>

ህወሓት፡- ሽምቅ ተዋጊ፣ የአገር መሪ፣ የክልል አስተዳዳሪ በመጨረሻም . . . (ይታገሱ አምባዬ)

ህወሓት፡- ሽምቅ ተዋጊ፣ የአገር መሪ፣ የክልል አስተዳዳሪ በመጨረሻም . . .

ይታገሱ አምባዬ

ሦስት አስርት ዓመታት ለሚደርስ ጊዜ በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ ዋነኛው ኃይል ሆኖ የቆየው ህወሓት ባለፈው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጻ ተግባር ላይ በመሣተፉ በብሔራዊ ምርጫ ሕጋዊ ሰውነቱን አጥቶ እንዲሰረዝ ተደርጓል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ኃያል የነበረውና በእድሜ ጎምቱ ከሚባሉት ፓርቲዎች መካከል አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ህወሓት ከሽምቅ ተዋጊነት፣ የአገር መሪነት፣ ከዚያም ወደ ክልል አስተዳዳሪነት በመጨረሻም ሕጋዊ ዕውቅናውን አጥቶ ከሞትና ከእስር ተረፉት አመራሮቹ ከያሉበት እየታደኑ ነው።
ታዲያ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ከየት ተነስቶ አሁን ካለበት ደረሰ? እነሆ በአጭሩ . . .
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የንጉሡ አስተዳደር ወድቆ ወታደራዊው መንግሥት ወደሥልጣን መውጣቱን ተከትሎ ነበር የካቲት 11/1967 ዓ.ም የትጥቅ ትግል መጀመሩን ያስታወቀው።
ለህወሓት የትጥቅ ትግል መነሻ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያቋቋሙት ማገብት (ማህበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ) የተባለው መደበኛ ያልሆነ ቡድን ነበር።
ማገብት የህወሐት ጥንስስ
የትግራይ ተማሪዎች ስብስብ የነበረው ማገብት ከ45 ዓመታት በላይ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና ለነበረው ለህወሓት መመስረት ዋነኛው ትንስስ ነበር።
ማገብት በስምንት አባላት ተመሰረተ ሲሆን እነዚሁ መስራቾቹም ኋላ ላይ ለህወሓት እንቅስቃሴ መመስረት ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።
ስምነቱ ግለሰቦች በሪሁ በርሀ (አረጋዊ በርሄ ዶ/ር)፣ ፋንታሁን ዘርአጽዮን (ግደይ ዘርአጽዮን)፣ ሙሉጌታ ሐጐስ፣ አምባዬ መስፍን (ስዩም መስፍን)፣ አመሃ ፀሃዬ (አባይ ፀሃዬ)፣ ዕቁባዝጊ በየነ፣ አለምሰገድ መንገሻ እና ዘርኡ ገሰሰ (አግአዚ) ናቸው።
ከጅማሬው ደርግን የተቃወመው ማገብት በትግራይ ሕዝብ ላይ ደረሰ ያለውን ጭቆና ለማስወገድ የትጥቅ ትግል ማድረግና መሪ ድርጅት እንደሚያስፈልግ ወሰነ፡፡ ለዚህም የተወሰኑት አባላቱ የኤርትራ አማጺ ቡድኖች ከነበሩት ከጀብሃና ከሕዝባዊ ግንባር ጋር ግንኙነት ለመመስረት ወደ ኤርትራ ሲሄዱ ሌሎቹ ደግሞ ከተማ ውስጥ ሆነው ሕዝብ ማደራጀት ጀመሩ።
ይህንን ተከትሎም አስራ አንድ የቡድኑ አባላት የትጥቅ ትግሉን ለመጀመር ወደ ጫካ ሲወጡ የመረጡት ደደቢት የተባለውን በረሀ ነበር።
የህወሓት አላማ
ቡድኑ የትጥቅት ትግሉ በጀመረበት ወቅት ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠልና ‘የሪፐብሊክ’ የመመስረት ጉዳይ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም ይህ ሐሳብ ከአንድ ዓመት በላይ እንዳልቆየ መስራቾቹ ይናገራሉ።
በ1968 ዓ.ም በተካሄደው የመጀመሪያው የድርጅቱ ጉባኤ ‘ነጻ ትግራይ’ የሚለው አጀንዳ በአብዛኛው አባል ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ ውድቅ ተደረገ።
ከዚያም የድርጅቱ አላማ የመደብ ትግል በማድረግ ለጭቁን ሕዝቦችን ‘የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት’ እንደሚታገል ቢገልጽም ህወሐትን የሚቃወሙ ድርጅቶት ግን ቡድኑ የትግራይን ሕዝብ ለመነጠል እንደተቋቋመ በመግለጽ ሲተቹት ቆይተዋል።
ክፍፍል በህወሓት ውስጥ
ህወሓት ከተመሰረተ ከአንድ ዓመት በኋላ በ1968 ዓ.ም በድርጅቱ ውስጥ ባሉ አመራሮች መካከል መከፋፈል አጋጥሞት የነበረ ሲሆን ይህም ‘ሕንፍሽፍሽ’ በመባል ይታወቃል።
በዚህ ወቅትም በአመራሮቹ መካከል የነበረውን መከፋፈል ለመፍታት የወሰደው እርምጃም ፀረ-ዲሞክራሲያዊ እንደነበር አንዳንድ ነባር ታጋዮች ያስታውሳሉ።
ከዚህም በኋላ በ1977 ዓ.ም በአመራር አባላቱ መካከል በድጋሚ ልዩነት ተፈጥሮ ከመስራቾቹ መካከል ከነበሩት ውስጥ አረጋዊ በርሀ (ዶ/ር) እና ግደይ ዘርአጽዮን የተባሉት አባላቱ ድርጅቱን ጥለው እንዲወጡ ተደርገዋል።
በወቅቱ የተደረገውን ግምገማና የተግባራዊ እንዲደረግ የቀረበውን አዲስ ወታደራዊ ዕቅድ ብዙዎቹ የድርጅቱ አባላት ቢደግፉትም “በጊዜው የተመሠረተው ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ትግራይ (ማሌሊት) የተባለ የፖለቲካ ክንፍ ግን ድርጅቱን በጠቃላይ እንቀየረው” የሚል ሐሳብ እንደነበረው የህወሓት ቀደምት አባል የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት በመጽሐፋቸው አስፍረዋል።
የህወሓት ኮሚኒስታዊ ባህሪ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ያበቃለት ቢመስልም የድርጅቱ ውስጣዊ ባህሪና አደረጃጀት ሳይቀየር ‘አብዮታዊ ዲሞክራሲ’ የሚል መልክ በመያዝ እስከ መጨረሻው መዝለቁ ይነገራል።
የሩስያና የቻይና አብዮቶች አድናቂ የነበረው ህወሓት እንደ መርህ ግን ብዙም የማትታወቀው በምሥራቅ አውሮፓ ውስጥ ያለችውን የአልባንያን ኮሚኒዝም ይከተል ነበር።
ህወሓት በአገሪቱ የሥልጣን እርከን ላይ ጉልህ ሚና በነበረው ወቅትና ከኤርትራ ጋር የተካሄደው የድንበር ጦርነት ካበቃ በኋላ በ1993 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ በአመራሩ ውስጥ ከፍተኛ ክፍፍል ገጠመው።
በዚህ የክፍፍል ወቅት በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚመራው ቡድን የበላይነቱን ይዞ በህወሓት ውስጥ ከፍተኛ ተሰሚነትና ተጽእኖ የመፍጠር አቅም የነበራቸውን ከፍተኛ የቡድኑን አመራር አባላት ከድርጅቱ እንዲባረሩ ተደረገ። በዚህም ሳቢያ የተወሰኑትም በውሙስና ተከሰው ለእስር ተዳርገው ነበር።
ከዚህም በኋላ በአቶ መለስ ዜናዊ የሚመራው አንጃ ድርጅታዊና መንግሥታዊውን ስልጣን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የበላይነት ለብቻው ለመያዝ ቻለ።
የህወሓት ግጭት አፈታት
ህወሓት ለ17 ዓመታት ባካሄደው የትጥቅ ትግል ወቅት ከፍልሚያ ውስጥ ገብቶ የነበረው ከወታደራዊው መንግሥት ጋር ብቻ አልነበረም።
ቡድኑ የትጥቅ ትግል በሚያደርግበት ጊዜ በተመሳሳይ ወታደራዊው መንግሥትን ተቃውመው ከወጡት ከኢዲዩ፣ ከጀበሃ፣ ከኢህአፓና ከሌሎችም ቡድኖች ጋር በወቅቱ የነበረውን ፖለቲካዊ ልዩነት በኃይል ነበር የተፈታው።
ከዚህ በተጨማሪም በወቅቱ በትግራይ ሕዝብ ስም ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ስብስቦች መካከል አንዱ የነበረው የግንባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ (ግገሐት) መሪዎቹን በተንኮል በመግደል ተጋዮቹን ድራሻቸው እንዳጠፋ ይነገራል።
ነገር ግን ከደርግ ጋር የሚደረገው ጦርነት እየሰፋ ከትግራይ ባሻገር ወደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ሲሸጋገር በየአካባቢዎቹ ያሉትን ሕዝቦች ይወክላሉ የተባሉ ድርጅቶችን ማቀፍ እንዲሁም ሊወክሉ ይችላሉ በሚል እንዲቋቋሙ ህወሓት ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
ይህንንም ተከትሎ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን)፣ ከኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ጋር በመጣመር ኢሕአዴግ የተባለውን ግንባር ፈጠረ።
በህወሓት የበላይነት ይመራ ነበር የሚባለው ኢሕአዴግ የደርግ መንግሥትን ከሥልጣን ካስወገደ በኋላ የሽግግር መንግሥት በማቋቋም በ1987 ዓ.ም አዲስ ሕገ መንግሥት ጸድቆ ምንም እንኳን ተግባራዊነቱ ላይ የተላዩ ጥያቄዎችና ትችቶች ቢነሱበትም ለአገሪቱ ብሔሮች እውቅናን ሰጥቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ ሥርዓቱ የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት ችላ ያለ ነው እየተባለ ሲወቀስ ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ግን በግንባሩ ውስጥ ለዓመታት የቆየው ቅሬታ ስር እየሰደደና እየጎላ መጣ።
የኢሕአዴግ ግንባር አባላት በድርጅቱና በአገሪቱ ላይ የለውጥ እርምጃዎች መውሰድ ሲጀመርሩና የግንባሩ መለያ የነበረውን ‘አብዮታዊ ዲሞክራሲን’ ሲተዉት ለህወሓት የሚዋጥ ጉዳይ አልነበረም የሚካሄዱት ለውጦች እየበረቱ ሲሂዱ የህወሓት ቅሬታም እየጠነከረ ሄደ።
በመጨረሻም የአራት ብሔራዊ ድርጅቶች ጥምረት የነበረው ኢህአዴግ ከስሞ የብልጽግና ፓርቲ ሲተካው ህወሓት በአዲሱ ስብስብ ውስጥ ላለመግባት ከመወሰኑ ባሻገር “ውህደቱ ሕጋዊ አደለም” በማለት ተቃውሞውን አስምቶ ነበር።
ስኬትና ትችት
የብሔር ጭቆና በኢትዮጵያ ውስጥ ነበረ ብለው በሚያምኑ ወገኖች በኩል ከዚህ ቀደም ከነበረው ሁኔታ በተለየ ህወሓት ወደ ስልጣን ከወጣ በኋላ በተዋቀረው ፌደራሊዝምና ሕገ መንግሥት ውስጥ ተገቢውን እውቅና እንዲያገኙ አድርጓል ብለው የሚቀበሉት አሉ።
ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ማኅበረሰቦች ምንም እንኳን በወረቀት ላይ እውቅና ቢያገኙም በተግባር ላይ በመተርጎሙ በኩል የጎላ ችግር እንደነበረም ይተቻሉ።
ህወሓት የደርግ መንግሥትን በመጣል የአገሪቱን ሥልጣን ተቆጣጥሮ ለሦስት አስርት ዓመታት መቆየቱና በሥልጣን ዘመኑ ውስጥ የተፈጸሙ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ደግሞ ሌሎች የሚያነሱት አሉታዊ ገጽታው ናቸው።
ከኤርትራ ነጻነትና ለኢትዮጵያ የወደብ ባለቤትነት መብት ቸልተኛ ነበር ብለው የሚወቅሱት ተቃዋሚዎችም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።
ህወሓት በበላይነት በሚመራው መንግሥት የመጨረሻ አስር ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡ ዓለም አቀፍ ተቋማት በተደጋጋሚ ቢመሰክሩም እየተንሰራፋ የመጣው ሙስናና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የተገኘው ውጤት ላይ አሉታዊ አሻራን አሳርፈውበታል።
የህወሓት መሪዎች
ህወሓት እንደተመሰረት ለአንድ ዓመት ያህል ከመስራቾቹ አንዱ የነበረው ገሰሰ አየለ (ስሁል) በጊዜያዊነት ከመራው በኋላ አቶ ስብሐት ነጋ ከ1971 ዓ.ም እስከ 1981 ዓ.ም ድረስ የድርጅቱ ሊቀ መንበር በመሆን መርተውታል።
ቀጥሎም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ በሞት እስከ ተለዩበት ጊዜ ድረስ ከ20 ዓመታት በላይ የህወሓት ሊቀ መንበር በመሆን አገልግለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ህልፈትን ተከትሎም በ2004 ዓ.ም አቶ አባይ ወልዱ የድርጀቱን ሊቀመንበርነት ቢረከቡም ብዙም ሳይቆዩ ድርጅቱን በተገቢው ሁኔታ መምራት አልቻሉም ተብለው እንዲነሱ ተደረገ።
በመጨረሻም በደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) መመራት የጀመረው ህወሓት በአገር አቀፍ ደረጃ የነበረውን ተሰሚነት አጥቶ በትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ ተወስኖ ለመቆየት ከተገደደ በኋላ ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ከባድ ጉዳት ደርሶባታል።
የህወሓት ፈተና
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከተመራው ለውጥ በኋላ በማዕከላዊው መንግሥት ውስጥ የነበረውን ጉልህ ሚና ያጣው ህወሓት ከፍተኛ አመራሮቹን ይዞ በገዢ ፓርቲነት ወደ ሚያስተዳድረው ትግራይ ካቀና በኋላ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የነበረው ግንኙነት ከመሻከር አልፎ ወደ ፍጥጫ መሸጋገሩ ይታወሳል።
በተለይ በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት ይካሄዳል ተብሎ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው ምርጫ ወደ ቀጣይ ዓመት እንዲሸጋገር ሲደረግ ህወሓት ተቃውሞውን በማሰማት በፌደራል መንግሥቱ ሕገ ወጥ የተባለውን የተናጠል ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ መወሰኑ አለመግባባቱን የበለጠ አባባሰው።
ምርጫው ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ ተካሂዶ ህወሓት መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ማሸነፉ ተገልጾ አዲስ ክልላዊ መስተዳደር መመስረት ቢችልም፤ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ያለው ግንኙነት ተቋርጦ ያገኝ የነበረው በጀትም ከክልሉ ይልቅ ለታችኛው የአስተዳደር አካል እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።
ህወሓት ባለፉት ሁለት ዓመታት የክልሉን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በስፋት በማሰልጠን የተለያዩ ወታደራዊ ትርኢቶችን በተደጋጋሚ ሲያሳይ በቆበት ወቅት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ከዛሬ ነገ ይፈነዳል በሚባል ፍጥጫ ውስጥ ቆይቶ ነበር።
በመጨረሻም የህወሓት ኃይሎች በክልሉ ውስጥ ለዓመታት በየቆው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከመቀመጫው መቀለ እንዲባረር እንዳደረገው ይታወሳል።
በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት እንዲሁም ላለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ የትግራይ ክልልን በበላይነት የመራው ህወሓት በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ከባድ ጉዳት ደርሶበታል።
የቡድኑ ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች በተለያዩ ከፍተኛ ወንጀሎች ተጠርጥረው የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው ሁለት ወራት ተቆጥረዋል።
ባለፉት ሳምንታትም በርካታ የህወሓት የአሁንና የቀድሞ አመራሮች በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውና ሌሎች ደግሞ መገደላቸው በአገሪቱ ሠራዊት መገለጹ ይታወሳል።
Filed in: Amharic