህን ጎሳዊ የውክልና ሥርዓት በቅኝ ተገዢዎቻቸው ላይ የዘረጉበት አመክንዮ – ‹‹እኛ ገዢዎቹ ከተገዢዎቹ የበለጠ ዘመናውያን ነን›› የሚል የሥልጣኔ የበላይነት ስሜት ተላብሰው ስለመጡ ነው የሚል ነው፡፡
ለምሳሌ፡- አንድ እንግሊዛዊ – ‹‹An English man is always an English man›› ብሎ ነው ስለራሱ የሚናገረው፡፡ እንጂ እኔ ሳክሶን ነኝ፣ እኔ የካሌዶን ጎሳ ነኝ፣ አሊያ ያኛው የካርቬቲ ነገድ ነው፣ ይሄ ጎሳው ካቬቲ ነው፣ ይሄኛው የኤፒዲ ጎሳ አባል ነው፣ ያኛው የዳምኖኒ ዘውጌ ነው፣ ያኛው ኖቫንቴ ነው፣ ወዘተ እያለ የዛሬዋን ታላቋን ብሪታንያን የመሠረቱትን ጥንታዊ የእንግሊዝ ነገዶች አይዘረዝርልህም ቢሞት፡፡
ታዲያ ራሳቸውን በጥንታዊ ጎሳዎቻቸው የማይገልጹትና የማይወክሉት እነዚሁ እንግሊዞች፣ ታዲያ ለምንድነው ቅኝ የገዟቸውን ሕዝቦች በጎሳቸው ሼል ውስጥ ከትተው ‹‹አይደንቲፋይ›› ለማድረግ፣ በጎሳቸው ለማወቅ፣ በጎሳቸው እየነጣጠሉ ለማድመጥ፣ በጎሳቸው አንጻር ስለነሱ ለማሰብና ለመረዳት የፈለጉት? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡
ስለራሱ ጎሳ ብትጠይቀው ትልቅ ስድብ እንደሰደብከው የሚቆጥር አንድ እንግሊዛዊ ቅኝ ገዢ፣ ደቡብ አፍሪካውያኑን ተገዢዎቹን ባንቱስታንና ቡሽሜን፣ ዞሳና ዙሉ፣ ሆቴንቶትና ናማ፣ ፒግሚና ማሳይ፣ ሳንዳዌና ሃድዛ፣ በርበርና ኮይሳን፣.. እያለ በጎሳ እየከፋፈለ መጥራትና ማደራጀትን ከየት አመጣው? – በማለት ይጠይቃሉ ምሁራኑ፡፡ እና ምላሻቸውንም ይሰነዝራሉ፡፡
ቅኝ ገዢዎቹ አፍሪካውያን ተገዢዎቻቸውንም ሆነ ሌሎች ቅኝ ተገዢ ሕዝቦቻቸውን በጎሳ መለኪያ የሰፈሩበት ዋነኛው ምክንያት – እንግሊዞቹ ራሳቸውን እኛ የሰለጠንን (ስለሆነም የጎሳና የነገድ አስተሳሰብንና አስተዳደርን የተሻገርን) ዘመናዊ ሰዎች ነን ብለው በማሰባቸው ነው፡፡ ይሄ ‹‹እኛ ስልጡኞች ነን›› ‹‹እኛ ከእናንተ ጥንታዊ ኋላቀር ማኅበረሰብ ከፍ ያልን፣ እና ራሳችንን በመሠረትናት ታላቅ ሀገር ዜግነት የምንገልጽ ሥልጡን እንግሊዛውያን ነን!››፣ ‹‹እናንተ ግን ከቺምፓንዚዎች የጋርዮሽ የመንጋ አስተሳሰብ ያልወጣችሁ፣ እና ሥልጡኑ ሰው የደረሰበት የእድገት ደረጃ ላይ ለመድረስ ገና ብዙ የሚቀራችሁ፣ ኋላቀር ጎሳዊ ህዝቦች ናችሁ!›› የሚለው ውስጣዊው አስተሳሰባቸው ነው – በዚያ መነጽር የሚቃኙትን አፍሪካዊ ነገር ሁሉ በጎሳና በነገድ፣ በጎጥና በዘውግ ውስጥ ጨምረው ካልሆነ በቀር አላሳይ የሚላቸው ዋነኛው ምክንያት፡፡
በ20ኛው ምዕተ ዓመት በአውሮፓውያን ምሁራን የተካሄዱ አፍሪካውያንን፣ ደቡብ አሜሪካውያንን፣ እስያውያንንና አውስትራሊያውያን የሀገሬውን ነባር ሰዎች – በአካባቢያቸው ከሚኖሩ የዱር አራዊቶች ጋር ጥንታዊ የጋርዮሽ አኗኗራቸውን፣ በዘመድ አዝማድ ተከበው የሚኖሩትን ማህበራዊ ሕይወት፣ የጦርነትና የእርቅ ሂደቶቻቸውን፣ እንዲሁም የመግባቢያና የምልክት አጠቃቀማቸውን፣ ወዘተ በማነጻጸር የተሠሩ በርካታ ጥናቶች አሉ፡፡
አንዲት ኬንያ ውስጥ የነበረች አውሮፓዊት አንትሮፖሎጂስ ሴት ልጇን እኩዮቿ ከሆኑ የማሳይ ህጻናት ጋር አነጻጽራ ባሳተመችው ጥናቷ አንድ የማሳይ ህጻን እስከ 7 ዓመት ዕድሜው አዕምሮው ብሩህ ቢሆንም፣ ከ7 ዓመቱ ጀምሮ ግን ማሽቆልቆል ይጀምራል የሚል ድምዳሜ አስቀምጣ እናገኛታለን፡፡ አሁንም ለምን አጠናች አይደለም፡፡ ግን የማሳዩ የልጇእኩያ የ7 ዓመት ህጻን ከዚያ ዕድሜው ጀምሮ በእንስሳት አደንና ጫካ ኑሯቸውን ከሚያቀኑ ቤተሰቦቹ (ወይም ጎሳዎቹ) ጋር ህይወቱን ሲያሳልፍ የሚገጥሙት በርካታ ውሱንነቶች ሳይታያት ቀርቶ ነው ማለት ግን ዘበት ይሆናል፡፡ ያን የሚጠይቅ የለም፡፡ እየተደናነቁ አንዱ በሌላው ጥናት ላይ እየጨመረ ብዙ ተመሳሳይ ጥናቶች ይፋ ይሆናሉ፡፡
እና የኛ ጎሰኛ የአዕምሮ ዝግመተኝነት በሳይንስ የተረጋገጠ እውነት ይሆናል፡፡ ይሄን አዕምሮ ከጎሳዊ ጎሮኖው ወጥቶ እንዴት ዘመናዊ አስተሳሰብን እንዲላበስ ትከጅላለህ? አብደሃል? ‹Are you crazy?› ነው የሚባባሉት፡፡ እስካሁንም እንደዚያ የሚባባሉ ይመስለኛል፡፡ ሌላ ቀርቶ ለዓለማቀፉ የኖቤል ሽልማት የበቃውን አብይ አህመድን ሲገልጹ (በኢንሳይክሎፒዲያዎች ሳይቀር) ‹‹ከብዙሃኑ የኦሮሞ ጎሳ የተገኘ…›› እያሉ ሲጽፉ ታገኛቸዋለህ፡፡ አንዴ የሆነ የጎሳ መጋኛ አያጠናግርህ፡፡ ካጠናገረህ ፀበል ራሱ የሚያስለቅቅህ አይመስለኝም፡፡ እንደዚያ ይመስሉኛል አንዳንዴ፡፡ ከኛ በላይ እነሱ በእኛ ጎሰኛ ማንነት ተለክፈው ቀርተዋል፡፡ ይገርመኛል በጣም፡፡
እንግዲህ እንደ ምሁራኑ ሂስ – ይህን ‹ፕረሚስ› አስቀምጠው ነው ቅኝ ገዢዎች ወደ እኛ የመጡት፡፡ ስለሆነም ራሳቸውን በማይገልጹበት የጎሳ መለኪያ እኛን ሲሰፍሩን ኖረዋል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ብዙ ነገሮችን አቅልሎላቸዋል፡፡ አንደኛ በገዢውና በተገዢው መካከል የማይታለፍ የሥልጣኔ ድንበር መኖሩን የሚያውጅ ነው፡፡ ሁለተኛም ያሰመሩትን የዘርና የቀለም ድንበር የሚደግፍ ሳይንሳዊ ምክንያት (‹ጀስቲፊኬሽን›) ሆኖም አገልግሏቸዋል፡፡ በመጨረሻም ብዙ ቅኝ ተገዢዎቻቸውን እርስበርስ በጎሳና በነገድ ከፋፍሎ በማቆየትና እርስ በርስ በማጋጨት ረገድ ለአገዛዛቸው ህልውና ዳጎስ ያለ ጠቀሜታን አትርፎላቸዋል፡፡
የሚገርመው ነገር ቅኝ ገዢዎቹ ከሄዱም በኋላ የመጡ የአፍሪካ መሪዎች፣ ከቅኝ ገዢዎቹ የተለየ አፍሪካዊ ማንነትን ለማቀንቀን ሲነሱ፣ ራሳቸውን ለመግለጽ የሞከሩት፣ ከቅኝ ገዢዎቹ ‹‹ዘመናዊ አውሮፓዊ›› የሥልጣኔ ትርጉም ጋር ተቃራኒ የመሠላቸውን፣ ነገር ግን ቅኝ ገዢዎቹ እኛን ሲሰፍሩ የኖሩበትን ያንኑ አፍሪካዊ የብሔር፣ የጎሳ፣ የነገድ፣ የዘውግ መለኪያ – ከነጋርዮሻዊ የአኗኗርና የአስተሳሰብ ዘይቤው ከወደቀበት አንስተው – ለራሳቸውና ለህዝባቸው እንደ ነፃነት ካባ በመደረብ ነበር፡፡
በሚገርም ሁኔታ ለምሳሌ ከቅኝ ግዛት ማግስት በአፍሪካውያን የተፈጠሩ የህዝብ ሙዝየሞች፣ የታወቁ የልብወለድ ሥራዎች፣ እና የሀገር ታሪኮች ሁሉ – በጎሳ ማንነቶች፣ ትውፊቶች፣ እና ታሪኮች የተሞሉ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ ቅኝ ገዢዎቹ ሥልጡን የሚሏቸውን የአውሮፓ ጎብኚዎች ለማስደነቅ በየሙዝየማቸው ይሰበስቡ የነበሩትን ጥንታዊ የጎሳ የዕደ ጥበብ ውጤቶች ነው በአፍሪካ ሙዝየም ውስጥ ገጥግጠው የምናገኛቸው፡፡ እና ምናልባት አንዳንድ በአውሮፓውያኑ ለመዝናኛነትና ለጀብዱ የሚታደኑ የዱር እንስሳትን የደረቁ አካሎች፣ ቆዳዎችና ቀንዶች ነው፡፡ እስካሁንም ድረስ፡፡
በራሳቸው ሙዝየሞች ግን አውሮፓዊ የጥበብ ሥራ ነው ብለው የሚያቀርቡልህ ዳ ቪንቺና ራፋኤል፣ ፒካሶና ሮዲን፣ በርኒኒና ዴላክሯ፣ ወይ ሌሎች የአውሮፓ የጥበብ ድንቃድንቆች የሠሯቸውን፣ የሰው ልጅ ምጡቅ አዕምሮ አምጦ የወለዳቸውን የሰውን ልጅ የሥልጣኔ ጫፍ ያሳያሉ የሚባሉ የፈጠራ ሥራዎችን ነው፡፡ የአፍሪካ ጥበብ ብለው ግን የሚያሳዩህ – ግፋ ቢል ጥንታዊ የምዕራብ አፍሪካ ከእንጨት የተጠረቡ የፊት ጭምብሎችን ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂ ስልጣኔው ዓለምን እየመራ ያለው፣ እና ራሱን ‹‹ያደጉ ሀገሮች›› ‹‹የበለፀጉ ሀገሮች›› ወይም ‹‹አንደኛው ዓለም›› ብሎ የሚጠራው ምዕራብ አውሮፓዊው (እና አሜሪካዊው) ሥልጣኔ – ራሱን የሚገልጽበትና ሌላውን ሕዝብ (እኛን) የሚገልጽበት ዓለማዊ አተያይ ነው፡፡
ስለሆነም በእነርሱ አስተሳሰብ መሠረት እኛ አፍሪካውያን የማንለወጥ፣ የማናድግ፣ የማንሻሻል፣ የአዕምሮ ፈጠራ የማይጎበኘን፣ ያንኑ የማይለወጥና አንድ የሆነ የጥንታዊ ኮተታችንን ይዘን እስከ ዓለም ፍጻሜ የምንጓዝ ዝንተዓለማዊ ጎሳዎች ነን፡፡ እነርሱ ደግሞ ራሳቸውን ከጎሳ አላቅቀው፣ ወደ ሀገራዊ አስተሳሰብ የተሸጋገሩ፣ ከሀገራዊ አስተሳሰብም አልፈው ወደ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ አስተሳሰቦች የተሸጋገሩ፣ ከዓለማቀፋዊ አስተሳሰብም አልፈው ወደ ግለሰብ ነጻነት የመጨረሻ እርከን የተሸጋገሩ፣ ከግሰለብም አልፈው ለእንስሶች መብት እስከመቆርቆር የደረሱ ዘመናዊ ሰብዓውያን ፍጡሮች ናቸው፡፡ እና ስለ በልካቸው ስለ ዜጋ መብት፣ ስለ ሀገራዊ ችግሮችና መፍትሄዎች፣ ስለ ግለሰብ ነፃነቶችና ገደቦች፣ ስለ እንስሳትና አካባቢ ጥበቃ በሚመለከቱ የሥልጡናን ሰዎች ጉዳዮች ዙሪያ አተኩረው ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡
እኛ ያልሰለጠንነውስ? እኛ ያልሰለጠንነው አፍሪካውያን የስነልቦና ቅኝ ተገዢዎች ደግሞ እነርሱ ከሄዱ ከግማሽ ክፍለዘመን በኋላም እነርሱ በሠፈሩልን የጎሳ አንቀልባ ውስጥ ተሸጉጠን፣ የዱር እንስሳቶቻችንንና ያልሰለጠነ ጥንታዊ ማህበረሰባችንን መጥተው እንዲጎበኙልን እየለመንን፣ በጎሳና በነገድ የማንነታችንን ከፍታ አሳይተን፣ በልካችን የተሰፋ ጎሳዊ ሥርዓትን እያቀነቀንን መንጎዳችንን እንቀጥላለን፡፡ በዚህ በዘመናዊው ዓለም፡፡ እና እኛን ከጎሳዊ ከረጢታችን ውጭ ለመቀበል የሚተናነቀውን የምዕራቡን ዓለም የሥልጡን ቅኝ ገዢነት አስተሳሰብ ምንጭ በጥልቅ ለመረዳት ለሚሻና ለሚችል ማንም ሰው – እየሆንን ያለው፣ እና እየተጓዝንበት ያለው ጎዳና በምንና ከምን እንደመጣ፣ እና ወደየት እንደሚወስደን መገመት አያዳግተውም የሚል እምነት አለኝ፡፡
ይህን አውሮፓውያን ያስተዋወቁትን እኛን አፍሪካውያንንና ሌሎች በቅኝ የተገዙ ህዝቦችን ሁላችንንም ከሁሉም ነገራችን በላይ ትልቁን ሥፍራ ሰጥተው በወል ያለበሱን የጎሳዊ ማንነታችን ብርድልብስ፣ እና ከዚህ አፍሪካን ከሸፈነው የጎሳ ብርድልብስ የወጣውን የተዛባ ጎሳዊ ምደባና አመለካከት መነሻ ምክንያት በተመለከተ – ይህን ያህል ካልን፣ እጅግ ገራሚ ስለሆነው የአውሮፓውያኑን ቅኝ ተገዢዎቻቸውን በጎሳ ጎሮኖ ከትቶ የማየት ተግባር በእኛ በአፍሪካውያን ስለተኮረጀበት አብነት ደግሞ እስቲ አንድ ምሳሌ ወስደን እንይ፡፡
ለምሳሌ የላይቤሪያን ነፃ የጥቁሮች ሀገር በአፍሪካ ለመመስረት አልመው የመጡት የአሜሪካ ጥቁሮች እነ አርተር በርክሌይ የተጠቀሙበት አንድ አሠራር ነበረ፡፡ ያም ምንድነው? እነ በርክሌይ በላይቤሪያ ‹‹The Locals›› የሚሏቸውን የሀገሬውን ቀደምት ነዋሪዎች አንድ አንድ ወኪሎችን ዓመታዊ የመቀመጫ ገንዘብ እያስከፈሉ በመንግሥታዊ መማክርት ውስጥ የማስቀመጥና ድምጻቸውን የማሰማት መብት እንዲኖራቸው ሲያደርጉ፣ ‹‹Citizens Proper›› ተብለው የሚቆጠሩትን ከአሜሪካ ፈልሰው የመጡት (እና በብዛት የተማሩትን) ጥቁሮች ማለትም እነ በርክሌይን ደግሞ የሀገሪቱን ዘመናዊ አስተዳደር መሥርተው በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ እየወሰኑ የሚቀጥሉ ሙሉ ዜጎች በማድረግ ላይቤሪያን ያስተዳደሩበት መንገድ ነው፡፡ ይህ ሞዴል ቅኝ ገዢዎቹ ራሳቸውን ከጎሳ ወኪልነት ከፍ በማድረግ፣ ተገዢዎቻቸውን ያገሬውን ሰዎች ደግሞ በጎሳ በመወከል፣ ያስኬዱት ከነበረው የቅኝ ግዛት አስተዳደር የተኮረጀና በአስተሳሰብ ደረጃ አዲስ ዓይነት ጥቁር ቅኝ ገዢ አውሮፓውያኑን በአስተሳሰብና በተግባር ተክቶ የታየበት አዲስ አፍሪካዊ ተሞክሮ ነበር፡፡
ይህ የተለያዩ ጎሳዎች በመንግሥታዊው የተወካዮች ምክርቤት መቀመጫ እንዲያገኙ የሚደረጉበት፣ ነገር ግን የሀገርን ጉዳይ ከጎሳ ማንነት በላይ የሆኑ ‹‹ሥልጡኖቹ›› ቅኝ ገዢዎች ብቻ የሚወስኑበት አካሄድ፣ በብዙ የቅኝ ግዛት አስተዳደሮችም ውስጥ የምናገኘው ሲሆን – በበኩሌ በግሌ – በወያኔ-ኢህአዴግ ዘመንም በተግባር የነበረው የብሄር-ብሔረሰቦች ሥርዓት እውነተኛው ተክለሰውነቱ ከዚህ ብዙም የተለየ ነው የሚል አመለካከት እንደሌለኝ በዚሁ አጋጣሚ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡
እንግዲህ የመጀመሪያዎቹን ዓይነቶች የቅኝ ግዛት ዘመን ጎሳዊ ማኅበረ-ሰቦች ከዘመናዊዎቹ የየሀገራቸው መንግሥታት ጋር ስለነበራቸው የግንኙነት ዓይነት ይህን ያህል ካልን፣ ወደ ሁለተኛውና ሶስተኛው የጎሳዊ ማኅበረሰቦችና የመንግሥት ግንኙነት ዓይነቶች ደግሞ ፈጠን ፈጠን ብለን ለመመልከት እንሞክር፡፡
ሁለተኛ ዓይነቶቹ ጥንታዊ (ነገዳዊ) ማህበረሰቦች ደግሞ ከዘመናዊው ሀገራዊ መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት በአንድ የሀገራዊ ፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ ‹‹ከፊል ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ማኅበረ-ሰቦች›› (Semi-Autonomous Societies) በማድረግ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህ በቅኝ ግዛትና በድህረ-ቅኝ ግዛት ዘመን የተስተዋለ የአስተዳደር ወይም የአገዛዝ ልማድ – በተለይ ሀገሩ ለአመጽ የሚያበረታታ ሁኔታ እንደማይፈጠር ገዢዎቹ ባረጋገጡባቸው ግዛቶች ሁሉ – ራሳቸው በቀጥታ ሀገሬውን ከማስተዳደር ይልቅ – ዋና ዋና የሚባለውን የኢኮኖሚና ፖለቲካ ምንጭ ለራሳቸው ከተቆጣጠሩ በኋላ – የሀገሬውን ጎሳዎች ግን – ለማዕከላዊው መንግሥት የሚጠበቅባቸውን ግዴታ እየተወጡ – ራሳቸውን በራሳቸው ባህላዊ በሆኑት (እና ለዘመናዊው አስተዳደር ባደሩት) የነገድ አለቆቻቸውና የጎሳ መሪዎቻቸው እንዲመሩ የሚተዉበት አስተዳደራዊ ዘይቤ ነው፡፡
አንድ ማጤን ያለብን ነገር አለ፡፡ ይኸውም እነዚህ በከፊል ራሳቸውን ያስተዳድሩ የነበሩ ብዙ የአፍሪካችን ባህላዊ የጎሳ አስተዳደሮች በጊዜ ሂደት ቀስ በቀስ በገዢዎቹ በሚዘወረው ዘመናዊው ማዕከላዊ አስተዳደር ሥር እየተጠቃለሉ እንደመጡ፣ አሊያም ራሳቸውን ወደ ዘመናዊው አስተዳደር እንዳሸጋገሩ፣ አሊያም በጊዜ ሂደት ጥንታዊ ጎሳዊ አኗኗርና ባህላዊ ነገዳዊ አስተዳደራቸውን እርግፍ አድርገው በሀገራዊው ዘመናዊ አስተዳደር ሥር ተጠቃለው መግባታቸውን ነው፡፡ ቦታውና ጊዜው ስለማይፈቅድልን ይህን በዝርዝር አልገባበትም፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የሀገሬውንና የቅኝ ገዢዎቹን የግንኙነት ሁኔታ ማየቱ ይሄን ሁለተኛውን ዓይነት ጎሳዊ-መንግሥታዊ ግንኙነት ምንነት ለመረዳት ጥሩ ምሳሌ ይሆናል፡፡
የመጨረሻው ሶስተኛው ዓይነት የጎሳዊ ባህላዊ ማህበረሰብ እና የሀገራዊ ዘመናዊ አስተዳደር ግንኙነት (ወይም ኢ-ግንኙነት) ደግሞ አለ፡፡ በዚህ ሥር ያካተትኳቸው ዘመናዊው ዓለም ፈጽሞ ያልጎበኛቸውን ጎሳዊ ማኅበረ-ሰቦችና ጥንታዊ ሥርዓቶቻቸውን ነው፡፡ እነዚህ በብዙ መልኩ ከዘመናዊዋ ዓለም የተነጠሉና – ያንኑ የጥንቱን ባህላዊ የጎሳ ማህበረሰባዊ አደረጃጀታቸውን የሙጥኝ ያሉ ብሔሮች እዚህም እዚያም በዓለም ላይ ተበታትነው የምናገኛቸው ጥንታዊ ነገዶች (Remote Tribes) በመባል የሚታወቁት ሲሆኑ – በአሁኑ ጊዜ – እጅግ ጥንታዊ ከመሆናቸው የተነሣ – ሀገራቸውና ዓለም ባሉበት እንዳሻቸው፣ እንደፍጥርጥራቸው ይሁኑ ብሎ የተዉአቸው ናቸው፡፡
የሚገርመው እነዚህ ሶስተኛዎቹ ዓይነቶች የዓለማችን ጥንታዊ ጎሳዊ ማህረበሰቦች – ልክ እንደ ዓይነተኛ የቱሪስት መስህብ ተቆጥረው – የዱር ብርቅዬ አራዊት በየሀገሩ እንደሚተዋወቁትና እንደሚጎበኙት ሁሉ – ምስላቸውና ጥንታዊ ሥርዓታቸው በየሚዲያው፣ በየብሮሸሩ፣ በየብሔራዊ መድረኩና በአንትሮፖሎጂካል ጆርናሎች ለዓለም ህዝብ እየተዋወቀ – በየዓመቱ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ቱሪስቶች የሚጎበኙ – እና የየሀገሩን የቱሪዝም ኢንደስትሪ ደግፈው የያዙ – ሰብዓዊ የገቢ ማግኛ አንጡረ ሀብቶች ሆነው ቀርተዋል፡፡
እውነቱን ለመናገር እነዚህ ባህላዊ ጎሳዊ ማህበረሰቦች ሀገራቸውን ከሚያስተዳድረው መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት በባህላዊ ጌጥነት፣ በገቢ ምንጭነትና በስታቲስቲክሳዊ አሃዝነት የማገልገል ግንኙነቶች ብቻ ናቸው ማለት ይቀላል፡፡ ዘመናዊው የፖለቲካ አስተዳደር ከእነዚህ ጥንታዊ ጎሳዎች የሚወስደው ሀገራዊ ግብዓት የለም፡፡ በእነዚህ ጥንታዊ ጎሳዎች አኗኗርና አደረጃጀት ውስጥ ጣልቃ አይገባባቸውም፡፡ እንዲያውም በየቻለው ሁሉ አጋጣሚ ያንኑ የጥንቱን ጋርዮሻዊ ሰብዕናቸውን ጠብቀው እንዲጓዙ ያበረታታቸዋል፡፡
በሀገራችን ለዚህ ብንጠቅስ፣ ለምሳሌ በደቡብ ኦሞ የሚገኙት የፀማይ፣ የበና ወይም የቢራሌ ማኅበረሰብ ወጣት ወንዶች ዘለዓለም ዓለማቸውን በሬ ደርድረው እየዘለሉ ቢኖሩ የፌዴራሉ መንግሥት ደስተኛ ደስተኛ ሆኖ የሚቀጥል ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ቢያንስ የእነዚህን ጥንታዊ ጎሳዎች ከዘመናዊው ዓለም የአኗኗር ዘይቤ ያፈነገጠ ባህላዊ ሥርዓት ለመመልከት ፈልጎ ከሚመጣ ብዙ የምዕራቡ ዓለም ቱሪስት ላይ መንግሥት ብዙ ሺህ ዶላሮችን በየዓመቱ ይሰበስባል፡፡ በተመሳሳይ የሐመር ጎሳዎች የተለያዩ የጭቃ ቀለሞችን በሰውነታቸው ላይ ለቅልቀው ራቁታቸውን የመንቀሳቀሳቸው ጥንታዊ ጎሳዊ ባህል፣ አሊያም የሙርሌ ሴቶች ጡታቸውን አስጣጥተው የመሄድ ጎሳዊ ባህል፣ ወይም ደግሞ የሙርሲ ሴቶች በጠፍጣፋ ክብ የሸክላ ምጣዶች ከንፈራቸውን ወይም ጆሯቸውን ወጥረው የማጌጣቸው ጎሳዊ ልማድ ባለበት መቀጠል – ለዘመናዊው የሀገሪቱ መንግሥት – በየዓመቱ የማይቋረጥ የውጭ ምንዛሬን ያስገኝለታል፡፡ እና እነዚህ ከዘመናዊው ዓለም ፈሊጦች የራቁ ጎሳዊ ማህበረሰቦች የሀገሪቱን መንግሥት ከሚዘውረው ማዕከላዊው መንግሥት ጋር ያላቸው ቁርኝት ጎሳዊ አኗኗራቸው እንዲቀጥል ከመሻት የመነጨ ኋላቀር የጥቅም ግንኙነት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
/የእኛን ሀገር ስለምናውቅ የራሳችንን በምሳሌነት አነሳሁ እንጂ፣ እንዲህ ዓይነቶቹ ጎሳዊ ማኅበረ-ሰቦች በአውስትራሊያም፣ በእስያም፣ በፓስፊክም፣ በካሪቢያንም፣ በደቡብ አሜሪካም፣ በአፍሪካም በብዙ ሥፍራ በጥቂት ቁጥር ተወስነው እናገኛቸዋለን፣ የግንኙነቱ ዓይነትም የሁለትዮሽ ጠቀሜታው ከሀገር ሀገር ቢለያይም ተመሳሳይ ባህርያትን የተላበሰ ነው፡፡ ከእነዚህ የተወሰኑት ቁጥራቸው አናሳ (Minority) በመሆኑ በብዙሃኑ ተውጠው ልዩ መብቶቻቸውንና ጥንታዊ ነገራቸውን እንዳያጡ ሲባል በየሀገሩ የተለያየ ባህል ተኮር ጥበቃና ያልተቋረጠ የብሔር አክቲቪዝም ይደረግላቸዋል፡፡ በእነርሱ ጥንታዊ ጎሳዊ ባህል ባለበት መቅረት የተነሣ ከሚገኘው ብሔራዊ ገቢ የተወሰነውም በልዩ ልዩ መልኩ ለየጎሳዎቹ አባላት ጥቅም እንዲውል በየሃገሩ መንግሥት እንደየአቅሙና ንቃቱ ጥረት ይደረጋል፡፡/
በማጠቃለያችን ማንሳት የምፈልገው አንድ ነጥብ – እነዚህ ጎሳዊ ባህላዊ አስተዳደሮች ከዘመናዊው መንግሥታዊ ሥርዓት ጋር በሚፈጥሩት ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት ቀስ በቀስ እየሟሙ በዘመናዊ ፖለቲካዊ ሥርዓቶች አስተዳደር መተካታቸውንና፣ የቀሩትም በሂደት በተመሳሳይ መካተታቸው ወይም ‹‹ቦዲ-ፖሊቲክ›› ወደምንለው ሀገራዊ የዜግነት ድርሻ ደረጃ ራሳቸውን ማድረሳቸው እንደማይቀር ነው፡፡ ይህን ስንል – እነዚህ ጥንታዊ ጎሳዊ ማኅበረ-ሰቦችና ጥንታዊ ጎሳዊ አስተሳሰባቸውና አስተዳደራዊ ሥርዓታቸው ምንም ዓይነት መልካም እሴቶች የሉትም፣ ወይም ማህበረሰቦቹ ሁሉንም ባህላዊ ትውፊቶቻቸውን ተገፍፈው ወደ ዘመናዊው ሀገራዊ ፖለቲካዊ ሂደት ይቀላቀላሉ ማለት አይደለም፡፡
የተቀየረውና የሚቀየረው ነገራቸው የተሳትፎ አድማሳቸው ነው፡፡ ይህ ባህላዊ የጎሳ ሥርዓትና የጎሰኝነት አስተሳሰብ ነው በየሀገሪቱ ባሉ ዜጎች ሁሉ በጋራ ለጋራ ጥቅም በሚዘወር ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት፣ በዘመናዊ ሀገራዊ አስተሳሰብና፣ ከብዙ ዓይነት የሀገሩ ህዝቦች ጋር በሚያወዳጃቸውና በሚያዛምዳቸው ሰፊ ዕድል የሚተካው፡፡ ከዚህ ውጭ በሊትሬቸር፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ እና በሌሎችም ብዙ ሰብዓዊ መስኮች ራሳቸውን እያበለጸጉ አይቀጥሉም ማለት አይደለም፡፡ በብዙ ሀገሮች እነዚህን ነገሮቻቸውን እንዳያጡ ብዙ እገዛ ይደረግላቸዋል፡፡
ብዙ እንዳልኩ፣ ብዙ ነገርም እንዳነሳሁ አውቃለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ጉዳዮች በዚህ መልኩ በጨረፍታ ብቻ የሚቋጩም እንዳልሆኑ አውቃለሁ፡፡ ከዚህ በላይ ብጽፍ ግን አንባቢን ያለመጠን እንደማሰልቸት ይቆጠራል፡፡ ጥቂት የመጨረሻ ጥያቄዎችን አንስቼ መሰናበት ግን ፈለግኩ፡፡
ለመሆኑ ከጥንታዊ አደረጃጀት ያልተላቀቁ የጎሳዊ ማኅበረ-ሰቦች በአንድ ሀገር ውስጥ በዝተው የመገኘታቸው እውነታ – ዘመናዊ ሀገራዊ አስተዳደርና ዘመናዊ የዜጎች ፖለቲካዊ ሥርዓት እንዳይመሠረት እንቅፋት ይሆናል ወይ? በጎሳዊ ‹ፖለቲካዊ› አጀንዳዎች ተወጥሮ እየተርገበገበ ያለውን መንግሥታዊ የአስተዳደርና ፖለቲካ ሥርዓታችንን – በሀገራዊ የጋራ ጉዳዮችና ርዕዮተ-ዓለማዊ አጀንዳዎች ዙሪያ ወደሚያውጠነጥን ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት ከፍ ማድረግ በተግባር የሚቻል ነው? ለመሆኑ እንደኛ ባለች ከ60 በላይ ጎሳዎች ከነ80 ቋንቋቸው በሚርመሰመሱባት ‹‹የጎሳ ቅርጫት›› ሀገር፣ ከጎሳዊ አጀንዳዎች የተላቀቀ ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓትን ለማዋለድ መከጀል ያስኬዳል? እንዴት?
(…/ ይቀጥላል)
Filed in: Amharic