>
5:13 pm - Sunday April 20, 3175

የብአዴን/አማራ ብልፅግና ኑዛዜ ...!!!  ( ታዬ ነጋ)

የብአዴን/አማራ ብልፅግና ኑዛዜ …!!! 

              
ታዬ ነጋ

ከሰሞኑ የፌዴራል የብአዴን ባለስልጣናት  ስለወቅታዊ ጉዳይ ተወያይተው ነበር፡፡ ብዙዎች አይተገብሩትም እንጂ ጥሩ ሀሳብ አንስተዋል፡፡
አቶ ላቀ አያሌው  በስብሰባው ያነሱት የኑዛዜ ሀሳብ እንደሚከተለው ቀርቧል።
በቅድሚያ የዛሬን መድረክ በመድፌ ቀዳዳ የመሽሎክ ያህል ቢሆንም እንድንገናኝ እድሉን ለፈቀደልንና ለአስተባበረን ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡
በመቀጠል መግለፅ የምፈልገው እኛ የድሮው ብአዴን/አዴፓ- የአሁኑ የአማራ ብልፅግና ወኪሎች በፖለቲካው ገበያና በገበያው ሥርዓት ውስጥ እየተጎማለልን ያለን ነገር ግን ሻጭም ሆነ ሸማቾች ዋጋችን ስንት እንደሚያወጣ በድፍረት ለመግለፅ የሚቸገሩብን ስብስቦች ነን ብዬ ብናገር ማጋነን አይደለም ፡፡
ይህን የምልበት ምክንያት በወያኔ ዘመንም ሆነ አሁናዊ ሁኔታችንን በማገናዘብ ነው ።  በወያኔ ዘመን እስከመጨረሻው ድረስ የወያኔ የበላይነትየለም ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው፤ ሀገር ለማፍረስ የሚያካሂዱት ዘመቻ ነው በማለት ከትህነግ በላይ ትህነግ ሆነን ስንከራከር ኖረን መጨረሻ ጥለውን ሄዱ፡፡ በእርግጥ መንከስ የሚችለው ጥርሳቸው ከወለቀ በኋላ ብዙ…. ብለናል ይህን አልክድም ፡፡
እኛ ከትህነግ በላይ ትህነግ ሁነን የህዝባችንን አንገት ስናስደፋ በማናውቀው ነገር ሁሉ ያዙኝ ልቀቁኝ ስንል  ኑረናል።
ነገር ግን ህዝባችን ቀድሞ ተረድቶ፡-
1. ንብረት ወደ ትግራይ እየተጓዘ ነው፤
2. መሠረት ልማት ፍትሐዊ አይደለም፤
3. በጀት ድልድሉ ኢ-ፍትሀዊ ነው፤
4. መሬታችንና ህዝባችን እየተወሰደ ነው፤
5. በመላ ሀገሪቱ የተመዛባ ትርክት ስለአማራ እየተነገረ
     ነው፤
6. የፌደራል ተቋማት በወያኔ አምሳል እየተቀረፀ ነው፤
7. አማራ የሚተዳደረው በትገራይ እና በኤርትራ ሰዎች ከእኛ
    ሰው ጠፍቶ ነው ወይ ??
8. እጅግ በጣም አሰቃቂ የሆነ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ
     መብቶች ጥሰት እየተፈፀመ ነው፤
… ወዘተ እየተባለ በህዝቡም ሆነ በብአዴን አባላት የማይነሳ አልነበረም፡፡ ነገር ግን የትህነግ ወኪሎችና የእነሱ ዙፋን አስጠባቂዎች ይህ የትምክህትና የጠባብነት አስተሳሰብ ነው ሲሉን እኛም ይህን ሳናላምጥ በመዋጥ በተራችን ወደ አርሶ አደሩ እየሄድን ከመሬቱና ከበሬዎች እንዲሁም ከጎጆው ውጭ የማያውቅን አርሶ አደር ትምክህትና ጠባብነት የሀገራችን ቀንደኛ ጠላቶች ናቸው እንለው ነበር፡፡
አንዳንዴም ብሔርን እንደቁሳቁስ በመቁጠር አንዱን እሳት ሌላውን ጭድ በማድረግ ቢገናኙ የሚቀጣጠሉ ነገር ግን ሀገር ለመበተን ሲሉ አንድ የሚሆኑ የፀረ-ዲሞክራሲ መገለጫዎች ሀገር አፍራሽ ናቸው በማለት እንድናወግዝ እየተነገረን እኛም ህዝብን እያደነቆርን መሄጃ አሳጥተን በትህነግ የፖለቲካ ገበያ ውስጥ አልፈን ብልፅግና ገበያ ደርሰናል ፡፡
ይህን የማነሳው ያለፈውን እያነሳሁ ጊዜ ለማጥፋት አይደለም ፡፡ ህዝቡ ከፖለቲከኞችና ከወኪሎች በተሻለ መንገድ ተገንዝቦ ሲነግረን ጆሯችን ድፍን እንደነበረ መለስ ብለን እንድናስታውስና ለዛሬም ትምህርት እንዲሆነን ለማስገንዘብ ነው፡፡
በብልፅግና የፖለቲካ ገብያስ አቶ ላቀ አያሌው ቀጥለዋል፡፡
በእኔ አስተሳሰብ በዛሬው የፖለቲካ ገበያም ህዝባችንን ሊጠቅም የሚችል በፖለቲካው ገበያ ላይ ዋጋ እያወጣን አይደለም ፡፡ ይህን የምልበት ምክንያት፡-
1. ያለፉት 46 ዓመታት ትህነግ መራሽ ሰቆቃ አልበቃ ብሎ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የአማራ ህዝብ በብዙ አካባቢዎች በማንነቱ ምክንያት ብቻ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እየተፈፀመበትና ሀብት ንብረቱ እየወደመበት ስለሆነ ነው ።
ለምሳሌ፡-
 በመተከል ዞን በተደጋጋሚ
 በማይካድራ
 በኦሮምያ ክልል በተለያዩ ወቅቶችና ቦታዎች
 በጉራ ፈርዳ —- ወዘተ
ይህ ሁሉ ማንነትንና እምነትን ብቻ ማዕከል ያደረገ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸም ከወንጀሉ ክብደትና ዓለም አቀፋዊነት አንፃር ሁሉም የብልፅግና አባላት ማውገዝ ነበረብን፡፡ ነገር ግን የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም ሆነና ነገሩ የዘር ማጥፍቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
2. ማንነትንና ዘርን መሠረት ተደርጎ የሚፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል እኛ የአማራ ህዝብ ወኪሎች ነን የምንል ሁሉ የዘር ፍጅቱን ልንከላከለው ይቅርና አጀንዳ አድርገን ጠንከር ያለ ተመሳሳይ አቋም እንኳን መያዝ አልቻልንም ፡፡ እንዲያውም የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከእኛ በእጅጉ የተሻለ ሁኗል፡፡
3. በተደጋጋሚ በአማራ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ሲፈፀም በአማራ ክልል ም/ቤትም ሆነ በፌደራል የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ወንጀሉን በሥሙ ጠርተው የዘር ማጥፋት (Genocide) ወንጀል መፈፀሙን ተቀብለው አቋም ሊወስዱ ይቅርና ብሔራዊ የሀዘን ቀን እንኳን ማወጅ አልቻሉም፡፡ይህ መሆኑ የእነርሱ ጥፉት ሳይሆን የእኛ የፖለቲከኞቹ ግዴለሽነት ነው ።
4. በየቦታው የዘር ማጥፋትና የዘር ማፅዳት እየተፈፀመባቸው ያሉትን ወገኖቻችንን ከአሰቃቂ ግድያ ባንታደጋቸውም እንኳን በማህበረሰባችን ባህልና ወግ መሠረት በክብር ግብዓተ መሬታቸው እንዲፈፀም ማድረግ ሲገባን ከውሻ ሞት በአነሰ መንገድ የቀብር ጉድጓድ በዶዘር እየተቆፈረ፣ አስከሬን ከየጫካው እየተለቀመና እንደ ቆሻሻ በቡል ዶዘር እየተዛቀ ከኢትዮጵያውያን ባህልና እምነት ውጭ አንዱ በአንዱ ላይ ተደራርቦ ጉድጓድ ውስጥ እንዲገባ ተደረገ፡፡ እውነት የህዝቡ ወኪሎች ከሆን ሞታቸውን ማዳን ባንችል እንኳን ቢያንስ የሟቾችን አስከሬን እንዴት በክብር ማሳረፍ አቃተን? ይህንስ ምን እንበለው?
5. እንደሚታወቀው ማነኛውም ሰው በህይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት አለው በሚል በሕገ መንግሥቱ በአንቀፅ 14፣ 15ና 16 ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ ለአማራ ህዝብ ሲሆን እየተተገበረ አይደለም፡፡ ነገር ግን እኛ የአማራ ወኪሎችም በዚህ ጉዳይ ምንም እያልን አይደለም፡፡ ሲሆን በእኛ ጀማሪነት ሁሉም ክልል ህገ መንግስት ተጥሷል እንዲል ማድረግ ነበረብን ምልናያቱም እውነት ነዋ ።
6. እኔ እስከገባኝ ድረስ ብልፅግና ማለት በመላ ኢትዮጵያ ያሉ የብልፅግና አመራሮችንና አባሎችን በጋራ እየገመገምንና እየተራረምን እንመራለን ብዬ አስብ ነበር፡፡ ነገር ግን ዛሬም በየክልሎች ህዝብና መንግሥት የሰጣቸውን ኃላፊነት በመተው ህዝብን እንደ በግ የሚያሳርዱ፣ ለሰብዓዊነትና ለሰው ልጅ ቅንጣት ያህል ክብር የማይሰጡ፤ የሚመሩት ክልል የደም መሬት ሲሆን የማይደነግጡ አካላትን መገምገምና ከኃላፊነት ማንሳት ቀርቶ ቀና ብለን ማየት አልተፈቀደልንም፡፡ ይባስ ብሎ እኛ ሳንፈቅድላችሁ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሀዘናችሁን እንኳን አትጻፉ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን አትናገሩ ተባልን፡፡ ታዲያ የእኛ በዚህ የብልፅግናም የፖለቲካ ገበያ  ውስጥ ዋጋ እያወጣን ነው ብዬ እንዳላስብ እየተገደድሁ ነው፡፡
7. በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 39 (3) የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በክልልና በፌደራል አስተዳደሮች ውስጥ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲሁም መኖር ብቻ ሳይሆን ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት ደግሞ የሕጎች ሁሉ የበላይ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት ተጥሶ ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ አማራዎች በየትኛውም የአስተዳደር እርከን ውክልና የላቸውም፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸውም አይዳኙም፣ አይማሩም፣ አይተዳደሩም፡፡ ታዲያ እኛ ምን እየሰራን ነው?
መረጃው የAmhara Media Network – AMN ነው።
Filed in: Amharic