>

በጥላቻ የወረወርከውን በፍቅር ብትፈልገውም ላታገኘው ትችላለህና ... (ይነጋል በላቸው)

በጥላቻ የወረወርከውን በፍቅር ብትፈልገውም ላታገኘው ትችላለህና …

ይነጋል በላቸው


  1. በትግራይ፣ በመተከል፣ በወለጋና በሌሎች አካባቢዎች በዘር ሐረጋቸው ምክንያትም ሆነ ህግን ለማስበር በሚል በተቀሰቀሰ ጦርነት ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችንን ፈጣሪ ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን፡፡ አማሮችን በተለይ ከነሽመልስ አብዲሣና ከነታዬ ልበ-ደንዳና ሠይፍ ፈጣሪ ይታደግልን፡፡ የንጹሓን ደም መፍረዱ ባይቀርም እኛንም አሁን የሚሰማንን ንዴትና ቁጭት አንድዬ ይቀንስልን፡፡ አንዳንዴ አለመገደል ከመገደል እንደሚብስ ቋሚዎች ያውቃሉ – የተገደለማ ተገላገለ፡፡
  2. ቋንቋ የመግባቢያ መሣሪያ እንጂ የዘር ሐረግ መገለጫ አይደለም፡፡ በዓለም እንዳሉ ከሚገመቱ ሰባት ሽህ ገደማ ቋንቋዎች ውስጥ የሰው ልጅ አንዱን ወይም እንደየሁኔታው የተወሰኑትን ይናገራል፡፡ ቋንቋ በምንም ዓይነት መንገድ በደም ከእናት አባት ወደ ልጅ አይተላለፍም፤ በውርስ ረገድ ቋንቋ ከበሽታና ከሀብት ንብረት እንኳን ያነሰ ነው – በመለማመድ ወይም በመማር ብቻ ስለሚገኝ፤ ከበሽታዎች መካከል የተወሰኑት በደም ይተላለፋሉ፡፡ ሌላው ይቅርና አረማመድና አተያይም ከቁም ነገር ተቆጥሮ አንዳንድ ልጆች ሲራመዱ ልክ እንዳባታቸው ሲንሻፈፉና ሲናገሩ ልክ እንዳጎታቸው ሲንተባተቡ ይስተዋላሉ – ቋንቋ ግን በጭራሽ ከማንም ከምንም አይወረስም፡፡ በልጅነትህ ከወላጆችህ ተነጥቀህ ጫካ ብትወረወር እንደእንስሳት በደመ ነፍስ ትጮሃለህ እንጂ ቋንቋ አይኖርህም – ይህንን እውነት በአስተሳሰብ ከከብት እምብዝም ለማይሻሉት የቀድሞና የአሁን ወያኔዎች በመርፌ ውጓቸው ወይንም በቀሰም አድርጋችሁ ጋቷቸው፡፡ አንተ ተረኛውና የኦህዲድ/ኦነግ/ብልጽግና አባሉ ወንድሜ ኦሮምኛን መናገር የቻልከው ይህን ቋንቋ በሚናገሩ ቤተሰቦችና ማኅበረሰብ ውስጥ በድንገተኛ አጋጣሚ – ሳትወድና ሳትፈቅድ – በመገኘትህ እንጂ “ዕድለኛ” ስለሆንክ አይደለም፡፡ ሌላውም ቋንቋ ሁሉ እንደዚሁ ነው፡፡ ቋንቋ እንደማንኛውም ፍጡር የሚወለድ፣ የሚያድግና የሚሞት ነው – ግን ጊዜ ሰጠኝ ብሎ በዐዋጅና የንጹሓንን አንገት በሜንጫ በማረድ ሳይሆን በራሱ ህግ፡፡ የቋንቋ አርበኝነት ሞኝነት ነው፤ ከተፈጥሯዊ ሂደት ጋር በከንቱ የመታገል ጅልነትም ነው፡፡ ቋንቋን ልትጠቀምበት እንጂ ልታመልከው አልተፈጠረም፡፡ ለሦስት ቀን ምድራዊ ዕድሜ ብለህ በቋንቋ ምክንያት ዘላለማዊት ነፍስህን አታጎሳቁላት ወንድሜ ደቻሣ፡፡ በኦሮምኛህ የምትኮፈሰው ወንድሜ ምናልባት አያቶችህ አገውኛ ወይም ደራሳኛ ተናጋሪ ነበሩ፡፡ በትግርኛ “ቋንቋሽ” በኩራት የምትበጣጠሸው አብረኸት እህቴ ቅድመ አያቶችሽ ምናልባት ዛሬ ወንድሞችሽ እንደጦር የሚፈሯቸውና እንደጠላት የሚቆጥሯቸው የጎጃም ገበሬዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አለማወቅ ማወቅን እየደፈቀው በቀላል ነገር እንደዋዛ ሀገር ስትጠፋ እያየን ነው! (ለጊዜውም ቢሆን)

ስለሆነም አማርኛን በማጥፋት በኦሮምኛ ለመተካት እንቅልፍ አጥታችሁ የምትደክሙ ወገኖቼ እባካችሁን ወደ ቀልባችሁ ተመለሱ፡፡ በተለይም የአክራሪ ኦሮሞ የኦነግ/ኦህዲድ/ብልጽግና ባለሥልጣናትና ቅጥር አክቲቪስቶች አደብ ግዙ፡፡ ይህን የምለው ለእናንተም ከማዘን ጭምር ነው፡፡ በዚያ ላይ ኦሮምኛን በየዋሃን ዘንድ እንዲጠላ አታድርጉት፡፡ ውብ ቋንቋውንና ትውፊቱን፣ ዘፈኑንና ረገዳውን … በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ በክፉ እንዲታይ እያደረጋችት ያለውን ጥረት አቁሙ፡፡ እንዲህ ጨርቃችሁን ጥላችሁ ስታብዱ ሁሉም በአግራሞት እያያችሁ ዝም ያለው በአሳፋሪ ተግባራችሁ ተደምሞና የነገውን ዕጣችሁን ተረድቶ እንጂ ወዶላችሁና ፈቅዶላችሁ እንዳልሆነ ልብ በሉ፡፡ እዩን እዩን ያሉ አሁን የት እንዳሉ ተመልከቱ፡፡ መጨረሻሁን ለማሳመር እናንተ ከነሱ የምትበልጡበት ምድራዊም ይሁን ሰማያዊ አንዳችም ምክንያት የለም፡፡ ገደቡን ያለፈ ብልጠት ለወያኔም አልጠቀመ፡፡ የናንተ ብልጠት ከቄሱ ሚስትም በለጠና ከማስገረም አልፎ በለበጣ እያሳቀን ነው፡፡ የጋራ አባቶቻችንን ታሪክ አንብቡና ከቂም በቀል የዕውር ድምብር ጉዞ ውጡ፡፡ አሁኑኑ! ነገ ጊዜ ላይኖራችሁ ይችላል፡፡ ጥጋቡን የተቆጣጠረ ወደርሀብ አይገባምና የምለውን ቆም ብላችሁ አስቡበት፡፡ ጥጋብ መጥፎ መሆኑ ይገባኛል፤ የኪስ መወፈርና የዝነኝነት ሥነ ልቦናም እንዲሁ፡፡ 

አማራ የተባሉትን ወገኖች ለማጥፋት መሞከር ይቻል ይሆናል፡፡ አንድን ህዝብ ለምንም ዓላማ ተብሎ ለማጥፋት መሞከር ከፍተኛ የዞረ ድምር ቢኖረውም በሙከራ ደረጃና በተወሰነ ስኬት ታጅቦ ጥቂት መጓዝ ይቻላል፤ የሀገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ የሚመሰክረውም ይህንኑ መሪር እውነት ነው፡፡ ሕወሓት የጀመረውን ኦነግ/አህዲድ/ብልግና የቀጠለው አማራን ከምድረ ገጽ የመደምሰስ ሂደት የሚጠቁመው ይህንኑ ነው፡፡ አማራን የማጥፋት ዘመቻው ይህንን ማኅበረሰብ ከቀደመ ርስቱና መኖሪያው በማፈናቀል ጭምር የታገዘ ስለመሆኑ በጉልበትና በጫካ ህግ ሽፋን የተወሰደበትን ግዛት በደሙ ሲያስመልስም አዲሶቹ ተረኞች እውነቱን ለመቀበል አለመድፈራቸውና ይባስ ብለውም ውንብድናውን ራሳቸው መቀጠላቸው አንዱ ምስክር ነው፡፡ “የዐይጥ ምስክር ድምቢጥ” እንዲሉ አማራን የፈሩ ድኩማን ሁሉ እየተደጋገፉ ይህን ህዝብ ለማጥቃት ዐይናቸውን በጨው አጥበው ተነስተዋል፡፡ እስከምን እንደሚጓዙና እንደሚሳካላቸውም ልናይ ጊዜው ቀርቧል፡፡ 

በዚህ አጋጣሚ ማሳሰብ የምፈልገው የአማራ ባለሀብቶች ሁለንተናዊ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባችሁ ነው፡፡ የአማራ ጠላቶች አማራን በሁሉም ረገድ ባዶ ማድረግ ዋና ዓላማቸው ነው፡፡ በልማት ረገድ የአማራን አካባቢዎች ማየቱ በቂ ምስክር ነው፡፡ ትግራይና ኦሮምያ ከሰማይ የወረደ በሚመስል የበጀት መና ሲምበሸበሹና ሌላ ክልልን ሳይቀር በዕርዳታ ስም ብዙ ገንዘብ በማፍሰስ ተወዳጅነትን ሲያተርፉ አማራው ክልል ለስም የሚበቃ አንድ ነገር እንኳን የለውም፤ ኤሌክትሪክ፣ ስልክ፣ ሀኪም ቤት፣ ትምህርት ቤት፣ ወዘተ. ሁሉ በዳዴ ደረጃ ነው ያለው – ያሳዝናል፡፡ ለነገሩ ልማቱ ቀርበት በድህነትም እንዲኖር በተፈቀደለት! እዚህ ላይ እንግዲህ ልማትን ብቻም ሳይሆን ሰውንም ማሳጣት አንዱ ዕቅዳቸው መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ስለዚህ የአማራ የሆነን ባለሀብትና ምሁር በየሰበብ አስባቡ ከማሰርና ከመግደል ስለማይለሱ እንቅስቃሴን በመገደብና አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ረገድ እንዳትዘናጉ አደራ እላለሁ፡፡ የሚያልፍ ቀን የማያልፍ ጠባሳ ጥሎ እንዳያልፍ ጉዳዩ የሚመለከታችሁ ጤነኛ የሁሉም ነገዶች አባላት ሁሉ በዚህ ነጥብ ላይ ትኩረት አድርጉ፡፡ እነዚህ ጉግማንጉጎች ልክ እንደነዚያኞቹ ሁሉ ያልፋሉ፤ የማይሽር ጠባሳ ትተው እንዳያልፉ ግን ሁሉም ወገን መረባረብ አለበት – የነጋበት ጅብ ማንንና የት ቦታ ላይ እንደሚነክስ አያውቅም፡፡ በበቀልና በጥላቻ የተሞላ ሰውም በመጥፎ ተግባሩ ለትውልድ የሚተርፍ መጥፎ አሻራ ሊተው እንደሚችል አይረዳም፡፡ ሰሞኑን የምሰማው ዜናና ሀተታ የሚጠቁመው ሰዎቹ ለይቶላቸው ማበዳቸውንና ምንም ዓይነት ወንጀል ከመሥራት እንደማይመለሱ ነውና እባካችሁን በዚህ ረገድ ጥንቃቄ አይለየን፡፡ ዝርዝሩን ትቼው ነው፡፡ እንጂ ስለሽመልስ ቁማር ብዙ ባወራ ደስ ባለኝ፡፡

መጪው እውነት ይህንን ይመስላል፡፡ አማርኛ የተሤረበትን ደባና ተንኮል ሁሉ ደረማምሶ ነፃ ይወጣል፡፡ የሽመልስ አብዲሣና የአቢይ አህመድ ሩጫ በቅርብ ሲቀጭ የኢትዮጵያን ከ80 በላይ ነገዶች በእኩል ያገለግል የነበረው አማርኛ ትንሣኤውን ያገኛል፡፡ ያም የሚሆነው ሌላ የተሻለ ምርጫ ባለመኖሩ ነው፡፡ አማርኛና አማራ የሚባሉት ግንኙነታቸው እጅግ ደብዛዛ ነው፡፡ እንግሊዝኛ የእንግሊዛውያን ንብረት እንዳልሆነ ሁሉ አማርኛም የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን እንጂ የአማሮች (ብቻ) አይደለም፡፡ ከኦሮምኛ በላይ አማርኛን የሚናገሩና ቅኔና ሰምና ወርቁን የሚያቀላጥፉ አክራሪ ኦሮሞዎች እንደ ድልድይ የሚያገለግለውንና የሁሉም እንጂ የማንም የግል ንብረት ያልሆነውን አማርኛን ለማጥፋት እንዲህ የሚራወጡት አማርኛን እየተጠቀሙ መሆኑ ራሱ ግርምትን መፍጠሩ እንዳለ ሆኖ የበሉበትን ወጪት ሰባሪ የሆኑት እነዚህ ሰዎች አማርኛን ባይናገሩ ኖሮ አሁን በየክልሎቹ እየተራወጡ “ዓለም አቀፍ ኦሮምኛን የማስፋፋት ዘመቻ” የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ ባልታዩ ነበር (በአማርኛ መጽሐፍ ደርሰው በሽያጩ ገንዘብ እንጀራ እየበሉበት “አማርኛን አትናገሩ” ሲሉ በጭረሻ አያፍሩም እኮ! እንዴቱን ያህል ቢረገሙና ቢደነቁሩ ይሆን)፡፡ “ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም” እንዲሉ ሆኖ፣ የአላዋቂ ሳሚ ነገርም ሆኖባቸው እንዲህ ሲንቀዠቀዡ ማየት ለጊዜው ቢያስገርመንም የነገውን ለምናውቅ ምራቅ የዋጥን ዜጎች በዚህ የ”ሕጻናት ልጆች” ጊዜያዊና ቀድሞ የተነገረለት ግርግር አንደነግጥም፡፡ እግዚአብሔር ራርቶ ካላለዘበልን በስተቀር እንዲያውም ከዚህም የከፋ አሳዛኝ ሁኔታ እንደሚገጥመን እንጠብቃለን፡፡ ለማንኛውም ቋንቋም ሆነ ባህል በወረራና በአስገዳጅ መንገድ እንደማይስፋፋ ታሪክ ራሱ ኅያው ምሥክር መሆኑን ልብ እንበል፡፡ 

  1. “አቢይ አህመድ ጠፋ፣ ታመመ …” ምናምን እያላችሁ ጥቂት የማይባሉ ተቃዋሚዎቹን የምታስጎመዡ አደብ ግዙ፡፡ ይሄ ሩጦ ያልጠገበ አቢይ የሚባል ጎልማሣ “ሞትኩ” የሚል ዜና በማሰራጨት የሚደሰትና ጠላት ወዳጅን በመለየት ጉዳት ለማድረስ የሚፈልግ ከሆነም ይሀ ዓይነቱ ጊዜ ያለፈበት ነገር ጠቃሚ አይደለምና ወዳጅ ካለው ይምከረው፡፡ የሕጻን ጠባይ ለትልቅ ሰው ስለማይገጥም ግዴለም ይቅርበት፡፡ የዕቃ ዕቃ ጨዋታ በትልቅ ሀገራዊ ፖለቲካ መክተት ለትዝብት ይዳርጋል፡፡ ደግሞም ምናልባት ለሚፈልገው አንድ ዓላማ ሲባል ከሚዲያ ተደብቆ ሀገር ምድርን ከማወዛገብ ጀማው እንዳይረበሽ ወዳጅ ዘመድም እንዳይደናገጥ ሲባል በቲቪ አንዴ ብቅ ብሎ አለሁ ማለትም ይቻላል፡፡ ራስን ማጀትና ሳሎን ውስጥ ወሽቆ አገርን ማስጨነቅ ጥሩ የአመራር ዘይቤ አይመስለኝም፡፡ በበኩሌ አቢይ እንዲማርና እርምጃውን እንዲያስተካክል እንጂ ሌላ መጥፎ ነገር እንዲደርስበት በጭራሽ አልመኝለትም፡፡ ባሕርይውን እንዲገራለትና “የሰፈረበት ዛር እንዲሰክንለት” ግን ለፈጣሪ እንጸልይለት – ጨርሶ ሳያጠፋን በፊት፡፡ አንዳንድ ዛር ፈረሱንም ሳይቀር ያሰቃያል!
  2. አማርኛን የጠሉና ላለመናገር የማሉ ወገኖች ውሳኔያቸውን በ“አስቸኳይ” ይቀልብሱና ይህን ቋንቋ ይልመዱ፤ ይነጋገሩበት – ከነጽሑፉ፡፡ ዓለም ያደነቀውንና ብዙ ፈረንጆች በፍቅር የሚማልሉለትን ይህን የአፍሪካ ኩራት የሆነ ቋንቋ መናቅ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ የእስካሁኑን እንርሳው፡፡ ነገን እናስብ፡፡ ነገ ደግሞ ሌላ ቀን ነው፡፡ ስንሻውና አምባቸው በግድ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ይገባሉ ብለህ ደግሞ አትጠብቅ፡፡ ኢትዮጵያ መኖር ካለባት፣ የኢትዮጵያ ትንሣኤ መበሠር ካለበት፣ ሀገራችን ከሙታን መንደር ተለይታ ኅያውነትን መላበስ ካለባት ጎይቶምም ይምጣ ገመቹ፣ ላሬቦም ይምጣ ኤርሴዶ፣ ያሲንም ይምጣ ገ/ክርስቶስ … ይህን ተለያይቶ የማይለያይ የወርቅ ፈትል ህዝብ የሚመራው በሌላ ቋንቋ ሣይሆን በአማርኛ ነው – ሰምታችሁኛል – በአማርኛ! ሀገር በየ50 ዓመት አይጠፈጠፍም፤ ሀገር ቂጣ አይደለም … ይህን የአንድ “ዕብድ ሰው” “ራዕይ” ለነፈዞቹ ንገሯቸው፡፡ 

5. ሁሉን ቢያወሩት ሆድ ባዶ ይቀራል፡፡ … ግን ግን ሕዝበ አዳም ጠባቧን ድልድይ መሻገር ከፈለግሽ ጠንክረሽ ጸልይ፡፡ መሆን ያለበት ሁሉ በጊዜው ይሆናል፡፡ የወርቅና የአልማዝ ዘመን እንዳለ ሁሉ የእንጨትና የኩበት ዘመንም አለ፡፡  ዝግባና ወይራ ጠፍቶ ደደሆና እምባጮ ሞፈር እየሆኑ ነው፤ ጋኖች ጠፍተው ወይም በፍርሀት ምክንያት ተደብቀው ምንቸቶች ጋን እየሆኑ ነው፤ ሀገርን የመምራት ዕድል አውላላ ሜዳ ላይ ወደቆ ያገኙ የአጋንንት ጭፍሮች እያደረጉ የሚታዩት ሁሉ ቀስ በቀስ መወገዱና አሁን የት እንዳሉ እንኳን በማናውቃቸው አዳዲስ መልካም እረኞች መተካቱ አይቀርም፤ ፈር የለቀቀ የጉዞ መስመር ውስጥ የገባን ዜጎች እንጠንቀቅ፡፡ መላእክት በፈጣሪያቸው በተፈተኑ ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል “ንቁም በበኅላዌነ እስከ ንረክብ አምላክነ!” ያለው ለዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊም የሚሰጠው አስተምህሮ ቀላል አይደለምና በየነፋሳቱ ሳንወናበድ ትክክለኛውን ኖላዌ ሔር በትግስትና በጸሎት እንጠባበቅ፡፡ በመንፈሣዊውም በዓለማዊውም ዓለማት የገጠሙን መሪዎች እንዳይሆኑ ሆነው በመበለሻሸት የዲያብሎስ አገልጋይ ሆነው ተገኝተዋልና ከአንድዬ በስተቀር መፍትሔና መሸሻም የለንም፡፡ እርሱም ስለማያሳፍረን በቅርብ የሠራውን አስገራሚ ድርጊት በቅርብ ይደግመዋል፤ አሜን ነው ታዲያ! አሜን፡፡ 

Email;  ma74085@gmail.com

Filed in: Amharic