>
5:13 pm - Tuesday April 20, 9717

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ ...!!!

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ …!!!

አብርሃም አለህኝ ጥሩነህ

 

*….የክፋትን እድፍ አጥበን የምናጠራበት፣ የቂምና ጥላቻን ሰንኮፍ ነቅለን ወደጥልቁ ባህር የምንወረውርበት ድንቅ ቀን ነው!!!
እነሆ በሀገራችን አቆጣጠር በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ከ30 ዓ.ም. ጀምሮ የጥምቀት በአል በህዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ታስቦ ይውላል።
በተለይም በሀገራችን ብሄር ብሄረሰቦች የተለየ ትርጉም ያለው ብዝሀነት በይፋ የሚንጸባረቅበት ታላቅ ብሄራዊ በአል ነው።
“ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እንዲሉ በአሉ  ደስታችንንና የወደፊት ተስፋችንን በታቦተ ህጉ ፊት የምንገልጽበት ቀን ነው።
የክፋትን እድፍ አጥበን የምናጠራበት፣ የቂምና ጥላቻን ሰንኮፍ ነቅለን ወደጥልቁ ባህር የምንወረውርበት ድንቅ ቀን ነው።
የጥምቀት በዓል ከመንፈሳዊ ገጽታው ባሻገር የሀገርና የህዝብ ሀብት ፣ የማይንቀሳቀስ ቅርስ ነው።
በአሉን ባልተገባ መንገድ መረዳትና የዜጎችን ቅስም በመሰባበር ፣ እርስ በእርስ በመናቆር ፣ ከበአሉ መንፈሳዊና ታሪካዊ አንድምታ ይልቅ  በተራ ስሜት መጫጫን ለጸብና ለእርስ በእርስ ግጭት እንዲውል መፍቀድ በየትኛውም ወገን ይሁን መወገዝ ያለበት ድርጊት ነው።
የጥምቀትን በዓል ስናከብር እርስ በእርስ እንጠባበቅ። ደስታችንንና ፌሽታችንን በልኩ እናድርግ። የአካባቢያችንን ሰላም በንቃት እንጠብቅ። ትርፍ ከማያስገኝልን ህገወጥ ድርጊት እንቆጠብ።
በአሉ ሰዎች እንዲተሳሰቡበትና በሰላምና በፍቅር ሆነው ፈጣሪያቸውን እንዲያመሰግኑበት ከፈጣሪ የተሰጠ ሀብት ነው።
በመለያየት ፣ በመፎካከርና እርስ በእርስ በመናቆር እናከብረው ዘንድ የተሰጠን በአል አይደለም። ስለሆነም እርስ በእርስ ከመዋደድና ከመከባበር የምናጎድለው ነገር ስለሌለ ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ወንድማማችነትን እናጥብቅ። ሀገራችን ኢትዮጵያን ከክፉዎች መዳፍ ፈልቅቀን እናውጣት። የክፉዎች መንፈስ የሚሸነፈው  በአንድነታችን ብቻ ነው። እንድ እንሁን !!!
በማያባራ የአውሬነት ባህርይ ህይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችን ነፍስ በገነት ያሳርፍልን። በህይወት ለተረፉት መጽናናትን ያድልልን።
የጠላት ዲያብሎስን የሞት ደብዳቤ በባህረ ዮርዳኖስ እንደተሻገርነው ሁሉ ያለምንም ጥርጥር ከፊት ለፊታችን ያለውን የፈተና ክምር ደረማምሰን በድል በመሻገር የብልጽግና ጉዟችንን እናሳካለን።

ሀገራችንና ህዝቦቿን ፈጣሪ ይጠብቅልን !!!

Filed in: Amharic