>

የዘንድሮው በዓለ ጥምቀት ለአገዛዙ ያስተላለፈው መልእክት (ከይኄይስ እውነቱ)

የዘንድሮው በዓለ ጥምቀት ለአገዛዙ ያስተላለፈው መልእክት

ከይኄይስ እውነቱ


አገራችን በአራቱም ማዕዝናት ሰላምና ጸጥታ ርቋት ባለበት በዚህ ቀውጢ ወቅት በተለየ ድምቀት (እምቢልታው፣ መለከቱ፣ ነጋሪቱ ወዘተ. ሳይቀር) የተከበረው የዘንድሮው በዓለ ጥምቀት ያስተላለፈልኝ መልእክት (ሃይማኖታዊው እሤቱና ፋይዳው እንደተጠበቀ ሆኖ) ቤተክርስቲያናችንን አትንኩ፣ ምእመኗን አትረዱ፣ ባገራችን ላይ የወጠናችሁትን ሴራ ባስቸኳይ አቁሙ በሚል ባገዛዙ ላይ የተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ጭምር አድርጌ ወስጄዋለሁ፡፡

ወደ ሕዝቡ ወርዶ የዜጎቹን ችግር የማያዳምጥ፣ ፈጥኖም የማይደርስላቸው፤ የአገርንና የሕዝብን ክብር እንዲሁም ተድላ ደስታ የማያስቀድም መሪ ማን ይወደዋል? ማን ያከብረዋል? ልዕልናን መከበርን የሚፈልግ አስቀድሞ ትህትናን ራስን ዝቅ ማድረግ ማወቅ ይኖርበታል፡፡

በቅድሚያ በመላው ዓለም ለምትገኙ የርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖት ክርስቲያኖች በሙሉ እንኳን ለጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በሕይወት በጤና አደረሳችሁ፡፡ በሃይማኖቱ አስተምሕሮ መሠረት በዓሉ ዕዳ በደላችን የተደመሰሰበት፣ የእግዚአብሔርን ልጅነት (ዳግም ልደት) ያገኘንበት፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምንወርስበት፣ የሥላሴ ምሥጢር (አንድነትና ሦስትነት) ገሃድ የወጣበት፣ ሰማያዊው በምድራዊው እጅ ተጠምቆ ትህትናን ያስተማረበት ወዘተ. መሆኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በዓሉ በተከበረባቸው የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገራት በሙሉ በዋዜማው በከተራ በዓል እና በዕለተ ጥምቀትም ቅዱሳን አባቶችና መምህራን በስፋት አስተምረዋል፤ ሰብከዋል፡፡ 

ጌታ በባሪያው በቅ/ዮሐንስ እጅ መጠመቁና መንገድ ጠራጊ የሆነው መጥምቁ ዮሐንስ በትህትና እኔ ባንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል እንጂ እንዴት አንተ ወደ እኔ ትመጣለህ? በማለት አይሆንም ሲለው፣ ጌታ ግን አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸምና ተድላ ደስታ ማድረግ ይገባናልና አለው፡፡ ያን ጊዜ ፈቀደለት፡፡ ይለናል ርእሰ መጻሕፍቱ (ማቴ.3÷13-16) ፡፡ ይህ ቅዱስ ቃል ያለውን ሃይማኖታዊ አንድምታ ለጊዜው እናቆየውና ለምድራውያን ነገሥታት ያለው መልእክት ምንድን ነው? ሕዝባችሁን ከፈጣሪ በታች ሆናችሁ በትህትና፣ በቅንነትና በታማኝነት አገልግሉ ማለቱ አይደለም? ወደ ሕዝቡ ወርዶ የዜጎቹን ችግር የማያዳምጥ፣ ፈጥኖም የማይደርስላቸው፤ የአገርንና የሕዝብን ክብር እንዲሁም ተድላ ደስታ የማያስቀድም መሪ ማን ይወደዋል? ማን ያከብረዋል? ልዕልናን መከበርን የሚፈልግ አስቀድሞ ትህትናን ራስን ዝቅ ማድረግ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ ‹መሪ› ነኝ የሚለው ‹ፓስተር› ምን እያደረገ ነው? ዜጎች በማንነታቸውና በእምነታቸው በየዕለቱ በሚታረዱበት በሚጨፈጨፉበት አገር ‹እንኳን አደረሳችሁ› ይለን ይሆን? ይህን ለማለት የሞራል ልዕልና አለው? ለምኑ ነው ያደረሰን? ለእልቂቱ፣ ለጭፍጨፋው፣ ለመፈናቀሉ? ዛሬ የትግራይ፣ የመተከል፣ የወለጋ፣ የኮንሶ ወዘተ. ወገኖቻችን በምን ሁናቴ ነው የሚገኙት?

አገራችን በአራቱም ማዕዝናት ሰላምና ጸጥታ ርቋት ባለበት በዚህ ቀውጢ ወቅት በተለየ ድምቀት (እምቢልታው፣ መለከቱ፣ ነጋሪቱ ወዘተ. ሳይቀር) የተከበረው የዘንድሮው በዓለ ጥምቀት ያስተላለፈልኝ መልእክት (ሃይማኖታዊው እሤቱና ፋይዳው እንደተጠበቀ ሆኖ) ቤተክርስቲያናችንን አትንኩ፣ ምእመኗን አትረዱ፣ ባገራችን ላይ የወጠናችሁትን ሴራ ባስቸኳይ አቁሙ በሚል ባገዛዙ ላይ የተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ጭምር አድርጌ ወስጄዋለሁ፡፡

ነፍሳቸውን በገነት በመንግሥተ ሰማያት ያኑርልንና አንጋፋው የዐደባባይ ምሁር ጋሼ መሥፍን በርካታ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገዛዝ ላይ ያለውን ተቃውሞ የሚያሰማው በቤተ እግዚአብሔር፣ በዓውደ ምሕረቱ፣ ፀዓዳ ለብሶና በሰንደቅ ዓላማው አጊጦና አሸብርቆ መሆኑን እንደተናገሩት ሁሉ፡፡

 

ለኢትዮጵያችን ሰላምና ለሕዝቧ ደኅንነት በየእምነታችሁ አጥብቃችሁ ጸልዩ፡፡

 

እነ እስክንድርን ባስቸኳይ ልቀቁ!!! ነፃነት ለኅሊና እስረኞች!!! 

ኦነግ ያገታቸው ልጃገረድ ተማሪዎች የሚገኙበትን ሁናቴ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቁ፡፡

ሕወሓትን እና ኦነግን ሕገ ወጥ በማድረግና በአሸባሪነት በመፈረጅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዐ ምድር አስተካክሉ፡፡

(የምርጫ ቦርድ የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነትን መሠረዙ አንድ የሚያበረታታ ጉዳይ ሆኖ፣ በአሸባሪነት ሊፈረጅ ይገባዋል፤ ትጥቅ ይዞ አገርንና ሕዝብን እያሸበረ ያለው ኦነግም ላይ ባስቸኳይ ሕጋዊ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡)

Filed in: Amharic