>

ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት! [ክፍል ፪] አቻምየለህ ታምሩ

ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት! [ክፍል ፪]

አቻምየለህ ታምሩ

የዐቢይ አሕመድ አፈቀላጤው ታዬ ደንደአ ስለ ዛጔ እና ስለሰለሞናውያን ታሪክ አላዋቂነቱን ያሳወቀበትን ዝባዝንኬ ከቤተ መጽሐፍት ያነበበውን  ሳይሆን ከቤተ ኦነግ የሰማውን ተረት  በፌስ ቡክ ገጹ  አጋርቶናል። የታዬ አለማወቅ የሚጀምረው የዛጔ ሥርወ መንግሥትን ከሰለሞናውያን ሥርዎ መንግሥት አውጥቶ በተረት የተፈጠረው የኩሽ መንግሥት ለማድረግ ሲውተረተር ነው። እውነቱ ግን የዛጔ ሥርወ መንግሥት ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ነው። የመጀመሪያው የዛጔ ሥርዎ መንግሥት መስራች ተደርጎ የሚቆጠረው መራ ተክለ ሃይማኖት የአክሱሙ የመጨረሻ ንጉሥ የድል ነዓድ አማች እንደነበረ በትውፊት የሚታወቅ ነው። የዛጔ ነሥታት የዘውዳዊ መለያ ዓርማቸው የተወረሰ ከሰለሞናውያን ነው። ለዚህ ደግሞ ከታች የታተመውን የንጉሥ ሐርቤን ዓርማ ብቻ መመልከት በቂ ነው። የንጉሡ ዓርማ  የዳዊት ኮከብ ነው። እንደሚታወቀው ዳዊት የሰለሞን አባት ነው። ከዚህ በላይ ሰለሞናዊነት ምን አለ?
ምን ይኼ ብቻ! ታዬ ያደነቀው የዛጔ ሥርወ መንግሥት ነገሥታት የሥነጽሑፍ፣ የሥነ ጥበብና የኪነ ሕንጻ ሥልጣኔ የዛጔ ሥርወ መንግሥት ነገሥታት የፈጠሩት አይደለም። የዛጔ ስነ ጽሑፍ፣ ስነ ሕንጻ፣ ስነ መንግሥት እና ማንኛውም የስርዎ መንግሥቱ መገለጫ  ሥልጣኔ ሁሉ ከአክሱማዊው ሰለሞናዊ ሥርዎ መንግሥት የተወረሰ ነው። ለዚህ ሩቅ ሳይሄዱ የፕሮፌሰር ዴቪድ ፊሊፕሰንን “Foundations of an African Civilisation”  እና የስርግው ሀብተ ሥላሴን “Ancient and medieval Ethiopian history to 1270”  መጽሐፍትን ማንበብ ብቻ ይበቃል።
ሌላው ታዬ ደንደአ ድንቁርና በሰጠው ድፍረት እየተመካ በጻፈው ተረቱ  ከዐፄ ይኩኖ አምላክ በኋላ ሸዋን ማዕከሉ ያደረገው ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ሥነ ጥበብና ሥነ ሕንጻን የሚጠላ ፀረ ስልጣኔ  እንደነበር አድርጎ ለማቅረብ የሞከረው ኦነጋዊ አላዋቂነቱ ነው። እውነቱ ግን ከዐፄ ይኩኖ አምላክ በኋላ ሸዋን ማዕከሉ ያደረገው ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት የሥነ ጥበብና የሥነሕንጻ ሻምፒዮን የነበረ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ የፈጠረው የሥነ ሕንጻና የሥነ ጥበብ ስልጣኔ ከኢትዮጵያ አልፎ በአውሮፓውያን ዘንድ ዓለምን የማሰስ ፍላጎት ምክንያት ለመሆን የበቃ የሥነጥበብ፣ የሥነ ሕንጻና የሥነጽሑፍ ስልጣኔ ዘመን ነበር።
ታዲያ ይህ ሁሉ ሥልጣኔ ዛሬ በቦታው የሌለው በግራኝ ጦርነት [ፉቱሕ አል ሐበሽን ያነቧል] እና በኦሮሞ የገዢ መደብ ወረራ ወደ ባድማነት ተቀይሮ በመውደሙ ነው። ስለዚህ ጸረ ሥልጣኔዎቹ ያንን ገናና ሰለሞናዊ ሥልጣኔ ያጠፉት ግራኝ እና በገዳ ሥርዓት እየተመራ አገራችንን በመውረር ያገኘውም ሥልጣኔ ሁሉ ያወደሙ የኦሮሞ የገዢ መደብ ነው።
ሸዋን ማዕከሉ ያደረገው ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ሥነጥበብ፣ የሥነሕንጻና የሥነጽሑፍ ሻምፒዮን እንደነበረ ለማወቅ የታሪክ ምንጭ የሚፈልግ ቢኖር ፕሮፈሰር ሀብታሙ መንግሥቴ ተገኘ “በራራ ቀዳሚት አዲስ አበባ” በሚል ባለፈው አመት በሬድ ሲ ፕሬስ ያሳተመውን መጽሐፍ፣ ፕሮፌሰር ማቲው ሳልቫዲሬ “The African Prester John and the Birth of Ethiopian-European Relations, 1402-1555” በሚል የሳተመውን መጽሐፍ እና በዚህ አመት የታተመውን የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ባልደረባየ የነበረችው የቬርና ክረብስ የጻፈችውን Medieval Ethiopian Kingship, Craft, and Diplomacy with Latin Europe (Springer International Publishing) መጽሐፍ እንዲያነብ እጋብዛለሁ።
በተለይም የቬረና መጽሐፍ ሙሉ ትኩረት የሰለሞናውያን ነገሥታት ለእደጠበብ፣ ለሥነ ጥበብ እና ለሥነ ሕንጻ የነበራቸውን ፍላጎት፣ ከአውሮፓ ወደኢትዮጵያ ሙሉ የሆነ የእደ ጥበብና የሥነ ጥበብ ሽግግር ለማደረግ ያደርጉትን ጥረት ላይ ስለሆነ በዚህ አርስት ላይ ፍላጎት ያለው ፈልጎ እንዲያነበው እመክራለሁ። ታየ ደንደአ እና መሰሎቹ እንደማያነቡ ስለማውቅ ቢያንስ ሰው አንብቦ እንዲነግራቸው ቢያደርጉ ከሀፍረት ይድናሉ እላለሁ፣ ለኛም ስራ ይቀንስልናል።
በተጨማሪም  ሸዋን ማዕከሉ ያደረገው ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት የነበረውን ከፍተኛ የሥነ ጥበብ እድገት ለማወቅ የሚፈልግ የኢያን ካምቤልን እና የዲያና ስፔንሰርን የምርምር ስራዎች (Cambell, “Historical Note on Nicolo Brancaleone,” 83-102; Spencer, “The Disocvery of Brancealone’s Paintings,”, 53-55; Spencer, Travels in Gojjam) ለአብነት ማንበብ ይችላል። ካምቤል በገጽ 86 ላይ ከዓፄ ዘርአ ያዕቆብ እስከ ግራኝ አህመድ አውዳሚ የሽብር ወረራ የነበረውን ዘመን የኢትዮጵያ ወርቃማ የጥበብ ዘመን (the era from the reign of Zara Yaiqob to the third decade of the 16th century remains a golden age for icon production in Ethiopia) ይለዋል ።
ሌላው ታዬ በድፍረት ሸዋን ማዕከሉን ያደረገውን ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ሥነ ጥበብና ሥነ ሕንጻን የሚጠላ ፀረ ስልጣኔ እንደሆኑ አድርጎ ለማቅረብ የሞከረው በዓለም በሰው ልጅ ቅርስነት ተመዝግበው የሚገኙት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በማን እንደተገነቡ የተጻፈውን ታሪክ ባለማንበቡ ነው። የተባበሩት መንግሥታት የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ መስሪያ ቤት በዓለምቅርስነት ከመዘገባቸውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እጹብ ድንቅ ከሚባሉት መካከል አንዱ የሆነው ቤተ[ገነተ?] ማርያምን ያሰራው ሰለሞናዊው ዐፄ ይኩኖ አምላክ ነው። የሰለሞናውያንንና የአማራን ሕዝብ ዓጽመ ርስታቸውንና ለም አገራቸውን እንጅ የሰሩትን ደግ ነገር ለማወቅ ፍላጎት የሌላቸው ኦነጋውያን መጽሐፍ ስለማያነቡ ይህን ሁሉ የተመዘገበ ድንቅ ታሪክ አያውቁትም።
ከቤተ[ገነተ?] ማርያም በተጨማሪ ሸዋን ማዕከሉን ባደረገው ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ነገሥታት የተገነቡ ሌሎች ብዙ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አሉ። ምን ይኼ ብቻ! የዛጔ ሥርወ መንግሥት ነገሥታት ቅዱሥ የሚል ስያሜ የተሰጣቸውኮ ሸዋን ማዕከል ባደረገው ሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት ነገሥታት ነው። በኋላም ዓፄ ይኩኖ አምላክ ተብሎ የነገሠው ተስፋ ኢየሱስ በዛጔው ንጉሥ ሥር የያኔው የደቡብ ኢትዮጵያ አስተዳዳር የነበረ ለቤተ መንግሥት የቀረበ ሰው ነበር። ታዬ ግን በኦነጋዊ ድፍረቱ እየተመካ የዛጔ ነገሥታትን ቅዱሥ የሚል ስያሜ ያወጡላቸውን ከይኩኖ አምላክ በኋላ የመጡ ነገሥታት የዛጔ ነገሥታት ጠላት አድርጎ ሊያቀርባቸው ይቃጣዋል።
ሰለሞናውያን ነገሥታት እንኳን ለጥበብ ቀርቶ እንደገናናወቹ የአለም ስልጣኔዎች የምግብ ሥርዓት የነበራቸው መንግሥታት ነበሩ። ምን ይሄ ብቻ! የቤተ መንግሥታቸው አቀማመጥ፣ ክፍፍል እና ተግባር ራሱን የቻለ ሥልጣኔ እንደነበረው በጽሑፍ የተከተበ ታሪክ ነው። የሰለሞናውያን ነገሥታትን  አስደናዊ የምግብ ወይም ባልትና ሥርዓት በሚመለከት ጀርመናዊው ማንፍሬድ ክሮፕና “The Serata Gebr: A Mirror View of Daily Life at the Ethiopian Royal Court in the Middle Ages’ በሚል  ያጠናውንና በNortheast African Studies  ቅጽ 10.2-3 የታተመውን ከገጽ 51-87 ድረስ ያለውን ማንበብ ይቻላል። የምግብ ሥር ዓት፣ ሥነ ጽሑፍ እና ስነ ጥበብ የገናናነት መገለጫ ሲሆን እንደ ሰለሞናውያን ነገሥታት ሁሉ በጽሑፍ የተከተበ የምግብ ሥርዓት እና ጥበብ የነበራቸው ሥርወ መንግሥታት  በአለም ላይ በጣም ጥቂት የሆኑ ገናና ሥርወ መንግሥታት ብቻ ነበሩ።
ሰለሞናውያን ለጥበብ የነበራቸውን ፍላጎት የሚያስታውሰን ነገሥታቱ በጎንደር ዘመን የተሰሩት አብያተ መንግሥት እና አብያተ ክርስትያን ብቻ አይደሉም። የጥበብ ሰዎች በሕዝቡና በመሳፍንቱ ዘንድ የነበራቸውን ስፍራ በሚመለከት ግርማ ጌታሁን ያሳተመውን ጎጃም ውስጥ የነበሩት መንበሮና ደብሽን የተባሉት የጋፋት አባቶች ያወጡትን ሕግ እና በጎጃሙ ንጉስ በተክለ ሃይማኖት ስር የነበሩትን የእደጥበብ ሰራቶች ማዕረግ፣ ክብር እና ድርጅት በሰፊው የጻፉት የዐይን እማኙ የአለቃ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራን መጽሐ ማንበብ ጠቃሚ ነው። ሙሉ ምንጩ የሚከተለው ነው፤ [Girma Getahun Ancient Customary Laws of the Gafat People: Journal of Ethiopian Studies, Vol. 30, No. 2 (December 1997), pp. 27-88)።]
በስተመጨረሻ የማቀርበው የኢትዮጵያ እውነት ሸዋን ማዕከል ያደረገው የሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት የኢትዮጵያ ነገሥታት ታዬ ባላዋቂ ድፍረቱ እየተመካ ፀረ-ስልጣኔ ኃይል ነበሩ ያላቸው እነዚህ ነገሥታት አርሶ አደሩን አፈር ገፊ፣ የብረት ሠራተኛን ቀጥቃጭ፣ ሸማኔን ቁጢጥ በጣሽ፣ የሸክላ ሠራተኛን ቡዳ እና ነጋዴን መጫኛ ነካሽ በማለት ሁሉንም ሞያ ሲያሸማቅቁ ነበር ስላለው ተረት ሰለሞናዊው ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ያወጡትን አዋጅ ነው። ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በተለይም በገዳ ሥርዓት ተቋማዊ ተደርጎ ይኖር የነበረውን ቱምቱ [ቀጥቃጭ ማለት ነው] እና ዱጉ [ፋቂ ማለት ነው]  እያሉ ሰውን በሞያው የማሸማቀቅ እና እንደ ጥዩፍ ይቆጠር የነበረበትን ሁናቴ ለማስቀረት አዋጅ አውጥተዋል።
ዐፄ ምኒልክ በአዋጅ ስላጠፉት የገዳ ሥርዓት ተቋማዊ ያደረገው ሰራተኛን በሥራው የማሸማቀቅ ጸረ ሥልጣኔነትና ስድብ ላምበረት ባርቴል “Oromo religion: Myths and rites of the Western Oromo of Ethiopia, an attempt to understand” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ1983 ባሳተመው መጽሐፍ ከገጽ 182 ጀምሮ “Despised Castes of Artisans” በሚል ርዕስ የጻፈውን 19ኛ ምዕራፍ ያነቧል።
ከታች ባተምሁት የዳግማዊ ምኒልክ  አዋጅ  ላይ በግልጽ እንደሚታየው ንጉሡ አርሶ አደሩ አፈር ገፊ፤  የብረት ሠራተኛው  ቀጥቃጭ፤  የሽመና ስራ የሚሰረው ቁጢጥ በጣሽ፤  የሸክላ ሠራተኛን ቡዳ እና ነጋዴን መጫኛ ነካሽ እየተባለ እንዳይሰደብ፤ ሁሉ ፍጥረት ከአዳምና ሔዋን የተገኘ እኩል የሰው ልጅ በመሆኑ ሰውን በሞያው የሚሰድብ ቢኖር በአንድ አመት እስራት እንደሚቀጣ ሕገ አውጥተዋል።
ታዬ ግን የሰለጠነው ዳግማዊ ምኒልክን ለማውገዝ እንጂ ለማድነቅ አይደለምና ይህ የሰለሞናዊው ነጉሥ ከዘመኑ የቀደመ ተራማጅነት፤ ዘውድ ጭነው ሳለ ገበሬ ከዘውድ በላይ መሆኑን፤ ማናቸውንም የእጅ ሞያ ሠራተኛ በስራው የሰደበ እኔን የሰደበ ነው ማለታቸው አያስደንቀውም። በተቃራኒው እንዲህ አይነት ዘመን ተሻጋሪ ሕግና ስርዓት ሰርተው ያለፉትን ሰለሞናውያን ነገሥታ አዋጅ እያወጡ እንዲጠፋ ባደረጉት ኋላ ቀርነት ይከሳቸዋል። ለሰው ልጅ ደረጃ አበጅቶ ቱምቱ [ቀጥቃጭ] እና ዱጉ [ፋቂ] የሚል የሞያ ማሸማቀቂያ አበጅቶ ይህንን ማሸማቀቂያ የጎሳ ሥም እስከማድረግ የደረሰውን ኋላ ቀር የገዳ ሥርዓት ግን የስልጣኔ ቁንጮ አድርጎ ሊሰብከን ይቃጣዋል። ድንቄም ሥልጣኔ!
ከላይ የታተሙት፤
1. የንጉሥ ሐርቤ የዳዊት ኮከብ ያለበት ማኅተም እና
2. ዐፄ ምኒልክ ጥር ፲፯ ቀን ፲፱፻ ዓ.ም.  ሠራተኛ በሠራተኛነቱ እንዳይሰደብ ያስነገሩት
አዋጅ ናቸው! አዋጁ የሚገኘው ብላቴን ጌታ ማህተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ባዘጋጁት “ዝክረ ነገር” መጽሐፍ  ውስጥ ከገጽ 421- 422  ላይ ነው።
Filed in: Amharic